ጌታቸው ሽፈራው
መቼም ይህን ጥያቄ ስጠይቅ የግንቦት 20ን ‹‹ድል››፣ የ2002ና የባለፈውን ሚያዚያ 2005 ዓ/ም የቀበሌ፣ የወረዳ……ምርጫም ጨምሮ በመከራከሪያነት በማንሳት ምን ነካው ኢህአዴግ እኮ እያሸነፈ ነው የሚሉ አይጠፋም፡፡ ለእኔ ማሸነፍ ማለት የህዝብን ልብና አዕምሮ (hearts and minds) መያዝ ሲቻል ነው፡፡ በሀይልማ ከሆነ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ በአጠቃላይ ቀኝ ገዥዎቹ አፍሪካውያንን በወታደራዊ ሀይልና በሌሎች አቅሞቻቸው በመብለጣቸው እስከ መቶ አመት ድረስ ገዝተዋል፡፡ በኤሲያን ደቡብ አሜሪካ ደግሞ ከ200 እስከ 800 አመትም የተገዙ ህዝቦች ነበሩ፡፡ ለጊዜው አሸናፊ የመሰሉት ቅኝ ገዥዎች የእነዚህን ህዝቦች ልብ መግዛት ባለመቻላቸው ጊዜ ጠብቀውም ቢሆን ተሸናፊዎች ሆነዋል፡፡ ኢህአዴግ አሸነፍኩት የሚለውን የመንግስቱ ሀይለማሪያም ደርግ ጨምሮ ህዝባቸውን በሀይል ጨምድደው የኖሩ ስርዓቶች የኋላ ኋላ ተሸንፈዋል፡፡ እነዚህ አካላት የተሸነፉት ህዝብን በሀይል እንጂ በሀሳብ ማሳመን ባለመቻላቸው ነው፡፡ ሰውን በሆዱ አሊያም በግድ ለዘላለም መግዛት አይቻልም፡፡ አንድም የሚፈልገው ነገር በየጊዜው ስለሚጨምር ይህን በየጊዜው የሚጨምርን ነገር ማሟላት አይቻልም፡፡ ማሟላት ቢቻል እንኳ ሰው የመጨረሻ ፍላጎቱ ነጻነት ነውና ዳቦ ጠግቦም ሆነ ሳይጠግብ ነጻነቱን መጠየቁን አያቆምም፡፡
ኢህአዴግም እስካሁን የኢትዮጵያውያንን ልብ በሀሳብ መግዛት አልተቻለውም፡፡ በብሄር፣ በስራና ጥቅማጥቅም፣ በማሳፈራራት፣ የሌሎቹ አስተሳሰብ እንዳይደርስ በማገድ ስልጣኑን ለማራዘም ቀና ደፋ እያለ ነው፡፡ ኢህአዴግ በዋነኝነት አሸንፍበታለሁ ብሎ የጀመረው የብሄርን ፖለቲካ ቢሆንም ይህ ቀመር የኢትዮጵያውያንን ልብ ሊገዛለት አልቻለም፡፡ ይህ እንደማያዋጣው ያሰበው ኢህአዴግ ኢትዮጵያውያን ሊሸነፉበት የሚችሉትን አስተሳሰቦች ለይስሙላህም ቢሆን ከጀመረ ጥቂት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚሊኒየም በዓልና የሰንደቅ አላማ ቀን የመሳሰሉትን አገራዊ እሴቶች ማንሳት ጀምሯል፡፡ ይሁንና እነዚህንም ቢሆን ከልብ ሳይሆን ለመቀስቀሻነት ብቻ እየተጠቀመባቸው በመሆኑ ሊያሸንፍባቸው አልቻለም፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ እስካሁን ኢትዮጵያውያንን ማሸነፍ አልቻለም፡፡
ኢትዮጵያውያን የሚሸነፉት መቼ ነው?
