Tuesday, August 25, 2015

አንደንቁዋሪው ዲስኩር … “ቁዋሚ ጥቅም እንጂ ቁዋሚ ወዳጅ የለም “! ቦጋለ ካሳዬ፣ አምስተርዳም

ብርሃኑ ነጋ በርሃ ገባ! ‘አሜሪካ ተቀምጠህ የጦርነት ፉከራኽን ተወን’! እያልን ስናብጠለጥለው እነሆ በተግባር አፋችንን ዘጋው አይደለም እንዴ? ተቀብለናል አቤ ቶኪቻው…. ስላቅህ እውነትነት አለው። ሰውየው መጀመሪያ የኢህአፓ አባል ሆኖ ነበር በ17 አመቱ የሽፈተው ። ዛሬ ደግሞ ከ40 አመታት በሁዋላ የአርበኝነት ትግል ለማካሄድ አስመራ ገብቱዋል። ምንም እንኩዋን ግንቦት ፯ ኤርትራ ከመሸገ ቢሰነባብትም ብርሃኑ ጨክኖ በዚህ እድሜው በርሃ ይገባል ብዬ በግሌ አስቤ አላውቅም ነበር።
ድጋፍ
ኢሳት ሬዴዮ ይሁን ቴሌቪዢን የብርሃኑን በርሃ መግባት ተከትሎ ለአርበኞች-ግንቦት-7 ድጋፍ እንዲገኝ እየተጋ ነው። አንድ ነጻ ካልሆነ የመገናኛ ብዙሃን የሚጠብቅ ስራ ነው ። ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ እንዲሆንለት ይመስለኛል ኢሳት የሚሰበሰበውንም ገንዘብ በብር እያሰላ እየዘገበ ነው። ሚሊዮን በሚሊዮን እየተሆነ ነው።
እንደ ኢትዮ-ሚዲያ ባሉ ድረ-ገጾች ስለ ብርሃኑ ነጋ ትጋትና ቁርጠኛ ውሳኔ የተሰነዘሩትን አድናቆቶች አንብቢያለሁ። አንዳንድ አሞጋሾች ከዚህ በፊት በብርሃኑ ነጋ ተለዋዋጭና በታኝ የፖለቲካ አቁዋምና እርምጃዎች የተሰነዘሩትን የፖለቲካ ትችቶችም እንደ ስም ማጥፋት ወሰደው አጣጥለዋቸዋል። ማደግደግን ባህላቸው ያደረጉ ሰዎች ወደ ነፈሰው መንፈሳቸው ምንም አያስገርምም። አንዳንድ ጮሌዎችም ከእንግዲህ ከጦርነት ውጭ አማራጭ ስለጠፋ እርምጃው ተገቢ ነው ብለውናል… ምንም እንኩዋን ቀደም ሲል በግንቦት ሰባት ተቃዋሚነታቸው ቢታወቁም። እነዚህ አይታመኑም። የመልመጥመጣቸው ሚስጥሩ ጦርነቱን ቢደገፉ የፈጠራ ይሁን የእውነተኛ ጦርነቶችን መግለጫዎች በመለጠፍ ድረ-ገጻቸውን የሚጎበኙ ሰዎች ይበዛሉ ከሚል የግል ጥቅም ፍለጋ ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም። እናውቃቸዋለን… አንዳንዶቹ ከዚሁ ከአምስተርዳም ናቸው… ስሙኒ ከክብራቸው የሚበልጥባቸው ።
ሲሳይ አጌና … ኤርሚያስና … ሙሉጌታ ሉሌ
በኢሳት ሰሞኑን ከሲሳይ አጌና ጋር ኤርሚያስና ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ የሰጡትን ድጋፍ ተመርኩዘን አንዳንድ ትዝብቶችን መሰንዘር ሳይጠቅም አይቀርም። ኤርሚያስ ብዙውን የቃለ-መጠይቁን ጊዜ ቢሻማም የብርሃኑን ጽሁፎችና ንግግሮች አንብቦ የሰጠው ምስክርነት ምንም አዲስ ነገር የለበትም። የብርሃኑ ነጋን የስልጣን ጉጉት ያወቅነው ገና በ17 አመቱ ነው። ብርሃኑ ከልጅነቱ ጀምሮ በኑሮ ችግር