አንዳንድ የኢህአዴግ ካድሬዎች ኢህአዴግ “ፋራ”
ነው ልትል ፈልገህ ነው በማለት መረጃ የለሽ ክስ ሊመሰርቱብኝ ይችላሉ፡፡“በርግጥ ፋራ ነው! ” ፕሮፖዛሌ
እንደሚለው ግን ኢህአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች አራዳ ይሁኑ ፋራ እስካሁን የሚታወቅ ነገር ስለሌለ በዚህ ዙሪያ ሳይንሳዊ ጥናት ማካሄድ
ያስፈልጋል (ስፖንሰር ከተገኘ እኔም ላጠናው እችላለሁ)በፕሮፖዛሉ ላይ እንደሰፈረው “አራዳ” የሚለው ቃል ጮሌ፣ አሪፍ፣ የገባው፣
ተቆንጥጦ ያደገ፣ የሰለጠነ፣ አሪፍ ወይም “ስማርት” ፓርቲና መንግስት ለማለት እንጂ ዱርዬ፣ ተደባዳቢ፣ ወይም “ጉልቤ” ፓርቲና
መንግስት ለማለት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ (በፓርቲያቸው ጽ/ቤት የሚደባደቡና የቢሮ ቁልፎች የሚደብቁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች
እንዳሉ ልብ ይሏል) ለመሆኑ “አራዳ” እና “ፋራ” የሚሉት ስያሜዎች መመዘኛቸው ምንድነው? ፕሮፖዛሌ ምሳሌ እየጠቀሰ ያብራራል፡፡
ለምሳሌ ቲማቲምና እንቁላል እንዲወረወርበት የሚፈቅድና የሚታገስ ፓርቲ ወይም መንግስት የገባው ወይም አሪፍ (Smart) ይባላል፡፡
(አሪፍ አይቸኩልም ሲባል አልሰማችሁም?) በሌላ በኩል ለምን ቀና ብላችሁ አያችሁኝ ብሎ ዜጐቹን ፊት የሚነሳ፣ የሚሳደብ፣ የሚያስፈራራ፣
ለስደት የሚዳርግ ወይም እስር ቤት የሚወረውር ደግሞ “ፋራ” ፓርቲ ወይም መንግስት እንደሚባል አዲሱ ፕሮፖዛል ይጠቁማል፡፡
ተቃዋሚዎችን
እንዳያንሰራሩ አድርጐ እግር ከወርች የሚያስር ፓርቲም ፋራ ነው፡፡ ገና ለገና የህዝብ አመጽ በመፍራት ኢንተርኔትን፣ አይፎንን፣
(እንደ ሶርያ መንግስት) ፌስቡክን ጠርቅሞ ዜጐችን ከቴክኖሎጂ ትሩፋቶች የሚያፋታ መንግስትና ፓርቲ እልም ያለ ፋራ ነው ይለዋል
- ፕሮፖዛሌ፡፡ (በ97 ምርጫ ቴሌ የቴክስት አገልግሎት አቋርጦ እንደነበር ትዝ አለኝ) ምርጫ የሚያጭበረብሩትንም (እንደ ጋምቢያና
ኮንጐ) ፋራ ፓርቲዎችና መንግስታት ይላቸዋል፡፡እኔ ብቻ ልግዛ የሚል “ራስ ወዳድ” ፓርቲም ከፋራዎቹ ጐራ ነው - ፕሮፖዛሉ እንደሚለው፡፡
እርስ በእርስ የሚጠላለፉና የሚወዛገቡ የፓርቲ አመራሮችም የፋራ ፓርቲ ውጤት ናቸው፡፡የፖለቲካ ምህዳርን የሚያጠብስ? እሱማ እልም
ያለ ፋራ ነው፡፡ (እኔ ሳልሆን ፕሮፖዛሉ ነው ያለው) መንገድና ኮንዶሚኒየም በመስራት የዜጐችን ኑሮ የሚያቀል ደሞ ስማርት ፓርቲ
ይባላል፡፡ ዜጐችን ከአቅም በላይ በሆነ ታክስ የሚያጨናንቅስ? እሱ በርግጥም ፋራ ነው ይላል - ፕሮፖዛሉ፡፡ ንብረትነቱ የህዝብ
በሆነ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ የእኔ ፕሮፖጋንዳ ብቻ ይሰራጭ ብሎ ክችች የሚል ፓርቲና መንግስት ፈጽሞ ስማርት ሊባል አይችልም
- የለየለት ፋራ ነው - እንደ ፕሮፖዛሉ መመዘኛ፡፡ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን በገፍ የሚያስርና የሚያንገላታ
(እንደ ኢትዮጵያ መንግስት)