ኢህአዴግ ለጊዜው ኢትዮጵያውያንን በበላይነት መራ እንጂ አላሸነፋቸው እያልን ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአንድ አካል በሀይል ቁጥጥር ስር የወደቀ ሰው በዚህ አካል ሀይል ቁጥጥር ስር እንዲገባ ያደረገውን እምነቱን ጣል እርግፍ አድርጎ እስካልጣለ ድረስ ተሸናፊ ሊባይ አይቻልም፡፡ በመሆኑም ለእኔ እነ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት አለሙ፣ ውብሸት ታዬ፣ በቀለ ገርባ የመሳሰሉት ዜጎች በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ቢሆኑም ከአካላቸው ውጭ እምነታቸውን መቆጣጠር እስካልቻለ ድረስ ተሸናፊዎች አይደሉም፡፡ በተቃራኒው ትናንት ‹‹ዜሮ ዜሮን›› ዘፍነው ዛሬ ‹‹ይቀጥል!›› ያሉት እነ ሰለሞን፤ ትንንት ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ድምጽ የነበሩትና አሁን በክብ ጠረጴዛ ለስርዓቱ ድምጽ የሆኑት እነ ሚሚ እንደልባቸው ቤተመንግስት መግባት ቢችሉም ኢህአዴግ ከልብና አዕምሯቸው በላይ ገዝቷቸዋል አሳዛኝ ተሸናፊዎች ናቸው፡፡ አሳዛኝ ተሸናፊ መጀመሪያ የተነሳበትን አያውቅም አሊያም ሲሸነፍም ድሮ ከነበረው አመለካከት በተቃራኒ ሁለመናውን የሚማረክ ነው፡፡ የእነዚህ ኢትዮጵያውያን ሽንፈት ጠንካራ ወታደር እያለው እራሱን ለጠላት በምርኮ እንዳቀረበ ጀኔራል እቆጥራቸዋለሁ፡፡ በተቃራኒው እነ እስክንድር ምንም ወታደር በሌለበት ብቻውን ከጠላት ጋር የሚፋለም ሲፋለም ተይዞ ስለ ክብሩ ሞትን ከሚጠባበቅ ጀግና ጀኔራል ጋር ቢመሰሉ አያንስባቸውም፡፡ ሽንፈት እንዲህ ለእየቅል ነው፡፡ ለአብዛኛዎቹ በተለይም ለታዋቂዎቹ መሸነፍ ጥቅም፣ ዝና ቀዳሚው ሲሆን በርካታዎቹ ኢትዮጵያውያን እንዳይሸነፉ ያደረጋቸው ኢትጵያውይነት ነው፡፡
አንድ ሰው በራሱ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ.. መሆኑን በማመኑ አሊያም ሌሎች በዚህ ምድብ ውስጥ ስላስገቡት ብቻ በብሄር ስም ሊጠራ ይችላል፡፡ አምኖም ሆነ ተወናብዶ በብሄር ማመኑ በራሱ ችግር ላይኖረውም ይችላል፡፡ ብሄር ችግር የሚያመጣው የመከፋፈያ መንገድና ለፖለቲከኞች መጠቀሚያ በሚያመች መልኩ ሲመነዘር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄር ለመከፋፈያና ለፖለቲከኞች መጠቀሚያ በሚያገለግል መልኩ ቢመነዘርም አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን በዚህ ደስተኛ ባለመሆናቸው ኢህአዴግም ለማስመሰያነት የሚጠቀምበት የአንድነት አጀንዳ ለማንሳት ፈራሁ ተባሁ እያለ ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያውያን በዚህ በኩል ከመሸነፍ ይልቅ ማሸነፍ ወደሚችሉበት መንገድ ተቃርበዋል ማለት ይቻላል፡፡
