Sunday, May 5, 2013

ቴሌም ከማን አንሼ! ቴሌ በቅርቡ “ኔትዎርክ በፈረቃ” ማለቱ አይቀርም!እንደ መምራት አይል!

 የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን (ኤልፓ የሚለው የጥንት ስሙ ይመቸኛል!) ሰሞኑን በኢቴቪ ለመጀመርያ ጊዜ የሰጠውን በትህትና የታጀበ ማሳሰቢያ መሰል መግለጫ ሰምታችሁልኛል? (“ደንበኛ ንጉስ ነው” ብሎ የነገረው ማን ይሆን?) የሚገርመው ግን ምን መሰላችሁ? መግለጫውን የጀመረው የሃይል እጥረት እንደሌለ በማብራራት ነበር፡፡ (“አልገድልህምን ምን አመጣው” አለ!) የኃይል እጥረት ባይኖር እኮ --- መግለጫው ራሱ አያስፈልግም ነበር፡፡ እናም ከተፈጥሮው ውጭ የሆነ ትህትናና ጭምትነት የተንፀባረቀበት የኤልፓ መግለጫ፤ ህብረተሰቡ የትንሳኤ በዓልን መብራት ሳይቋረጥ ማክበር እንዲችል ለማድረግ ያለመ ይመስላል፡፡
ግን ምን ያደርጋል --- እሱ የኃይል ችግር የለብኝም የሚል ውሃ የማያነሳ ማብራርያ ቢያስቀድምም እኛ የተረዳነው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ለዚህም እኮ ነው ከፍተኛ የኃይል ችግር እንደገጠመው ገብቶን ስለቀጣዩ መብራት አልባ ቀናትና ወራት ቁዘማ የገባነው፡፡ እስቲ አስቡት ---- እኛ የፋሲካን በዓል በመብራት ደምቀን እንድናከብር እኮ ፋብሪካዎች ለአንድ ሳምንት ያህል ከምሽቱ 12 ሰዓት - 4 ሰዓት የኮርፖሬሽኑን ሃይል እንዳይጠቀሙበት ክፉኛ ተማፅኗል፡፡ ግን እኮ እንደሌላው የመንግስት መ/ቤት “የአቅም ውስንነት አለብን” ብሎ ቢያምን ማንም የሚጠይቀው አይኖርም ነበር (እዚህ አገር ማለቴ ነው!) በውጭ አገራትማ አቅም ከሌለህ ምን ትሰራለህ ተብሎ ወይ ይዘጋል ወይ አቅም ላለው ይሰጣል፡፡
ባለፈው ረቡዕ መሰለኝ --- በኢቴቪ የምሽት ዜና ፕሮግራም ላይ አንድ የመንግስት መ/ቤት የሚሰራውን ግድብ ለምን በቃሉ መሠረት እንዳላጠናቀቀ ሲጠየቅ፤ “የአቅም ውስንነት እንዳለብን አንክድም” ብሎ ተገላገለ፡፡ የናንተን ባላውቅም እኔ በበኩሌ “የአቅም ውስንነት” ጥያቄ የማያስነሳ ጥፋትንና ድክመትን መሸፈኚያ ጥሩ ምክንያት መሆኑን ያወቅሁት በጣም በቅርቡ ነው፡፡ (ለገዛ አገራችን ባዕድ እኮ ነን!) በነገራችሁ ላይ ከሳምንት ይሁን ከ15 ቀን በፊት በመላው አዲስ አበባ ረዘም ላሉ ሰዓታት ተቋርጦ ለነበረው የኤሌክትሪክ ሃይል፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምህረቱ ደበበ “የኃይል መቋረጡ የተከሰተው በውጫዊ ምክንያት ነው” የሚል አስደንጋጭና ሽብር የሚነዛ ምላሽ በኢቴቪ መስኮት አቀበሉን፡፡
(የመብራቱ አንሶ ድንጋጤ ይጨምሩልን!) እኔማ “እቺ ግብፅ የተባለች አገር ትንኮሳ ጀመረች እንዴ” እስከሚል ስጋት ደርሼ ነበር - በወቅቱ፡፡ ነገሩን ሲያብራሩት ግን ምንም “ውጫዊ ምክንያት” የሚያስብል ነገር እንደሌላቸው ገባኝ (የደበቁን መረጃ ከሌለ በቀር) መቼም የኤልፓ ጀብዱ ማለቂያ የለውም አይደል፡፡ አንዱን የኮርፖሬሽን ኃላፊ ጋዜጠኛ ይጠይቃቸዋል - በመብራት ድንገተኛ መቋረጥ ዙሪያ፡፡ ብዙ ዜጎች የኃይል መቆራረጥ በኑሯቸውና ሥራቸው ላይ ትልቅ እንቅፋት እንደሆነባቸው ጠቅሶ “ወደፊት ችግሩን እንዴት ለመፍታት አስባችኋል?” ይላቸዋል፡፡ እኚህኛው እንደሌላው ኃላፊ ስለአቅም ውስንነት ወይም ሌላ ሰበብ ለመደርደር አልተጨነቁም፡፡ ምናልባት እያሰቡ የነበሩት ቶሎ ኢንተርቪው አልቆ፣ ቀዝቃዛ ቢራ መጎንጨት ሊሆን ይችላል - ልክ ሥራውን በአግባቡ እንደተወጣ ሃላፊ፡፡ እናም እንዲህ አሉ “ምን መሰለህ----የኃይል ችግሩ በቀጥታ ከእድገቱ ጋር የሚያያዝ ነው --- በዚህም የተነሳ ለብቻው የሚፈታ ሳይሆን ከልማቱ ማደግ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው ---- እስከዛው ግን የአጭር ጊዜ መፍትሄዎችን ቀርፀናል፡፡
