Monday, May 6, 2013

የድንበር የለሹ ጋዜጠኞች ድርጅት ሲውዲን ቅርንጫፍ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን ሸለመ


ቴዎድሮስ አረጋ

ስቶክሆልም ስዊድን
የድንበርየለሹ የጋዜጠኞች ድርጅት ወይም ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ በመባል የሚታወቀው የስዊድን ቅርንጫፍ ማህበር በስደት ላይ የሚገኘውን የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጅ መስፍን ነጋሽንንና ሁለቱን በኢትዮጵያ ለ14 ወራት በቃሊቲ እስርቤት ታስረው የተፈቱትን ስዊድናውያን ጋዜጠኞች የማህበሩ የ 2013 የመናገር እና የመጻፍ ነጻነት ሽልማት አበረከተላቸው። ትናንት ከቀትር በኋላ ዓለምዓቀፉ የተባበሩት መንግስታት የመናገርና የመጻፍ ቀን አስመልክቶ እዚህ ስቶክሆልም ከተማ በተካሄደው ዝግጅት ላይ በስዊድን የሚገኘው እና የመናገርና የመጻፍ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አንዱ አካል የሆነው የድንበርየለሹ የጋዜጠኞች ድርጅት ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው ማህበሩ እንዚህን ሶስት ጋዜጠኞች ለመሸለም ያነሳሳው ተሸላሚዎቹ ሙያዊ ግዴታቸውን በመወጣት የመናገርና የመጻፍ መብት በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም እንዲከበር እያደረጉ ላለው ትግል እውቅና ለመስጠት እንደሆነ አመልክቷል። ማህበሩ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፡እነዚህ ጋዜጠኞች ሊሸለሙ የበቁበት ሌላው ምክንያት በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች አሸባሪ ተብለው እየተፈረጁ እየታሰሩ መሆኑን ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም የዚህ ዓመቱ ሽልማት በኢትዮጵያ ላይ ትኩረት ያደረገው በአሁን ሰዓት በስልጣን ላይ ያለው መንግስት  በተቀነባበርና በተቀናጀ መልኩ እያደረገ ያለውን የአፈና ስርዓት በመባባሱ ነው ብሏል።

ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ መስፍን ነጋሽ ባደረገው አጭር ንግግር ከድርጅቱ የተበረከለት ሽልማት አገርቤት የሚገኙ ወይ በእስር አልያም በአስቸጋሪ ሁኔታ የሙያ ግዴታ እየተወጡ ላሉ የሙያ አጋሮቹ እያደረጉ ያለውን ትግል እውቅና የሚሰጥ ነው ብሏል። የተሰጠው ሽልማት እዚህ በስደት ላይ ሆኖ እያደረገ ያለውን የጋዜጠኝነት ስራ በይበልጥ እንዲገፋበት እንደሚያበረታታው ገልጿል።
ማርቲን ሺብዬ በበኩሉ በዓካል ተገኝቶ ይሄንን ሽልማት ለመቀበል መቻሉ ደስተኛ መሆኑን ገልጾ ርእዮት ዓለሙ እና ሌሎች አብረውት የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች እና አሁንም በእስር ላይ ሆነው ቀናቸውን የሚቆጥሩት የሙያ ባልደረቦቹ ደህንነት እንደሚያሳስበው ተናግሯል። ፎቶግራፈሩ ዩዋን ፐርሹን በበኩሉ በነጻው ፕሬስ ላይ የተቃጣውን አደጋ መዋጋት የሚቻለው የጋዜጠኝነት ሙያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በመጠቀም እንደሆነ ገልጿል። ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር እና እንዲሰደዱ በማድረግ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አገራት ውስጥ መመድቧን ጠቁሞ እንደዚህ ዓይነቱን እኩይ ድርጊት ለመታገል ደግሞ ያልተቋረጠና የተቀናጀ ጥረት በሁሉም ወገኖች እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
መስፍን ነጋሽ በመጀመሪያ ማለትም እንደዓውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2010 ዓም ወደ ዩጋንዳ ተሰዶ ከዛም ወደ ስዊድን በመምጣት የፖለቲካ ጥገኝነት በ 2012ዓም በማግኝት የሚኖር ሲሆን በአሁን ወቅት ለኢትዮጵያውያንና ዓለምአቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በተከታታይነት ጽሁፎችን በማቅረብ ላይ ይገኛል።
ሶስቱ ተሸላሚ ጋዜጠኞች ከሽልማቱ ስነስረዓት በኋላ በሰጡት መግለጫ ዓለም ዓቀፍ ህብረተሰብ እና ሌሎች የመብት ተሟጋች ቡድኖች በአሁን ሰዓት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሆነው የመናገርና የመጻፍ መብት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከበር የሚንቀሳቀሱ ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በተለያዩ መልኮች እንዲደገፉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። በመጨረሻም በኢትዮጵያው የሚገኘው የጠቅላይ ፍርድቤት እስክንድ ነጋ እና አንዱዓለም ዓራጌ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ ባለፈው ዓመት በሽብር ወንጀል ተከሰው የተላለፈባቸው ውሳኔ እንዲጸና መወሰኑ የሟቹ ጠቅላይ ምንስቲር ስርዓት ምን ያህል ተጠናክሮ ዜጎችን በጸረ ሽብር ህግ ስም በማስፈራራትና በማንገላታት መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

No comments:

Post a Comment