Sunday, May 12, 2013

የወያኔ የዘር ማጥራት ዘመቻ


Dawit Melaku ( Germany)            

ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ላለፉት 38 ዓመታት  አንግቦት የተነሳው አንድን ብሔር ለይቶ የማጥራት(Ethnic cleansing) ዘመቻ  ዛሬም ቀጥሎበታል፡፡ይህ ቡድን በስልጣን እስካለ ድረስም ወደፊት ይቀጥላል፡፡ዜጎች በገንዛ ሀገራቸው ከእንስሳት ያነሰ ክብር ተነፍገው ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወሩ፣ ንብረት እንዳያፈሩ፣ ያፈሩትንም ንብረት በተደራጁ ዘራፊዎች እንዲነጠቁ እየተደረገ  ነው፡፡በተለያዩ ሀገራት የእንስሳት መብት ተከራካሪ ወገኖች ስለእንስሳት አያያዝ እና እንክብካቤ ተደራጅተው በጋራ እየተንቀሳቀሱ  በሚገኙበት ባሁኑ ወቅት ከጊዜው ጋር አብሮ መራመድ የተሳናቸው ዘረኛ ቡድኖች በተለያዩ ጊዜያት በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ወገኞቻችን ላይ የሚፈጽሙት ጭካኔ የተሞላበት ግፍ  የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ልብ የሚያደማ ነው፡፡
“ዶሮን አስረዝሞ ሲያስፘት የፈቷት ይመስላታል” እንደሚባለው የኢትዮጵያ ህዝብ አጋጣሚዎችን እየጠበቀ እስካሁን በትግስት ስለጠበቃቸው ከስተታቸው መማር የማይችሉት እና ትግስትን ከፍራቻ የሚቆጥሩት ወያኔዎች ዛሬም ከተጠናወታቸው የጥላቻ ዛር መላቀቅ አልቻሉም፡፡ይሁን እንጂ ይህን የመሰለ አሳፋሪ እና ትውልድ የማይረሳው ወንጀል የፈፀሙ የወያኔ ባስልጣናት እና ጉዳይ አስፈፃሚ የክልል ጀሌዎቻቸው ለፍርድ የሚቀርቡበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም፡፡የወያኔዎች ግፍ በዝርዝር ለመጥቀስ ብዙ ጊዜ እና ራሱን የቻለ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ የሚጠና ቢሆንም በጉልህ ከሚጠቀሱት መካከል የጎንደር እና የወሎን ለም መሬቶች ወደ ትግራይ ክልል ለመቀላቀል በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ አማርኛ ተናጋሪዎች ቤታቸው በእሳት እየጋየ አብረው ሲለበለቡ በተደራጀ መልኩ አልተቃወምናቸውም፡፡በሀረር፣በበደኖ፣ በአርሲ፣ በአርባጉጉ፣ወዘተ ወያኔዎች በለኮሱት እሳት ወገኖቻችን ሲታረዱ፤አይናቸው እያየ በገደል ሲወረወሩ እያንዳንዱ በግሉ ከማዘን ባለፈ የተወሰደ ስር-ነቀል  እርምጃ አልነበረም፡፡ዶሮ ጫችቶቹዋን በጭልፊት ስትነጨቅ ለጊዜው ስትጮህ ትቆይእና ድጋሜ መጥታ እስክትነጥቃት ዝም ብላ እንደምትጠብቀው እኛም ያለፉትን በደሎች በሆዳችን አምቀን እንደያዝነው የቀደመው ጠላት አሁንም ለድጋሜ ጥፋት ይዘጋጃል፡፡

“ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም፡፡” እንደሚባለው ዘረኛው ቡድን አላማየ ብሎ የተነሳው እና አሳካዋለሁ ብሎ የሚያልመው አማርኛ ተናጋሪዋችን በሙሉ ማጥፋ እና የሀገሪቱን ብሄራዊ ቋንቋ ሳይቀር ምርጥ ብሎ በሚጠራቸው በታላቋ ትግራይ ቋንቋ መተካት ነው፡፡ በ1993 ዓ.ም 25,000 አማራዎች ከምስራቅ ወለጋ እንዲፈናቀሉ ተደርጉዋል፡፡ምናልባት እነዚህ አማራዎች እንደሌሎች ሁሉ ብዙ ያልተነገረላቸው በመሆኑ እና ወደፊትም ወያኔዎችን ለፍረድ በሚቀርቡበት ሁኔታ ላይ ይበልጥ ሊረዳ ስለሚችል ባይኔ ያየሁትን እና ነገ ተዳፍኖ እንዳይቀር በማሰብ ዘርዘር አድርጌ አቀርበዋለሁ፡፡ ተፈናቃዮች ለበርካታ ዓመታት በአካቢው ይኖሩ የነበሩ እና እዚያው ቦታ ተወልደው ለአቅመ-አዳም እና ለአቅመ-ሄዋን የደረሱ ሁሉ ይገኙበታል፡፡እነዚህ ተፈናቃዮች ከምስራቅ ወለጋ ሲፈናቀሉ መጥተው ያረፉት ምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ ነበር፡፡ለበርካታ ቀናት እዚህ ቦታ ሲሰቃዩ ከቆዩ በኋላ ወደ አዊ ዞን በዳንግላ ወረዳ ስር በሚገኘው ጃዊ በረሃ እንዲሰፍሩ ተደረገ፡፡ጃዊ   በበረሃማነቱ የሚታወቅ፤ቢጫ ወባ ተብሎ የሚጠራው የወባ ዝርያ አመቱን ሙሉ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰትበት፤ ለሰው መኖሪያ የማይመች ምንም አይነት መሰረተ-ልማት  የሌለበት ፣ረግረጋማ ፤   በጫካ  የተሸፈነ ቦታ ነው፡፡ያኔዎች እነዚህን ተፈናቃዮች ጃዊ እንዲሰፍሩ ያደረጓቸው መፈናቀላቸው ተገቢ ስላልሆነ ለወደፊቱ ቤት ሰርተው ንብረት አፍርተው እንዲኖሩ በማሰብ አደለም፡፡ነገር ግን እነዚህን ሰዎች  ለማጥፋት  የተሻለ አማራጭ ስላገኙ ነው፡፡ይኸውም አማራጭ ሁለት ዓይነት ጠቀሜታ ያስገኝላቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ጠቀሜታ ከቡሬ በማራቃቸው ተፈናቃዮችን በተመለከተ በውጭ ለሚኖሩት ኢትዮጵያውያን እና ለመገናኛ ብዙሀን መረጃ እንዳይወጣባቸው  በማድረግ ይረዳቸዋል፡፡በዚህም በውጭው አለም ያላቸውን በውሸት የታጀለ ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜታ ሊያተርፉ እንደሚችሉ ይገምታሉ፡፡ ሁለተኛው እና ትልቁ ጠቀሜታቸው ግን እነዚህን ተፈኛቃዮች በወያኔዎች ተገደሉ ከሚባል በገዳይነቱ በሚታወቀው  በተለምዶ ቢጫ ወባ(Phalisipharum malaria) ተብሎ በሚጠራው የወባ በሽታ በማስጨረስ   በህመም  ሞቱ መባል የተሻለ የተቀነባበረ ሴራ መሆኑን በመረዳታቸው ነው፡፡በዚህም መሰረት ሰፋሪዎቹ በቂ ህክምና በማይገኝበት ለስሙ ብቻ የተቋቋመች አንዲት አነስተኛ ክሊኒክ፤ በግዳጅ መልክ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የጤና ባለሙያዎች፤የተወሰኑ የሚዋጡ እንክብሎች ብቻ እየቀረቡ ፤በሽተኞች በድንኳን ውስጥ እየተኙ እንዲታከሙ ተወስኖባቸዋል፡፡ በዚህም ያልተሟላ ህክምና በየቀኑ በግምት ከ20-30 ሰዎች የሞትን  ጽዋ ይጎነጩ ነበር፡፡