ያልገጠመውና በግል ጥረቱም ሰኬታማ የሆነ ሰው ነው። የተሻለች ኢትዮጵያን ለልጆቹ ለማወረስ ቆርጦ መነሳቱንም ከራሱ አንደበት ሰምተናል። ጽፎአል። ራሱ የነገረንን ነው ኤርሚያስ የደገመልን…እኔ የምለው… ያልሰማን መስሎት ይሆን? ወይስ ደግመን ደጋግመን መስማቱ የብርሃኑ ደጋፊ ያደርገናል ብሎ አስቦ ነው? ያው ካድሬዎች የሚያደርጉት ይኼንኑ አይደል? መቼ ይለቃቸዋል ልክፍታቸው።
ሲሳይ አጌና… አቶ ሙሉጌታ ሉሌን ቀደም ሲል አንዳርጋቸው ኤርትራ እንደገባ ዲያስፖራው ከሻእቢያ ጋር የሚደረግ ትግል አደጋ አለው… አያዋጣም ብሎ በወሰደው አቁዋም ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጠይቆዋቸው ሲተቹ፤ …ኢሳያስ ሃሳቡን ከቀየረ በኤርትራ በኩል የሚደረገው ትግል አደጋ እንዳለው የዲያስፖራውን ስጋት ይጋሩ ነበር ። በቀደም ግን ለሲሳይ ተመሳሳዩ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ምንም ስጋት አልነበረበትም። አበስገበርኩ! የሚያስብል ነው ።
ደግሞ እንደርሳቸው ትንታኔ ከሆነ ለምሳሌ ባንድ ወቅት ጠላት የነበሩት አሜሪካና ጃፓን አሁን ወዳጆች ናቸው። ወታደር ሲሳይ አጌኒሻም … “ያውም የሄሮሺማና ነጋሳኪ እልቂትም ተከስቶ” ብሎ አስተያየታቸውን አዳብሮላቸዋል ። ስለዚህ ቁዋሚ ጥቅም እንጂ ቁዋሚ ወዳጅ ስለሌለ፣ በሌሎችም ጎረቤት አገሮች የትጥቅ ትግል ማካሄድ ስለማይቻልና የሰላሙ ትግልም ስለተዳፈነ በኤርትራ እቅፍ ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ተነስቻለሁ የሚለውን አርበኞች ግንቦት-7ን መደገፍ አለብን ነው መልእክታቸው። ይኼንኑ የጃፓንና የአሜሪካን ታሪካዊ ጠላትነትና የዛሬው የጥቅም ወዳጅነትን አቶ ሙለነህ እዮዬልም ደግመውታል ።
ከሾክ የተጠጋ ቁልቃል
ቁዋሚ ጥቅም እንጂ ቁዋሚ ወዳጅ የለም የሚለው መርህ በመንግስታት መካከል የሚሰራበት ለመሆኑ አሌ የሚል የለም። ይሁን እንጂ በዚሁ መርህ የአሜሪካንና የጃፓንን ግንኝነት ከኤርትራና ገና ሊቁዋቁም ከሚችለው የድህረ ወያኔ ኢትዮጵያዊ መንግስት ጋር ማስተያየት ግን ትልቅ አደጋ አለው። እንደውም ንጽጽሩ … “ድሃ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ እከክ ይበጣጥሰው ነበር” ከመሆን አይዘልም።
እንዴት? ጃፓንና አሜሪካ በባህልም ሆነ በታሪክ በጣም የተለያዩ አገሮች ናቸው። መጀመሪያ ጦር የጫረቺውም ጃፓን ናት። ምክንያቱዋም በሁለቱ አገሮች የነበረው የንግድ ልውውጥ አለመመጣጠን ነበር። የጃፓን ባህር ሃይል የአሜሪካ ግዛት የሆነቺውን ሃዋይ(Hawaii) በዴሴምበር 7/1941 ፒርል ሃርበር(Pearl Harbor) በድንገት በመደብደቡ አሜሪካን ካለውዴታዋ ወደ ሁለተኛ አለም ጦርነት እንድትገባ ተገደደች። በመቀጠልም አሜሪካ ጃፓንን ተመጣጣኝ ባልሆነ የአቶሚክ ቦንብ አነደደጃት። በነገራችን ላይ ሲሳይ እንዳለው ሳይሆን … የሄሮሺማና የነጋሳኪ ቁሱል አልጠፍም። ዛሬም ጃፓናውያን በአሜሪካ ላይ ትልቅ ቂም አላቸው። በየጊዜው በሚደረገው መታሰቢያ ላይ አሜሪካኖች አይገኙ!! የሚል ተቃውሞም ያሰማሉ።
