ሚያዚያ 16. 2013
በታክሎ ተሾመ
በታክሎ ተሾመ
አገራችን ኢትዮጵያን አስመልክቶ በድርጅት፤ በቡድን፤ በተናጥል የሚደረጉ የመፈከር እንቅስቃሴ መኖራቸው
ያለና የሚጠበቅ ነው። በሁሉም ዘንድ የሚደረጉ መፈከሮች የሩቅና የቅርብ ዓላማን
የሚያመላክት መሪ ቃል ቢሆንም ፍሬ ቃሉ በሁሉም ዘንድ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም የመፈከሮችን ይዘት
ድርጅቶችም ሆነ ደጋፊዎች የሩቁንም ሆነ የቅርቡን ዓላማ ሳያሳኩ መንገድ ላይ ወደ ኋላ መመለስ
የሚታይበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ይህ ደግሞ ከልብ ሳይታለምበትና ለመሰዕዋትነት ሳይዘጋጁ የሚጀመሩ እንቅስቃሴዎችና
ድጋፎች አሻራ ቢስ ወይም እድለቢስ መሆናቸው አይቀሬ ነው።
የተለያዩ ድርጅቶች፤ ስቪክ ማኅበራት፤ ግለሰቦች በአንድ አጀንዳ ዙሪያ
ሊስማሙ እንደማይችሉ እያወቁ በሥም አንድነት ወይም ውህደት የምትለው ቃል ሽፋኗ ሲያምር ውስጧ ግን ነጣቢ
ትሆናለች። ደጋፊዎችም ለመደገፍ የተነሳሱትም ቢሆን ዓላማውን በውል
ያልተገነዘቡ ሰለሚሆን መጨረሻው ማጉረምረም ነው።
በተለያየ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥታት ሥልጣናቸውን በውርስና
በጠበንጃ አፈሙዝ እንደሚይዙ በተከታታይ ታይቷል። የማስመሰያና
ዴሞክራሲን የሚያብረቀርቅ የወረቀት ሕጎችን መደጋገም ዋነኛ መለያ ባሕሪያቸው
ነው። ነገር ግን በወረቀት ላይ ያሰፈሩት የዴሞክራሲው ይዘት
ምንነቱ የማይታወቅ ስለሚሆን ነፃነቴ ተገፈፈ የሚል ጥያቄ ሲነሳ ቦግታው
መልኩን ይቀይራል። ሕዝብ ያልጠመረጣቸው ባለሥልጣናት (መንግሥታት) ሕልውናቸውን
ለማስቀጠል ኃይልን በመጠቀም ለነፃነት ትግል የሚነሱትን ማሰርና መግደል ይጀምራሉ።
ስለሆነም በነፃነትና በባርነት መካከል በሚነሱ ግጭቶች ምክንያት አገሪቱ አኬልዳማ ትሆናለች፤ ሆናለችም።
የቀዳማዊ ኃ. ለሥላሴ የግዛት ዘመን እንዲያበቃ የሕዝብ ብሶት
ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ተቀጣጥሎ ጐርፉ አይሎ በውርስ ሥም የተገኘው ሥርዓት ተወግዶ በደርግ
መተካቱን እናስታውሣለን። ያ ውሾ፤ ውሾ ተብሎ ድንጋይ የተወረወረበትና የተሰደበበትን ሥርዓት ዛሬ
ላይ ሆኖ ለሚያስታውስ ለድጋፍም ሆነ ለተቃውሞ ትምህርት ሰጭ መሆኑ አልቀረም።
ከዚህ ላይ በመረጃ የተደገፈ ትንታኔ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን
እንደጨበጠ ፊውዳሊዝም ይውደም አለ። ከዘውዱ ስርዓት የተወሰነ ጠቃሚ ጐኖችን ልውሰድ ሳይል
መቶ በመቶ የአፄውን አገዛዝ አሽመድምዶ ኮነነው። ኮሚኒዝም፤ ሶሻሊዝምና ወዛደራዊነት
