Saturday, May 18, 2013

የተቃዋሚ ድርጅቶች ሰላማዊ እንቅልፍ: ለምን?


መልስ ለአማኑኤል ዘሰላም
ሚያዚያ 23 ቀን 2005 ዓ.ም
መግቢያ
በኢትዮጵያ ሃገራችን የወያኔ/ኢህአዴግ ስርዓት በህዝብ ላይ እየፈፀመ የሚገኘው በደል እጅግ ከመጠን ያለፈ ደረጃ ላይ መድረሱ እሙን ነው:: በአንፃሩ ደግሞ ተቃዋሚ ድርጅቶቻችን በህዝብ ላይ እየተፈፀመ የሚገኘውን መከራ የማስቆም ብቃት ሊኖራቸው ሲገባ፤ በተቃራኒው፤ እንኳን የህዝብን መከራ ማስቆም ቀርቶ፤ ወያኔ/ኢህአዴግ በራሳቸው ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና መቋቋም አቅቷቸው በየአደባባዩ ከህዝብ ባልተለየ መልኩ ሲያማርሩ ይታያሉ:: ይህ በሃገራችን እየታየ የሚገኘው የተዛባ ታሪካዊ ክስተት አሳሳቢነትን የተገነዘቡ ኢትዮጵያን ምሁራን ፣ ፀሃፊዎችና፣ ሌሎች ግለሰቦች የበኩላቸውን መፍትሄ ሲሰነዝሩ ማየት እንግዳ አይሆንም:: እንደ አብነት ለመጥቀስ ያህል "የትግራይ ህዝብ ዝምታ ሲተረጎም" በአብርሃ ደስታ፣ "የተቃዋሚዎች ድክመትና ለስልጣኑ ያላቸው ርቀት" በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ "መሪዎች ፈራን ካሉ፤ ተመሪዎችስ ምን ይሁኑ?" በፊልጶስ፣ እንዲሁም በፕ/ር አል ማሪያም የተፃፈውን "Ethiopia’s opposition at the dawn of democracy?" ፅሁፎችን ማንሳት ይቻላል::
እኛም በተመሳሳይ መልኩ ከዚህ ቀደም "የተቃዋሚ ድርጅቶች ሰላማዊ ትግል? ወይንስ ሰላማዊ እንቅልፍ?" በሚል ርዕስ ገንቢ ይሆናሉ ያልናቸውን ሃሳቦች ማስፈራችን ይታወቃል:: ይህንን ፅሁፋችንን በተመለከተ አማኑኤል ዘሰላም የተባሉ ተቆርቋሪ ኢትዮጵያዊ መጋቢት 25 ቀን 2005 ዓ.ም የፃፉትን አነበብን:: ግዜአቸውን ሰውተውና ፅሁፋችንን አንብበው ሃሳባቸውን ስላካፈሉን እጅግ በጣም እያመሰገንን፤ በጠቀሷቸው ነጥቦች ዙሪያ ተወያየን:: በፅሁፋቸው ብዙ ገንቢ ሃሳቦችን ያሰፈሩ ቢሆኑም፤ ለትግሉ ወሳኝ የሆኑ መሰረታዊ ችግሮች ያልተዳሰሱ በመሆናቸው፣ እነኝህ ችግሮች በአብዛኞቹ ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚንፀባረቁ ስለሆኑ፣ በዋነኝነት ደግሞ በኢትዮጵያ የህዝብ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከተፈለገ፤ ትግሉን ለመምራት ፈቃደኛ የሆኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች እነኝህን ችግሮች መፍታት የግድ ያስፈልጋቸዋል ብለን ስለምናምን፤ በጉዳዩ ዙሪያ ብዙ መሰራት እንዳለበት ተረዳን::

ከዚህ በፊት ባሰፈርነው ፅሁፍ ለእኛ የታዩንን ችግሮች ለመፍታት አጋዥ የውይይት መነሻ ሃሳብ ይሆናሉ ብለን በማሰብ ጥቂት ጥያቄዎችን ማቅረባችን ይታወሳል:: ችግሮቹ መሰረታዊ ቢሆኑም ከላይ ከጠቀስናቸው ፀሃፊ በስተቀር በጥያቄዎቹ ዙሪያ ለመወያየት የደፈረ አንድም የተቃዋሚ ድርጅት ተወካይ አልነበረም:: ስለሆነም ለህዝብ እንታገላለን የሚሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች ከህዝብ ለሚመጡ ማንኛውም አስተያየቶች ጆሯቸውን ክፍት በማድረግ፣ ስህተታቸውን ዓርመውና፣ ከህዝብ ጋር በመወያየት ሃገራችንን ከጥፋት ማዳን ካልቻሉ ከታሪክ ተጠያቂነት እንደማይድኑ ለማስገንዘብ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ እውነታውን እንዲያውቅ "እኛው በኛ.." እንዲሉ ከዚህ ቀደም ለጠቀስናቸውና ለሌሎች መሰረታዊ ጥያቄዎች "የተቃዋሚ ድርጅቶች ሰላማዊ እንቅልፍ: ለምን?" በሚል ርዕስ ሃሳባችንን እንደሚከተለው ለማስፈር ወሰንን::
ስለእኛ በጥቂቱ
ከላይ በጠቀስነው ፅሁፋችን ላይ ‘ስምንቶቹ’ ከተሰኘው መጠሪያ ስማችን በተጨማሪ ስለማንነታችን ያልገለፅንበት ምክንያት ሃሳባችንን ለማካፈል አስፈላጊ መስሎ ስላልታየንና ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስለሌለው ነበር:: ነገር ግን ፅሁፉን በተመለከተ ሃሳባቸውን ያካፈሉን ከላይ ስማቸውን የጠቀስናቸው ፀሃፊ ስለማንነታችን የተሳሳተ ግምት በመውሰዳቸው፤ እንዲሁም በሰጡን ሃሳብ መነሻነት ከአንባቢ ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅ ይረዳን ዘንድ ጥቂት ስለኛ መናገርን መረጥን::
