Friday, May 17, 2013

አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች “እንቅልፍን” በተመለከተ


«የተቃዋሚ ድርጅቶች ሰላማዊ ትግል ? ወይንስ ሰላማዊ እንቅልፍበሚል ርእስ፣ ስማቸዉን ያልጠቀሱ አንድ ኢትዮጵያዊ የጻፉትን ጽሁፍ አነበብኩ። አገር ቤት ባሉ «የተቃዋሚ ፓርቲዎች ነን» በሚሉ ድርጅቶች ላይ ያተኮረ ጽሁፍ ነዉ። አገር ቤት የሚንቀሳቀሱ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች እያሉ፣  እስከመቼ ሕዝብ መብቱና ነጻነቱ ተረግጦ እንደሚኖር ያሳሰባቸው ይመስላል።  ተቃዋሚዎች በሥራ ላይ ሳይሆን በእንቅፍል ላይ እንዳሉም በመግልጽ ተቃዋሚዎቹ ሊመስልሱት የሚገባ ጥያቄዎችን አስቀምጠዋል።
«የሕዝብ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንታገላለን የሚሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች ምን እየሰሩ ነው?  ሕዝብን አስተባብረው ወደሚፈለገው ለውጥ መጓዝ ያልቻሉበትስ ምክንያት ምንድነውየሚሉት ጥያቄዎች በዋናነት የተቀመጡ ናቸዉ፡፡
ይመስለኛል እኝህ ጸሃፊ በዉጭ አገር የሚኖሩ፣  በሕዝባቸው ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደረሰ ባለዉ ግፍ ያዘኑና የተቆጡ፣ አገራቸዉን የሚወዱ ኢትዮጵያዊ መሰሉኝ። ጊዜ ወስደው፣ ካላቸው አገራዊ ተቆርቋሪነት የተነሳ፣ ይህን መልካም ጽሁፍ ስላበረከቱልን  ምስጋናዬንና አክብሮቴን ላቀርብ እወዳለሁ።

ስለተቃዋሚዎች በምናነሳበት ጊዜ ተቃዋሚዎችን በተለያዩ ክፍሎች ልንመድባቸው እንችላለን። መስክረም 2005 / አል ማርያም “Ethiopia’s opposition at the dawn of democracy?” በሚል ጽሁፋቸዉ ተቃዋሚዎችን በአምስት ከፍለዋቸዋል። ታማኝ ተቃዋሚዎች፣ ዝምታን የመረጡ ወይም ዝም እንዲሉ የተገደዱ ተቃዋምዊዎች፣ ያልተደራጁ ተቃዋሚዎች፣ የተከፋፈሉ ተቃዋሚዎች፣ አንድ ሆነው መርህ ያላቸዉ ዴሞክራቲክ ተቃዋሚዎች። / አል ማሪያም ከዘረዘሩት አምስቱ በተጨማሪ፣  በስድስተኛነት በዉጭ አገር ያሉትን ተቃዋሚዎች እጨምራለሁ። እንግዲህ የትኛዉ አይነት ተቃዋሚች እንደሆኑ ሳንለይ፣ በጅምላ በተቃዋሚዎች ላይ ትችት ማቅረብ ትንሽ የሚያስቸግር ይመስለኛል።
በዉጭ አገር ያሉ ተቃዋሚዎች በዉጭ አገር ያሉ ተቃዋምዊች ናቸው። ከሕዝቡ እንደመራቃቸው፣  ሕዝብን መርተዉና አደራጀተዉ የሚፈለገዉን ዉጤት ማምጣት ይችላሉ ብሎ ማሰብ ትንሽ አሰቸጋሪ ነዉ። አንዱ ትግሉን የጎዳዉ ትልቁ ችግር፣ አገር ቤት የሚኖረዉ ሕዝብ፣  በነዚህ ዉጭ አገር ባሉ ድርጅቶች ላይ ብቻ ተስፋ ማድረጉ ነዉ። በስፋት ትግሉን በአገር ቤት ከመቀላቀል ይልቅ፣ ዉጭ ያሉ ድርጅቶች ታግለዉና ተዋግተዉ ነጻ እንዲያወጡት ይጠበቃል። ይህ ትልቅ ስህተት ነዉ።
እዉነትን እና የተጨበጠ መረጃ  ይዘን የምንነጋገር ከሆነ፣  እንኳን የሚጠበቀዉን ለዉጥ፣  ፈረንጆች እንደሚሉት በሪሞት ኮንትሮል ከሩቅ ሆኖ ሊያመጣ ቀርቶ፣  ጭላንጭል ተስፋ የሚሰጥ ድርጅት በዉጭ አገር አለ ለማለት ይቸግራል። (ከተሳሳትኩ ለመታረም ዝግጁ ነኝ ) መሰረቱን አሰመራ ያደረገዉ የግንቦት ሰባት እና የኦነግ ትብብር፣ እንደ ኢሕአፓ- ያሉ ድርጅቶችን ያቀፈው ሸንጎ፣ በነዶር እሸቱ የሚመራዉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር መንግስት የመሳሰሉ በዉጭ አገር በርካታ ድርጅቶች አሉ። እናውቃቸዋለን። አብረዉን ነዉ ያሉት። ጥረታቸውን ድካማቸውን እናከብራለን። ነገር ግን እነዚህ ድርጅቶች ፍቃደኛ ሆነዉ፣  ከአገር ቤት የተነጠለ ትግል ምንም ሊያመጣ እንደማይችሉ ተረድተዉ፣ አገር ቤት የሚደረገዉን ሰላማዊ ትግል በማገዝ አስተዋጽኦ  ሊያብረክቱ ይችላሉ እንጂ በራሳቸዉ ምንም ሊያመጡ አይችሉም። ይሄን ሐቅ ኢትዮጵያዉን በጥንቃቄ መገንዘብ ያለብን ይመስለኛል።
አገር ቤት ወዳሉት ተቃዋሚዎቾ ስንመለስ፣  / አል ማርያም እንዳሉት ታማኝ ተቃዋሚዎች አሉ። እነዚህ ለይስሙላ «ተቃዋሚዎች አሉ ለማስባል» በገዢዉ ፓርቲ የተጠፈጠፉ የዉሽት ተቃዋምዊች ናቸው። የአየለ ጫሚሶን ቅንጅት እንደምሳሌ መጥቀስ እንችላለን።
ታማኝ ተቃዋሚ ያልሆኑ፣ ነገር ግን እንደሚገባው ያልተደራጁ በመካከላቸው ክፍፍል የነበረባቸዉና ያለባቸዉ በርካታ የተቃዋሚ ድርጅቶች አሉ። የአንድነት ፓርቲ፣ የሰማያዊ ፓርቲ፣ የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ አረና ትግራይ የመሳሰሉ ከሰላሳ በላይ የሚሆኑ ድርጅቶች  የመከፋፈሉን እና የመደራጀቱን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተዉት በአንድ ላይ ለመስራት ጥረት እያደረጉ ነዉ። የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ፈርመዉ፣ የዲሞክራሲ ተቋማት ጻና ገለልተኛ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የጋራ ትግል ጀምረዋል። እንግዲህ ይህ በአንድነት ለመስራትና ለመንቀሳቀስ የሚደረገዉ ጥረት በራሱ ትልቅ ሥራ ነዉ።
እህል ሳይዘራ አይታጨድም። ሳይታጨድ አይወቃም። ሳይወቃ አይፈጭም። ሳይፈጭ አይቦካም። ሳይቦካም አይጋገርም። ብዙዎቻን የምንጠበቀው ዉጤት እንዲመጣ ከፈለገን፣ ብዙ መሰራት ያለብን ሥራ አለ። በአቋራጭና በአንዲት ጀንበር ድል አይገኝም። አገር ቤት ያሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች አይመስለንም እንጂ፣  በዉጭ አገር ያሉ ሜዲያዎች እየተከታተሉ በስፋት አይዘግቡትም እንጂ፣ እጅግ በጣም ከባድና ዉስብስብ በሆነ ሁኔታ ሕዝቡን ለማደራጀትና ለማስተማር እየሞከሩ ነዉ። አቶ በቀለ ገርባ  የኦፌኮ አመራር አባል ናቸዉ። በእሥር ቤት ይገኛሉ። አቶ አንዱዋለም አራጌ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል ናቸው። በእሥር ቤት ይገኛሉ። / ርዮት አለሙ ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ቅርበት ያላት ናት። በእሥር ቤት ትገኛለች።
«የተቃዋሚ ድርጅቶች አያሌ አባሎቻቸውና መሪዎቻቸውንም ጨምሮ በወያኔ የሃሰት ውንጀላ በየ እስር ቤቱ ውስጥ ታጉረው እየማቀቁ ቢሆኑም ድርጅቶቹ ህዝብን አስተባብረው ጫና በመፍጠር ለማስፈታት ያደረጉት ሙከራ የለም» ሲሉ ከላይ የጠቀስኳቸው ጸሐፊ ትችት አቅርበዋል። አንድ የዘነጉት ጉዳይ ቢኖር ግን እነዚህ ዜጎች መጀመሪያዉኑ የታሰሩት፣ ድርጅታቸው ሥራ እየሰራ ስለነበረና መታሰራቸውም ከሥራ የተነሳ እንደሆነ ነዉ። ጸሃፊዉ እንዳሉት፣ ሕዝብ ብሉ መሪዎችን ለማስፈታት እንዲነሳ ደግሞ መደራጀት አለበት። ህዝብን ለሰላማዊ ትግል ለማደረጀት መረጃ ቁልፍ ነዉ። ያለ መረጃ ያለ ንቃት ሕዝብን ማደራጀት አይቻልም። ሕዝብ ከፍርሃት እንዲላቀቅ፣ በራሱ እንዲተማመን ለማድረግ ሕዝብን ማስተማርና ማሳመን የግድ ነዉ። የአንድነት ልሳን የሆነችዉ የፍኖት ጋዜጣም በአገዝዙ እንዳትታተም እስከተደረገችበት ጊዜ ድረስ፣ በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫዉታለች; የፍኖት ጋዜጣ አዘጋጆችም ሆነ የአንድነት ፖርቲ አመራር አባላት ሊታሰሩ እንደሚችሉ እያወቁም፣ ሳይፈሩ መረጃዎች ለሕዝብ ለማቅረብ ሞክረዋል። ይህ አይነቱ ሕዝብን የማስተማርና የማንቃት እንቅስቃሴ ሌላዉ ትልቅ ሥራ ነዉ።
ገዢዉ ፓርቲ ግን በብርሃነ ሰላም ማተሚያ ቤት ፍኖት እንዳትታተም አደረገ።  የአንድነት ፓርቲ ግን ዝም ማለትን አልመረጠም። ጫና በበዛ ቁጥር ግፊቱን ቀጠለ። የፍኖት ማተሚያ ማሽንን ለመግዛት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
ከአንድነት ፓርቲ ጋር በቅርበት የሚሰራ አንድ የፖለቲካ ድርጅት አለ። ሰማያዊ ፓርቲ ይባላል። (በጣም ተስፋ አደርጋለሁ ሰማያዊ ፓርቲ ከአንድነት ፓርቲ ጋር እንደሚዋሃድ) ሰማያዊ ፓርቲ አገራዊ አጀንዳ አንግቦ  30000  ሺህ በላይ ለሆነው ወገናችን ደም መፍሰስ ምክንያት የነበረዉ፣ የግራዚያኒ ሓዉልትን በተመለከተ፣ በአዲስ አበበ ስድስት ኪሎ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ ነበር። የዜጎች የመሰብሰብ መብት በአገዛዙ ተረግጦ፣ ከአርባ በላይ ኢትዮጵያዉያን ታስረዉ ነበር። ዶር ያእቆብ ኃይለማሪያም እንዲሁም በርካታ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባላት ወህኒ በመውረድ የአገዛዙን አምባገነንነት አጋልጠዋል። ለካቴና እጆቻቸዉን በመስጠት ለሕዝቡ ድፍረትን  በተግባር አስተምረዋል። ይሄ ትልቅ ሥራ ነዉ።
በዋቢ ሸበሌ በተደረገ ሥነ ስርዓት፣ ገንዘብ ከፍለዉ እንዳይገቡ የታገዱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች፣  ከሆቴሉ አስተዳደር ጋር ሲከራከሩ የሚያሳይ ቪዲዮ በበርካታ ድህረ ገጾች ተለቆ አይተናል። የተወሰኑ ወደ ሆቴል ቤቱ ሲገቡ የተወሰኑቱ ግን እንዳይገቡ ሲከለከሉ ነዉ ያየነዉ። ምን ያህል የአፓርታይድ አይነት ሥርዓት በአገራችን እየተስፋፋ እንደሆነ ነዉ በይፋ ለማረጋገጥ የተቻለዉ። ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎቿ እኩል የሆነች ሳይሆን፣ አንዱ የሌላዉ የበላይ ሆኖ፣ አንዱ ሌላዉን እየረገጠና እየጨቆነ የሚኖርባት አገር እንደሆነች ነዉ፣ የሰማያዎ ፓርቲ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ያስተማረዉ። ይሄም እራሱን የቻለ ትልቅ ሥራ ነዉ።
እንግዲህ እነዚህን ምሳሌ የምጠቀሰው «በአገር ቤት ያሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች ያንቀላፉ ናቸዉ»  ለሚለዉ የተሳሳተ አባባል እርማት ለመስጠት ነዉ።  የድርጅቶች ልሳኖች እንዳይታተሙ እያታገዱ፣ ያን አልፎ በመሄድ የማተሚያ ማሽን ለመግዛት ጥረት እየተደረገ፣ ኢትዮያዊ አጀንዳዎች ተይዘው ተቃዉሞ ለማሰማት እየተሞከረ፣ በዚያም ምክንያት ዜጎች እየታሰሩ  ምንም ነገር አልተሰራም ማለት ትንሽ ያስቸግራል። ያለ ማጋነን፣  በዉጭ አገር አለን ከሚሉና በብዙ ሺህ ዶላሮች  ከሚደገፉ ድርጅቶ ጋር ሲነጻጻሩ፣  አገር ቤት ያሉ ደርጅቶች ከሃያ በላይ እጥፍ ትልቅ አስተዋጾ እያደረጉ ናቸዉ።
ይህን ስል መሰራት የነበረባቸውን ሥራዎች በብቃት ሰርተዋል ማለቴ አይደለም። ይህን ስል መተቸት የለባቸውም ማለቴ አይደለም። በቅርቡ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ያቀረባቸውን ጠንካራ ገንቢ ትችቶች መመልከት ይቻላል።  በርግጥ አገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች ብዙ ማስተካከል ያላባቸዉ አሰራሮች፣ መስራት ያላባቸዉ ተግባራት አሉ።በተለይም መድረክ የሚባለው ስብስብ ትልቅ ችግር አለበት።
ነገር ግን አልተሰሩም የምንላቸውን ተግባራት ለምን አልሰሩም ብለን ዳር ሆነን ከምንከስ፣ ለምን መሰራት ያላባቸውን እንዲሰሩ አናግዛቸውም ባይ ነኝ። አገር ቤት ያሉ የተቃዋሚ አመራር አባላት ብቻቸዉን ሁሉንም ሊሰሩ አይችሉም።
ሕዝቡን ለማደራጀት ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መሥራት ይጠይቃል። ለዚህም ቴለቭዥን፣ ራዲዮ፣ ጋዜጣ፣ ኢንተርኔት የመሳሰሉ አስፈላጊ ናቸዉ። በአገራችን ቴሌቭዥኑን እና ራዲዮዉን እንርሳው ገዢዉ ፓርቲ ከቻይና ባገኘዉ ቴክኖሎጂ በቀላሉ አፈና በማድረግ መረጃዎች ለሕዝብ እንዳይደርሱ ማድረግ ይችላል። ኢንተርኔትን በተመለከተ ከሶማሊያና ከኬንያ በባሰ መልኩ ኢንተርኔት በኢትዮጵያ እንዳያድግ ተደርጓል። የብሮድ ባንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ክፍል 0.1 % ያነሰ ነዉ። በመሆኑም በፌስቡክ በመሳሰሉ ሜዲያዎች በብቃት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለመስራት ያስቸግራል።
የቀረዉ እንድ መንገድ ጋዜጣ ነዉ። ይችኑ የቀረችዋን ለማፈንም ገዢው ፖርቲ ማተሚያ ቤቶችን  በመጠቀም ነጻ ጋዜጦች እንዳይወጡ እያደረገ ነዉ። ፍትህ ጋዜጣ ተዘግታለች። ፍኖት ጋዜጣ አትታተም።
የአንድነት ፓርቲ ግን ዝምታን አልመረጠም። እየተንቀሳቀሰ ነዉ። የማተሚያ ማሽን ገዝቶ ሕዝብን ለማስተማርና ለማደራጀት እየጣረ ነዉ። እንግዲህ ከኛ የሚጠበቀዉ የሥራዉ አካል መሆን ነዉ። የማተሚያ ማሽኑን ለመግዛት 50 ሺህ ዶላር አካባቢ ያስፈልጋል።በዉጭ አገር የሚኖረው ኢትዮጵያዊ 2 ሚሊዮን ይጠጋል። 50 የሚሆኑቱ አንድ ዶላር፣  5 ሺህ የሚሆኑቱ  አሥር ዶላር፣ 5 መቶ የሚሆኑቱ አንድ መቶ ዶላር፣  አምሳ የሚሆኑቱ አንድ ሺህ ዶላር ቢያዋጡ ይሄ ማሽን በቀላሉ ሊገዛና ለጥቅም ሊዉል ይችላል። አንድ ተብሎ ነዉ ወደ ሁለት የሚኬደው። መቶ ሜትር መሮጥ ሳንችል የማራቶን ወርቅ መጠበቅ የለብንም። መደመር ሳይቻል ማባዛቱ የማይሞከር ነዉ።
እንግዲህ አገር ቤት ያሉ ትግሉን ወደፊት እንዲወስዱ እንደምንጎተጎታቸው ሁሉ፣  እኛም የድርሻችንን ለመወጣት እንዘጋጅ። ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት !
አማኑኤልዘሰላም
amanuelzeselam@gmail.com

No comments:

Post a Comment