በተቃራኒው ግን ብሄርን በዋነኛ መሳሪያነት የሚጠቀመው ኢህአዴግ ያሸነፈ የመሰላቸው ‹‹እሳትን በእሳት›› በሚል ይህን ቀመር የመረጡ አልጠፉም፡፡ ኢህአዴግ ያደርጋቸውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴዎች ከብሄር አይን ብቻ በማየት በብሄር ቀመር ለመፍታት መጣር እስካሁንም ተቃውሞው ጎራ ውስጥ አልጠፉም፡፡ ይህ አንድ ስልት አይደለም ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም በተለይ በኢትዮጵያውይነት እናምናለን የሚሉትም አጀንዳ ሲያደርጉት ፖለቲካውን መርህ አልባ ያደርገዋል፡፡ ለአብነት ያህል ከየክልሉ የሚባረሩ ኢትዮጵያውያንን በኢትዮጵያውይነታቸው ሳይሆን በአማራነታቸው ብቻ መመንዘር እየተበራከ ነው፡፡ በእርግጥ ኢህአዴግ በተወሰነ ማህበረሰብ ላይ የሚያደርገው ይህ እርምጃ ተቃዋሚዎችን ወደዚህ የኢህአዴግ መስመር ሊጎትት ይችል ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ የሚፈልገውም እያንዳንዱ ጉዳይ በአገር ማዕቀፍ ሳይሆን በብሄር አይን እንዲመነዘር ነው፡፡ ለተቃዋሚዎች ውድቀቱ የሚሆነውም ኢህአዴግም ይህን አንድ ማህበረሰብ ላይ የሚያደርገው እርምጃ የብሄር ፖለቲካውን እንዳይበርድና ኢትዮጵያውያን በአንድ ማዕቀፍ ይልቅ በቋንቋ የሚከፋፈሉበትን ‹‹የእኛ›› እና ‹‹እነርሱ›› ፖለቲካ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ስለሆነ በእሱ መስመር መግባታቸው ነው፡፡ በዚህ የኢህአዴግ ቀመር መሰረት ‹‹አማራ›› በመሆናቸው ‹‹ከቤንሻንጉል››፣ ከደቡብ ብሄራዊ ክልሎች ተባረሩ የሚል ክርክር አሸናፊ ሊሆን አይችልም፡፡ እነዚህን ህዝቦች በብሄር አምኖ የመደበ ተቃዋሚ ‹‹ውጡልን›› ያላቸው ፖለቲከኞች ወክለነዋል የሚሉትን ብሄር መብት ኢህአዴጋዊ በሆነው በዚሁ ቀመር ሊያምን ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ጉዳዩ መታየት ያለበት በኢትዮጵያዊ መዕቀፍ እንጂ በብሄር ማዕቀፍ አይደለም፡፡ ተቃውሞው በብሄር ማዕቀፍ ሳይሆን በኢትዮጵያውይነት ከዚያም አለፍ ሲል በሰብአዊነት ሲሆን የትግል አንድነቱ በመርህ ላይ የተመሰረተ ያደርገዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎችም ወደውም ሆነ በግድ ወደ ኢህአዴግ ቀመር እየተንፏቀቁ በመሆኑ ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ በደል ሲደርስበት ይህን ህዝብ እንወክላለን የሚሉት አካላት ብቻ በቀዳሚነት ድምጻቸውን ያሰማሉ፡፡ አማርኛ ተናጋሪው ላይ በደል ሲደርስ በብሄርና አንድነት መካከል ግራ የተጋቡት ተቃዋሚዎች ድምጽ ሲያሰሙ ‹‹ሌላውን›› ህዝብ የሚወክሉት አካላት ድምጻቸው እምብዛም አይሰማም፡፡ በትግራይ ህዝብ ላይ በደል እንደሚደርስ የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ ነው፡፡ በዚህ በኩል ህውሃት/ኢህአዴግ ባያሸንፍም ለጊዜው የተሳካለት ይመስላል፡፡ በቅርቡ ወደ ተቃውሞ ጎራው ለመቅረብ እየሞከሩ ያሉት ትግርኛ ተናጋሪዎች የትግራይን ህዝብ በደል ብቻቸውን የሚናገሩ ሆነዋል፡፡
ኢላማውን ያልለየ ተቃውሞ
