Friday, May 31, 2013

ሃምሳም ሰውም ይውጣ ሃምሳ ሺህ ግን አንድ ፀባይ እሱም “ፍፁም ሰላማዊ!”abetokichaw

935293_421802944584325_731290226_nአቤት የርዕሴ ርዝመት… ደግሞ በዛ ላይ ቀጥሎ የምናገረውን ማሳበቁ! “ቢወዳት ነው ቢጠላት ባሏ በሻሽ አንቆ ገደላት” አይነት ሆነኮ፡፡
ለማንኛውም ቀጥሎ ስለ ሰላማዊ ሰልፉ ጥቂት ልናወጋ ነው፡፡ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ እና በጥቅሉ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ስለ ሰላማዊ ትግል ስናወራ ስለ ሙስሊም ኢትዮጵያውን በማውራት ብንጀምር የወጋችንን ደረጃ ከፍ ደርገዋል ሞገስም ይሰጠዋል እና  እንቀጥል…
መንግስታችን በዛን ሰሞን በገዛ ቴሌቪዥኑ የሙስሊሙን ህብረተሰብ ተቃውሞ በሌላው ህብረተሰብ ላይ የተቃጣ ትንኮሳ አስመስሎ ኮሳሳ የሆነ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲሰራ አይተን ታዝበን ታዝበን ታዝበን አልወጣልንም፡፡
በተደጋጋሚ እንዳየነው ሙስሊም ኢትዮጵያውን ከአመት በላይ በመስጂዳቸው ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ያሳዩን ጨዋነት ገዢዎቻችንን ያሳፈረ ነበር የሚለው ቃል አይገልፀውምና “አፈር ያስበላቸው ነበር” ማለት ይሻላል፡፡ (አረ እንደውም አፈር ደቼ እንበል እንጂ… ሃሃ… “ደቼ” የምትለውን ቃል ትርጓሜ ከሳቴ ብርሃን መዝገበ ቃላትን ላይ ባገላብጥም፤ ደቸር፣ ደቻሪ ደቻራ፣ ደችሮ ብሎ ይዘላታል እንጂ ትርጉሟን አላስኮርጅ አለኝ…) የምር ግን የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጨዋነት የተላበሰ ተቃውሞ ገዢውን እና አሳሪውን መንግስታችንን አፈር ደቼ ያበላ ነበር ከሚለው ውጪ ገላጭ ቃል ከየት ይገኝለታል?

የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ የሌላው ኢትዮጵያዊም ጥያቄም ነው፡፡ ኢትዮጵያውን ሙስሊሞች፤ “መንግስት በሀይማኖት ጣልቃ አይግባ” ይላሉ፡፡ ሌላውም ኢትዮጵያዊ፤ “አዎን እንኳንስ በሀይማኖት እና በታክሲ ወረፋም ጣልቃ መግባት ነውር ነው” ይላል፡፡ ኢትዮጵያውን ሙስሊሞች፤ “መንግስት የምንጠይቀውን ጥያቄ በእስር እና በጠብ መንጃ አይመልስልን” ይላሉ፡፡ ሌላውም ኢትዮጵያዊ “አዎ ሰው ማሰርን በሬ እንደማሰር አታቅልሉት ሰው ለመጥመድም በሬ እንደመጥመድ አትቸኩሉ” ይላል፡፡ በጥቅሉ ኢትዮጵያውን ሙስሊሞች “ድምፃችን ይሰማ” ይላሉ፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊም፤ “ጮክ ብሎ ዜና እናሰማለን ማለት ብቻ ዋጋ የለውም የእኛንም ድምፅ መስማት ልመዱ” ሲል በየአጋጣሚው ሁሉ ይጮሃል፡፡
እስከ አሁን ኢትዮጵውን ሙስሊሞች በአንድ ላይ ሆነው በየሳምንቱ በየ መስጂዳቸው ድምፃችን ይሰማ ሲሉ የቆዩ ሲሆን፤ የተቀረው ኢትዮጵያዊ ደግሞ በጋራ ሆኖ ኡኡ የሚልብት አማካይ ቦታ ተቸግሮ “የት ሄጄ ልፈንዳ” እያለ ይገኛል፡፡
አሁን እድሜ ለሰማያዊ ፓርቲ፤ ሁሉን በጋራ የሚያሰባስብ አንድ መድረክ ተፈጥሯል፡፡ እሁድ ግንቦት 25 ዋቄፈታውም፣ ኦርቶዶክሱም፣ ሙስሊሙም፣ ፕሮቴስታንቱም፣ ካቶሊኩም በአንድ የሚሰባሰቡበት መድረክ ተፈጥሯል፡፡ በጥቅሉ ኢትዮጵያውያን በአንድ ድምፅ ተባብረው “ድምፃችን ይሰማ” ይላሉ፡፡ መንግስት ሊሰማም ላይሰማም ይችላል፡፡ የጋራ የሆነው የሰማዩ አምላክ ግን እንደሚሰማ ግን በጣም ርግጠኛ ነን!
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤
እስከ አሁን በደረሰኝ ወሬ ከቢሸፍቱ (ደዘዎች) እና ከአዳማ (ናዝሬት) በርካቶች በሰልፉ ለመታደም ተነሳሽነት አሳይተዋል፡፡ እንደ ቅንጅት ጊዜው በክልላችሁ ተሰለፉ ካልተባሉ በስተቀር፤
በመጨረሻም
ፖሊስ እና ወታደሩ የተሰላፊው ወገን መሆኑን መርሳት ራስን ከመርሳት ጋር እኩል ነው፡፡ ተሰላፊዎች ሃምሳም ሁኑ ሃምሳ ሺህ አንድ ፀባይ ግን ያስፈልጋል እርሱም ፍፁም ሰላማዊ መሆን! ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሚሊዮን ሆነው አቤት ሲሉ የአቤቱታው ፀባይ አንድ ነበር ፍፁም ሰላማዊ! (ይቺን ነው መኮረጅ!)
በመጨረሻው መጨረሻ
ለሰላማዊ ተቃዋሚዎች፤ ሰላሙን ያብዛ! ብለን እንመርቃለን!
አሜን!
abetokichaw

No comments:

Post a Comment