ይለምልም የሚል ርዕዮተ-ዓለም መጠቀም ሲጀምር መጭው በውል ሳይጠና አንዳንዶች
ባላወቁት ነገር እየዘለሉ፤ እየፎከሩና እያጨበጨቡ ደርግን አጀቡት፤ ከዚህ ውስጥ ብዙ የተለሳለሱ
ቢኖሩም መኢሶን በዋናነት ይጠቀሳል።
መድረሻው የማይታወቅ ኮሚኒዝምና ሶሻሊዝም በግራ እጅ መፈከር ሲታጀቡ
ሶቭየት-ኅብረትና ኩባን የመሳሰሉ የራሳቸውን ሰዎች በሰላይነትና በአማካሪነት አስገቡ። ባዕዳን አገጣሚውን በመጠቀም
አገሪቱ እንዳትረጋጋ ሁከት እየፈጠሩ ባሻጥር ስንት እውቅ የጦር መኮንኖች
አለቁ። በተቃራኒው የኤርትራና የትግራይ ተቃዋሚዎች ኮረኮንቻው መንገድ አስፋልት ሆነላቸው።
በወቅቱ የነበሩ ተቃዋሚዎች ኢዲህ፤ ኢሕአፓ፤ ሻዕቢያ፤ ጀበሃና ህወሀት ከደርግ ጋር የሞት የሽረት
ትግል አድረጉ። በዚህ ወቅት ብዙ ወጣትም ሆነ አዛውንት ደርግም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች
የሚያራምዱት ፖለቲካ ምንነቱ ሳይረዳቸው በቀላሉ በደጋፊነት በመሰለፍ ብዙዎች የሞትን ጽዋ እየተጎነጩ
በየሜዳውና በየጢሻው ወድቀው ቀርተዋል። በኋላም እንደታየው የመፈክሮች መነሻና መድረሻ
በውል ለይቶ ያላወቀ ድጋፍ ስጭ እንደ ተልባ የተሸራተተበት ጊዜም ተከስቶ ነበር። አንዳንዶች ለምን ደጋፊና
ተቃዋሚ እንደሚሆኑ በግራሞት ሲጠይቁ ምክንያቱን አጉልቶ የሚያሳይ ምንም ምክንያት
አልነበራቸውም።
ደርግ አንዳንዴ ሞኝና ተላላ ስለነበር ሰዎች ለምን እንደሚደግፉት ሳያጣራ ከጎኑ
እያሰለፈ የራሱን ሞት አፋጥኖ ኖሮ እንዳልነበር ሆኖ ቀረ። ደጋፊዎችም
ቢሆኑ ለምን እንደሚደግፉት ስለማያውቁ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ከደርግ ጋር መቆም ሳይችሉ ቀርተው ጅብ በበላ ዳዋ ተመታ እንዲሉ አብረው ታሹ፤
በንብረት ላይም ከፍተኛ ምዝበራ ተካሂዷል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ዳር ደንበሯ የተጠበቀ እንደነበር
ነጋሪ አያስፈልግም።
ከደርግ በኋላ ወያኔ ኢሕአዴግ ከጫካ ተነስቶ ከአፄውም ሆነ ከደርግ በጎ ጎኖች ልነሳ
ሳይል የነበሩትን ስርዓቶች ሙሉ በሙሉ ሐጢያተኛ በማለት አብጠለጠላቸው። ሕወሀት ጐንደርን በመከራ ጐጃምን በከዘራ
ሸዋን በጭብጨባ እንደማንም ብሎ በሰዎች ድጋፍ ትልቁ ቤተ መንግሥት ገባ። ይሁን እንጂ ለምን ድጋፍ እንደሰጡት በውል
የሚታወቅ ባይሆንም ሕወሀት ከደርግ ይሻል ይሆናል በሚል ቀቢፀ ተስፋ እንደሆነ ግምት መስጠት ይቻላል።
የዓላማውን ምንነት ሳይረዱ ድጋፍ መስጠት አደጋው
ከባድ መሆኑ አይቀሬ ነው። አምባገነኖች የዚህ ዓይነት ድጋፍ ስለሚቸራቸው ጦሩንም
ሆነ የአገሪቱን ሃብት በመቆጣጠር ፈጥነው የመደራጀት ኃይል
ይኖራቸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን፤ አሁን እየሆነ ያለውም
በዚህ የተነሳ ሳይሆን አይቀርም። አንድ ሰው ሊደግፍም ሆነ ሊቃወም
መብት ቢኖረውም መጀመሪያ ንጥር ባለ መልክ ማሰብን ግድ
ይላል። ነገር ግን ሳይታሰብና በድንገተኛ ሁኔታ የሚሰጥ ድጋፍ ትግሉ በተራዘመ ቁጥር
ደጋፊዎች እየቀነሱ የኋላ ኋላ ቡጥልቅ ብሎ ዝቅ ማለትን ልብ ይሏል።
ሕወሀት ኢሕአዴግ ቤተ-መንግሥት እንደገባ እግር ለመስደድ (ለመትከል) ሲል ዴሞክራሲያዊ ባሕሪነት
ለማሳየት ደርግን እያወገዘ የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት ያልፈነቀለው ድንጋይ
አልነበረም። አርሶ አደሩ የመሬቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ሌላም፤ ሌላም ያልተሞከረ ነገር አልነበረም። ሕወሀት
ከደርግ ይሻላል በሚል ተስፋ ወይም እምነትን ያላዘለ ድጋፍ የሕወሀትን አዲስ አበባ መግባት የተወሰኑ አካላት
ደግፈውት እንደነበር አይታበልም።
የሕወሀት (ኢሕአዴግ) መንግሥት ራሱን ሊጠቅም በሚያስችል ሁኔታና የፈረንጆችን ቀልብ ለመሳብ ነፃ
ፕሬስ፤ ሠራተኞች፤ ገበሬዎች፤ የትምህርት ተቋማት እስከ ፖለቲካ ድርጅቶች ወዘተ ድረስ የዴሞክራሲ መብቶችን የሰጠ የሚያስመስሉ
በአዋጅ ፈቅዶ ዴሞክራሲያዊ ሊያስመስሉ የሚችሉ ምርጫዎችም ተካሂደዋል። ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ነፃ ፕሬስና ኢሰመጉም
ተመስርተው ነበር። ነገር ግን ውስጡ ለቄስ እንዲሉ ሕጉን ያላከበረ በሚል ሽፋን
ንፁሐን ዜጐች በእስርና በሞት ይቀጣሉ። ባጠቃላይ ራሱ ያወጣቸውን አዋጆች መልሶ
በመቀልበስ ፀረ-ዴሞክራሲ፤ አሸባሪ ወዘተ ምናምን በሚል ማሰርና መግደል ያዘወትራል። ከዚህ በተጓዳኝ ሰዎች ኅሊናቸው የፈቀደውን
እንዳይናገሩ አንድ አምስት በሚል በየሰው ጉያ ሰላዮችን ያሰማራል። ሥልጣን የጨበጠው ሕወሀት
(ኢሕአዴግ) ቀስ በቀስ ሕዝቡን ማደንዘዝ ጀመረ። እርትራም ሄደች። ለምን እንደ ደገፈ
ሳይረዳው የቀረ ሕዝብ መከራ ሲወርድበት ማማረር የጀመሩ ታሰሩ፤
ተገደሉ፤ ተሰደዱ።
በሕወሀት ኢሕአዴግ አገዛዝ የአገሪቱ ሉዓላዊነት ተደፍሮ ኤርትራ ከእናት ኢትዮጵያ መገንጠሏ የሁሉን አንጀት
አሳርሯል። ይኽ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ዳር ደንበሯ እየተደፈረ መሬቷ ለባዕዳን አገራት ሰዎች
እየተቸበቸበ ነው። የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ዳር ደንበሯ መደፈሩ ብቻ
ሳይሆን ሕዝብ በተወለደበትና ባደገበት አገር እንደ ሰው የመኖሩ ሕልውናው ተደፍሯል።