ለምሳሌ ህብረተሰቡ በጄነሬተር የመጠቀም ባህሉን ማዳበር ይገባዋል ----በእርግጥ ይህን ግንዛቤ ለመፍጠር በኛም በኩል ብዙ ተሰርቷል ለማለት አያስደፍርም ---አየህ ---እነቻይና እንዲህ ያሉ ችግሮችን የሚፈቱት የኃይል አማራጮችን በመጠቀም ነው ---እንደሶላር ኢነርጂ ያሉ ----የኛ ህዝብ ግን ከመጠን በላይ በኤሌክትሪክ ኃይል ላይ ዲፔንደንት ነው----ስለዚህ ምን አስበናል መሰለህ? በህብረተሰቡ ዘንድ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት ፕሮጀክት ነድፈን እየተንቀሳቀስን ነው ” አያችሁልኝ አይደል--- ግሩም መልስ! ውሃና ፍሳሽ ስለውሃ በየጊዜው መጥፋት ቢጠየቅ ደግሞ ምን ይላል ብዬ አስባለሁ መሰላችሁ? “ችግሩ ምን መሰለህ ---- ህብረተሰቡ ከቧንቧ ካልቀዳ ውሃ ያገኘ አይመስለውም፣ ነገር ግን በሰለጠኑትም አገራት ቢሆን ቧንቧ ሲንፎለፎል አይውልም ---እነሱ ግን የውሃ ማጠራቀሚያ በርሜል የመጠቀም ባህል ስላዳበሩ ችግሩ ጎልቶ አይታይም፣ ስለዚህ በእኛም አገር ሮቶ የመጠቀም ባህል እንዲዳብር ህብረተሰቡን ማስተማር ይኖርብናል --- አንዳንዴ የታሸገ ውሃ መጠጣትም እኮ ጥሩ ነው --- የቧንቧውን ያህል ጥራት ላይኖረው ይችላል ግን ቢያንስ በቧንቧ ውሃ ላይ ያለውን ጥገኝነት ለማስወገድ ያግዛል ብዬ አስባለሁ” እናንተ ግርም እኮ ነው የሚለው፡፡
አሁን እነዚህ ኃላፊዎች ስለኛ የሚያወሩ ይመስላሉ? እኔማ ምን ጠረጠርኩ መሰላችሁ? ኃላፊዎቹ የሚያወሩት ስለኛ አገር ሳይሆን ያቺ ኢቴቪ ብቻ ያውቃታል ስለተባለችው የአፈታሪክ (ሌጀንድ) አገር ሳይሆን አይቀርም --- (ቢሆን ነው እንጂ!) መቼም ለኛ ኑሮ ለከበደን ህዝቦች መብራት ሲጠፋ የ20ሺና 30ሺ ብር ጄነሬተር ገዝተው ይጠቀሙ፣ ውሃ ስትሄድ የታሸገ ውሃ ይጠጡ ወዘተ-- የሚል በጭካኔ የተጠቀለለ መፍትሄ ሊቀርብልን አይችልማ! (እድል ቀንቶን ነዳጅ ካልተገኘ በቀር) አንዱ ጋዜጠኛ ባልደረባዬ የቴሌኮም ከፍተኛ ሃላፊን በሞባይል ስልክ ኢንተርቪው እያደረገ ሳለ፣ በኔትዎርክ መቆራረጥ ሥራው እንደተስተጓጎለበት ሲያጫውተኝ፣ አንድ ከጭንቀት የሚወለድ መፍትሄ ብልጭ አለልኝ፡፡ ለነገሩ መፍትሄው አዲስ የሚባል አይደለም ፤ ኤልፓ ስንት ዓመት የተጠቀመበት ነው፡፡ ምን መሰላችሁ --- ኢትዮ ቴሌኮም ይሄን ቢለው ቢለው አልፈታ ያለውን ችግር ለምን ፈረቃ በማውጣት አይሞክረውም - “ኔትዎርክ በተራ ወይም በፈረቃ” በማድረግ፡፡ እንዲህ ሲሆን መጨናነቁ ስለሚቀንስ የተሻለ ጥራት ያለው ኔትዎርክ እናገኛለን ብዬ አስባለሁ፡፡
እንዴ ሁላችንም ከምናጣ ተራ በተራ ይሻለናል እኮ! በነገራችሁ ላይ ኢትዮቴሌኮም “connecting you to the future” የሚለውን “ሞቶ” ነገሮች እስኪስተካከሉ ድረስ ቢተወው ይሻላል የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡ ብዙዎች እኮ ---- “የፊቱ ቀርቶብን ከአሁኑ ዘመን ባገናኘን” እያሉት ነው፡፡ እኔ ደግሞ ወደ ኋላ እንዳይመልሰን ነው ስጋቴ - “connecting you to the past” ዓይነት፡፡ በሉ ኔትዎርክ ከመጨናነቁ በፊት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በቴክስት ሜሴጅ መላክ ልጀምር - መልካም በዓል ይሁንላችሁ! ልብ በሉ - የፋሲካ ደስታችሁን ሳይበረዝ ሳይከለስ ማጣጣም የምትሹ ከሆነ፤ መብራት፣ ውሃና ስልክ ቢጠፋም አንናደድም ብላችሁ ለራሳችሁ ቃል ግቡ፡፡ ወይም ደግሞ ሁሉም ቢቋረጥም አንዳችም ነገር እንዳልጎደላችሁ ለራሳችሁ በማሳመን በዓሉን በዘዴ ለማለፍ ሞክሩ! (ፈረንጆቹ “fake it until you make it!” እንደሚሉት)
ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment