Tuesday, May 7, 2013

“ኢትዮጵያዊነት”


ኢትዮጵያዊነት በዘፈቀደ የመጣና በዘፈቀደ ሊደበዝዝ የሚችል አርእስተ-ጉዳይ አይደለም፡፡ አዲስና ቅኝ አገዛዝ ሰራሽም አይደለም፡፡ ለረጅም ዘመናት አብሮ በመኖር ከቁሳዊና ማህበራዊ ውህደት የመጣ ታሪካዊና ሕያው ህልውና ነው፡፡ ሉዓላዊነትም ነው፡፡ ትላንት የነበረ ዛሬም ያለ ለወደፊትም የሚኖር ነው፡፡
ኢትዮጵያዊውም በአገሩ ጉዳይ በቁመቱ ሙሉ እንባውን ሲለቀው ነው የምታገኙት፡፡ 
ኢትዮጵያዊነት አሁንም ሕያው በሆኑ፣ አሁንም የጋለ ልቦና፣ የሞቀ አእምሮ ባላቸው በብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ደምና አጥንት ውስጥ የሚገኝ እምነት ነው፡፡ አንዳንድ ፀሐፊዎች ጉድጓድ ውስጥ እንዳለችው እንቁራሪት ካልሆኑ በስተቀር የኢትዮጵያዊነት አድማስ አይጠፋባቸውም ነበር፡፡ 
ዓላማ ብላችሁ ኢትዮጵያዊነትን ማንኳሰስ የያዛችሁ ሰዎች ያልገባችሁ ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያነት ሲያስመርርና ሲያስጠላ የነበረ አጀንዳ አልነበረም፡፡ ይልቅስ የሚያስመርሩና የሚያስከፉ የነበሩት የኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ መንግስታቶች ናቸው፡፡
ችግሩም የነበረው ኢትዮጵያዊነት ላይ ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግስቶች ላይ ነው፡፡ ህዝብ ማለት እስከ አሁን መንግስት ሆኖ ባለማወቁና ህዝባዊ መንግስትም እስከ አሁን ባለመኖሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ለፈተና መቅረብ አይችልም፡፡ እነዚህም ህዝባዊ ያልሆኑት መንግስታቶች ሲያምሱንና ሲያተራምሱን ቢኖሩም ከስልጣን የወረዱት በኢትዮጵያዊነት ጥንካሬ መሆኑ አይካድም፡፡ ቢያንስ 39 ዓመታት ጀምሮ እስከ አሁን የተደረገው የተለያየ ፖለቲካ ትግል የሚያስረዳው በመንግስታቶች ላይ የነበረውን ምሬትና ጥላቻ እንጂ በኢትዮጵያዊነት ላይ አለመሆኑን ያስረዳል፡፡ ህዝቡም ሆነ የትግል ድርጅቶች ያራመዱት መራራ ትግል እኩልነትን፣ ወንድማማችነትን፣ ፍትህንና፣ ዲሞክራሲን የነፈጋችን መንግስት አንፈልግም ይዉረድልን ብለው ሲያምፁና ሲረሽኑ ኖሩ እንጂ ኢትዮጵያዊነቴን አልፈልግም ብለው በማመጻቸው የተጨፈጨፉበት ጊዜ የለም፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ሊያገኙት የሚገባቸው ዲሞክራሲያ መብትና አድሎ የሌለው አስተዳደር ያጡት መላው ኢትዮጵያዉያኖች ናቸው፡፡ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ያስተዳድሩት በነበሩ የመንግስት አካላት ሰለባ ሆኖ ቆየ እንጂ በህዝብነቱ እንደ መንግስት ማንንም በድሎ፣ ረግጦ፣ አፍኖ አያቅም፡፡
ወንደሞቼ! አውቃችሁም ሆነ ሳታውቁ ኢትዮጵያዊነትን አትቅረፉ፡፡ ትግላችሁ ማነጣጠር ያለበት ለዲሞክራሲያዊ፣ ለፍትህ፣ ለዕኩልነት፣ ለፍትሐዊ ምርጫና ለነፃነት መሆን አለበት፡፡ በዚህች 21 ዓመታት ዉስጥ ብቻ እኩልነት እና አንድነት ጠፍቷል፡፡ ለዝች ሀገር ስንቱ መስዋዕትነት ከፈለ? ስንቱ ታሰረ? ስንቱ ተሰዋ? ስንቱስ ተሰደደ? መንግስታት ላይ እንጅ በኢትዮጵያዊነት ላይ መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ለጊዜው ማድበስበስ ይሞክር እንጅ መልሶ መላልሶ የበላይነቱን የሚይዝ የጋራ መድረካችን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከሌለ፣ ክብር ካጣ፣ ቅድሚያ ካጣ፣ የሞራልና ስነ ምግባር ሀብት (የሞራልና የኤቲካል ቫሊው) መሆኑ ከቀረ በየጊዜው ብሔረ-ሰባዊነት ብቻ ልንገባ ነው፡፡ በዚህም በስነ ምግባርና በስነ አእምሮ ይዞታችን እንገነጣጠላለን፡፡ 