አንድ ትግል እንደ ትግል ውጤታማ ለመሆን ኢላማውን መለየት ይገባዋል፡፡ ካልሆነ ከእንሰሳ መንጋ ውስጥ ገብቶ ያየውን ሁሉ ለመያዝ የሚቋምጥና ሁሉን ሲያሯሩጥ ውሉ ደክሞ የሚመለስ አዳኝ እንሰሳ መሆን ነው፡፡ የሚይዘውን ታዳኝ ቀድሞ ያልለየ አዳኝ ትርፉ ድካምና ታዳኙ ማንቃት ብቻ ነው፡፡ በፖለቲካ ስልትም ቢሆን ተለይተው መቀመጥ ያለባቸው ኢላማዎች ይኖራሉ፡፡ ከአንድ በላይ መለየት ያለባቸው እንኳ ቢኖሩ በቅደም ተከተል መቀመጥ የግድ ይላቸዋል፡፡ ይህ ገንዘብን፣ የሰው ሀይልንና ጊዜን ለመቆጠብም ሆነ በአጭር ጊዜ ውጤት ለማምጣት አይነተኛ መንገድ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የሚከተለው ተስፋ መቁረጥና መጀመሪያ ከተመረጠው የትግል ስልት ማፈንገጥ ሲብስም ከተቃውሞው ጎራ መውጣትና እንዋጋዋለን በሚሉት ሀይል መዋጥ ወይንም መሸነፍ ነው፡፡
ይህ ችግር በአገራችን የተቃውሞ ጎራም ተከስቷል፡፡ በተለይ ብሄር ለዚህ አላማውን ያልለየ የፖለቲካ ኪሳራ የሚዳርግ የመጀመሪያው ምክንያት ነው፡፡ ብሄር ስስ፣ የፖለቲከኞች መጠቀሚያና እንደፈለገው የሚጠመዘዝ በመሆኑ ኢላማን ለመለየት እንዳይቻል ያደርጋል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄርን በቀዳሚነት የጀመሩ ሀይሎች ተሸንፈዋል፡፡ ተሸንፈዋል ስንል ሀሳባቸውም ማለታችን ነው፡፡ ለብነት ያህል ለመጀመሪያ ጊዜ ብሄርን ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ይዞ ብቅ ያለው ጀብሃ አስከፊ ሽንፈት ከገጠማቸው ፓርቲዎች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ ይህ ፓርቲ በኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ብቻ ሳይሆን ትግርኛ ተናጋሪውን የኤርትራ ህዝብ ሲከፋፍል ኖሯል፡፡ ለኤርትራ ችግር የገዥዎችን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ህዝቦች ራሱ ባስቀመጠው የብሄር ቁና እየሰፈረ ሁሉም ላይ ለመዝመት ሞክሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት መሳሪያና ስንቅ ሲያስታጥቀው ከነበረው ህውሃት በታች የሆነው ሻቢያም በኢትዮጵያ ገዥዎች ብቻ ሳይሆን በአማርኛ ተናጋሪው ህዝብ ላይ የመረረ ጥላቻ የነበረውና ኢላማውን መለየት ያልቻለ ፓርቲ ነው፡፡ ምንም ያህል ስልጣን ላይ ቢወጣም ሻቢያ ያኔ ‹‹ከአማራ ነጻነት አወጣችኋለሁ›› ብሎ ያታለላቸው ህዝቦችን ልብ መግዛት ባለመቻሉ አሁን በመሸነፍ ላይ ይገኛል፡፡ ከ30 በመቶው በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ስም የተቋቋመው ኦነግ ከነገስታቱም ይሁን በጊዜው ከነበሩት ልሂቃን ይልቅ ‹‹አማራ›› መባሉን በማያውቀው ኢትዮጵያዊ ላይ ሁሉ በመዝመት ጊዜ፣ ጉልበቱንና አቅሙን አዳክሟል፡፡ ከምንም በላይ ወክየዋለሁ ከሚለው ኦሮምኛ ህዝብ ሳይቀር ይህ ህዝብን በጅምላ የማስጠላት ፖለሲው ላይ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ በየትኛውም አለም ሰፊ ህዝብ እወክላለሁ የሚል ፓርቲ አንድነትን በማጠናከር እንጂ በጠባብነት ሁሉ ላይ በመዝመት አይታወቅም፡፡ በጠባብ ብሄርተኝነት ተራው ህዝብ ላይ ሲዘምት የነበረው ኦነግም ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ለመውጣት ተገዷል፡፡ በቅርቡ ይህን ስህተቱን ያመነ የሚመስለው ኦነግ ህዝብ ላይ ሳይሆን አላማውን ልሂቃን ላይ በማድረግ በኢትዮጵያውይነት ማዕቀፍ ወደፖለቲካ መድረኩ እንደገና መመለሱ እየተነገረለት ነው፡፡