እሱም ዕጣ ክፍሉ ከፋራዎች ጐራ ነው፡፡ በማስፈራራት የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም የሚሞክርም (እንደ ወያኔ አምባገነኖች)
ምድቡ ከፋራ ፓርቲዎች ነው፡፡ የሰው ነገር የማይሰማና ራሱን ብቻ የሚያዳምጥም የትም ሊመደብ አይችልም - ከፋራዎች ተርታ እንጂ፡፡
ተቃዋሚውን እያሳደደ የሚገድል መንግስትስ? እንዲህ ያለው ፋራም አራዳም አይደለም - “ንክ” ነው፡፡ እንዲህ ያለ መንግስት ሁነኛ
ሆስፒታል መግባት አለበት -የአዕምሮ ሃኪም (ስፔሻሊስት) ነው ለዚህ መድሃኒቱ፡፡ በመጨረሻም ፕሮፖዛሉ ፋራና አራዳ ፓርቲዎችንና
መንግስታትን በመለየት በየጐራቸው የሚመድብ ተቋም ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ይጠቁምና ፓርቲዎች ለምርጫ ሲወዳደሩ አባላቶቻቸው “ስማርት”
ወይም “ፋራ” የሚሉ ባጆችን ደረታቸው ላይ ማንጠልጠል እንዳለባቸው ይገልፃል፡፡ ለምሳሌ - “ኢህአዴግ - አራዳ ፓርቲ”
ወይም “ኢህአዴግ ፋራ ፓርቲ” አሊያም “ኢዴፓ - አራዳ ፓርቲ” ወይም “ኢዴፓ - ፋራ ፓርቲ” የሚል ሊሆን ይችላል፡፡
ከዛስ? ከዛማ ቀላል ነው፡፡ ህዝብ የሚፈልገውን ይመርጣል - ከስማርትና ከፋራ ፓርቲዎች፡፡ ፕሮፖዛሌ እንደሚለው ፋራና አራዳ ፓርቲዎች
የሚለዩበት ዋና ዓላማው፣ ዜጐች ድምጽ ሲሰጡ ፋራዎችን መርጠው እንዳይሸወዱ (እንዳይፀፀቱ) ለማድረግ ነው፡፡ በተግባር
ያልተፈተኑ አዳዲስ ፓርቲዎችን ለመመዘን ደግሞ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን መገምገም እንደሚያስፈልግ ፕሮፖዛሌ ይመክራል፡፡ የፖለቲካ
ፕሮግራማቸውን በማየት ብቻ ፋራ ይሁኑ አራዳ ማወቅ እንደሚቻል አንዳንድ “ጥናቶች” ይጠቁማሉ፡፡ በነገራችን ላይ ምርጫ ቦርድ
ራሱም በስማርትና ፋራ ምድብ ውስጥ እንደሚካተት ፕሮፖዛሌ ይጠቁማል፡፡ እኔ የምለው ግን ያለፉትን አራት ብሔራዊ ምርጫዎች ያስተናበረው
ብሔራዊ የምርጫ ቦርዳችን “ፋራ” ነው “አራዳ”? በነገራችን ላይ አቶ በረከት የ97ና የ2002ን ምርጫ የገለፁበት ቋንቋ ማርኮኛል፡፡
(ልብ አድርጉ ቋንቋው ነው የማረከኝ! ይዘቱ አልወጣኝም!) “የ97 ምርጫ - በሰላም ተጀምሮ በረብሻ የተጠናቀቀ” ሲሉት “የ2002
ምርጫ - በሰላም ተጀምሮ በሰላም የተጠናቀቀ” ብለውታል፡፡ (ግጥም ሊመስል እኮ ትንሽ ነው የቀረው!) ውድ አንባብያን
- ፋራና ስማርት የምትሏቸውን የአገር ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ዳያስፖራን አይመለከትም) በመለየት ለዲሞክራሲ ባህላችን መዳበር
የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታበረክቱ ተጋብዛችኋል፡፡ ስፖንሰርሺፕ ከባለሃብቶች እስኪገኝና ፕሮፖዛሉ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ብቸኛው
አማራጭ “አራዳ” ፓርቲዎችን ያብዛልን እያልን መፀለይ ብቻ ነው፡፡
እግዚአብሔር
አራዳ ፖርቲ ይስጠን!!!
ኢትዮጵያ
በክብር ለዘላለም ትኑር !!!
ከሰብኣዊ
No comments:
Post a Comment