የኢህአዴግ የታሪክ ሽሚያ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ኢህአዴግ ታሪክን በራሱ አስተሳሰብ ከመተርጎም ባለፈ የራሱ ለማድረግ በርካታ ሙከራዎችን አድርጓል፡፡ ኢህአዴግ መለስ ይህን ያህል ባላበረከቱበት አሊያም ተቃራኒውን ሚና በተወጡበት ‹‹መለስና የብሄር ጥያቄ›› የሚል መጽሐፍን በትዕዛዝ አጽፏል፡፡ ታዲያ በትዕዛዝ ካልሆነ ጤነኛ ሰው ደግሞም ‹‹ምሁር›› ያውም ብቸኛው አለማቀፍ ዩኒቨርሲቲ በሆነው የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንዴት እንዲህ አይነት መጽሐፍ ይጽፋል? አንዳንዶቹ እንደሚሉት ደግሞ ኢህአዴግ በዚህ ከቀጠለ ‹‹መለስና የአድዋ ድል!›› የሚል መጽሐፍም በቅርቡ ሊታተም ይችላል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በዚህ ርዕስ ስም በትዕዛዝ ለመጻፍ የማያንገራግሩ ምሁራን ሞልተውታል፡፡ መቼስ ቢሆን አቶ መለስ በጊዜው ባይኖሩም ጣሊያን ኤርትራን ቆርጦ ባስቀረበት ጦርነት የመሪያችን አያት ከጣሊያኖች ጎን ሆነው መዋጋታቸው ከብሄር ጥያቄው በተሻለ ከአቶ መለስ ታሪክ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ይኖረዋልና በአድዋ ጉዳይ መጽሐፍ ቢጻፍበት የሚያስገርም አይሆንም፡፡ የአቶ አስረስ የልጅ ልጅ ደግሞ ይችውን ኤርትራን ‹‹የኤርትራ ህዝብ ከየት ወደ የት?›› በሚል ‹‹የአብዮታዊ ዴሞክራሲ›› መጽሐፍ አጋዥነት ዳግም ከኢትዮጵያ እንድትለይ አድርገዋል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ‹‹ሌጋሲ›› ማለት! ያውም አቶ ኃይለማሪያም አስቀጥለዋለሁ እንደሚሉት የ‹‹ባዳ›› ሳይሆን የአያት!
አሁንም የኢህዴግ የታሪክ ሽሚያ ቀጥሏል፡፡ የአባይ ግድብ የኢህአዴግ ግድብ አይደለም፡፡
እነ አቶ ተመስገን ዘውዴ ለግድቡ ግንባታ 300 ሺህ ብር በላይ የሰጡት ግድቡ ፖለቲካ ድንበር የማይለየው የኢትዮጵያውያን ግድብ በመሆኑ ነው፡፡ ኢህአዴጎችማ ይህ ግድብ ከመገደቡ 20 አመት (ከዚያም አለፍ ብሎ) ጀምረው ሁለት ሶስት ግድብ የሚያስገድብ ገንዘብ ሲዘርፉ ኖረዋል፡፡ በየ አስር አመቱ በሙስና ስም የሚመዘዘው ካርድ ዋናው ምክንያቱ ሙስና አይሁን እንጅ ስርዓቱ ውስጥ ያለውን የሙስና ናሙና ግን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ እናም ያለፉትን ባልስቴራ በወርቅ የተቀየረባቸው፣ ኢትዮጵያውያን
በቁም የተዘረፉበትና
ታጋይ ባለሀብት
የሆኑበትን 22 ድፍን የሙስና አመታት ለማድመቅ የአባይን ወንዝ ውሃ በግንቦት 20 ቀን አቅጣጫውን እንዲቀይር ተደርጓል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አንድም ስራው ሳያልቅ ለግንቦት 20 በቶሎ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ ‹‹ባለሙያ›› ተብየዎቹ ይህን ትዕዛዝ አንቀበልም የማለት ሞራል የላቸውም፡፡ እናም እንደማንም እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ አሊያም ከወርና ሁለት ወር በፊት ውሃውን ማስቀየስ እየተቻለ ለግንቦት 20 አቆዩት ተብለው ቁጭ ብለው ሰንብተዋል፡፡ አሁንም የኢህዴግ የታሪክ ሽሚያ ቀጥሏል፡፡ የአባይ ግድብ የኢህአዴግ ግድብ አይደለም፡፡
ይህ ብቻ አይደለም ‹‹የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ››ም ለግንቦት 20 ተብሎ ዘግይቷል፡፡ አሊያም ሳያልቅ ተመርቋል፡፡ ዋናው ትዕዛዙ ከላይ መምጣቱ ነው፡፡ እነዚህ እንግዲህ የግንቦት 20 ፍሬዎች መሆናቸው ነው፡፡ በተለይ የስፖርት አካዳሚው ከፖለቲካው ሸሽቶ በስፖርት የተደበቀውን ወጣት ለመያዝ ያስችላል ተብሎ ነው፡፡ በቀጣይነት በርካቱ ታሪኮች እየተጎተቱ ለግንቦት 20 ማድመቂያዎችና የኢህአዴግ ታሪኮች ተደርገው መቅረባቸው የማይቀር ነው፡፡ ጉዱ ገና እኮ ነው የ30ዎቹንም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ግንቦት 20 ላይ እንመርቃለን እንዳይሉ? ምን ይህ ብቻ ወይዘሮ አዜብ አሊያም ሌላ የአቶ መለስ ቀርብ የነበረ ሰው ‹‹አቶ መለስ የዘመን መለወጫ በዓልን ከግንቦት 20 ጋር ለማድረግ አላማ ነበራቸው›› ብሎ ቢያወራ ‹‹ሌጋሲውን›› ለማስቀጠል የማይደክመው ኢህአዴግ የዘመን መለወጫንም አራት ወር ወደኋላ ጎትቶ ግንቦት 20 ሊያደርገው ይችላል፡፡ እንዲያውም የአቶ መለስን ስብዕና የሚያገንን ፖለቲካዊም ሆነ ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው ዶክመንተሪ ተሰርቶለት! ዋናው ይህ ሁሉ ታሪክ ፈራሽ መሆኑ ነው፡፡ አይ ሰው ፈራሹ! አይ ታሪክ ፈራሹ! አይ ኢህአዴግ ፈራሹ!
ከቅድስ ይርጋ
No comments:
Post a Comment