መከራው በሁሉም ብሄር-ብሄረሰብ የደረሰ ቢሆንም ሕወሀት ኢሕአዴግ ገና በማለዳ
በረሃ ላይ እያለ የአማራውን ዘር ለማጥፋት እንደተነሳ ከሕወሀት አብራክ የተፈጠሩና
ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ አብረው የነበሩትና በድርጊታቸው ተጸጽተው አገራቸውንና ሕዝባቸውን ይቅርታ ጠይቀው ያጠፉትን
ለመካስ በቁርጠኝነት እየታገሉ ያሉት እነ አቶ ገ/መድህን አርአያ ነግረውናል። ተጣበበ ካልተባልኩ
እውነትም በተለየ ሁኔታ አማራ የሚባለው ብሔረሰብ በየጊዜው የሚደርስበትን የመከራ ግፍ
እያየን እንዳላየን እያለፍነው ነገ ለኔ የሚለው የተረሳ ይመስላል። ሰው በሁከት እየኖረ ብርሃኑ እየጨለመ፤ ሃብት ንብረቱ
እየተሞጠለቀ የሰዎች ፊት በሃዘን እየጠቆረ እንደሰው ተፈጥረው እንደ ሰው መኖር ከማይችሉበት ዘመን
ደርሰዋል።
በኢሕአዴግ ሽፋን የሚንቀሳቀሰው ሕወሀት ሕዝቡን ሊያደናግሩ የሚችሉ ዜናዎች ማሰራጨቱ
የተለመደ ነው። አንዱን ብሄረሰብ ከሌላኛው ጋር ለማጋጨት ወይም ነጥሎ ለመምታት ሲፈልግ መንግሥት ላቀደው
ለዓባይ ግድብና ለሌሎችም ፕሮጋራሞች የዚህኛው ብሄረሰብ ድጋፍ ሰጠ በማለት ምሸት ወይም ጠዋት በመንግሥት
ዜና ማሰራጫ ይተላለፋል።
በዚህ ጊዜ የውጩም ሆነ የውስጥ ተቃዋሚ የመንግሥት ዜና ውሸት
መሆኑን በማያሻማ አማርኛ መግለጽ ሲቻል በሽፍንፍኑ ተቀብለው እንዲህ ተደረገ የሚል ዜና ሲተላለፍ ይደመጣል።
በዚህ ጊዜ ተቃዋሚዎች የሚሉትን ዜና ሕዝቡ ሲያዳምጥ ተቃዋሚዎች አምነውበታል
በሚል ዜናውን ለመቀበል ይዳዳል። ይሁን እንጂ በበጐ ዓይን ከተመለከትነው በተቃዋሚዎች
እይታ የመንግሥትን የውሸት ዜና ያጋለጡ እየመሰላቸው ነው
በሚል ማለፍ ሳይሻል አይቀርም።
መንግሥት ከሕዝብ የሚደርስበትን ተቃውሞ በተለያየ መልክ እያለዘበ ይህው 22 ዓመት እያለፈው ነው።
መቃወምና መደገፍ በውል ተለይቶ ካልታወቀ ለትግሉ ስኬት አደናቃፊ ነው። ምክንያቱም ሊደግፉ
የሚፈልጉ አካላት ወይም ግለሰቦች መጀመሪያ ለመደገፍ በቂና አሳማኝ ሁኔታዎችን መመርመር ተገቢ ነው።
ነገሮች በውል ከተለዩ ሰዎች ከሚደግፉት አካል ጎን በመሰለፍ ያልተቋረጠ
ድጋፋ እየሰጡ መፈከሩን ከግብ ማድረስ ይቻላል።
በጠበንጃ አፈሙዝ ሥልጣን የያዙትን ታግሎ ለመለወጥ ብሎም መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ ለማምጣት
በሚደረገው ትግል ዙሪያ አወንታዊና አሉታዊ የሆኑ ያልተስተካከሉ ወይም ሊስተካከሉ የማይችሉ አጋጭ ሁኔታዎች በየጊዜው ይከሰታሉ።
ለአንድ ዓላማ ወጥ ትግል እንዳይካሄድ በተወሰነ መልክ ቀጥታውን መንገድ ወይም ያሰበውን መንገድ ትቶ ወደ ሌላ መንገድ
ገደም የሚሉ መኖራቸውን እየታዘብን ነው። በዚህ ምክንያት የፖለቲካ ድርጅቶች አንድ አገናኝ መንገድ ለመያዝ
ልዩነቶችን አጥብቦና አዋድዶ እጅ ለእጅ ተያይዞ የነፃነቱን ትግል ማጎልበት አዳጋች ይሆናል።
በአገር ቤትና በስደት የተደራጁ ፓርቲዎች በትግል ሥም ከ22 ዓመት በላይ ያለ ውጤት መታየታቸው
የሚያስገርም አይሆንም። ለምን ቢሉ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ደጋፊዎች በአንድ አላማ ዙሪያ አልተሰባሰቡም እና ነው። ከዚህ በተጨማሪ
መንግሥት ሕገ-ወጥ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑ እየታወቀ ካለማወቅም ይሁን ብሔርተኝነት እየተፀናወታቸው አንዳንዶች ድጋፍ
መስጠታቸው በጣም አሳዛኝ ነው።
መደግፍና መቃወም የራስ መብት ቢሆንም አገርና ሕዝብ ለሚጎዳ መንግሥት ለምን ድጋፍ ትሰጣላችሁ ተብለው
ሲጠየቁ ቀጥተኛ የሆነ መልስ መስጠት አይደፍሩም። በሌላ በኩል መንግሥትን የሚጠሉ ደግሞ
ለፖለቲካ ድርጅቶች ለምን ድጋፍ እንደሚሰጡ ሲጠየቁ የድርጅቱን ዓላማ ሳያገናዝቡ
በስሜት ወይም ከፓርቲው መሪ ጋር ቅርበት እንዳላቸው
ብቻ እንጂ የድርጅቱን አካሄድ በመመርመር አይደለም። በመሆኑም ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ በውል ተጢኖ
ከእምነት ጋር ያልተቆራኘ ስለሚሆን ውጤቱ አጉራሪ ይሆናል።
ከላይ ለማስጨበጥ እንደሞከርኩት የተቃዋሚና የደጋፊዎች ጠንካራና ደካማ ጎን እንደተጠበቀ ሆኖ
ወደፊት የተሻለና ለውጤት የሚያበቃ ትግል ለማካሄድ የሁሉ አገር በሆነችው ዙሪያ ጥርት ባለ መልክ የትግል አቅጣጫ
መያዝ አገሪቱን ከወደቀችበት መታደግ ይቻላል።
ያለው መንግሥት እጅግ የተናጋ መሆኑን ተቃዋሚዎች አዘውትረው ይናገራሉ፤
ይጽፋሉ። ባንፃሩ ወያኔ ኢሕአዴግ አለን የሚሉት ተቃዋሚዎች ከመጮህ ባለፈ አንድ ሆነው ተደራጅተው
ለድል እንደማይበቁ በድፍረት ሲናገር እየተደመጠ ነው። በእርግጥ ማጋነን አይሁንብኝ
እንጂ ንቋል።
መቼም እውነት እየመነመነች ለተወሰኑት እንደ እሬት እየሆነች ድክመት በተነሳ ቁጥር
የሚያኮርፉ መኖራቸውን በትዝብት እያየን ነው። ቢሆንም ድክመቱን ድክመት፤ ጥንካሬውን ጥንካሬ ብሎ መናገር ፍራቻ
ሳይሆን የማንነት መገለጫ ነውና ተስተካክለን በሁለት እግራችን ቆመን የሕዝብ ተስፋ መሆን እስካልተቻለ ድረሰ የራስን
ድክመት ሽፍኖ ወያኔን መሳደብ የሚበጅ አይመስለኝም። እውነቱም ይኽ መሆኑን አምንበታለሁ። እስኪ ሁላችን ኅሊናችንን
እንመርምር፤ በሥም ሁሉም መሪ አዋቂ አልሆነም እንዴ? እግዜአብርሄር ሰውን እኩል አድርጎ ቢፈጥረውም ሰዎች
በራሳቸው ጥረት ከሰዎች እንደሚለዩ አያጠያይቅም። ታዲያ ይህ ከሆነ መደማመጥና መከባበር
ለምን በራቸው ሊጠብ ቻለ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።