አሜሪካ ጃፓንን ካንበረከከቻት በሁዋላ እስከዛሬ ድረስ በጦር ሃይሉዋ እንደተቆጣጠረቻት ነው። በዚያች በትንሽ አገር ዛሬም 24 የአሜሪካ የጦር ካምፖች አሉ። ጃፓን ራስዋን ለመከላከል ብቻ የሚያስችላት ጦር ነው ያላት። ከአሜሪካ እውቅና ውጭ ሌላ የወጭ አገር ጦር በአገርዋ ማስገባትም አትችልም። ሂንሪ ኪሲንጀር አዲሱ ዲፕሎማሲ በሚለው ስራቸው ላይ ጃፓን በጦር ሃይል (irrelevant) ፋይዳ የላትም ሲሉ መስክረዋል።
አዎ… ጥቅሞ ቁዋሚ ነው ወዳጅ ተለዋዋጭ ነው። ዛሬ የአሜሪካን እንዲሁም የተቀረው ምእራብ ጥቅም በቻይና የበላይነት መጎዳቱ ከቀጠለ በቻይና ላይ ሊወሰድ በሚችለው እርምጃ ጃፓን ሁነኛና አማራጭ የሌላት ወዳጅ ናት። ጦርነት ከተጀመረም ጃፓን ሁነኛ መንደርደሪያ ናት። በተቃራኒው የቻይናም ኢላማ የሚያነጣጥረው ጃፓን ላይ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው… ምንም እንኩዋን ቻይናን መንካት ሊቢያ ወይም ኢራቅ ጦር መጀመር አይነት ባይሆንም። ቻይናን መንካት የኒኩላር ጦርነት ማስነሳት ስለሚሆን ማንም አሽናፊ አይሆንም። ስለዚህ በአሜሪካና በቻይና መካካል ጦርነት ብሎ ነገር የማይታሰብ ነው። ይሁን እንጂ የአሜሪካ ቻይናን መግታት ፖሊሲ(containment) ተግባራዊ እንዲሆን… ከሾክ የተጠጋ ቁልቃል ሲያለቅስ ይኖራል እንዲሉ ጃፓን የአሜሪካ ተባባሪ መሆኑዋ የግድ ነው። ጃፓን በጦር ሃይል ተጠፍንጋ ስለታየዘች የመከላከያ ጦር ፖሊሲዋን እንደ ነጻ አገር ማራመድ አትችልም። በዚህም ረገድ ቁዋሚ ጥቅም እንጂ ቁዋሚ ወዳጅ የሚለው መርህ ለጃፓን በሁሉም ዘርፉ አይሰራም። አላቻ ጋብቻ ነውና። በሌላ አነጋገር ጃፓን ዘላቂ ጥቅሜ ከምእራቡ ይልቅ ከቻይና ጋር በሚኖረኝ ግንኙነት ይበልጥ ይከበራል የሚል እሳቤ ብታነሳ ከአሜሪካ የወታደራዊ የበላይነት ለመላቀቅ አብዮት ማካሄድ ይጠበቅባታል ማለት ነው። ከሾክ የተጠጋ ቁልቃል ሲያለቅስ ይኖራል ይሉሃል ይኼ ነው።
በእርግጥ ጃፓናውያን በጦርነት ቢሽነፉም ከአሜሪካ ጥሩ ጥሩውን ነገር ተምረው በተለይ በአውቶሞቢልና በኤሌትሮንኪስ መጥቀው በመሄዳቸው ከምእራቡ ጋር ጥቅማቸው በጣም የተሳሰረ መሆኑን መካድ አይቻልም።
