Thursday, May 16, 2013

ይድረስ ለፖለቲካ ቁማርተኞች


ተሰማ ስማቸው

አንድ የፌደራል ፖሊስ አባል አስራ ሁለት ሰዎችን ገደለ የሚለውን አሳዛኝ ዜና ከሰማን ወዲህ ይህችም መጥፎ አጋጣሚ እንደሌላው ክስተት ሁሉ የፖለቲካ ትርፍ ማካበቻ ሆና ታይታ ብዙ አስገራሚ ምላሾችን ታዝበናል። የፖለቲካ ቁማር ትልቁ ችግር አንዱን ወይንም ሌላውን ቆማሪ ደግፈህ ብትናገርም፣ ሁለቱን ብትቃወምም፣ ዝም ብትልም የጨዋታው አካል ነህ። ህይወትህ ባይነካ ስሜትህ ይነካል። ዛሬህ ባይነካ ነገ ይነካል።  ስለዚህ ዝም ማለት አልቻልኩም። የምናገረው የመቀባጠር ያህል ቢሆንም፣ ለፖለቲካ ቁማርተኞች እና (ከነሱ ጋር የምጋራው ማንነት ካለኝ ለኔም ይሆናል) ይህን ማለት ወደድኩ።


የፖለቲካ ቁማርተኞች ሆይ የሚያስጨንቃችሁን እናውቃለን፤ እንቅልፍ የሚነሳችሁን እናውቃለን። እንኳን በንጹሃን ተራ ሰዎች ሞት ይቅርና ታላቁ መሪያችሁን በሌላ ወገን አምባገነኑ የምትሉትን  ገዥያችሁን  አስከሬን አጋድማችሁ ትቆምራላችሁ። የእኛ እንባ የሞኝነት እንባ ናት። የኛ ሃዘን የጅልነት ሃዘን ናት፤ ለናንተ። እንኳን የተደረገ ያልተደረገም ነገር ቢሆን ፈጥራችሁ ታወራላች ሁ፤ የፖለቲካ ትርፍ ካገኛች ሁ፤ ጓደኝነት አታውቁም። ቅንነታችሁን ሽጣችኋል፤ ጸጉር ትሰነጥቃላችሁ፤ በእያንዳንዷ ኮሽታ የፖለቲካ ትርፍ ይታያችኋል፤ ያስጎመዣችኋልም። እውነቴን እነግራችኋለሁ፣ የያዛችሁትን ስልጣን ላለመልቀቅ (ከመንግስት ወገን ያላችሁት)  የሌላችሁን ስልጣን ለማግኘት (ተቃዋሚ ነን የምትሉት) የዛሬዋን ኢትዮጵያ በዛሬዋ ሶርያ ለመለወጥ ዝግጁ ናችሁ ብዬ እፈራችኋለሁ። 

ቁጥር ነን ለናንተ እኛ፤ ስንራብ በቁጥራችን ትከራከራላችሁ፤ ስንገደል በቁጥራችን ትከራከራላችሁ፤ ስንፈናቀል በቁጥራችን ትከራከራላችሁ፤ በቃ ቁጥር ነን ለናንተ እኛ። 
ሃይማኖቶቻችን ተረቶች ናቸው ለናንተ፤ እንደ ጭቃ ጠፍጥፋችሁ እንደገና ብትሰሩን ሁሉ ያምራችኋል፤ ታሪካችን ተረት ናት ለናነተ፤ እንደሚመቻችሁ መልሳችሁ ብትጽፏት ደስ ይላች ኋል፤ ለእውነት ደንታ የላችሁም እናንተ፤ በስልጣን እና በጉልበት እውነትን ተፈጥራላችሁ። መጀመሪያ የሌለ አላማ ትፈጥራላችሁ፤ ለዚያ አላማ እንድንሞትለት ታደርጋላችሁ፤ ከዚያ ይሄ እኮ ሰው የሞተለት አላማ ነው ትሉናላች ሁ።  ቆይ እኛ የናንተ ህልም ስእል ማሳመራይ ቀለሞች ነንበምንድነው የገዛችሁን?  በእውቀት ነው የገዛችሁን? በገንዘብ ነው የገዛች ሁን? በፍቅር ነው የገዛችሁን? ምንድነው የልብ ልብ የሚሰጣችሁ

እኛ ጥሎብን ብዙ የህይወት እይታችን የተቀዳው ከሃይማኖትና ከባህል። ቅንነት፣ ፍቅር፣ የዋህነት፣ ጓደኝነት፣ መተሳሰብ ወዘተ ያማልሉናል። ሰላም እንፈልጋለን። ሃብት ብናገኝ ከድ ህነት ብንወጣም እንወዳለን። ዘፋኝ እንኳን የምንወደው "ፍቅር ያሸንፋል" የሚል ከሆነ ነው።  ለናነተ ይሄ ሁሉ የቁማር ገንዘብ ነው። እኛ ግብ የምንለው ለናንተ መሳሪያ ነው። ስልጣንን እና ባለስልጣንን ለመነቅነቅ በምንወዳቸው እና በምናከብራቸው እሴቶቻችን ላይ ትረማመዳላች ሁ። ስልጣንን ለመጠበቅ በእንባችን፣ በሃዘናችን፣ ሃይማኖታችን፣ በታሪካችን፣ በቋንቋችን፣ በብሶታችን፣ በተስፋችን፣ ባለን ነገር ሁሉ ትቆምራላችሁ። 


ኑሮአችሁን ለማሻሻል እንፈልጋለን ትላላችሁ፤ ይወዱናል ብለን ስንዘናጋ እንደማትወዱን ታሳዩናላችሁ። የምትፈልጉት እኛን አደራጅታችሁ መንዳት ነው። እናንተ እንድታስቡ እኛ እንድንከተል። ተረታችሁን እየሰማን እንድናንቀላፋ። 

ልዩነታችን፣ ራሳችንና ሌሎችን የምናይበት መንገድም ዋነኛ የቁማር ገንዘባችሁ ነው። የፖለቲካ ትርፍ ካያች ሁ፣ ፍር ሃት፣ ጥርጣሬ ሌላው ቀርቶ ጥላቻ እንኳን ስር ቢሰድ ደንታ የላችሁም። እንደየሁኔታችሁ ስልጣንን ለመጠበቅ ወይም ስልጣንን ለመነቅነቅ የማትጫኑት ቁልፍ የለም። ለሃይማኖታችን ያለን ቀናኢነት፣ ለቋንቋችን እና ለራሳችን ያለን ክብር፣ ስለሌሎች ህዝቦች ያለን የተሳሳተ አመለካከት፣ የተጠቃሚነት መንፈስ፣ የተጎጅነት መንፈስ፣ ሁሉም ከመጫን የማትመለሷቸው ቁልፎች ናቸው። ለዚሁ ቁማርና ትርፍ ስትሉ ጀግና ትገድላላችሁ፣ ጀግና ትፈጥራላችሁ፣ እውነት ትሰውራላችሁ፣ እውነት ትፈበርካላች ሁ፣ ጠላት ትፈጥራላችሁ፣ ወዳጅ ትመስላላችሁ፣ ትገድላላችሁ፣ ታሳድዳላችሁ፣ ታዋርዳላችሁ፣ ትዋረዳላችሁ። 

የፖለቲካ ቁማርተኞች ሆይ፣ የፖለቲካ ነጋዴዎች ሆይ፣  ለቁማራችሁ እና ለንግዳችሁ የስነ ምግባር ገደብ አበጁለት። 

1 comment: