Wednesday, May 1, 2013

ይድረስ ለአፈናቃይ “መንግስታት”




ሕዝብን ማፈናቀል ዘር የማጥፋት ወንጀል
(ጄኖሳይድ) ነው
(ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ በሳምንታዊው የሰንደቅ ጋዜጣ በ8ኛ ዓመት፣ ቁጥር 397፣ የሚያዝያ 9 ቀን 2005 ዓ.ም እትም ላይ “ብሔር ተኮር የሕዝብ መፈናቀል ጉዳይ መንግስት ግልጽ አቋም ሊይዝና ሊያራምድ ይገባል” በሚል ርዕስ የቀረበው ርዕሰ አንቀጽ ነው።
ሰንደቅ ጋዜጣ ከምስረታዋ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለችና እያደገች መምጣቷን ብቻ ሳይሆን፤ ለሌሎች ጋዜጦች አርኣያ መሆን የሚችል የአሰራር ስርዓት ማዳበሯን ተገንዝቤአለሁ። ጋዜጣዋ በተለይ ከቅርብ ጊዜአት ወዲህ የምታቀርባቸው አነጋጋሪ ዜናዎች እና ገዢው ፓርቲ እና መንግስት “እንዲህ ቢያደርጉ” በሚል መንፈስ የሚቀርቡ ርዕሰ አንቀፆች አቀራረባቸው ብቻ ሳይሆን ይዘታቸው ጭምር ይበል የሚሰኙ መሆኑንም አስተውያለሁ።
ከላይ ቀንና ቁጥሩን በጠቀስኩት ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ የቀረበው ርዕሰ አንቀጽ ትኩረት ያደረገው ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ክልል ተወላጆችን በተመለከተ ሲሆን፤ ተመሳሳይ “ብሔር ተኮር” መፈናቀሎች በተለያዩ ክልሎች መካሄዳቸውን በማውሳት እንዲህ ያለው የማፈናቀል ሂደት ይቆም ዘንድ መንግስት ግልጽ አቋም ሊኖረው እንደሚገባ ሰንደቅ አሳስባለች። በዚህ ጉዳይ ላይ ሰንደቅ ብቻ ሳትሆን ሌሎች ጋዜጦችም የዜና ሽፋን መስጠታቸውንና በአንዳንድ ድረ ገፆችም ላይ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኖ መሰንበቱን ተመልክቻለሁ።
ይኸው “ብሔር ተኮር” የማፈናቀል እርምጃ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተደጋጋሚ የተፈጸመና ሊቆምም ያልቻለ የታሪካችን አሳፋሪ ክፍል አድርጎ መውሰድ የሚቻል ይመስለኛል። ከሁሉም ከሁሉም የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ከስህተታችን ለመማር አለመቻላችን ብቻ ሳይሆን በአንዳንድ ክልሎች ተደጋግሞ ሲፈጸም መስተዋሉ ጭምር ነው።
በዚህ የማፈናቀል ሂደት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያልተሳተፈና “ከደሙ ንፁህ ነኝ” ማለት የሚችል ክልል የለም ማለት ይቻላል። ምክንያቱም አንዳንድ ክልሎች በማፈናቀሉ ሂደት በቀጥታ ባይሳተፉ እንኳ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙ ማፈናቀሎችን እያዩና እየሰሙ በዝምታ ማለፋቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።
የችግሩን መጠን በአግባቡ ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ ባለፉት 21 ዓመታት ከተፈጸሙት የማፈናቀል ሂደቶች የተወሰኑትን አለፍ አለፍ እያልን እንመልከት። የመጀመሪያው “ብሔር ተኮር” የማፈናቀል እርምጃ የተወሰደው በሽግግሩ ዘመን በምዕራብ ሐረርጌ “ዎተር” እና “በደኖ” በተባሉ አካባቢዎች ለረጅም ዓመታት በአካባቢው የኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆችን “ከክልላችን ውጡ” ከማለት አልፈው በጅምላ በመጨፍጨፍ “እንቁፍቱ” (ገደል) ውስጥ የተጣሉበት ሁኔታ ይመስለኛል። ይህ እርምጃ ትክክል አለመሆኑን በመገንዘብ በወቅቱ የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚቴ አቋቁሞ እንዲጣራ ማድረጉንም አስታውሳለሁ። ያንን “ብሔር ተኮር” ዘር የማጥፋት እርምጃ በፊታውራሪነት ያስፈጸመው ኦነግ መሆኑን አጣሪ ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት ገልፆ እንደነበርም አይዘነጋም። በወቅቱ የኦነግ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ ፓርቲያቸው በድርጊቱ እጁ እንዳለበት አምነው ምክር ቤቱ ፊት ቀርበው የእምነት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን፣ ይቅርታም ጠይቀዋል።