የሆኖ ሆኖ ይኽ ቁዋሚ ጥቅም እንጂ ቁዋሚ ወዳጅ የለም የሚባለው መርህ በጣም የተወሳሰበ ጉዳይና እንደ አገሮቹ ግንኙነት የሚለያይ መሆኑን የምወዳት የጦቢያ መጽሄት አዘጋጅ ሙሉጌታ ሉሌ ሊያጤኑት በተገባ ነበር። ስተውታል… ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻ ላይ ላዩን ነው የተናገሩት።
ታሪክ ይፍረደኝ
የጃፓንና የአሜሪካ ግንኙነት ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ጋር በጣም የሚለይ ነው። እንዴት ?አንደኛ ነገር … ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል የነበረቺና የተፈጠረቺውም የተቀረውን ኢትዮጵያ ለመቆጣጠር እንደ መንደርደሪያ ሁና ነው። የኢትዮጵያ እባጭ ናት። የዶግ አሊ፣ የአድዋ፣ የማይጨው፣ የሰላሳ አመታት ‘የነጻነት ትግል’ና በባድሜ ተመካኝቶ በቅርቡ የተካሄዱት ጦርነቶች አውራው ምክንያት ምንድን ነበር? ከተከዜ በስተደቡቡ የሚገኘውን የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብት ለመቆጣጠር እንደሆነ ማንም ይስተዋል ብዬ አልገምትም። ኢታሊያ በአድዋ ከተመታች ከአርባ አመታት በሁዋላ ኢትዮጵያን ስትቆጣጠር ያአቆመቺው አስተዳደር ዛሬ ከሞላ ጎደል የወያኔው አይነት እንደነበር ሁላችንም እናውቃለን። አላማዋም የኢትዮጵያን አገራዊ ስሜት በጎሳ ንዶ ህዝቡዋን በማራራቅ የተፈጥሮ ሃብቱዋን ካላ ብዙ ተቀናቃኝ ለመጋጥ ነበር። አርበኞችም ፍታ አልሰጣት አሉ… የሙሱሎኒ ጥጋብም ጠንካራ ጠላቶች ስላስነሳበት የኢታሊያን የፍሽዝምን አስተዳድር ውድቀት አፋጠነውና ውጥኑ ሳይሳካ ቀረ እንጂ።
ኤርትራም ነጻ ወጣሁ ካለች በሁዋላ ከወያኔ ጋር የከፈተቺው ጦርነት የድንበር ሳይሆን… ከተከዜ በስተደቡቡ ያለውን ሃብት ወያኔ ብቻውን እኔን ሻእቢያን ጥሎ መብላት የለበትም ከሚል ምቀኝነት ነው።
ነገሩን ዘርዘር እናድርገውና… የአባይን ወንዝ በዋነኛነት አንስተን እንወያይ። ወያኔ የህዳሴን ግድብ ገድቦ ለመጭረስ ደፋ ቀና እያለ ነው። የህዳሴ ግድብ ተሰርቶ ቢያልቅ ገቢው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልማት ሳይሆን ለትግራይ ልማት እንደሆነ በአባይ ትግራይ ዶክመንት ላይ ተንጸባርቁዋል። በተጨባጭም ዛሬ በግድቡ ዙሪያ ሊሰሩ ለታቀዱ የንግድና የቢሮ ተቁዋማት የመሬት ቅርምቱ ለትግሬ ባለጊዜዎች ብቻ መደልደሉ የሚያመለክተው ወያኔ የተዋጋው ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያን ሃብት ለብቻውና እንዳሻው ለመጋጥ መሆኑን መስካሪ ነው። የአባይ ምንጭ ይሁን ወንዝ አገረኛ ተቀናቃኝ እንዳይነሳም ጎጃሜን በመዳህኒት ማምከኑ፣ በኤድስ መበከሉም ተቀናቃኝ ሊሆን የሚችል እንዳይነሳበት አስቀድሞ ለማሽመድመድ የሚካሄድ ሌላው ዘዴ ነው። በድሮ መተከል