እኛ "ስምንቶቹ" በሚል ስም የምንጠራ፤ የተለያዩ የውይይት ሃሳቦችን በመስጠትና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ የምንገኝ አምስት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ሶስት በውጭ ሃገር የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች፤ ባጠቃላይ ስምንት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ነን:: በሃገራችን ስላለው ነባራዊ ሁኔታና ህዝቡ ላይ በወያኔ/ኢህአዴግ እየደረሱበት ስላሉት በደሎች በማንሳት ስንወያይ ብዙ ጊዜ ከሚያስገርሙን ነገሮች አንዱ እውነታው ህዝብ እየተሰቃየ፣ እየተበደለ፣ እየተጨቆነ፣ ያለአግባብ ቤቱን፣ ቀዬውንና፣ ንብረቱን እየተቀማ ሆኖ ሳለ ነገር ግን 'ህዝቡ ለምን ዝም ብሎ ተቀመጠ?' የሚለው ጥያቄ ነው:: ይህም ጥያቄ የህዝብ መብትን ለማስከበር እንታገላለን የሚሉት የተቃዋሚ ድርጅቶች ምን እየሰሩ ነው? ለምን ህዝቡን አስተባብረው ወደሚፈለገው ለውጥ መጓዝ አልቻሉም? የሚሉትን ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች አስከተለብን:: ስለሆነም በነዚህ ወሳኝ ያልተመለሱ ጥያቄዎች መነሻነት የተቃዋሚ ድርጅቶች እየተከተሉ ያሉትን መንገድ በቅርበት በመመርመርና በዓለማችን በሌሎች ሃገራት ከተደረጉ ትግሎች ጋር በማወዳደር መፍትሄዎችን ለመጠቆም የበኩላችንን አስተዋዕፅዎ በማድረግ ላይ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ነን::
ሰላማዊ ትግል በተቃዋሚ ድርጅቶች እይታ
ሰላማዊ ትግል በአምባገነናዊ ጨቋኝ አገዛዝ ስር የወደቀ ህዝብ ነፃነቱንና መብቱን ለማስከበር ሰላማዊ የሆኑ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም የሚያደርገው ትግል ነው:: ይህ ህዝባዊ የትግል ስልት የጋራ ራዕይን ለመጨበጥ በአንድነት መቆምን፣ ለጨቋኞች ትብብር መንፈግንና፣ እምቢተኝነትን ያካትታል:: ህዝብ ነፃነቱን ለመጎናፀፍ ሃይሉን በማስተባበር ሰላማዊ በሆኑ መንገዶች የበላይነቱን የሚያረጋግጥበት የትግል ስልት ሲሆን፤ ይህንንም እውን ለማድረግ ያጣውን የማንነት ክብርንና በራስ መተማመንን መልሶ እንዲገነባ ማስቻልን፣ ከገዢዎቹ ቁጥጥር ውጪ የተለያዩ ህዝባዊ ተቋማትን በማቋቋም ህዝብን ማደራጀትን፣ ህዝብ ግዙፍ ወደ ሆነ ከገዢዎች ጋር ያለመተባበር እንዲሸጋገር የሚያስችሉትን ቅድመ ሁኔታዎችንና እቅዶችን መንደፍን፣ ግዙፍ ህዝባዊ አመፆችንና የተቃውሞ ሰልፎችን በተቀናጀ መልኩ ማካሄድን፣ አምባገነኖች በህዝብ ላይ የሚፈፅሙትን ግፎች በማጋለጥ ስርዓቱ በሃገር ውስጥም ሆነ በሌላው የአለም ክፍል ውግዘት እንዲደርስበት ማድረግንና፣ ሌሎች ጥበብን የተላበሱ ማራኪ ህዝባዊ እርምጃዎችን መውሰድን ይጠይቃል::
በአለማችን የሰላማዊ ትግልን ተመራጭነትና የህዝብን እምቅ ሃይልና ወሳኝነትን የሚያረጋግጡ ብዙ የተሳኩ የህዝብ ሰላማዊ ትግሎች ተካሂደዋል:: በህንድ በታላቁ ማሃተመ ጋንዲ መሪነት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1947 የተካሄደውና ህንድ ከእንግሊዞች ቅኝ አገዛዝ ነፃ እንድትወጣ ካስቻላት ሰላማዊ ትግል ጀምሮ፣ በአሜሪካን በ1960ዎቹ በዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ መሪነት የተደረገው የጥቁር ህዝብ ትግል፣ በደቡብ አፍሪካ በ1980ዎቹ የአፓርታይድ ስርዓትን የሰባበረው፣ በፊሊፒንስ በ1986 ለአምባገነኑ ፈርድናንድ ማርቆስ ውድቀት ምክንያት የሆነው፣ በፖላንድ በ1989 የኮሚኒስት ፓርቲውን ከስልጣን ያስወገደው፣ በታይላንድ በ1992 የወታደራዊ አገዛዙን ያንኮታኮተው፣ እንዲሁም በቅርቡ በቱኒዚያና በግብፅ የተካሄዱት የህዝቦች ሰላማዊ ትግሎች እንደምሳሌ ሊጠቀሱ ይችላሉ::

በማንኛውም የመንግስት አስተዳደር ሙሉ ስልጣኑና ጉልበቱ ያለው በህዝብ ዘንድ ብቻ ነው:: በአሜሪካን አገር ኒውዮርክ ከተማ የሚገኘው የአልበርት አንስታይን ኢንስቲቱት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ጂን ሻርፕ በማንኛውም መንግስታዊ አስተዳደር ውስጥ የህዝብ ወሳኝ ተፅዕኖንና መሪዎች ያለህዝብ ህልውና እንደሌላቸው ለማስገንዘብ "ከአምባገነን ስርዓት ወደ ዴሞክራሲ" በተሰኘው መፅሃፋቸው በተጨባጭ እንዳሰፈሩት "መሪዎች በራሳቸው ታክስ ሊሰበስቡ፣ ጨቋኝ ህጎችን በህዝብ ላይ ሊጭኑ፣ ...፣ ኬላዎችን ሊቆጣጠሩ፣ ገንዘብ ሊያትሙ፣ መንገዶችን ሊገነቡና ሊጠግኑ፣ ገበያዎች በሚፈለገው መጠን አቅራቦት እንዲኖራቸው ሊያስችሉ፣ ... ፣ የጦርና የፖሊስ ሰራዊቶችን ሊያሰለጥኑ፣ ... አይችሉም:: ይህንን በተግባር የሚፈፅምላቸው ህዝብ ነው:: ህዝብ ይህንን አገልግሎቱን እምቢኝ ካለ አምባገነኖች ፈፅሞ መምራት አይቻላቸውም::" ብለዋል:: በአንፃሩ ደግሞ ሃይል ሙሉ ለሙሉ የህዝብ ሆኖ ሳለ አምባገነኖች ህዝብ ታዛዥ አገልጋያቸው ሆኖ እንዲኖርና በስልጣናቸው ለመቆየት ከመግደል፣ ከመከፋፈልና፣ ከማሰቃየት ጀምሮ እስከ ማስፈራራትና ሰላም መንሳት ድረስ የሚችሉትን ጭካኔ ሁሉ እንደሚፈፅሙ አስረድተዋል::
አምባገነኖች ምንግዜም አምባገነኖች ናቸው:: በአምባገነኖች ስር ለወደቀ ህዝብ በሰላማዊ ትግል ነፃነት፣ ፍትህና፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት በቀላሉ ወይንም በአንባገነኖቹ በጎ ፈቃድ የሚገኝ አይደለም:: ስለሆነም ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ከመሸጋገሩ በፊት ህዝብ የአምባገነኖችን ዱላ ለመቋቋምና ለመመከት ብሎም የተጠማውን ድል ለመጎናፀፍ፤ የጨቋኞቹንና የሃገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ በሳል የሰላማዊ ትግል እቅድና ስልት በመቀየስ፤ እራሱን በስነልቦና፣ በቁሳዊና፣ በጠንካራ የሰው ሃይል አደረጃጀት አጠናክሮ፣ ችሎታና አቅሙን በእርግጠኝነት መገንባት ይኖርበታል:: የተቃዋሚ ድርጅቶች በእንዲህ አይነቱ ሰላማዊ የህዝብ ትግል የመሪነቱን ድርሻ ለማበርከት እስከፈቀዱ ድረስ ህዝብ ከላይ የተዘረዘሩትን ብቃቶች እንዲያጎለብት የማድረግ ግዴታና ሃላፊነት አለባቸው:: ይህንን ግዴታቸውን ለመወጣት በቅድሚያ ከፍተኛ ግብ መቀየስና ጠንካራ አደረጃጀትና እቅድ መንደፍ ይጠበቅባቸዋል:: ከሁሉም በላይ ህዝብ ጉዳት እንዳይደርስበት የመከላከልና ከአንባገነኖች የሚሰነዘሩ አይቀሬ ጥቃቶችን የመመከት ችሎታና አቅም ሊኖራቸው ይገባል::
የተቃዋሚ ድርጅቶች የሚታገሉለትን እምነት እውን ለማድረግ ችሎታቸውን በብቃት መተግበር ሳይችሉ አምባገነን መሪዎችን ለማስወገድ መግጠም የለባቸውም:: ስለሆነም ጠንካራና የተቀናጀ አደረጃጀትና ብልህ አካሄድ ሳይኖራቸው አምባገነኖችን ቢጋፈጡ ትርፉ ግድያ፣ እስርና፣ እንግልትን፣ ከዚህም ባለፈ ለመቅረፍ አስቸጋሪ የሆነ የስነልቦና ውድቀትንና ስር የሰደደ ፍርሃትን በህዝብ ውስጥ ማስረፅ ብቻ ነው::
እንዲታወቅልን የምንፈልገው የተቃዋሚ ድርጅቶቻችን የሚችሉትን አላደረጉም የሚል እምነት የለንም፤ ድል በአንድ ጀምበር እንዲመጣ የምንጠብቅ የዋሆችም አይደለንም:: እጅግ ብዙ መስዕዋትነትን እንደከፈሉ፣ ከባድ መከራና ስቃይን እንደተቀበሉ እናውቃለን:: ከላይ የጠቀስናቸው ፀሃፊ ይህንን ለማሳሰብ "እህል ሳይዘራ አይታጨድም:: ሳይታጨድ አይወቃም:: ሳይወቃ አይፈጭም:: ሳይፈጭ አይቦካም:: ሳይቦካ አይጋገርም::" ብለዋል:: ለማሳሰብ የፈለጉት ድል እንዲመጣ ብዙ መሰራት እንዳለበት ይመስለናል:: ነገር ግን እህልን ከመዝራታችን በፊት የተዘራው መብቀሉንና ፍሬ ማፍራቱን እርግጠኛ መሆን ይኖርብናል:: ይህንንም ለማረጋገጥ የሚዘራበትን መሬትና ሌሎች ግባቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ማግኘትና ማመቻቸት ያስፈልጋል:: በእኛ እምነት የእኝህ ፀሃፊ አባባል የብዙዎች ተቃዋሚ ድርጅቶች መሰረታዊ ስህተትን የሚያንፀባርቅ ይመስለናል:: አሁን በተግባር እንደምናየው ተቃዋሚ ድርጅቶች ወያኔ/ኢህአዴግ በሚያደርስባቸው ጫና ምክንያት እጅግ ብዙ መስዕዋትነትን ቢከፍሉም፣ ብዙ መከራና ስቃይን ቢቀበሉም፣ ነገር ግን ልክ ፀሃፊው እንዳሉት ሁሉ ተቃዋሚዎችም የትግሉን ሜዳ ወይንም መድረክ በአስተማማኝ ሳያበጁና ሳያስተካክሉ፣ ትግሉ በሚፈልገው መልኩ በብቃት ሳይጠነክሩና ሳይደራጁ አምባገነኑን የወያኔ/ኢህአዴግን ስርዓት መጋፈጣቸው የከፈሉት መስዕዋትነትንና የተቀበሉት መከራና ስቃይን መና አስቀርቶት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የወጠኑትን ትግል ተቀላቅሎ ለነፃነቱና ለመብቱ እንዲታገል ሳይሆን በቸልተኝነትና በፍራቻ ተውጦ በዝምታ እንዲጨቆን አድርጎታል::
ይህንን ለማስገንዘብ ከዚህ ቀደም ባሰፈርነው ፅሁፍ ያነሳናቸውን ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎችን በድጋሚ ማንሳት ያስፈልጋል:: ወያኔ/ኢህአዴግ ስልጣኑን ከተቆናጠጠበት እለት ጀምሮ የጭቆና መረቡን በህዝብ ላይ ጭኖ ያሻውን እያደረገ ይገኛል:: ይህንን መሰረት በማድረግ ያነሳናቸው ጥያቄዎች የሚከተሉት ነበሩ:: የመጀመሪያው ጥያቄአችን ‘ባሁኑ ሰአት የኢትዮጵያ ህዝብ እየተሰቃየ፣ እየተበደለ፣ እየተጨቆነ፣ ያለአግባብ ቤቱን፣ ቀዬውንና፣ ንብረቱን እየተቀማ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ለምን ዝም ብሎ ተቀመጠ?’ የሚል ሲሆን ሁለተኛውና ሶስተኛው ደግሞ ‘የህዝብ መብትን ለማስከበር እንታገላለን የሚሉት የተቃዋሚ ድርጅቶች ምን እየሰሩ ነው?’ የሚለውና ‘ለምን ህዝቡን አስተባብረው ወደሚፈለገው ለውጥ መጓዝ አልቻሉም?’ የሚሉት ናቸው::
ከላይ የጠቀስናቸው ጥያቄዎች ትክክለኛ መልሶች የሚያመላክቱት ተቃዋሚዎች የሃሳብ፣ የቁሳቁስ፣ የገንዘብ፣ የሰው ሃይልና፣ የአደረጃጀት እጥረት ብሎም ወያኔ/ኢህአዴግን የመታገል ብቃት እንደሌላለቸው ነው:: ይህ የጉልበት እጥረት የተቃዋሚ ድርጅቶች ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን በእጅጉ ገድቦት፤ እየከፈሉ ያሉት መስዕዋትነትን፣ እየተቀበሉ ያሉትን እንግልት፣ እስር፣ ግድያና፣ ሌላም ሌላም በደሎችን መና አስቀርቷቸው፤ ትግሉን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ከማድረግ ይልቅ፤ ህዝብን ተስፋ እያስቆረጠውና ፍርሃት እየለቀቀበት ይገኛል:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከጊዜ ብዛት የነበራቸው ሃይል እየተሟጠጠ በመምጣቱ፤ ልክ እንዳልተደራጀ ህዝብ ሁሉ ወያኔ/ኢህአዴግ ያሻውን ወንጀል በፈፀመ ቁጥር በመደናገጥ መግለጫዎችን ሲያዥጎደጉዱ ማየት የተለመደ ሆኗል::
በእኛ እምነት የተቃዋሚ ድርጅቶች የሚያካሂዱት ትግል የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት ያደረገ የሰላማዊ ትግል ስትራቴጂን የተከተለ አይመስለንም:: ተቃዋሚ ድርጅቶቻችን እያደረጉት ያለው የአምባገነኖች ጭቆና እጅጉን በተንሰራፋባቸው ሃገራት የሚደረግ ሰላማዊ ትግልን ሳይሆን፤ እንደ አሜሪካ ያሉ የዲሞክራሲ ስርአት በሰፈኑባቸው ሃገራት የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህዝብ እንዲመርጣቸው ገዢ ፓርቲዎች ስህተት ሲፈፅሙ በማጋለጥ የሚያደርጉትን ዲሞክራሲያዊ ትግልን ይመስለናል::
ይህንን ለማወቅ ‘በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ አለ ወይ?’ የሚለውንና ‘በኢትዮጵያ የመናገር፣ የማምለክ፣ እንዲሁም ሌሎች የሰው ልጅ ሰብአዊ መብቶች ይከበራሉ ወይ?’ የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል:: በእኛ እምነት መልሱ የለም ነው:: ይህ ሁኔታ በግልፅ በሚታይበት ሃገር፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ የመናገርና፣ የማምለክ ነፃነት በሌለበት ሁኔታ፤ ሌሎች ዲሞክራሲ የሰፈነባቸው ሃገራት ውስጥ እንደሚታየው ሁሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች በምርጫ ተወዳድረው ለማሸነፍ እየሞከሩ ይገኛሉ:: ይህ ሁኔታ ለጅብ ስጋ አቅርቦ እንዳይበላ ከመመኘት አያልፍም፤ ዛሬ ጅቡ ባይተናኮልም ስጋው እንደሚወሰድበት ከገመተ ከመባላት ወደኋላ እንደማይል ግልፅ ነው::
የተቃዋሚ ድርጅቶች ወያኔ/ኢህአዴግ ምንም ፎረም ወይንም ሜዳ እንደማይሰጣቸው ግልፅ ነው:: ነገር ግን እንታገላለን ካሉ የትግል መነሻቸው የወያኔ/ኢሃዴግ በጎ ፈቃድ ሳይሆን የራሳቸው እምነት መሆን አለበት:: የወያኔ/ኢህአዴግ መጥፎ መሆን ውጤት ላለማምጣታቸው በቂ ምክንያት ሊሆን አይገባም:: ስለሆነም እውነታውን ተረድተው አካሄዳቸውን ማስተካከል ወይንም እራሳቸውን ከትግሉ አግልለው ሃላፊነታቸውን ለአዳዲስ አመራሮች ማስተላለፍ ግድ ይላቸዋል እንላለን:: ነገር ግን እነኝህን አማራጮች መጠቀም ካልቻሉ በህዝብ ላይ ለሚደርሰው ሰቆቃና ግፍ ወያኔ/ኢህኣዴግ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችም ባልተናነሰ መልኩ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል::
በእኛ እምነት ህዝብ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ሊያሳዩ ያልቻሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ተስፋ እያደረገ ዘላለማዊ ስቃይንና ጭቆናን ይቀበላል የሚል የዋህ አመለካከት የለንም:: በቅርቡ ህዝብ እራሱን አደራጅቶ የራሱን ነፃነት በራሱ መንገድ እንደሚጎናፀፍ ጥርጥር የለንም:: ነገር ግን አሁንም ግዜው በተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ የረፈደ

አይመስለንም:: ተቃዋሚ ድርጅቶቻችን ይህንን ሊያስተውሉና ያሉባቸውን ስህተቶች ተረድተው ድክመታቸውን አስተካክለው ወደ ትክክለኛው ትግል ሊገቡ ይገባል እንላለን::
"ህዝቡ የተቃዋሚ ድርጅቶችን የራሱ አላደረገም::" ለምን?
ማንኛውም የነፃነት ትግል ያለህዝብ ቀጥተኛ ተሳትፎ ግቡን ሊመታ አይችልም:: ስለሆነም ህዝብ የትግሉ ባለቤት እንዲሆን ማስቻል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው:: ይህ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን የሁሉም ህብረተሰብ አካላት ሃላፊነት ቢሆንም፤ ትልቁ ድርሻ የፖለቲካ ድርጅቶች ይመስለናል:: ህዝብን የማንቃት፣ የማስተማርና፣ አደራጅቶ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን የማስቻሉ ሃላፊነት የተቃዋሚ ድርጅቶች ድርሻ ሆኖ ሳለ፤ ድርጅቶች ይህንን ማድረግ ባለመቻላቸው ለተከሰተው ችግር በዋነኝነት መጠቀሳቸው የግድ ነው::
አንዳንድ የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው በተደጋጋሚ እንደሚያስተባብሉት፤ ድርጅቶች የበኩላቸውን ጥረትና መስዕዋትነት እያደረጉ ቢሆንም፤ ህዝብ ድርጅቶችን የራሱ አድርጎ ባለመውሰዱና ባለቤትነት ተሰምቶት ትግሉን ባለመቀላቀሉ ምክንያት የተቃዋሚ ድርጅቶች ውጤታማ አለመሆናቸውን በመግለፅ፤ ለችግሩ ህዝብን ሲወቅሱና በተጠያቂነት ሲፈርጁት ይታያሉ:: ሁላችንም በግልፅ እንደምናየው የህዝብ ትግሉን አለመቀላቀልና ድርጅቶችም ከህዝብ ተነጥለው የበኩላቸውን ትግል እያደረጉ መሆኑ ግልፅ ነው:: ነገር ግን እነኝህ የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው የዘነጉት ዋናው ጉዳይ ህዝቡ የትግሉ አካል መሆን ያልቻለበትን ምክንያት በመመርመር መፍትሄዎችን የማግኘት ሃላፊነት የህዝብ ሳይሆን የተቃዋሚ ድርጅቶች ግዴታ መሆኑን ነው:: ስለሆነም በዚህ ንዑሥ ርዕስ እንዳስቀመጥነው "ህዝቡ የተቃዋሚ ድርጅቶችን የራሱ አላደረገም::" ለምን? ለሚለው አብይ ችግር መፍትሄ ማግኘትና ህዝብን የትግሉ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን ማስቻል ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ፤ መፍትሄ ይሆናሉ ያልናቸውን ሃሳቦቻችንን ጠቆም ለማድረግ እንወዳለን::
ለችግሩ ትክክለኛውን መፍትሄ ለማግኘት “የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ነፃነቱን አግኝቶ፣ በሰላም፣ በፍቅርና፣ በመተሳሰብ እንዲኖር ከዚህም ጋር ተያይዞ እድገትና ለውጥ እንዲመጣ ምን መደረግ አለበት?” “ይህንን እውን ለማድረግ የህዝቡና የተቃዋሚ ድርጅቶች ድርሻ ምንድ ነው?” “ከነዚህ ጉዳዮች አንፃር በተጨባጭ እየተከናወነ የሚታየው እውነታ ምን ይመስላል?” የሚሉትን መወያያ ጭብጦች ማንሳት የሚያስፈልግ ይመስለናል:: በተለይ የተቃዋሚ ድርጅቶች ሚና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እንላለን::
በእኛ እምነት የተቃዋሚ ድርጅቶች ትልቁ ራዕይ ‘የኢትዮጵያ ህዝብ በእኩል ሙሉ ነፃነቱ ተጠብቆለትና በኢኮኖሚ በልፅጎ የሚኖርባት ሃገር ኢትዮጵያን ማየት’ ሊሆን ይገባል:: ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ በኢትዮጵያ ሰላም መስፈኑ አስፈላጊ ነው:: ሰላም እንዲኖር ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅር፣ መተሳሰብና፣ ቅንነት የተሞላበት ትብብር ብሎም የኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት አስፈላጊ ይመስለናል:: በዚህ ረገድ የብሄር ፖለቲካን መሰረት ያደረጉ ድርጅቶች ወያኔ/ኢሃዴግን ጨምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍቅርን፣ መተሳሰብንና፣ ቅንነት የተሞላበት ትብብርን ብሎም የኢትዮጵያ አንድነትንና ሉአላዊነትን እንዲያጎለብት ያስችሉታል ብለን አናምንም:: እነዚህ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል የብሄርንና ሌሎች ልዩነቶችን አጉልተው በማፅረፅ፤ ልዩነቶቹ ውበቶቹ መሆናቸውን በማሳየት ፍቅሩንና አንድነቱን ከመገንባት ይልቅ፤ የግለኝነት አስተሳሰቦችን በማጎልበት አንዱ ሌላውን እንዲያገልና እርስ በእርስ እንዲጠላላ እያደረጉት ይገኛሉ:: ስለሆነም ለኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ነፃነትንና የኢኮኖሚ እድገትን ዘላቂነት ባለው መልኩ ሊያጎናፅፉት አይችሉም::
የኢትዮጵያ ህዝብ ለረጅም አመታት ያልተቀየረ የመንግስት አስተዳደርና የፖለቲካ ሂደት እንደጎዳው በተደጋጋሚ በተግባር በማየቱ እጅግ ያንገሸገሸው መሆኑ በግልፅ እየታየ ይገኛል:: ነገሮች አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠሉና ህዝብ ትግሉን የሚቀላቀልበት በቂ ምክንያት እስካልቀረበለት ድረስ፤ በኢትዮጵያ የሚፈለገው ለውጥ ሊመጣ ፈፅሞ አይችልም:: ዛሬ አማርኛ ተናጋሪዎች ከጉራ ፈርዳ ከተባረሩ፤ ኦሮሞዎች ከደቡብ ክልል ከተባረሩ፤ ነገ ደግሞ የትግራይ ሰዎች ከሌላው ክልል የሚባረሩ ከሆነ፤ ይህን አይነት ሁኔታ በሚቀጥልበት ሂደት ውስጥ ህዝብ የሚፈልገውን ነፃነት ሊያገኝ አይችልም:: ይህን መሰሉ ጥላቻን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ሂደት ተቀባይነት ባለው አዲስ ሃሳብ መተካት አለበት:: ይህም እውን እንዲሆን የተቃዋሚ ድርጅቶች መነሳት ያለባቸው ከታሪካችን ቁንፅል ድክመቶችና ከነበሩ ውሱን ችግሮች ሳይሆን፤ ወደፊት ልንፈጥራት የምንፈልጋት ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያ የሚያስፈልጓት መዋቅሮችና ሃሳቦች ምንድን ናቸው ከሚለው መሆን አለበት:: ኢትዮጵያ ውስጥ ቀጣይነትና ዘላቂነት ያለው ነፃነት ሊመጣ የሚችለው፤ ከሱም ጋር ተያይዞ ብልፅግና ሊመጣ የሚችለው፤ ኢትዮጵያውያንን በእኩልነት ሊያስተዳድር የሚችል፤ ኢትዮጵያውያንን በእኩልነት የሚያካፍል አዲስ ህገመንግስትና አዲስ የአገዛዝ መርሆ ሲኖር ብቻ ነው::
ባሁኑ ሰአት ተቃዋሚ ድርጅቶች ከወያኔ/ኢህአዴግ በተሻለ መልኩ ህዝብን ሊማርክና ወደ ትግሉ ሊቀላቅል የሚያስችል አዲስ ሃሳብ የማፍለቅ እጥረት በእጅጉ ይታይባቸዋል:: የተቃዋሚ ድርጅቶች ህዝብ ትግሉን እንዲቀላቀል ከፈለጉ ወያኔ/ኢሃዴግ እንደ ስርዓት ሊቀጥል የማይችልበትንና ህልውናውን ሊቀጭ የሚችል ሃሳብ/ideology፤ ነገር ግን በህዝብ ዘንድ አሳማኝና ፋይዳ ያለው የአገዛዝ አማራጭን በማፍለቅ፤ ህዝብ ወደነርሱ እንዲመጣ እጃቸውን አጣጥፈው በመጠበቅ ሳይሆን፤ እነርሱ ወደህዝብ ወርደው አማራጮቻቸውን ለህዝብ በማቅረብ ሊማርኩትና ትግሉን እንዲቀላቀል ማስቻል ይኖርባቸዋል::
የተቃዋሚ ድርጅቶች በእኛ እይታ
ከላይ የጠቀስናቸው ፀሃፊ ሊያሳስቡን እንደሞከሩት በፅሁፋችን ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶችን በጥቅሉ በአንድ ጎራ መመደባችን ተገቢ አለመሆኑን በመግለፅ፤ በኢትዮጵያ ብዙ አይነት የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች ስለመኖራቸው አስምረውበታል:: በተለይ በፕ/ር አል ማሪያም "Ethiopia’s opposition at the dawn of democracy?" በሚል ርዕስ መስከረም 2005 የተፃፈ ፅሁፍን ዋቢ ጠቅሰውና የራሳቸውን አክለው ተቃዋሚዎችን በስድስት ክፍሎች መመደብ እንደሚቻል ነግረውናል:: በዝርዝር ሲያስቀምጧቸውም “ታማኝ ተቃዋሚዎች፣ ዝምታን የመረጡ ወይም ዝም እንዲሉ የተገደዱ ተቃዋሚዎች፣ ያልተደራጁ ተቃዋሚዎች፣ የተከፋፈሉ ተቃዋሚዎች ፣ አንድ ሆነው መርህ ያላቸው ዴሞክራቲክ ተቃዋሚዎች” የሚባሉትን አምስት ጎራዎች ፕ/ር አል ማርያም በፅሁፋቸው ያሰፈሯቸው መሆኑንና ያላካተቱት ሌላ ተጨማሪ ጎራ ያሉትን "በውጭ ሃገር ያሉ ተቃዋሚዎች" በማለት በዝርዝር ለማስረዳት ሞክረዋል::
ወደ ዋናው ሃሳብ ከመግባታችን በፊት የተቃዋሚዎች እና የተቃዋሚ ድርጅቶች በሚሉት ስሞች መካከል የትርጉም መወሳሰብ/መጋጨት እንዳይኖር በሁለቱ ስሞች መካከል ያለንን የትርጉም ልዩነት ለአንባቢያን ግልፅ ማድረግ ያስፈልጋል:: በእኛ ትርጓሜ ተቃዋሚዎች የሚለው ስም ጥቅል ስም ሲሆን ተቃዋሚ ድርጅቶችንና ሌሎች ግለሰቦችን በስሩ ያካተተ ነው:: በአንፃሩ ደግሞ ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚለው ስም የሚወክለው ተቃዋሚ ግለሰቦችን በአባልነት የሚይዙ ተቋማትን ይሆናል:: ስለሆነም ፅሁፋችን ተቃዋሚ ድርጅቶችን ብቻ የሚመለከት መሆኑን ልናሰምርበት እንወዳለን::

ፀሃፊው እንደ ስድስተኛ ተጨማሪ የተቃዋሚ ጎራ አድርገው ያቀረቧቸው "በውጭ ሃገር ያሉ ተቃዋሚዎች" ከሚኖሩበት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ልዩነት ውጭ ከአምስቱ የተለየ ጎራ ውስጥ ሊያስመድባቸው የሚችል ትርጉም ያለው ምክንያት ያለ አይመስለንም:: እኝህ ፀሃፊ "አንዱ ትግሉን የጎዳው ትልቁ ችግር አገር ቤት የሚኖረው ህዝብ በነዚህ ውጭ አገር ባሉ ድርጅቶች ላይ ብቻ ትስፋ ማድረጉ ነው:: ...ይህ ትልቅ ስህተት ነው::" በማለት ህዝብን ወቅሰዋል:: ነገር ግን ያላስተዋሉት ሁለት ዋናና ወሳኝ ጉዳዮች አሉ:: አንደኛው በምንም አይነት ምክንያት ህዝብ በጅምላ ሊሳሳት አይችልም:: ሁለተኛው ህዝብ ቢሳሳትም እንኳን ህዝብ የሚደግፈው ሃሳብ እስከሆነ ድረስ ማንኛውም በዲሞክራሲ የሚያምን ግለሰብም ሆነ ተቋም ሊቀበለው እንጂ ህዝብን በጅምላ ስህተት እንደሰራ ሊወቅስ አይገባውም:: ይህ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው::
በእኛ አስተሳሰብ ተጨባጭ የሆነ ውጤትን ሊያስመዘግብ የሚችልና ህዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆነበት የነፃነት ትግልን ለማከናወን ዋናው መሰረታዊ መነሻ፤ ‘ህዝብ አምኖበት ሊቀበለው የሚችል ሃሳብ/ideology ማፍለቅ መቻል ነው::’ ከላይ የጠቀስናቸው ፀሃፊ በፅሁፋቸው እንዳሰፈሩት ‘ህዝብ ተስፋ የጣለባቸው በውጭ ሃገር የሚኖሩ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ነው’ ብለዋል:: ይህ እውነት ከሆነ ደግሞ ህዝብ ተስፋ እየጣለ የሚገኘው አጠገቡ እንታገልልሃለን እያሉት የሚገኙትን በሃገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችን ሳይሆን፤ በውጭ የሚገኙትን ይሆናል ማለት ነው:: እንደኛ አስተሳሰብ ህዝብ ይህንን የወሰነበት ምክንያት በሃገር ውስጥ ከሚገኙት ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚጠብቀውን ሃላፊነት የመወጣት ብቃት አላገኘም:: እኛም በዚህ የህዝብ ፍላጎት ሙሉ ለሙሉ እንስማማለን:: ስለሆነም በሃገር ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚታገሉት ለህዝብ እስከሆነ ድረስ፤ ህዝብን ከመውቀስ ይልቅ፤ መሬት ላይ የሚጨበጥ ውጤት ለማሳየት ከስተታቸው ተምረው፤ ህዝብ ከነሱ የሚጠብቀውን ብቃት በተግባር እያሳዩ በመጓዝ ህዝብን ወደነሱ መሳብና መማረክ ሲችሉ ብቻ ነው::
እኝህ ፀሃፊ "በውጭ አገር ያሉ ተቃዋሚዎች በውጭ አገር ያሉ ናቸው::" ብለዋል:: በእኛ አመለካከት በውጭ አገር ያሉ ተቃዋሚዎች በውጭ ተወስነው የሚቀሩ አይመስለንም:: ፀሃፊው በውጭ ሃገር ስላሉት ተቃዋሚዎች የተሳሳተ ግንዛቤና ግምት ያላቸው ይመስለናል:: በዓለማችን ህዝባቸውንና ሃገራቸውን ከጬቋኝ ገዢዎች ለማላቀቅ በሃገር ውስጥ ሲታገሉ ቆይተው ጨቋኞች በፈጠሩባቸው ጫና ምክንያት ወደ ሌላ ሃገር በመሄድ በውጭ ሃገር ሆነው በሃገር ውስጥ የሚደረግ ትግልን አቀናጅተውና መርተው ህዝባቸውን ለነፃነት በማብቃታቸው ታሪክ ሁልጊዜ የሚያወድሳቸው አያሌ ታላላቅ ሰዎች አሉ:: ለእማኝነት ያህል የታንዛኒያ ህዝብ 'ምሁሩ' እያለ የሚጠራቸው ዶ/ር ጁሊየስ ኔሬሬና የአፍሪካ አባት የሚባሉት ታላቁ የነፃነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላን መጥቀስ ይቻላል:: ወደ ሃገራችንም ስንመለስ፤ የሌሎች ሃገራት የነፃነት ታጋዮች እንዳደረጉት ሁሉ፤ በውጭ ሃገር የሚኖሩ ተቃዋሚዎች ከአገር ውጭ ሆነው ህዝብን በማደራጀትና ትግሉንም በማቀናጀት፤ አስፈላጊ በሆነበት ሰአት ሁሉ ወደ አገር ውስጥ ከመግባት የሚያግዳቸው አንድም ምክንያት አይታየንም:: ለትግሉ ወሳኝ የሆነው ነፃ መድረክ በሌለበት፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት መብት በሚከለከልበት፣ ገንዘብ ይዞ የስብሰባ አዳራሽ መከራየት በማይቻልበት፣ የእራት ዝግጅት ማዘጋጀት በማይፈቀድበት ሁኔታ በወያኔ/ኢህአዴግ በጎ ፈቃድ ብቻ ከሚደረግ ትግል ይልቅ "በውጭ ሃገር ያሉ ተቃዋሚዎች" የሚከተሉት የትግል ስትራቴጂ ውጤት ለማምጣት የቀረበ ይመስለናል:: እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ወያኔ/ኢህአዴግም ከደርግ ጋር በነበረው ትግል ወቅት እራሱን አጠናክሮ የትግሉን መድረክ በሃገር ውስጥ እስከሚገነባ ድረስ ይጠቀም የነበረው የጎረቤት ሃገሮችን እንደነብር ነው:: ስለሆነም የወያኔ/ኢህአዴግን አረመኔአዊ ጫና በህዝብ አጋርነት መከላከልና ነጻ የሆነ መድረክ መፍጠር እስኪቻል ድረስ በውጭ ሆኖ መደራጀት ወሳኝ ነው እንላለን:: ነገር ግን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው እውነታ በሃገር ውስጥና በውጭ ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች ለአንድ አላማ ህዝቡን አስተባብረው በቅንጅት መስራት ካልቻሉ በቀር በተናጥል የሚደረጉ ትግሎች ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት ይህ ነው የሚባል ፋይዳ ያመጣሉ ብለን አናምንም::
የተቃዋሚዎች ጎራ በሚመለከት ለእኛ የሚስማማን አመዳደብ መሰረታዊ የፖለቲካ እምነቶቻቸውንና የመርሆቻቸውን ልዩነት መሰረት በማድረግ የሚደረግ አመዳደብ ነው:: ስለሆነም በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን ወያኔ/ኢህአዴግን ከመቃወም ውጪ በሁለት ክፍሎች ልንመድባቸው እንችላለን:: የመጀመሪያዎቹ በፖለቲካ ፍልስፍናቸው የነፃነትን ትርጉም በዋናነት ከወል መብት ጋር የሚያያይዙ ድርጅቶች ሲሆኑ፤ መሰረታዊ ግባቸውን ለብሄር ነፃነት ቅድሚያ በመስጠት ኢትዮጵያን መመስረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ድርጅቶች ናቸው:: የነኝህ ድርጅቶች ፍልስፍና ከወያኔ/ኢሃዴግ የፖለቲካ ፍልስፍና ጋር መሰረታዊ ልዩነት የለውም:: ነገር ግን በተቃዋሚው ዙሪያ እንዲሰለፉ ያደረጋቸው ብቸኛው ምክንያት ከወያኔ/ኢሃዴግ ጋር ባለመስማማት ያነገቡት የስልጣን ጥያቄ ነው:: በሁለተኛው የተቃዋሚ ድርጅቶች ጎራ የሚመደቡት ደግሞ፤ በፖለቲካ ፍልስፍናቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማንኛውም ባህሎች ሃይማኖቶችና ሌሎች የወል መብቶች በእኩልነት መከበር አለባቸው፤ ነገር ግን ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ መሰረቱ ከዘርና ከሃይማኖት ውጭ ተፈጥሮአዊ የሆነው የግለሰቦች ሰባዊ መብት መከበር ነው የሚሉ ናቸው:: ስለሆነም እነኝህ ተቃዋሚ ድርጅቶች በኢትዮጵያ በዘር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን ሳይሆን፤ በግለሰብ መብት ላይ ያተኮረ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ/ት በዜግነቱ/ቷ ብቻ እኩል እንደሆነ የሚያረጋግጥ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍቅርና አንድነትን የሚጠብቅ አማራጭ የፖለቲካ አስተዳደርን ለህዝብ በማቅረብ የሚታገሉ ድርጅቶች ናቸው::
