Monday, May 27, 2013

ደርግን በደርግ የተካው ግንቦት 20

ዳዊት ሰለሞን
በአስራ ሰባት መርፌ
በጠቀመው ቁምጣ
ለለውጥ ያጎፈረው
ስልጣን ላይ ቢወጣ
አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ
(
ቴዲ አፍሮ)
ግንቦት 20/1983 በኢትዮጵያ የመንግስት ለውጥ የተደረገበት በመሆኑ ቀኑ በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ያሳደረውና በሂደትም የሚያሳድረው ተጽእኖ ለውጡን በፈጠሩት አካላት ዲስኩር ብቻ ተተንትኖ ያበቃል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለውጡን የማይደግፉትና በለውጡ አቀንቃኞች ‹‹የቀድሞው መንግስት ናፋቂዎች›› የሚሰኙት ጭምር በአንድም በሌላም መንገድ ቀኑ ይነካቸዋልና ድምጻቸውን ሊያሰሙ ይገባቸዋል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግንየኢትዮጵያቴሌቪዥን 1984 ግንቦት ሃያ ጀምሮ ስለ ቀኑ እንዲናገሩ ሰፊ የአየር ሰዓት የሚቸራቸው ለተጋዳላዮቹ ብቻ ነው፡፡

ተጋዳላዮቹ በበኩላቸው ስለ ግንቦት ሃያ ሲያወሩ በዋናነት ማተኮር የሚፈልጉት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ስላሳለፉት የበረሃ
ህይወት ነው፡፡ እስከ አፍኛጫው ታጥቆ የነበረ የሚለትን ደርግን ስለ ተፋለሙባቸው ውጊያዎች፣የጦር ሜዳ ጀብዱዎች ይተርካሉ፡፡ ጠላትን ለመግደል ስለ ፈጸሙት ጀብድ ሲያወሩ ግን ማን እንደሚሰማቸው እንኳን የሚጨነቁ አይመስሉም፡፡ 17 ዓመታት የተደረገው ጦርነት በወንድማማቾች መካከል በመሆኑም የያኔዎቹ ታጋዮች ግዳይ መጣላቸውን ሲያወሩ ባሏን በሞት የተነጠቀች እመበለት፣ልጇን ያለ ውዴታው ያጣች እናት፣አባታቸውን ለጦርነቱ የገበሩ ልጆች በቴሌቭዥን መስኮት ያደምጧቸዋል፡፡ በየዓመቱ ግንቦት ሃያ በመጣ ቁጥር እነዚህ ቤተሰቦች ምን ሊሰማቸው እንደሚችል ማሰብ ህመም ይፈጥራል፡፡
‹‹አገር ለመገንጠል ወንበዴዎች ተነስተዋል›› በሚለው የደርጉ የእናት አገር ጥሪ መሰረት የዘመቱ ወታደሮች የደርግ ተብለው በየግንቦት ሃያው‹‹ጠላት››እየተባሉ መጠቀሳቸው በጦርነቱ መንስዔ አካላቸውን ላጡ ሁሉ ከህሊና የማይሽር ጠባሳ ነው፡፡
ኢህአዴግ ግንቦት ሃያን በማስመልከት ለህዝቡ የሚያሰራጫቸው ፕሮፓጋንዳዎች ሁለት ጫፍ የረገጡ ናቸውፕሮፓጋንዳዎቹ ለምን አላማ እንዲውሉ ታስበው ድርጅቱ እንደመንግስት በተቆጣጠራቸው ሚዲያዎችእንደሚያሰራጫቸው ማሰብም ገዢውን ፓርቲ ከግንቦት ሃያ በፊት ከነበረበት የጫካ አስተሳሰቡ አለመላቀቁን ለመታዘብ ያስችለናል፡፡
ገዢው ፓርቲ ወደ ምኒልክ ቤተመንግስት ከገባ 22 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ድርጅቱን ለዚህ ያበቁት ተጋዳላዮችም በአሁኑ ሰዓት በእድሜና በተለያየ ምክንያት ከጨዋታ ውጪ እየሆኑ ነው፡፡ ድርጅቱ አዳዲስ ፊቶችን በተወሰነ ደረጃ እያሳየን የሚገኝ
ቢሆንም አዲስ ፊቶቹ በቀድሞዎቹ ( old guareds )መንገድ ግነቦት ሃያን እያከበሩ ይገኛሉ
በግንቦት ሃያ ክብረ በዓል ከሚቀርቡልን ዲስኩሮች መሃል የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የጦርነቱ ታሪክ ነው፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ወቅት በጦር ሜዳ ውሎ አቻ እንደሌለው ሊነግረን የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡ ከጦርነቱ ጀብድ ባሻገር ግን የጦርነቱ ውጤት ምንድን ነው በማለት እንድንጠይቀው አይፈቅድም፡፡ ተጋዳላዮቹ ለምን ነበር ይህን ሁሉ ዋጋ የከፈሉት አዎን መልሱ ለእነርሱ ቀላል ሆኖም ይሆናል፣የተዋጋነው ደርግን ለመጣል ነው ሊሉን ይችላሉ፡፡
እርግጥ ነው ደርግ በህዝብ ልጆች ደም ቤተመንግስቱን የገነባ ጅላጅል አምባገነን ነበር፡፡አዲሶቹ ገዢዎቻችን ደርግን በመጣል
ደርግን በስም ባይሆንም በግብር ከመሰሉ የደርግ ውድቀት ለህዝቡ እውን አልሆነም ማለት ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የለውጡ ራስ ተደርገው ይታዮ የነበሩትን አቶ መለስ ዜናዊን ‹‹መንግስቱ ኃይለማርያምን መሰልከኝ›› ያሉት፡፡ነጋሶ ቆይተውም ቢሆን በመለስና በመንግስቱ መካከል ልዮነት አለመኖሩን ተገንዝበዋል፡፡ አቀንቃኙ ቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ)ለለውጥ ያጎፈሩት አብዮተኞች ለቤተመንግስቱ አዲስ
ከመሆናቸው ውጪ እናመጣዋለን ያሉትን ለውጥ አለማምጣታቸውን ስልጣንን ከጨበጡ 14 ዓመታት በኋላ ማቀንቀኑ አይዘነጋም፡፡ በኢህአዴግና በደርግ መካከል ልዮነት አለመኖሩን በአስረጂነት ከምንጠቅሳቸው ድርሳናት መካከል‹‹ነጻነትን የማያውቁት ነጻ አውጪዎች›› የሚለው የአንዳርጋቸው ጽጌ መጽሀፍ ተጠቃሽ ነው፡፡
ኢህአዴጋዊያን በግንቦት ሃያ የሚቀሰቀስባቸው የበረሃ ትውስታ ለሰላማዊ ትግል ውጤታማነት የሚያስተላልፈው
መልእክት በዜሮ ሊባዛ የሚችል ነው፡፡ ደርግ ከአፈሙዝ ውጪ የጨበጠውን ስልጣን የሚያስጠብቅበት የህዝብ መተማመኛ
አልነበረውም እናም ኢህአዴጋዊያን ደርግን በሚገባው ቋንቋ በማናገር ስልጣኑን አሳጥተውታል፡፡ ጥያቄው አሁንስ ነው?
የተጋዳላዮቹን የበረሃ ህይወት ስትመለከቱ ወደ ህሊናችሁ የሚመጣው ምንድን ነው? ኢህአዴግ ከብረት ውጪ የሚገባው ቋንቋ የለውም የሚሉ ሃይሎች ጥራኝ ዱሩ ማለታ ስለመጀመራቸው እየሰማን ነው፡፡ገዢው ፓርቲ የመጣበት መንገድ ሰላማዊ
ባለመሆኑም የግንቦት ሃያ የጦርነት ዲስኩር እነዚህ ሃይሎች የጀመሩት ትግል ፍትሃዊ መስሎ እንዲታያቸው እንደማጣቀሻ
ሊወስዱት ይችላሉ፡፡
በእኔ እምነት ኢህአዴግ በግንቦት ሃያ ሊየሳየን የሚፈልገው እውነታ ደርግን በመፈንገል ወንበሩን ስለ መውረሱ ብቻ
ነው፡፡ ደርግን ማውገዝ ከደርግ የሚነጥለው ስለሚመስለው የወደቀውን ስርዓት በግንቦት ሃያ እየደጋገመ ይረግመዋል፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በትግሉ ሜዳ አልፈው አራት ኪሎ የደረሱ አልያም የግንቦት ሃያ ፍሬ ነን የሚሉ በዚህ ወር ከደርግ በኋላ እየመሩት ስለሚገኘው ህይወት መጠየቅ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ፡፡
ርዕይ የሌለው ግንቦት ሃያ ርዕይ ባለው ሌላ ግንቦት ሃያ እስካልተቀየረ ድረስ እነ ቀሽ ገብሩን እያስታወሱ እነ ብርቱካንን ማሳደድ አይቀሬ ይሆናል፡፡የግንቦት ሃያ ፍሬዎችም ስለ እነርዕዮት አለሙ የሚጠይቃቸውን ድምጽ እያፈኑ ስለቀሽ ገብሩ ብቻ ስናወራ ስሙን ማለታቸው ቅንጣት የይሉኝታ ስሜት አይፈጥርባቸውም፡፡ግንቦት ሃያ ላስከፈለው የህይወት ዋጋ ቦታ የሚሰጥ አካል አግኝቶ ቢሆን ቀኑን ሁላችንም የአገራችን ካርኒቫል ባደረግነው ነበር፡፡ነገር ግን ይህ ባለመሆኑ በመስከረም ሁለትና በግንቦት ሃያ መካከል ያለው ልዮነት ጠፍቶብን አስረጂ እንፈልጋለን
finotenesanet


No comments:

Post a Comment