Sunday, May 5, 2013

ሉሲ “ኢህአዴግ ሆናለች” የሚሉ አሉ! ዜግነቷን ሳትቀይር አገሯ ብትገባም “ዳያስፖራ” ሆናለች።




እኔ የምላችሁ --- ሰሞኑን ሉሲ ከአሜሪካ ወደ አገሯ መመለሷን ሰማችሁ አይደለ? ያውም “ሆም ስዊት ሆም” ን እያዜመች፡፡ (የአገር ፍቅር ይላችኋል ይሄ ነው) የአሁኑ ትውልድ ቢሆን እኮ እንኳንስ አምስት ዓመት ሙሉ አሜሪካ ተቀምጦ ይቅርና ለሳምንት ሴሚናር ቢሄድ እንኳ መጀመርያ የሚያስበው በሆነ መላ እዚያው የሚቀርበትን መንገድ ነው፡፡ (ሉሲ አንጀቴን በላችው!) በእርግጥ በፈቃዷ ትመለስ በተፅዕኖ እስካሁን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻልኩም፡፡ ምናልባት ራሷ ብትጠየቅ እኮ “ሆድ ይፍጀው” ልትለን ትችላለች፡፡ (እንደዝነኛው ድምፃዊ! ) የሆነ ሆኖ ግን ወዳም ይሁን ተገዳ ወደ እናት አገሯ ተመልሳለች፡፡ የሚገርመው ምን መሰላችሁ? አንዲት አገር ወዳድ ብትገኝ ሰላም ነሷት፡፡ አምስት አመት ዓመት ሙሉ ምንም ያላሏት ዳያስፖራዎች፤ ወደ አገሬ ልሄድ ነው ብላ ስትነሳ ያለስሟ ስም ሰጧት አሉ - “ሉሲ ኢህአዴግ ሆናለች” በማለት፡፡እሷ ምን ብትል ጥሩ ነው? “መብቴ ነው!” (እንዴት አንጀቴን እንዳራሰችው አልነግራችሁም!)
አንዳንድ ወገኖች ትክክለኛዋ ሉሲ ሳትሆን ኮፒዋ ወይም ፎርጂዷ ነው የመጣው ሲሉ የነዙት አሉባልታም መሠረተቢስ መሆኑ ተረጋግጧል የሚል ዜና በኢቴቪ ሰምቻለሁ (ሌላ የአንጀት መራስ አትሉም) ኢትዮጵያዊቷ ድንቅነሽ፤ዜግነቷን ቀይራለች ወይም ባል አግብታ “ግሪንካርድ” አግኝታለች የሚለው ወሬም እስካሁን በተጨባጭ መረጃ ሊረጋገጥ እንዳልቻለ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ አንድ ነገር ግን አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡ አሁን ሉሲ በእርግጠኝነት ዳያስፖራ ሆናለች፡፡ ለምን መሰላችሁ? በአሜሪካ አምስት ዓመት ለጥጣ እኮ ነው የመጣችው፡፡ ይሄ ደግሞ “ዳያስፖራ” ከሚባሉት ዜጎች ተርታ ለመመደብ ብቁ ያደርጋታል፡፡እንኳንስ አምስት ዓመት ከአገሯ ውጭ የኖረችው ሉሲ ቀርቶ፣ አንድ ዓመት ተቀምጠው የመጡትም እኮ “ዳያስፖራ ነን” በሚል የዳያስፖራዎች ዓይነት መብት እየጠየቁ አስቸግረዋል - ምንጮች እንደሚሉት፡፡ እሷ ግን ዳያስፖራ ብትሆንም ቅሉ፤ እንደሌሎች ዳያስፖራዎች “ከታክስ ነፃ መኪና ላስገባ” ወይም ደግሞ “የመኖርያ ቤት መሥሪያ ቦታ ይሰጠኝ” የሚል ጥያቄ አላቀረበችም በሚል አድናቆትና ምስጋና እየጎረፈላት ነው ተብሏል - የአድናቆቱና ምስጋናው ባለቤት ባይታወቅም፡፡ “አገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ከማለት ይልቅ እኔ ለአገሬ ምን አደረግሁላት” የሚለውን የጆኔፍ ኬኔዲ አባባል በተግባር በመተርጎምም ለብዙዎቹ የአገሯ ልጆች አርአያ መሆኗ እየተነገረ ነው - የአፋሯ ድንቅነሽ፡፡ በአምስት ዓመት የአሜሪካ ቆይታዋ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኘች ሲሆን ለህዳሴው ግድብ ታበረክተዋለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አንዳንድ ወገኖች ግምታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “ለሉሲ አምባሳደር የሚል ሹመት ሊሰጣት ይገባል” የሚል ጥያቄ ውስጥ ውስጡን እየተወራ ነው ይላሉ - ምንጮች፡፡ በእርግጥ ባለፈው ረቡዕ በኢቴቪ በተላለፈ ዜና ፤ ሉሲ በአሜሪካ የአምስት ዓመት ቆይታዋ “ስኬታማ የአምባሳደርነት ሚናዋን እንደተወጣች” ተዘግቧል፡፡ ይሄ ዘገባ ለሉሲ ተጨማሪ ውዳሴ ቢያመጣላትም፣ በየውጭ አገራት ለተመደቡ የኢህአዴግ ሹመኛ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ግን ያልታሰበ ወቀሳ አምጥቶባቸዋል - “የሉሲን ያህል እንኳን አልሰራችሁም” የሚል፡፡እርግጥ ነው ሁሉም አምባሳደሮች በአንድ ላይ እንኳን 1.5 ሚሊዮን ዶላር ለአገራቸው አላስገቡም፡፡ ምናልባት ከአገራቸው አስወጥተው ይሆናል እንጂ - ይላሉ፤ ውጭ ጉዳይ አካባቢ ለሉሲ የአምባሳደርነት ሹመት እንዲሰጥ ሎቢ የሚያደርጉ ቡድኖች፡፡ ራሱን “የሰው ዘር የቅሪት አካል ተቆርቋሪ” በሚል የሚጠራ አንድ አገር በቀል ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ ኢህአዴግ ሉሲን የውጭ ምንዛሪ መሰብሰብያ አድርጓታል በሚል ክፉኛ የወቀሰ ሲሆን መኩሪያችን ትሆናለች ያልናት የሰው ዘር ምንጭ ሉሲ፤ “በሙዚየም በክብር መቀመጥ ሲገባት ለስደት ኑሮ መጋለጧ አሳስቦኛል” ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡ ስጋቱን የተጋራው ባያገኝም፡፡ እኔ በበኩሌ ግን ሉሲ ኢህአዴግም ሆናለ በሚለው ዳያስፖራዎች ተጋርቻለው!  “ዌልካም ባክ ሆም” ብያታለሁ (የአገር ኩራት እኮ ናት!)
ከሰብኣዊ




No comments:

Post a Comment