የተቃዋሚ ድርጅቶች በሁለት ወይንም በስድስት ጎራ መመደብ በኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት ዙሪያ ለመወያየት ቅድመ ሁኔታ ሊሆን የሚገባ አይመስለንም:: ነገር ግን ዋናው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ "ከዝንጀሮ ቆንጆ..." እንደሚባለው ሁሉ፤ መሬት ላይ በተጨባጭ የሚታይ ውጤት ማሳየት የቻለ ተቃዋሚ ድርጅት አለመኖር ነው:: ስለሆነም ወያኔ ባሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያሻውን ወንጀል እየፈፀመ ይገኛል::
ማጠቃለያ
ሃሳባችንን የምንቋጨው በምንወዳት ኢትዮጵያ ሃገራችን ቀደምት ታሪካችን የምንኮራና በህዝባችን እጅግ የምንተማመን መሆናችንን በማስመር ነው:: አበው "ነገር በምሳሌ ..." እንዳሉት፤ በቅርቡ የአረብ ስፕሪንግ” ተብሎ የሚጠራው በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪካ የተካሄደውን የህዝብ አመፅ እንደ አብነት ማንሳቱ ጠቃሚ ይመስለናል:: ቱኒዚያ የአረብ ስፕሪንግ ጀማሪዋ ሃገር መሆኗ ይታወቃል:: የህዝብ አመፁ በቱኒዚያ በተሳካ ሁኔታ ከተጠናቀቀና ቤንአሊም ከተባረረ በኋላ ይህ የህዝብ አመፅ ወደ ግብፅ ሊሄድ ይችላል ይሆን? በሚለው ጥያቄአዊ ሃሳብ ላይ የፖለቲካ ጠበብቶች ብዙ ብለው ነበር:: በተለይ ቱኒዚያ ግብፅ አይደለችም ስለዚህ የህዝብ አመፁ እንደ ቱኒዚያ ሁሉ በግብፅ ሊከሰት አይችልም የሚለውን አስተሳሰብ ደግፈው ምክንያታቸውን ሲደረድሩ የነበሩ ብዙ ናቸው::
ቱኒዚያ ግብፅ አይደለችም የሚል ሃሳባቸውን ለማስረዳት ሲጠቅሷቸው ከነበሩት ምክንያቶች መካከል በቱኒዚያ ህዝብ መካከል ያለው የሙስሊሙና የክርስትናው ሃይማኖቶች ውጥረት ግብፅ ካለው እጅግ በጣም ያነሰ ስለሆነ በግብፅ ህዝብ አንድ ሆኖ ሊታገል አይችልም፣ ቤንአሊ እንደ ሙባራክ ጨካኝ አይደለም፣ ሙባራክ ጠንካራ የጦር ሰራዊት አለው ስለዚህ በቀላሉ ከህዝብ መካከል ጥቂቶችን ገድሎ ሊቀጨው ይችላል፣ ቱኒዚያዎች ከግብፆች የበለጠ የተማሩ ናቸው፣ የፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያዎችንም ቱኒዚያዎች በስፋት ተጠቃሚዎች ስለሆኑ ግብፅ ውስጥ እንደ ቱኒዚያ ያለ አመፅ ሊከሰት አይችልም፣ ሌላም ሌላም… እያሉ ትንታኔዎችን ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወቃል:: ይታዩአቸው የነበሩት ምክንያቶች ግብፆች በሙባረክ አምባገነናዊ አገዛዝ ለአመታት ብዙ ተረግጠዋል፣ ተጎድተዋል፣ ተበዝብዘዋል፣ እነርሱ በድህነት እየማቅቁ ሳሉ ጥቂት ግለሰቦች በሃብት ሲትረፈረፉ ምንም አላደረጉም የሚሉት ብቻ ነበሩ:: ነገር ግን ፍፃሜው ላይ የታየው እውነታ፤ ግብፆች እጅግ ማራኪ የሆነ የህዝብ ትብብርና ሰላማዊ ተጋድሎን በአደባባይ ለአለም ህዝብ በሚገባ ማሳየታቸውና፤ አስፈሪና ጨካኝ እየተባለ ሲነገርለት የነበረውን የሙባረክ ስርዓት ከትከሻቸው ላይ አሽቀንጥረው መጣል

መቻላቸው ነው:: በዚህ ዙሪያ ምሁሮቹና ፖለቲከኞቹ ያለማስተዋል ችላ ብለውት የነበረው ዋናው ቁምነገር የህዝብ እምቅ ሃይል በአምባገነኖች አስፈሪነት ሊሟሽሽ ፈፅሞ እንደማይችል ነበር::
የወያኔ/ኢህአዴግ ቡድን ስልጣን ከተቆናጠጠበት ሰአት ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እጅግ ስር የሰደዱ ችግሮችንና በደሎችን ሲፈፅም ኖሯል:: የኢትዮጵያ ህዝብ የተጫነበት ህመም ከግብፅና ከቱኒዚያ እጅግ የከፋ ነው:: በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ 11ኛው ሰአት ላይ እንደሚገኝ ለሁላችንም ግልፅ ነው:: ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደ ግብፆቹ ሁሉ፤ የወያኔ/ኢህአዴግ ጦር ሰራዊት መብዛት፣ ፍቅር እያለው በዘር በሃይማኖት ሳይወድ መከፋፈሉ፣ ጥቂቶች ሲበለፅጉ እርሱ ግን በድህነት መማቀቁ፣ በተቃውሞ ሰልፍ ብሶቱን ለማሰማት በወጣ ቁጥር በአጋዚው የወያኔ ሃይል በተደጋጋሚ በግፍ መጨፍጨፉ፣ መታሰሩና፣ ስቃይን መቀበሉ የህዝብን እምቅ ሃይል በበለጠ ያጎለብትለት እንጂ ሊያዳክመው ፈፅሞ አይቻለውም::
ነገር ግን በግብፅ የተደረገው የተሳካ አመፅ ዝም ብሎ በመላ የመጣ አይደለም:: የአመፁ አስተባባሪዎችና አንቀሳቃሾች እጅግ በጣም በሳል ስራዎችን ስለሰሩ፣ የህዝቡን የልብ ትርታ እጅግ አድርገው በመረዳታቸው፣ ቁስሉ ስለተሰማቸው የሙባረክ ስርዓት ህዝብን እንደሚያጠፋ ስለተረዱት እውነታውን ለህዝብ ስላመላከቱት ብሎም ህዝብ ወዶና በቃኝ ብሎ ትግሉን እንዲቀላቀል ስላስቻሉት ነው:: የኛም ፖለቲከኞችና የድርጅት መሪዎች ፍፁም የሆነ የአመለካከትና የአካሄድ መሰረታዊ ለውጥ በማድረግ፤ የህዝብ ቁስል ሊያማቸው፣ እውነታውንም ሊነግሩትና፣ አደራጅተው ከዚህ ስቃይና መከራ ሊታደጉት ይገባል:: ስለሆነም እጅግ ብዙ ስራዎች እንደሚጠብቃቸው መረዳት ያለባቸው ይመስለናል:: ከግብፆቹ ተምረው እራሳቸውን ካስተካከሉ የምንመኛትን፣ ለሁሉም እኩል የሆነችና፣ የህዝብ የበላይነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን በቅርቡ እንደምናያት ጥርጥር የለንም::
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
ስምንቶቹ
Email: nleethiopia@gmail.com

No comments:

Post a Comment