የሌሎች አካባቢዎች ባለስልጣናት ከዚህ አሳፋሪ ድርጊት ትምህርት ሊወስዱ ባለመፈለጋቸው በበደኖና እና በዎተር ከተፈጸሙት ጭፍጨፋዎች በመጠን፣ በዓይነትና በአፈጻጸማቸው መለስተኛ የሆኑ መፈናቀሎች አነስተኛ የቆዳ ስፋት ባላት በሐረሪ ክልል ጭምር በቀጣይ ዓመታት ተፈጽሟል።
የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ በሐረር ከተማ ተገኝቼ አንዳንድ ወጣቶችን አነጋግሬአለሁ። በወቅቱ ያነጋገርኳቸው የሐረር ወጣቶች “እኛ የተወለድነው፣ ያደግነው፣ የተማርነው፣… እዚህ ከተማ ነው። ነገር ግን የሐረሪ ብሔር ተወላጅ ባለመሆናችን ዲግሪ ቢኖረንም በክልሉ የመንግስት መ/ቤቶች መቀጠር አልቻልንም። በዚህም ምክንያት ብዙ ወጣቶች የሚሰሩት በሌሎች ታዳጊ ክልሎች ነው። ….. የሐረሪ ብሔር ተወላጅ ያልሆነው ሁሉ ጀጎል ውስጥ ተወልደን ለዘመናት ከኖርንበት የቀበሌ ቤት እንድንወጣና ጀጎል የሐረሪ ብሔር ተወላጆች ብቻ መኖሪያ እንድትሆን ተደርጓል::… ሌላው ቀርቶ ጀጎል ላሉት ሐረሪዎች እና ከጀጎል ውጪ ላለነው የሶማሌ፣ የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የጉራጌና የሌላ ብሔር ተወላጆች ውሃ የሚሰራጨው ፍጹም አድሎአዊና አግላይ በሆነ ሁኔታ ነው….” ማለታቸውን አስታውሳለሁ። እንዲህ ያለ የለየለት የዘረኝነት አታሞ የሚደለቅባትና “ብሔር ተኮር” አድሎና መድሎ የሚፈጸምባት ሐረር፣ በዚያው ወቅት “የሰላምና የመቻቻል” ተምሳሌት ተደርጋ መሸለሟ እስከ አሁን ድረስ ይገርመኛል፣ ይደንቀኛል።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም ቢሆን በሶማሌ እና በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መካከል አንዱ ሌላውን የመግፋትና “ከተማዋ የእኔ ብቻ መሆን አለባት” የሚለው አስተሳሰብ ተደጋጋሚ ግጭቶችን ቀስቅሶ እንደነበር ይታወሳል። ለዚህም ነው ዛሬ የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባዎች በየሁለት ዓመት ተኩል በሶማሌና በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች በፈረቃ እንዲያዝ የተደረገው።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች “ብሔር ተኮር” የአባራሪና የተባራሪ ትእይንት በተደጋጋሚ ተስተውሏል። እንደ አማራ ክልል “ብሔር ተኮር” ተባራሪዎች ብዙ አልተነገረለትም እንጂ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተባረዋል። የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ በወለጋና በቤንሻንጉል አጎራባች ወረዳዎች የደረሰውን “ብሔር ተኮር” ጭፍጨፋ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሲያጣራ እንደነበር አይዘነጋም። በደቡብ ክልል በከፋ፣ በሸካ፣ በሸክቾ፣… አካባቢዎች፤ እንዲሁም የዛሬ ዓመት ገደማ በጉራፈርዳ ወረዳ የተደረገውን “ብሔር ተኮር” ማፈናቀል የምናስታውሰው ይመስለኛል።
ኢህአዴግ በአንድ አካባቢ የተከናወነ መልካም ተሞክሮን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ወስዶ የማላመድና የማስፋፋት (Scaling up) አሰራርን እንደሚከተል ተደጋግሞ ታይቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ “ብሔር ተኮር” የማፈናቀሉም ሂደት እንደ “መልካም ተሞክሮ” ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው እየተሸጋገረ እነሆ ዘንድሮ ላይ ደርሰናል።