አሁንም አንባቢያን ልብ እንዲሉልኝ የምፈልገው ያለንበት ዘመን አስገራሚ ብቻ ሳይሆን ትዝብት ላይ
የሚጥል ነው። አልፎ አልፎ በተወሰነ መልኩ የውጩ ፖለቲካ ቡድናዊ ይዘትና ቁርጠኝነትን ያልተላበሰ፤ ግልጽነት
የሌለው ነው። ዌብሳይት ላይ የሚወጡ መጣጥፎችን ገለብ፤ገለብ አድርገን ሳይሆን አተኩረን ብናነባቸው
ይዘታቸው ከስድብ አያልፍም።
የውጩ ትግል ጠቀሚታነቱ አያጠራጥርም፤ ነገር ግን ለውጥ ሊመጣ የሚችለው አገር ቤት ውስጥበሚደረገው ትግል ነው። ሁሉም እንዲህ ብሎ
የሚያስብ ይመስለኛል። የ1966 ዓ.ም የየካቲትን አብዮት ምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። እንዲህ እንደዛሬው
በውጭ አገር መኢሶንና ኢሕአፓ ተመስርተው ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገው ነበር። ይሁን እንጅ መሠረታዊ
ለውጥ የመጣ አገር ቤት በተደረገው ትግል ነው። ስለዚህ የውጩ ትግል እንደተጠበቀ ሆኖ በዋናነት የውጩ ከአገር ቤቱ ትግል ጋር
ቢቀናጅ የትግሉ ውጤት ሊወሳሰብና ሊራዘም እንደማይችል ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
የመንግሥት የአፈና መዋቅር አላፈናፍን ባለበት ወቅት የአገር ቤት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ከፍተኛ ትግል እያደረጉ መሆኑ እውነት ነው። ለዚህ
ማስረጃ በየጊዜው በተለያየ መገናኛ እየቀረቡ ሲጠየቁ በድፍረትና በወኔ የመንግሥትን እኩይ ተግባር እያጋለጡ ነው። የተሳለ ቢላዋ ካለበት አገር ተቀምጠው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ
አደንቃለሁ። ስለዚህ የውጩ ኃይል የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል። ተወደደ
፤ተጠላም ከተሞክሮ አንፃር ሲታይ ውጭ ሆኖ መንግሥትን መቀየር ያስቸግራል። ይህ ሲባል የማንንም የትግል
ሞራል ዝቅ ለማድረግ ታስቦ ሳይሆን ከተጨባጩና ከእውነታው አንፃር በመነሳት ነው።
ከዛሬ ነገ መንግሥት የተሻለ ሥራ ይሠራል በሚል
ሕዝብ ለረጅም ዓመታት ተዘናግቷል። ቢሆንም በየጊዜው እልቂቱ ከመባባስ አልቦዘነም። ኢትዮጵያን መታደግ
የሚችለው ወጣቱ መሆኑ አያጠያይቅም። ከዚህ በፊትም ለውጥ የመጣ በወጣቱ ትግል መሆኑ አይታበልም።
ወጣቱ ከዘመኑ ፖለቲካ ጋር መጓዝ የሚችል ፤የመመራመር ዕድል ያለው በመሆኑ ዛሬም ወጣቱ
ተደራጅቶ ከተንቀሳቀሰ የገዥዎችን ዕድሜ በማሳጠር አገሪቱን መታደግ
ይችላል። ይህ ሲባል ግን ልዩነቶችን በማጥበብ የተባበረ ትግል መጠየቁ እርግጥ
ነው። ሕዝብ ነፃነቱን እንደተነጠቀ አይኖርም። ለዚህ ማስረጃ ከሌሎችና ደቡብ አፍሪካም፤
ዘምባቢዌና በአሜሪካ የጥቁሮችን ትግል ልብ ማለት ይቻላል።
ሕዝብ ከቀዬው መፈናቀል፤ እስር፤ ስደትና ሞት ብሶታል። ስለዚህ ካለፈው ተሞክሮ አዲስ የትግል ስልት
ከተቀየሰና በጋራ ተንቀሳቅሶ ትግል ከተጀመረ ግደል ሲሉት የሚገድል ወታደር ሳይቀር ከሕዝብ ጐን እንደሚሰለፍ
በርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል። ሰው ባገሩ ተወልዶ እንደሰው መኖር ካቃተው
የመጨረሻው እድል እየገደሉ መሞት ነው። በባርነት ሆኖ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ትርጉመቢስ ስለሚሆን
ሁሉም ማሰብ ያለበት ዘመኑ የሥልጣን ሳይሆን የነፃነት ጥያቄ መሆን ይገባዋል።
በዘርና በሃይማኖት የሚከፋፍል መንግሥት ዘላለማዊ አይደለም፤ አምባገንነኖች ዘላለማዊ አይደሉም፤
መጨረሻቸው ውድቀት መሆኑ የማይታበል ሃቅ ነው። ነገር ግን ለመኖር እየተነፈሱ ያሉት የሕዝቡ ወይም የተቃዋሚ
ድርጅቶች አንድነት አለመፍጠር ነው።
ተቃዋሚዎች አንድ ያልገባቸው ነገር ቢኖር ኢንተርኔት ላይ ሆነው መንግሥት ተናግቷል፤
ውስጡ ተቦርቡሯል፤ አሁኑን የሽግግር መንግስት፤ ሸንጐ ምናምን የሚለው ጋጋታ ውጤት ያመጣል ማለት
ሞኝነት ነው፤ ለትግሉ በጣም አደናጋሪና ያልሆነ ተስፋ ሰጭ ስለሆነ መቆም አለበት። ስለዚህ
ሳይዘናጉ የውጩን ከአገር ቤቱ ትግል ጋር በማቀናጀት ይበልጥ ወጣቱን ማደራጀት ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ አገሬ
ሕዝቤ የሚል ዜጋ በአንድነት መቆም ካቃተውና ዋናውን ጠላት ትቶ እርስ በርስ መቦጫጨቅ
በእሳት ላይ እንደመጫዎችት ያስቆጥራል የሚል እምነት አለኝ።
ሥልጣንና ገንዘብ ዘላለማዊ አይደሉም፤ ገንዘብ ይጠፋና ድህነት ይመጣል ፤
ሁሉም በየተራ አላፊዎች ናቸው፤ ታሪክ ግን ሞቶ አይሞትም። አንድ ምሳሌ መጠቅስ
የሚቻል ይመስለኛል። ለኢትዮጵያም ሆነ ለሕዝቦቿ እልቂት የጥፋት ማህንዲስ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ
እንዲሁም የኦርቶዶክስ አከርካሪ በጣሽ አባ ጳውሎስን ስናስታውስ የሥልጣንና የሃብት ጉዳይ የት ደረሰ ብሎ መጠየቅ
ተገቢ ነው:: አገርን፤ ሕዝብንና ሃይማኖትን ለማጥፋት ያቀዱትን ዓላማ ሳያሳኩ በድገንት ታመውና
ሰው እግዜር ይማራችሁ ሳይላቸው የምድሪቱን ዓለም ጥለው መሄዳቸውን ልብ ይሏል። ታዲያ ለየትኛው
እድሜ ነው በባርነት ለመኖር እርስ በርሳችን የምንጨካከነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ
ይመስለኛል። አገርና ሕዝብ እየጠፋ መሆኑ ሃቅ ነው። ታዲያ ለምን
ሆድ አደር መሆን ተፈለገ? እያንዳንዱ የመኖር ሕልውናው እስከ መቼ
መሆኑን የሚያውቅ አለ? የሌላውን መልስ ባላውቅ ይህን ያህል ዓመት ነው የሚል መልስ
የለኝም።( አላውቅም ነው መልሱ )
ሆድ ክፉ ነው፤ አገርና ሕዝብ ያስረሳል። ለሆድ ማደር ብሄርን
አይለይም፤ ለሆድ ማደር ከጊዜያዊ ጥቅም አልፎ ረጅም ዓመታትን አያስጉዝም። በሰለጠነውና ሆድ ጠግቦ በሚያድርበት ዓለም
የሚኖሩ የመንግሥት ደጋፊዎች ፈጣሪ ልብ ሰጥቷቸው ወደ ሕዝባቸው
ቢመለሱ በኢትዮጵያዊነት እንጅ በክደት ደረጃ ሊፈረጁ እንደማይችሉ ከዚህ በፊት በጣሊያን
ወረራ ሕዝብ ሆደ ሰፊና ይቅር ባይነቱን አስመክሯል። በመሆኑም ያለፈው አልፎ ጥርጣሬን አስወግዶ ለነፃነት ትግል
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልባዊ ድጋፍ ቢያደርግ የባርነት ቀንበራችን ይሰበራል።
መንግሥት እድሜውን ጨርሷል፤ በውስጡ መተማመን የለም፤ ባለሥልጣናት በሙስና
ተዘፍቀዋል። ምን ሊደርስባቸው እንደሚችል ውቃቢያቸው እየነገራቸው ሁሌ ደም
ለመቋደስ ሕፃን፤ ወጣትና አዛውንት ሳይቀር በጥይት እየፈጁ ነው፤ ደም አስክሯቸዋል።
ያለፈውን ትተን ሰሞኑን ባህር -ዳር ከተማ ውስጥ የተደረገውን ዜና በኢሳትና
ኢትዮ ሜዲያ ላይ ተመልክተናል።ይህ በቂ ማስረጃ ነው። ሌላ ማስረጃ የሚፈልግ ካለም መጨመር ይቻላል። አገርን
ሊታደግ በሚችል መንገድ የተቃዋሚዎች እኔ በልጥ ትግል አስፈላጊ ቢሆንም
መንግሥት እድሜውን ጨርሷል ከማለት ውጭ ሊታይና ሕዝብ ሊከተለው የሚችል የትግል
እስትራቴጅ የላቸውም። ይኽም በጣም አሳዛኝ ጉዳይ ነው። ይህን ድክመት ከቶም
ሸፍኖ ማስቀረት አይቻልም የሚሞክር ካለም ትዝብት ይሆናል።
አቶ ሥልጣን አደገኛ ነው። ተቃዋሚዎች አገር ከሚያጠፋው መንግሥት የተሻለ ለመሆን
በመጀመሪያ ደረጃ ዴሞክራሲን መልመድ፤ አገራዊ ራዕይ ካላቸው ወገኖች ጋር ግንባር ለመፍጠር ዝግጁ
መሆን፤ አስፈላጊውን የትግል ስልት በመጠቀም ቁርጠኛ መስዋትነት መላበስ፤ ከአፍ ውጭ ተግባራዊ
ኢትዮጵያዊነትን ማስቀደም፤ሌሎችንም አገራዊ መስፈርቶችን ይዞ ከመንግሥት የተሻለ ሆኖ ለመገኘት አንድነትና ኅብረትን
በማጠንከር ብሎም ለድል ሊያበቃ የሚችል የጋራ የትግል ሥልት ማድረግ አማራጭ መሆኑን ድርጅቶችም
ደጋፊዎችም ልብ ሊሉት ይገባል። በዚህ ሁኔታ ትግል ከተካሄደ ሕዝብ የሚመርጠውን
ስለሚያውቅ ሥልጣን ላይ መውጣት ይቻላል። ነገር ግን በግር ግር የሚያዝ ሥልጣን ለሕዝብ
ጥቅም ሰላማይውል አንፃራዊ በሆነ መንገድ ከግል ዝናና ከንዋይ የፀዳ ስለማይሆን አገራችን ሁሌም ከጥፋት ነፃ
አትሆንም። ስለዚህ የ22 ዓመት ተሞክሮ ትምህርት ሰጥቶን ኢትዮጵያን እንታደጋት።
No comments:
Post a Comment