በብሄር ላይ የተመሰረቱ ፓርቲዎች የጊዜ ጉዳይ እንጂ መሸነፋቸው የግድ መሆኑን ታሪክ ያስረዳል፡፡ ሶቬት ህብረትና ዩጎዝላቪያ በአንድ ወቅት ታላቅ ቢመስሉም በዚህ ኢላማውን በማይለይ የፖለቲካ ቀመር ምክንያት ተበታትነዋል፡፡ ሶቬት ህብረት በወቅቱ አሜሪካን የምትገዳደር አገር ለመሆን ብትበቃም የኋላ ኋላ ተፈረካክሳ ግዛቶቿ ከአሜሪካ ስር ሆነዋል፡፡ ተከፋፍላ የነበረችው ጀርመን አውሮፓን መግዛት የቻለችው አንድ በመሆኗ ነው፡፡ የፋሽስትና ናዚ ፓርቲዎች ኢላማ ለይተው ሳይሆን በአለማቀፋዊ ‹‹የእኛ›› እና ‹‹እነርሱ›› ዘረኝነት ፖለቲካ ህዝብን ለጥቂት ጊዜ ማንቀሳቀስ የቻሉ ቢሆንም ሲሸነፉ ይከተሉት የነበረው ስርዓት የሚወገዝ፣ የሚናቅና የሚያስቀጣ ሆኗል፡፡ ጀብሃ፣ ሻቢያ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ በብሄር ፖለቲካቸው ምክንያት ተሸንፈዋል፡፡ ህውሃት እስካሁን በሀይል ቢገዛም የሻቢያ መስራች ጀብሃ፣ ከዚያም የህውሃት አጋዥ ሻቢያ ክስረት ሽንፈቱ ወደማን እየመጣ ለመሆኑ ጠቋሚ ነው፡፡ ምን አልባት እነሻቢያ ብቻ ሳይሆን እነኢህአፓ፣ መኢሶንና የመሳሰሉትን አልተሸነፉም? የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችል ይሆናል፡፡ ለእኔ የእነዚህ ፓርቲዎች ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ማለት አልችልም፡፡ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ እንጀብሃ፣ ሻቢያ፣ ህውሃት፣ ኦነግና ኦብነግ ያሉ ተገንጣይ ፓርቲዎችን ጸረ ኢትዮጵያዊ አቋም የምታስተናግድበት ቦታ ያላት አይመስልም፡፡ ለዚህም ህውሃት ለይስሙላህም ቢሆን የጀመረው የአገራዊ አንድነት፣ የኦነግ የስልት ለውጥ እና የአብዛኛዎቹ ሽንፈት ዋነኛ ማስረጃ ነው፡፡ ምንም እንኳ እነ መኢሶንና ኢህአፓ በፓርቲነት ባይኖሩም ጀምረውት የመነረውን ኢትዮጵያን ለክፉ የማይሰጥ ‹‹የብሄር›› ፖለቲካቸውን የአሁኑ ኢህአዴግ እንኳን አውን ሊያደርገው አልቻለም፡፡ ምን አልባት ከቀደም ፓርቲዎች ስህተት መማር ከቻሉ ተቃዋሚዎች የኢህአፓንና መኢሶንን አንዳንድ መስመሮች መፍታት የሚችሉ ይመስለኛል፡፡ በተለይ እነዚህ ቀደም ፓርቲዎች ብሄርን ከጠባብ ብሄርተኝነት ይልቅ ለአገር አንድነት በሚጠቅም መልኩ ለማዋል ጥረት ማድረጋቸው የሚታወቅ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ባለው ፖለቲካችንም አላማን ያልለየ ፖለቲካ ይስተዋላል፡፡ በእርግጥ ለዚህ ዋነኛ ምንጩ ህውሃት/ኢህአዴግ ነው፡፡ ህውሃት ትግርኛ ተናጋሪውን ህዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ በመነጠል ለመያዣነት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ይህም