ዘንድሮ “ብሔር ተኮር” የማፈናቀልና የማባረር ወርተራው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው። የዘንድሮውን ከቀዳሚዎቹ ለየት የሚያደርገው ከተፈናቃዮች መካከል ሁለት ነፍሰ ጡሮች ተባረው ወደ ትውልድ ቀያቸው እየተጓጓዙበት በነበረው አውቶቡስ ውስጥ መውለዳቸው እና የአፈናቃዩ ክልል ፕሬዝዳንት ማፈናቀሉ ስህተት መሆኑን ተቀብለው ተፈናቃዮች እንዲመለሱ መወሰኑን መግለጻቸው ነው። ፕሬዝዳንቱ የወሰዱት እርምጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ከአንድ ኃላፊነት ከሚሰማው አስተዋይ አመራር የሚጠበቅ በጎ እርምጃ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል።
በአጠቃላይ፤ ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በርካታ “ብሔር ተኮር” የማፈናቀል እርምጃዎች በተለያዩ ክልል የመንግስት ኃላፊዎች ሆን ተብሎ ታቅዶና ታስቦበት መፈጸሙ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው። የጉዳዩን አሳሳቢነት በበቂ ሁኔታ ለመገንዘብ ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች በቂ ናቸው የሚል እምነት አለኝ።
ለመሆኑ የማፈናቀሉ ምክንያት ምንድነው?
የ“ብሔር ተኮር” ማፈናቀሉ ምክንያቶች “ተራ ጥላቻ፣ ቂም፣ ቁርሾና ምቀኝነትን” ጨምሮ በርካታ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። ይሁን እንጂ፣ በሰንደቅ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ ላይ እንደተገለጸውና መፈናቀሎቹ በተፈጸሙባቸው ጊዜአት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እንደተንጸባረቀው ተደጋግሞ የሚጠቀሱት ሁለት ምክንያቶች ናቸው። እነሱም፤ አንደኛ “በሕገ ወጥ መንገድ ሰፈርክ፣ ደን ጨፈጨፍክ” የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ “የአካባቢው ተወላጆች ሀብትና ንብረት ሳያፈሩ፣ ሕይወታቸው ሳይለወጥ አንተ ትናንት መጥተህ በእነርሱ መሬት ላይ ሀብት አፈራህ፣ ገንዘብ አገኘህ፣ ተለወጥክ” የሚል ነው።
መገናኛ ብዙሃኑ እንደገለጹት፣ እነዚህ ምክንያቶች የ“ብሔር ተኮር” ማፈናቀሉ እውነተኛ ምክንያቶች ከሆኑ፣ ድርጊቱ “ዘርን የማጥፋት” (Genocide) ወንጀል መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል። ይህንን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ “ዘርን የማጥፋት” (Genocide) ወንጀል በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተሰጠውን ብያኔ (Definition) እንደሚከተለው እንመልከት።
እ.ኤአ በ1951 ዓ.ም በ130 አገሮች የጸደቀው የተባበሩት መንግስታት ኮንቬንሽን አንቀጽ 2defines genocide as: “any of the following acts committed with intent to destroy, in whole or in part, a national, ethnical, racial or religious group, as such: (a) Killing members of the group; (b) Causing serious bodily or mental harm to members of the group; (c) Deliberately inflicting on the group conditions of life calculated to bring about its physical destruction in whole or in part; (d) Imposing measures intended to prevent births within the group; (e) Forcibly transferring children of the group to another group.”
