Tuesday, May 14, 2013

ከ15 ሰዎችን በላይ የገደለው የፌደራል ፖሊስ ጉዳይ....

15 ሰዎችን በላይ የገደለው የፌደራል ፖሊስ ጉዳይ....(ከአካባቢው ሰዎች የአይን እማኞች እና ነገሩን በቅርብ
ከሰሙ ወገኖች የተገኘ መረጃ)በባህርዳር ከተማ የሚገኘውን የአባይ ድልድይ ጠባቂ የነበረው የፌዴራል ፖሊስ አባል አፍቅሪያታለሁ የሚላት ልጅ ሌላ ጓደኛ እንደያዘች ማመን አልቻለም፣ አሉኝ የአካባቢው ሰዎች።ትናንትና እሁድ ከከሰዓት በኋላ አባይ ማዶ፣ ከብአዴን ዋና ጽህፈት ቤት በስተጀርባ ወደሚገኘው የልጅቷ ቤት የተጓዘው ይሄው
ፖሊስ ልጅቷ እሱን እንደማትፈልገው እና ከእርሱ ጋር መሆን እንደማትችል ስትነግረው እሷንም ጓደኛዋንም እንደሚገላቸው ዝቶ ይመለሳል።
በዚህ የተደናገጠችው ተፈቃሪ ሁኔታውን ለማሳወቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መሄዷን አንድ የአካባቢው ሰው ቢነግሩኝም ስለሁኔታው ግን ከፖሊስ ማረጋገጥ አልቻልኩም።ምሽት ላይ ይሄው የፌዴራል ፖሊስ ሙሉ ዝናሩን እንደታጠቀ
መሳሪያውን አቀባብሎ ወደ ልጅቷ ቤት ይገሰግሳል።በዚህ መሃል ሊያስቆመው የቻለ ጓደኛም ይሁን "አለቃ" አልነበረም።
ልጅቷ ቤት እንደደረሰ እሷን ማግኘት ባይችልም እናቷን ያገኝና ተኩሶ ይገላቸዋል።

ከዚያ በኋላ ከቤት ወጥቶ መንገድ ላይ ያገኘውን ሰው ሁላ እየገደለ ሲሄድ በቦታው የሰማእታትን ሃውልትና የብአዴን
ጽህፈት ቤትን ይጠብቁ የነበሩ ብዙ የፌደራልና የክልል ፖሊሶች አንድም የማስቆም እርምጃ ለመውሰድ አለመሞከራቸው የአካባቢውን ነዋሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ አሳዝኗል፣ አስቆጥቷል።በስልክ ያናገርኩት አንድ ወጣት በከፍተኛ ንዴት ውስጥ ሆኖ "በጊዜው የብአዴንን ጽህፈት ቤት ሲጠብቅ የነበር ሌላ የፌዴራል ፖሊስ አባል መሳሪያ ይዞ ስለነበር እባክህ ተኩሰህ ጣለው ስንለው አይ እኔ እጠየቃለሁ ብሎ በዝምታ ይመለከት ነበር።"ብሎ ነግሮኛል።
በዚህ ጅምላ ግድያ ከሞቱት ሰዎች ውስጥ አንዲት የሁለት አመት ህጻንም እንደምትገኝበት የነገሩኝ የአይን እማኞች።
ፖሊሱ ህጻኗን በሚገድልበት ወቅት አንድ መኪና እያሽከረከረ የነበረ ወጣት ከመኪናው ወርዶ ድርጊቱን ሊያስቆመው ሲሞክር እሱንም እንደገደለው አያይዘው ገልጸውልኛል።
ከተገደሉት መካከል የስምንት ሰዎች የቀብር ስነስርአት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አያሌው ጎበዜ በተገኙበት በአባይ ማዶ ደብረ አባይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እንደተፈጸመ ለማወቅ ችያለሁ። በቀብሩ ስነስራት ላይ አቶ አያሌው የድርጊቱ ምክንያት ምንም ይሁን ምን ድርጊቱን የፈጸመው ሰው ተገቢውን ቅጣት ያገኛል ካሉ በኋላ አያይዘው በዚህ ድርጊት ውስጥ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ተባባሪ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ለፍርድ ይቀርባሉ ብለዋል።
ገዳዩ ፖሊስ እስካሁን የደረሰበት አልታወቀም።በዚህ ሃላፊነት በጎደለው የጭካኔ ተግባር ህይወታቸውን ላጡ ሁሉ ፈጣሪ ነፍሳቸውን ይማር።
ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይስጥ።
ድርጊቱ ሲፈጸም በዝምታ የተመለከቱ የፖሊስ አባላትን ጨምሮ በዚህ አረመኒያዊ ተግባር አውቀውም ይሁን በቸልተኝነት የተሳተፉትን በሙሉ መንግስት ለፍርድ ያቅርብ።
በመጨረሻም .....
ይህ ሁሉ ወገን በግፍ ተገድሎ ይሄ ሁሉ ሰው አልቆ በሁኔታው ላይ ዝምታን በለመረጡ የመገናኛ ብዙሃን ዳንኪራ
በሚያስጨፍሩ FM ራዲዮ ጣቢያዎች (ከድርጊቱ በላይ) አዘንኩ።
(
በርግጥ ብርቃችን አይደለም ማዘን)
ታሪክ ግን አንድ ቀን ይፈርዳል።
ከሰለሞን መንገሻ

No comments:

Post a Comment