የብሔረሰባዊነት ፖለቲካ መድረክ ኢትዮጵያዊ እኩልነት ከሌለበት የመጨረሻው የነፃነት መድረክ ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ በአንድ ብሔረሰብ ውስጥ የሚኖሩ የአውራጃና ወረዳ ነዋሪዎች መካከል እንኳን ከተለያዩ አጋጣሚዎች በመነጩ የታሪክ፣ የልማት፣ የባህልና፣ የተፈጥሮ ቅሪቶች ልዩነቶች ይታያሉ፡፡ በነዚህም ልዩነቶች ሳቢያ በተከሰቱ የስነ አእምሮአዊና ቁሳዊ ኑሮ መበላለጥ ምክንያት ከተፈጥሮ የሚገኘው ሁኔታ የምንጠላውን አድሎአዊነት ሊያስከትል ይችላል፡፡ እየታየም ነው፡፡ እንዲሁም የችግሮች መጠን ወደ ቀበሌና ሰፈር ከዛም ወደ ቤተሰብ እየሸሸ ዞሮ ዞሮ ስፋት ወደ አለው ወደ ግለሰቦች መብትና ነፃነት፣ ወደ ኢትዮጵያዊነት ከረጅም ጊዜ በኋላ ይመለሳል፡፡ 
ስለ አገራችን ኢትዮጵያ መባል ያለበት ሁሉ ተብሏል ተፅፏል፡፡ አሁን የቀረን ወደ ተግባር መለወጥ ብቻ ነዉ፡፡
1.
የአገር ታሪክ እንዲረገጥ የጀግና ገድል እንዳይነሳ ትውልድ የሚኮራበት የጀግንነትና የባህል ሀብት እንዲጠፋ ይሞክራሉ፡፡
2.
አንዱ ከሌላው አስበልጠው በማሳየት ብዙዎችን በህሊና ባርነት ሥር አውለዋል፡፡
3.
ያልተፃፈ እየተነበበ ያልተባለ እየተገለጠ ነው፡፡
4.
የኢትዬጵያን ታሪክ በአዲስና በማናውቀው መንገድ ያስረዱናል፡፡ ዘለፍ አለች ስድብ አለች አገር ደረጃ ሳይቀር ግለሰቦች የፖለቲካ ቡድኖችና የብሔረሰብ ድርጅቶች ኢትዬጵያዊ ጨዋነት በጐደለው መልክ ይዘለፋሉ፡፡
5.
ኘሮፓጋንዳው መንግስት ህዝቡን እንዱያውቅ የሚጥር ሳይሆን ህዝብ በግድ የመንግስትን ጥራትና መልካምነት እንዲገነዘብ ማስገድድ ነው፡፡ ይኸ ስልት ደግሞ ደንቁሮና ሰጥ ለጥ ብሎ የሚገዛ ስርዓት ነዉ፡፡
6.
ህዝብ ከህዝብ ላይ እንዲነሳ አንዱ ዘርን የበላይ ያደረገ ስርዓት ነዉ፡፡
ኢትዮጵያ በጣም ረዥም ታሪክ ያላት አገር መሆነዋን ማንም ያዉቀዋል፤ ዛሬ ኢትዮጵያ መናጢ ደሃ ከሚባሉት አገሮች ዉስጥ መጨረሻ ግድም እንደምትገኝም ማንም ያዉቃል፡፡ ህዝብ አላጣችም መሪ አጣች እንጅ፡፡ህዝቡ ግን ምን ያርግ ሲፈራረቁብን የነበሩት አንባገነን መሪዎች ናቸዉ ተጠያቂ፡፡ እዝች ጋር ከፕ/ መስፍን ንግግር ልዋስና 21 ዓመታት ዉስጥ የኢትዮጵያ ግዛት ተቀንሷል፣ ፍቅሩም ተቀንሷል፤ ተስፋዉም ተቀንሷል፤ የተከበሩ ህዝቧን አሳንሰዉ ብሄር ብሔረሰቦች ብለዉ ቀንሰዉታል፡፡ ቁልቁለት መሄድ እንደባህል ሁኗል፡፡ ጥላቻን አቅፈን ወደ ፍቅር ልንደርስ አንችልም፤ ጥፋትን እያሰብን ልማትን ማካሄድ አንችልም ብለዋል፡፡ አላህ መሪዎቻችንን ከመሞታቸዉ በፊት ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲል ልቦና ከቅን መንፈስና ከወኔ ጋር ይስጣቸዉ፡፡ ታሪካችንን ከዜሮ ለመጀመር ለምን ይዳዳናል???…….. ስምን ወይም ምልክትን በመለወጥ ታሪክን ለመለወጥና ባለቤት ለመሆን አይቻልም፤ ሐዉልት ማፍረስ፣ ጀግኖቻችን ማዋረድ፣ ሬሳ መደብደብ ታሪክ አይሆንም፡፡ ቁም ነገሩ ወቅቱን እና ጊዜዉን ጠብቆ ታሪክ መስራት ብቻ ነዉ፡፡
በታላላቅ የዓለም መድረኮች ላይ ተናግረዉ ማሳመን የሚችሉ መሪዎችን ያፈራች ሀገር እንደ እነ / አክሊሉ ሀብተወልድ ዐይነትን ያፈራችን ሀገር የአሁኖቹ መሪዎች ግን ለልመና እና ለታዛዥነት እጃቸዉን ይዘረጋሉ፡፡ 
‹‹
ያለ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ልትሆን አትችልም፡፡ ስለ ኢትዮጵያ መሻሻልና ማደግ መሰረቱ እኛው ነን፡፡ ስለዚህ አዲስ የሥራ መንፈስና የአምራችነት ባህል በመካከላችን መዳበር አለበት፡፡››
ትርፋችሁ ድካማችሁ ብቻ ይሆናል፡፡ 
አገራችን ኢትዮጵያ ከነክብሯ ለዘላለም ትኑር!!!

No comments:

Post a Comment