በዚህ ብያኔ (Definition) መሰረት፤ ሰዎችን በዘራቸው፣ በጎሳቸው ወይም በሃይማኖታቸው፣… ምክንያት ሆን ብሎ፣ አቅዶና አስቦበት መግደል፣ አካላዊና መንፈሳዊ ጥቃት ማድረስ፣ ሆን ብሎ በማፈናቀል ጉዳት ማድረስ፣… “ዘርን የማጥፋት” (Genocide) ወንጀል አድርጎ መውሰድ የሚቻል ይመስለኛል። 
“ዘርን የማጥፋት ወንጀል” የሚለውን ለጊዜው እንተወውና “ደን ጭፍጨፋ” ወደሚለው ምክንያት እንመለስ። በግሌ እንኳን ደንን ያህል የሀገርንና የህዝብን ሕልውና የሚነካ ጉዳይ (ኮልጌትንና የጥርሽ ብሩሽ እንደልብ ባለበት ዘመን) ለጥርስ መፋቂያ የሚሆን ቅጠል መበጠስም መወገዝ አለበት። ይሁን እንጂ፣ ደን መጨፍጨፉን የምናስታውሰው እነዚህ “ሕገ ወጦች” ለአስር እና ለሃያ ዓመታት ከኖሩና ሀብት ካፈሩ በኋላ ነው እንዴ? መፍትሄውስ “ደን ስለጨፈጨፋችሁ፣ ያፈራችሁትን ሀብትና ንብረት ቁጭ አድርጋችሁ፣ ማቄን ጨርቄን ሳትሉ ወደ መጣችሁበት ተመለሱ” ማለት ነው? እንበል፣ ደን የጨፈጨፉትና ሕገ ወጥ ሰፈራ የመሰረቱት ሰዎች የዚያው ክልልና የዚያው አካባቢ ተወላጆች ቢሆኑ ኖሮ ወደ የት ይባረሩ ነበር? ወይስ ያካባቢው ተወላጅ ከሆነ ያሻውን ወንጀል የመስራት መብት አለው ነው ነገሩ? በኔ እምነት እንዲህ ያለው እርምጃ በየትኛውም ደረጃ ኃላፊነት በተሰጠው የመንግስት አካል ሊፈጸም የማይገባው ነው።
እነዚህ “ሕገ ወጦች” ከሰሜንም ይምጡ ከምስራቅ፣ ከምዕራብ ይፍለሱ ከመሀል አገር ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ጥርጥር የለውም። የሀገሪቱ ሕገ መንግስት ደግሞ ዜጎች በፈለጉት አካባቢ ሄደው ለመስራት፣ ሀብት ለማፍራትና ለመኖር እንደሚችሉ ደንግጓል። እናም እነዚህ “ሕገ ወጥ” የተባሉት ሰዎች ከተወለዱበት ክልል ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ሌላ ክልል ሄደው ኑሮአቸውን መመስረታቸው ከቶም ወንጀል ሊሆንና ወደ መጣችሁበት ተመለሱ ሊባሉ አይችሉም። ደን መጨፍጨፍና ሕገ ወጥ ሰፈራ ማካሄድ ግን ወንጀል ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ፤ ዜጎች (ሰሜንም ይወለዱ ደቡብ) ሕግ ጥሰው፣ ስርዓት አፋልሰው፣ ጥርስ ሰብረው፣ ቋንጃ ቆርጠው፣ ንብረት ዘርፈው፣ ቤት አቃጥለው፣ እንስሳ ነድተው፣ ወይም ሌላ ወንጀል ሰርተው ቢገኙ በአገሪቱ ሕግ መሰረት ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲቀጡ ይደረጋል እንጂ “ወደተወለዳችሁበት ቀዬ ተመለሱ” ማለት ተገቢም ሕጋዊም አይመስለኝም። እናም የክልል መንግስታትም ሆኑ የአካባቢ አስተዳደሮች ደን በመጨፍጨፍም ሆነ በሕገወጥነት ሰፍሮ ያገኙትን የሌላ ክልል ተወላጅ ኢትዮጵያዊ በሕግ መሰረት እንዲቀጣ የማድረግ እንጂ እንደ ጠላትና ወራሪ ኃይል ሀብትና ንብረቱን ወርሰው ወይም የትም እንዲበትን አድርገው “ከክልላችን ውጣ” ብለው የማባረር ስልጣንም መብትም የላቸውም። እንዲህ ያለ ድርጊት ፈጽመው ከሆነም፣ ድርጊቱ ዘርን የማጥፋት ወንጀል (Genocide) ከመሆን ውጪ ሌላ ስያሜ ሊሰጠው የሚችል አይመስለኝም።
በየአካባቢው ሕገ ወጥ ሰፈራም ሆነ ደን ጭፍጨፋ መኖሩን መካድ የሚቻል አይመስለኝም። ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑም እርግጥ ነው። ወንጀለኞችን የዚህ ተወላጅ ነህ የዚያ እያሉ በማፈናቀልና በማባረር ግን የችግሩን ምንጭ ማድረቅ የሚቻል አይመስለኝም። እንዲህ ያለው እርምጃ ከበስተጀርባው ቂም፣ ቁርሾና ምቀኝነትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ፍላጎት መኖሩን ያመላክት እንደሆነ እንጂ አንዳችም ፋይዳ የለውም።
ከአንድ የሆነ አካባቢ የተፈናቀሉ የስጋ ዘመዶች ያሉኝ እስኪመስል ድረስ ለተፈናቃዮች ጥብቅና የቆመ ሃሳብ ማቅረቤ ለእኔም ተሰምቶኛል። እናም፣ የጽሁፌን ሚዛን ለመጠበቅ ስል በተፈናቃዮች በኩል የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለመጠቆም እወዳለሁ።  
በመሰረቱ “ብሔር ተኮር” የማፈናቀሉን ተግባር የሚፈጽሙትና የሚያስፈጽሙት ኃላፊነት የተሰጣቸው የመንግስት አካላት እንደሆኑ ስለሚነገርና (ለመሆናቸው ጥርጥር የለውም) የእነርሱ ጥፋት እንደ አንድ ተራ ዜጋ ተራ ጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ባለመሆኑና ፖለቲካዊ አንደምታም ስላለው በእነርሱ በኩል የሚስተዋሉ ችግሮችን ቀዳሚ አድርጌ አቀረብኩ እንጂ ተፈናቃዮቹ እና ተፈናቃዮቹ የፈለሱባቸው ክልል የመንግስት ኃላፊዎችም ቢሆኑ እንከን የለሽ፣ ጥፋት አልባ ናቸው የሚል እምነት የለኝም።
ከሁሉ በፊት፣ ዜጎች በመላ ሀገሪቱ ተንቀሳቅሰው የመኖርና ሀብት የማፍራት ሕገ መንግስታዊ መብት ያላቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን መብታቸውን የሚያገኙበት ሕግና ስርዓት ሊበጅ እንደሚገባ አምናለሁ። አንድ ሰው በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት አለህ ስለተባለ የትም በመሄድ ደን ይጨፍጭፍ፣ ዘር ማንዘሩን በመሰብሰብ ሕገ ወጥ  ሰፈራን ያስፋፋ ማለት አይደለም። ሀገሪቱ ውስን ሃብት (Scarce Resource) ነው ያላት። ያን ውስን ሀብቷን አግባብ ባለውና ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ካልተጠቀምንበት ደግሞ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች “Tragedy of the Commons” የሚሉት ነገር መከሰቱ ጥርጥር የለውም።
የየአካባበው ተወላጆች ለሕግ የበላይነት ተገዥ ሆነውና መንግትንና ሕግን ፈርተው በተሰጣቸው ኩርማን መሬት ሕይወታቸውን ሲመሩ፣ ደፋሮችና ሕግ የለሾች ከአንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢዎች ጋር በመመሳጠር ያገኟትን “አንገት ማስገቢያ” መሬት ወደላይም ወደታችም እየለጠጡ በማስፋፋት ለዘመናት ተጠብቆ የኖረን ደን መመንጠር ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው። በግሌ ለእንደዚህ ዓይነት ወንጀለኞች ጥብቅና የመቆም ፍላጎት የለኝም።
ለመሆኑ እነዚህ ዜጎች ከትውልድ ቀያቸው ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ የሰፈሩት በምን ሁኔታና መንገድ ነው? ባለፉት 21 ዓመታት በመንግስት እውቅና የተሰጠው የሰፈራ ፕሮግራም የተካሄደ ቢሆንም፤ ፕሮግራሙ የተፈጸመው ሰፋሪዎችን ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ወስዶ በማስፈር ሳይሆን፣ በአንድ ክልል ውስጥ ያሉ ሰፋሪዎችን ከአንድ ዞን ወደ ሌላው በመውሰድ የተከናወነ ነው። ከዚህ ውጪ ግን የአንድ መንደር ሰዎች በራሳቸው ፍላጎት፣ በተንጠባጠበና ቀድሞ ሄዶ የሰፈረው ኑሮውን ካደላደለ በኋላ በመጀመሪያ ቤተሰቡን፣ ቀጥሎ ዘመዶቹን፣ ቀጥሎ ጓደኞቹንና ጎረቤቶቹን አስከትሎ በመሄድ ቀዳሚው የያዛትን መሬት በመለጠጥ፣ ከእርሻው ጎን ያለን ጫካ በመመንጠር የተከናወነ ሕገ ወጥ ሰፈራ ነው። እንግዲህ ብዙዎቹ “ብሔር ተኮር” ማፈናቀሎች እየተከሰቱ ያለው በዚህ መልኩ የሰፈሩትን ሕገ ወጦች ለማስወገድ በሚል ሰበብ ይመስለኛል።
ይህንን የሰፈራና የማፈናቀል ሁኔታ ሳውጠነጥን በርካታ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች ይደቀኑብኛል። ሁለት ክልሎችን በሚያዋስኑ ወረዳዎች የሚኖሩ ዜጎች የግጦሽም ይሁን የእርሻ መሬት ፍለጋ መንቀሳቀስ፣ ደን መመንጠርም ይሁን መንደር መስርቶ መኖር የህዝብ ቁጥር በጨመረ ቁጥር የሚከሰትና ወደፊትም የማይቀር እንደሆነ አስባለሁ። እንዲህ ያለው ሰፈራ ኢኮኖሚያዊ ከሆነ ችግር የለውም። ችግር የሚሆነው የአጎራባች ክልልን ለም መሬት ወደ ሌላው ክልል እንዲጠቃለል ለማድረግ ታስቦ የተደረገ እንደሆነ ነው። ይህ ዓይነቱ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ወለጋ ዞን የተደረገው ዓይነት አካሄድ ፖለቲካዊ ይዘት ስላለው መላ ሊበጅለት ይገባል።