በተለይ ነፍሰ-ጡር እናቶችና ህፃናት ወዲያውኑ ለእልቂት ተዳርገዋል፡፡በቦታው አንቡላንስ ስላልነበር ሰዎችን ወደ ህክምና መስጫ ቦታው ለማምጣት በቃሬዛ ተሸክመው ነበር የሚያመጧቸው፡፡የወባው ገዳይነት አስታማሚ ሁኖ ተሸክሞ የመጣው ሰው ያመጣው በሽተኛ ምርመራ ተደርጎለት የተወሰኑ የሚዋጥ መድሃኒቶች እስኪሰጠው ድረስ የብርድ ስሚት ተሰምቶት ጸሀይ ልሙቅ ብሎ በደቂቃዎች ውስጥ በዚያው ህይወቱ ያልፍል፡፡በጣም የሚገርመው እና የወያኔዎችን  አረመኔነት የሚገልጸው ደግሞ በህይወት ያሉት ሞትን ሸሽተው እግር አውጭኝ በማለት ወደሚያውቋቸው ዘመዶቻቸው እና ወዳጆቻቸው ህይወታቸውን ለማትረፍ ቦታውን ለቀው ሲሄዱ በአካባቢው በሚኖሩ የወያኔ ታጣቂዎች ተይዘው እንዲመለሱ እየተደረገ ፤ሆን ተብሎ የመድሀኒት እጥረት እንዲከሰት በማድረግ፤ፈዋሽነታቸው አጠራጣሪ የሆኑትን የአዲግራት መድሀኒት ፋብሪካ ምርቶች ብቻ በማቅረብ ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡እነዚህን ወገኖቻችን በግፍ ሲያስጨርሱ ለፍርድ እንዲቀርቡ አላደረግንም፡፡  ሃላፊነትንን ባግባቡ አለመወጣትም በወያኔዎች መንደር ስለማያሰጠይቅ በወቅቱ በስልጣን ላይ የነበሩ ባለስልጣናትም ምንም አልተባሉም፡፡ይልቅስ በወያኔዎች ዘንድ የሚያስጠይቀው ለህዝብ መቆርቆር ፤ሰባዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ  ፤ፍትህ እንዲሰፍን መጠየቅ ነው፡፡ለዚህም ነው ለነፃነት የሚታገሉ ጀግኖት በቃልቲ እስርቤት እየማቀቁ የሚገኙት፡፡አንዱአለም አራጌ መቼ ነው ኢፍትሃዊነቱን የምታቆሙት፤መቼ ነው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ የምትወርዱት ፤መቼ ነው ማሰቃየት የምታቆሙት መቼ ነው ማሰር  የምታቆሙት ነበር ያለው ፡፡ሙሉውን ቃል ይህን ይመልከቱ፡፡http://www.youtube.com/watch?v=eIAewbwI9oo፡፡  ይህን የመሰለውን የመብት ተከራካሪ ነው በግፍ አስረው የሚያሰቃዩት፡፡ይህ ነው ለወያኔዎች ሽብርተኝነት፡፡
በ2004 ዓ.ም 30,000 አማራዎች ከደቡብ ክልል ጉራፋይዳ ወረዳ ተፈናቅለዋል፡፡እነዚህን ተፈኛቃዮች በተመለከተ የዘረኛነት መሀንዲስ የሆነው፤ አሁንም በሙት መንፈስ ሀገሪቱን የሚመራው አቶ መለስ ዜናዊ  ተፈናቃዮችን በተመለከተ ለይሰሙላ ለተቋቋመው ምክር ቤት ሪፖርት ሲያቀርቡ” ከምስራቅ ጎጃም የመጡ ቁጥራቸው 30,000 የሚሆኑ አማራዎች ተፈናቅለዋል፡፡እነዚህ አማራዎች በአንድ አጋጣሚ  በሰፈራ ምክንያት ወደክልሉ የመጡ፤ ከ10 አመት በላይ የተቀመጡ ፤ጉራፋይዳ ምስራቅ ጎጃም እስኪመስል ድረስ አስተዳደሩም ሁሉም አማራዎች ናቸው፡፡ችግሩ አማራዎች መሆናቸው አይደለም! የእነዚህ ሰዎች ስለተፈናቀሉ አማራው ተነክቷል ወይ?; አማራው ቀርቶ ምስራቅ ጎጃም ተነክቷል ወይ” ችግሩ ያለው አንዳንድ በኢትዮጵያ አንድነት እንታወቅ ፤ መለያ ባህሪያችን የኢትዮጵያ እንድነት ነው የሚሉ የመንደርተኝነት ጥያቄ ያነገቡ ቡድኖች የሚያናፍሱት አሉባልታ ነው፡፡ በማለት ነው የመለሱት፡፡የሪፖርቱ ሙሉ ማብራሪያ ይኸን ይመስላል http://www.youtube.com/watch?v=H-dqM6Iq6ck እንግዲህ 30,000 ሲፈናቀል አማራው አልተነካም ማለት ምንያክል መጠነ ሰፊ የጥፋት ድግስ እንደደገሱ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ እነዚህ ተፈናቃዮች የት እንደገቡ ማንም እርግጠኛ ሁኖ መናገር የሚችል የለም፡፡አንድም በጅምላ ጨርሰዋቸዋል አለያም ሰው በማያያቸው ቦታ ወስደው እንደ በፊቶቹ በበሽታ እንዲያልቁ አድርገዋል፡፡
በቅርቡ ቁጥራቸው ከ10,000 የማያንሱ የአማርኛ ተናጋሪዎች ከቤኒሻንጉል ጉምዝ መተከል ዞን በግፍ ከቀያቸው ከተፈናቀሉ በኋላ በመላው ዓለም ውግዘት እና ተቃውሞ ሲገጥማቸው  ወደመጡበት ተመልሰው እንዲሰፍሩ ተደርጉዋል፡፡እነዚህ ተፈኛቃዮች ንብረታቸውን ተዘርፈው ቤታቸው ተቃጥሎ የእለት ምግብ እንኳን ያልያዙ እንደመሆናቸው አሁንም ለከፋ ችግር ተጋልጠው ይገኛሉ፡፡ተፈኛቃዮች ህይወታቸው አደገኛ ሁኔታ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል መገመት ያቻላል፡፡ካለፈው ልምድ በመነሳት ወያኔዎች እንዚህን ወገኖቻችንን ህክምና እንዳያገኑ በማድረግ ሊያጠፏቸው ስለሚችሉ  አስፈላጊውን እርዳታ በማሰባሰብ ልንደርስላቸው ይገባል፡፡
በመጨረሻም መጠኑ ይለያይ እንጂ የወያኔ  የብሔር ፖለቲካ ያላፈናቀላቸው ፤እስራት እና ግድያ ያልደረሰባቸው  ብሄሮች እና ብሄረሰቦች አይገኙም፡፡እያናዳንዳችን በተደራጀ እና በተቀናጀ መልኩ እነዚህን ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ በማድረግ እና ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሀገራችን ከገባችበት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት በጋራ መቆም ያገባናል፡፡ የአቶ መለስን ራዕይ እናስፈጽማለን እያሉ አሁንም በቀቢጸ-ተስፋ ከወዲያ ወዲህ የሚባዝኑትም ሆኑ እንደ አቶ ታምራት ላይኔ ያሉ በስደት ላይ የሚገኙ ወንጀለኞች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እነሱ በሚሰጡት ቀጥተኛ ትእዛዝ መሰረት ለሞቱት ፣ለተፈናቀሉት፤ለወደመው ንብረት፣ለደረሰው ስነልቦናዊ በደል ቀጥተኛ ተጠያቂዎች በመሆናቸው በዓለም አቀፍ ፍርድቤት ጉዳያቸው እንዲታይ እና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኑ እንዲደረግ ለመላው  ወገን ወዳድ ጥሪየን አስተላልፋለሁ፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ተኑር!

No comments:

Post a Comment