Wednesday, May 8, 2013

በአፍሪካ ሕብረት 50ኛ አመት ክብረ በአል ዕለት በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ተጠራ *ሰልፈኞች ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ


ከመጪው ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚከበረውን የአፍሪካ ሕብረት 50ኛ አመት የወርቅ እዮቤልዩ በአል ላይ ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ተደረገ።
ሰልፉን ያዘጋጀውና የሚመራው በቅርቡ የተመሰረተው ሰማያዊ ፓርቲ ሲሆን የሰልፉም አላማ ፓርቲው ከዚህ በፊት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ለመንግስት ጥሪ አቅርቦ መልስ ያላገኙ አራት ርዕሰ ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ መሆኑን ተገልጿል።
የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ስለሺ ፈይሳ፣ የፓርቲው የሕግ ጉዳይ ኃላፊ ወጣት ይድነቃቸው ከበደ እና የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሮን ሰይፉ በጋራ በፓርቲው ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት የተቃውሞ ሰልፉ የሚደረገው የተለያዩ ሐገራት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መሪዎች በሚገኙበት ድምፃችን ለማሰማት ነው ብለዋል።
በዚሁ መሠረት ከግንቦት 15 እስከ 17 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ጥቁር ልብስ በመልበስና ግንቦት 17 ቀን 2005 ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ አራቱን ጥያቄዎች እንዲመለሱ ፓርቲው ግፊት እንደሚያደርግ አመራሮቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል።
የፓርቲው አመራሮች መመለስ ይገባቸዋል ያሉዋቸው አራቱ ጥያቄዎች መካከል፣ ለፍትህና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን የሚታገሉ ጋዜጠኞችን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና አባላትን በአሸባሪነት ስም ማሰርና ማሰቃየትን አጥብቀን የምንቃወም መሆኑንና እስረኞችንም እንዲፈቱ የጠየቅን ቢሆንም እስካሁን ምንም መልስ ያልተገኘ በመሆኑ፤ የዜጐችን ሰብዓዊና ሕገ መንግስታዊ መብቶችን በመጣስ ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ ኢሰብዓዊ በሆነ ድርጊት በታጠቁ ኃይሎች እንዲፈናቀሉ ማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመሆኑ የድርጊቱ ፈፃሚዎች ለፍርድ እንዲቀርቡና የተፈናቀሉት ዜጎችም በአስቸኳይ ወደየመኖሪያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ በመንግስትም ሆነ በግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው የጠየቅን ቢሆንም አሁንም ገና የሚፈናቀሉ ዜጎችን ስም ዝርዝር በየማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ ተለጥፎ እያየን በመሆኑ፤ መንግስት በኃይማኖታችን ጣልቃ አይግባ፣ የእምነት ስርዓታችንና የሃይማኖት መሪዎቻችንን እምነታችን በሚፈቅደው ብቻ እናከናውን ያሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን በአሸባሪነት ወንጀል በመክሰስ በእስር እንዲማቅቁና ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጣስ መደረጉ እንዲቆምና ያነሷቸውም የእምነት ነፃነት ጥያቄዎቻቸው እንዲከበር የጠየቅን ቢሆንም እስካሁን የተገኘ መልስ ባለመኖሩ፤ መንግስት የኑሮ ውድነትን፣ የሥራ አጥነትንና በሙስና የተዘፈቁ የመንግስት ሌቦችን የሚቆጣጠርባቸውን መንገዶችና ፖሊሲዎች በማውጣት ሐገራችንን ከቀውስና ዜጎችንም ከሰቆቃ እንዲያወጣ በተደጋጋሚ ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ሰሚ አጥተው በመቆየታቸው እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ አሁንም አጥብቀን የምንጠይቅ መሆኑ ለማስገንዘብ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ፓርቲው በጣሊያን ሀገር ለፋሺስት ግራዚያኒ መናፈሻና ሐውልት መቆሙን ተከትሎ በፓርቲውና ከሌሎች የሲቪክ ማህበራት ጋር ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራቱ የተወሰኑ የፓርቲው አመራሮችና የሰልፉ አስተባባሪዎች ታስረው መለቀቃቸው አይዘነጋም።

No comments:

Post a Comment