እኔን ግርም የሚለኝ ግን ከጎጃም ተነስቶ ጉራፈርዳ ወይም ከወሎ ተነስቶ ሸክቾ የሚደረገው ሰፈራ ነው። እንዲያው ነገር ፍለጋ ካልሆነ በስተቀር ለጎጃም ነዋሪዎች ቅርብ የሆነው ፓዌ ነው ጉራፈርዳ? ወይስ ሁመራ ነው ሸክቾ? ወይስ መተማ? በርግጥም የፍልሰቱ መንስዔ የእርሻ መሬት ፍለጋ ነው ከተባለ በስነ ልቡናም ሆነ በሌላ፣ ለአማራ ክልል ሰዎች የተሻለው ወደ ሁመራ ወይም ወደ መተማ ማቅናቱ ነው እንጂ ወደ ጉራፈርዳ መውረዱ አይመስለኝም። ስለሆነም እንዲህ ያለው አካሄድ ቢታረም መልካም ነው።
ከላይ የአፈናቃይ ክልል የመንግስት ኃላፊዎችን በሰፊው እንደተቸሁ ሁሉ የተፈናቀሉ ዜጎች የመጡባቸው ክልል ኃላፊዎችም ቢሆኑ ተጠያቂ መሆናቸውን ለመግለጽ እወዳለሁ። በዚህ ረገድ የአማራ ክልል አመራር አካላት በዋናነት ተጠያቂዎች ናቸው። ባለፉት 21 ዓመታት ከተፈጸሙት “ብሔር ተኮር” ማፈናቀሎች በርካታዎቹ ከአማራ ክልል የመጡ ዜጎች ጋር የተያያዙ ነበሩ። ታዲያ የክልሉ ገዥ ፓርቲና የመንግስት አካላት በተደጋጋሚ እየተስተዋለ ያለን ችግር እንደ ችግር ወስደው ተገቢውን ጥናት በማድረግ መፍትሄ ሊያበጁለት ሲገባ፣ መሸኛ ጽፈው በመስጠት ሰፋሪዎችን መርቀው የሚሸኙበት ሁኔታ ነው የሚስተዋለው።  
“ካንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም” እንዲሉ የክልሉ ባለስልጣናት ለክልሉ ተወላጆች እውነተኛ ወኪሎችና ተቆርቋሪዎች ነን የሚሉ ቢሆን ኖሮ በእኔ ግምት ሁለት ነገሮችን ማድረግ ይችሉ ነበር።አንደኛ፤ በክልሉ ውስጥ የእርሻ መሬት ችግር ያለባቸውን ዜጎች በመለየት በዚያው በክልሉ ውስጥ ባሉ ለሰፈራ ምቹ በሆኑ አካባቢዎች ለማስፈር እቅድ አውጥተው መስራት። ሁለተኛ፤ በክልሉ ለእርሻ ምቹ የሆነ መሬት ያለ መሆኑን በመግለጽ በተለያዩ አካባቢዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሰፍረው የስጋት ኑሮ ለሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ጥሪ ማድረግ፣ እንዲመለሱ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ተመላሾች በነበሩበት አካባቢ ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ይዘው የሚመጡበትን ሁኔታ ከተለያዩ ክልሎች ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ሁኔታ ማመቻቸት ይችሉ ነበር። እኔ አቶ አያሌው ጎበዜን ብሆን ኖሮ ሁልጊዜ “አማራ ተፈናቀለ፣” የሚለውን ዜና መስማት ስለማልፈልግ ይህንን እርምጃ እወስድ ነበር። አማራ ክልል እንደ ሌሎቹ ክልሎች ሁሉ ለተወላጆቹ በቂ የሆነ መሬትም ሀብትም ጉራፈርዳ ድረስ የሚያስወርድ ሁኔታ ያለ አይመስለኝም።¾(ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 398 ረቡዕ ሚያዚያ 16/2005)

No comments:

Post a Comment