Wednesday, May 1, 2013

“ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዜጎችን መፈናቀል ላልተገባ የፖለቲካ ትርፍ እያዋሉት ነው” የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር


በዘሪሁን ሙሉጌታ
ተፎካካሪ ፓርቲዎች እራሳቸውን አደራጅተውንና ሕዝቡን አንቅተው የሀገሪቱን ፖለቲካ አንድ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በተልካሻ ምክንያት በውስጥ ጉዳይ ተወጥረው በግለሰቦች አሰጥ አገባ ላይ የተጠመዱ ከመሆን አልፈው በአማራው ብሔር ወገናችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና መፈናቀል በመግለጫ እያጧጧፉ ያልተገባ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘትና ከዲያስፖራው ወገናችን ገንዘብ ለመሰብሰብ እየተጠቀሙበት ነው ሲል የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ወቀሰ።
ማህበሩ ሰሞኑን ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ሀገሪቱ ያለችበት የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳይ አስከፊ ሁኔታ እየተሸጋገረ በመሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ ከሀገር ውጪ ያሉ ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሃይሎችና ገዚው ፓርቲ ጨምሮ ወደ አንድ መድረክ ወጥተው ብሔራዊ የምክክር መድረክ እንዲቋቋም ሲል ጠይቋል።
ማህበሩ በመግለጫው በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጊዜአዊ የፖለቲካ ትርፍ ብቻ በመሯሯጥ ከዲያስፖራው ድጋፍ በሚያስገኝ ተግባር ላይ ከመተራመስ አሳፋሪ ድርጊት እንዲቆጠቡ ሲል አሳስቧል።

ማህበሩ ሁሉም ወገኖች የሚሳተፉበት ብሔራዊ መድረክ ለማቋቋም የአንድነት ዲሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ (አንድነት) እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ቀዳሚውን ኃላፊነት እንዲወስዱ ጥሪ ቢያደርግም ችላ በማለታቸው ማዘኑንም በመግለጫው አያይዞ አቅርቧል።
ገዢው ፓርቲ ለውይይት ዝግጁ ካለመሆን አልፎ የሰላማዊ ትግል በር በመዝጋት ከምርጫው ትርፍ ሳይሆን መክሰሩን፣ የጠቀሰው የማህበሩ መግለጫ፣ የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት በሰለጠነ፣ ሀገራዊ ስሜት፣ በዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ ውይይት መፍታት ተገቢ ነው ብሏል።
ባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ጥር 14 ቀን 2004 . በኢትዮጵያ አንድነት ውስጥ በኢኮኖሚና ዴሞክራሲዊ አስተዳደር የዳበረ ጤናማና በስነ-ምግባር የታነፀ ብቁ ወጣት የማህበረሰብ ክፍል መፍጠር በሚል የተቋቋመ የሲቪክ ማህበር ነው።

No comments:

Post a Comment