በብሄር ስም በተወናበደው ህዝብና በአንዳንድ ተቃዋሚዎች ዘንድ ትግርኛ ተናጋሪው ህዝብ ተጠቃሚ እንደሆነ ተደርጎ እየቀረበ ነው፡፡ ይህን ህውሃት ይፈልገዋል፡፡ ምክንያቱም ትግርኛ ተናጋሪውን ህዝብ ልብ ለማግኘትም ሆነ ሌላውን ለማሸነፍ የሚጠቅመው ይህ ስልት በመሆኑ ነው፡፡ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦችም ይወክሉናል በሚሉት ስር ከመስራት ውጭ በኢትዮጵያውነት ማዕቀፍ ለመታገል አማራጭ እንደሌላቸው ያምናሉ፡፡ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውጭ ሌሎች ተቃዋሚዎች በአገር ማዕቀፍ የሚታገሉ በመሆኑ በብሄር ስም የሚታገሉትም በመዳከማቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶችም ጎን ተስልፎ የአገሪቱን ኬክ ለመካፈል፣ ራሱን ለመከላከልና ለጥቅም እንዲቋምጥ ያደርገዋል፡፡ ማህበራዊ ድህረገጾችን ጨምሮ በአገር ውስጥ በሚደረገው ተቃውሞ ጠባብ ብሄርተኝነት የወለደውን እሳት በሌላ ጠባብ ብሄርተኛ እሳት ለመዋጋት የሚደረግ ጥላቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በንጉሳዊያኑ ዘመን አማርኛ ተናጋሪ ህዝብ አልተጠቀመም ብለው የሚከራከሩ ሀይሎች በኢህአዴግ ዘመን ትግርኛ ተናጋሪው ህዝብ ተጠቅሟል ወደሚል መርህ አልባ ፖለቲካ እያዘነበሉ ነው፡፡ ህወሓት ከሌሎቹ ‹‹የኢህአዴግ አባል›› ድርጅቶች በላቀ መከላከያውን፣ ደህንነት፣ የውጭ ጉዳይ፣ ፍርድ ቤት በአጠቃላይም የኢትዮጵያን ተቋማ ይዟል፡፡ በእርግጥ ቅጥር በዘመድ አዝማድ፣ በጓድነት፣ በፖለቲካዊ ቅርርብ ነውና እነዚህ ሰዎች በርካታ ሰዎችን (የህወሓት አባላትን) ስበዋል፡፡ ይህ ከህወሓት የበላይነት እንጅ ትግርኛ ተናጋሪው ኢትዮጵያዊ እንደ ህዝብ ገዥ በመሆኑ የተፈጠረ አይመለኝም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከህውሃት ጎን ባለመሆናቸው እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ጥቃት እየደረሰባቸው የሚገኙ ትግርኛ ተናጋሪዎች የብሄር ፖለቲካ ለመጠቀሚያነት ብቻ እያገለገለ የሚገኝ ቀመር መሆኑ እየተዘነጋ ይመስላል፡፡ ይህ የኢህአዴግን ቀመር መጠቀም ኢህአዴግን እቃወማለሁ የሚል አካል ሁሉ ኢትዮጵያውያንን ወደ ብሄር ፖለቲካ በመግፋት የራሱን ሽንፈትና የኢህአዴግን ድል ማፋጠኑ የግድ ነው፡፡ በአንድ ወቅት በብሄር ሳይሆን በኢትዮጰያውነት ማዕቀፍ ይህን ብልሹ ፖለቲካ ሲታገል የነበረው የአውራምባው ዳዊት ሌሎች ባደረጉበት ግፊት (የራሱ ጽናት ማጣትም ተጨምሮበት) የብሄር ፖለቲካውን እየታከከ ነው፡፡ ይህ የኢህአዴግ ቀመር ነው፡፡ ይህ ብሄርን መሰረት ያደረገና አላማውን ያልለየው ‹‹የእኛ›› እና ‹‹እነርሱ›› ፖለቲካ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጥረው ሽንፈትን ብቻ ነው፡፡ የኢህአዴግ የብሄር ፖለቲካም የሚያሸንፈው ያኔ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment