Tuesday, August 25, 2015

ቴዲ አፍሮ

ህወሀት ቴዲ አፍሮን ከልክ በላይ እየገፋው ነው:: ለቴዲ የህወሀት ኢትዮጵያ አላስቀምጥ ብላዋለች:: ምናልባትም ቴዲ ከሀገር ተሰደደ የሚል መራር ዜና ልንሰማ የምንችልበት ጊዜ እየቀረበ እንደሆነ ይሰማኛል:: በግሌ በተለይ ሰሞኑን የሚደርሱኝ መረጃዎች የህወሀትን የዕብሪት ለከት ማጣት የሚያሳዩ ቴዲንም ከሚወደው ህዝብና ከሚሳሳላት ሀገሩ እንዲለያይ የሚገፋፉ ናቸው:: ቴዲ መሰደድ እንደማይፈልግ የትኛውንም በደል ተቋቁሞ በሀገሩ መኖር ለምርጫም የማይቀርብ ጉዳይ እንደሆነ ባውቅም ትዕግስትም ልክና ድንበር አለውና የሰሞኑ ግፊትና ግፍትሪያ ከመራር ውሳኔ ሊያደርሰው እንደሚችል አምኜአለሁ::

ቴዲ ከእናቱ ቤት መሀል አዲስ አበባ እሱ ወደ ሚኖርበት ሲ ኤም ሲ በየጊዜው ሲመላለስ በደህንነቶች ታጅቦ: በመንገድ ላይ እያስቆሙ መከራውን አሳይተው በሚፈትሹት የህወሀት ሰዎች ተንገላቶ መሆኑ አስገራሚ ነው:: ቤቱ በደህንነቶች እጅ ላይ ወድቋል:: ዙሪያውን ይቆጣጠሩታል:: እንዳሻቸው እየጠሩ ያስፈራሩታል:: ከተቃዋሚዎች ጋር ትገናኛለህ በሚል ክብረ ነክ ምርመራ ያደርጉበታል:: በቅርቡ ባለቤቱ ታማ ወደ ኬኒያ ይዟት ሊሄድ ሲል መንቀሳቀስ የጀመረን አውሮፕላን እንዲመለስ አድርገው እንደ ወንጀለኛ በተሳፋሪ ፊት እየገፈተሩ ወስደውታል:: በተደጋጋሚ የውጭ ጉዞዎቹ እንዲሰረዙ አድርገዋል:: በርካታ ሌሎች ጥቃቶችን ፈጽመውበታል:: ለፊታችን አዲስ ዓመት በላፍቶ ያዘጋጀው ኮንሰርትም ሊሰረዝ እንደሆነ ከውስጥ ያገኘሁት መረጃ ያመለክታል:: በአዲስ አበባ ለህወሀት የሚጮሁ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች የላፍቶው ኮንሰርት የሚሰረዘው በስፖንሰር እጦት ነው በሚል ቢያራግቡም እውነታው ግን የምንመርጥልህን እንጂ የመረጥካቸውን ዘፈኖች አታቀርብም ብለው ጣልቃ በገቡ የደህንነት ሰዎች ግፊት ነው::
ቴዲን ህወሀት ከሀገር ገፍትሮ ሊያስወጣው እየሞከረ ነው:: መንፈሰ ጠንካራ የሆነው ቴዲ እስከአሁን በትዕግስት እየመከተ ነው:: ሰው ነውና መንግስትን የሚያክል ሃይል ተነስቶበት ብቻውን ይመክታል ማለት አይቻልም:: ከጎኑ መቆም ግድ ይላል:: ህወሀት ቴዲ ላይ አይደለም ሰይፍ የመዘዘው:: ትውልዱ ላይ ነው:: ኢትዮጵያዊነት ላይ ነው::

No comments:

Post a Comment