በዛሬው ቢነሻንጉል አማሮች የተፈናቀሉት በመለስ ዜናዊ ትእዛዝ ነበር። የወያኔ ኢትዮጵያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብርሃኔ ገብረክርስቶስ ተባራሪዎቹን “ወራሪዎች ናቸው” ማለቱ አማራን ከአባይ አካባቢ የማጥፋት የወያኔ ፖሊሲ አካል መሆኑ በግልጽ አመልካች ነው። በቅርቡም ወያኔ በቤንሻንጉሌዎች የአማራን ስጋም አስበልቱዋል። በወልቃይት የተካሄደው የአማራ ጽዳትም የአማራን ለምለም መሬቱን ነጥቆ ለትግሬ ብቻ እንዲውል የታቀደ መሆኑን ግማሽ ሚሊዮን ትግሬ ሰፍሮ ተወላጁ በመጥፋቱ ተመሳክሮአል።
ቅጥረኝነት
ከዚሁ ከአባይ ወንዝ ሳንወጣ የግብጹ መሪ የነበረው ሙርሲ ካቢኔት ኢትዮጵያ ውሃውን እንዳትጠቀም እንደ ኦነግ ያሉ ድርጅቶችን መርዳት…የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ደግሞ አገራችንን በማዳከሙ ሚና ማስተባበር እንደሚያስፈልግ ሲወያይ በአደባባይ ሰምተናል። በዚህም መሰረት ይኽንኑ ተግባር ለማስፈጸ’ም የአካባቢው አገሮች በተለይ ኤርትራ በቅጥረኝነት ለመስራት የቀደማት እንደሌለ የሙርሲን ካቢኔት ውይይት ተከትሎ የኢሳያስ አፈወርቂን የካይሮ ጉብኝት ሁነኛ ፍንጭ መስጠቱ ማጤን ደግሞ ደጋግሞ በእባብ ከመነደፍ ያደናል። ኢስያስ አፈወርቂ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ ግብጽ የአሜሪካን መሳሪያዎች እንዳስታጠቀቺው አይ ምጽዋ በሚለው መጽሃፊ ላይ በሚገባ ተመልክቶአል። ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በግብጽ እንደሚረዱ እየሰማን ነው። እንግዲህ ከሞኝ ሰፈር… ይቆረጣል ሞፈር… እንዲሉ ወያኔ፣ ሻእቢያና ግብጽ በአባይ ውሃ ላይ ሲፎካከሩና ሲተባበሩ ዋናው ባለንብረቱ የበይ ተመልካች ብቻ ሳይሆን እንዲጠፋም ተፈርዶበታል።
አባይን የተቆጣጠረው ወያኔ ብርሃኑ ነጋን ባስቀደመው ሻእቢያ ቢፈነገል የአባይ ባላቤት በጭራሽ ኢትዮጵይውያን አይሆኑም። ወያኔን በመዋጋት ደማችንን ያፈሰስነው ዋጋ ነው ተብሎ በባለተራው ሻእቢያ መድማትና መጋጥ ነው የሚከተሉት። እንዲህ ያለውን ጫወታ ደግሞ በሁለተኛው አለም ጦርነት ወቅት በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ላይ እንግሊዝ አድርገዋለች። ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ከስደት ሲመለሱ አገሪቱን ቀደመው የተቆጣጠሩት እንግሊዞች ንጉሰ ነገስቱን ስልጣ አልባ አድርገው ለ፫ ኣመታት እዳስቀመጡዋቸውና ከእንግሊዞች ለመላቀቅ ትልቅ ትግስትና የዲፕሎማሲ ስራዎች እንደተካሄዱ ማንም አይደተውም። ይኼም ቁዋሚ ጥቅም እንጂ ቁዋሚ ወዳጅ የሚባለው መርህ ላይ ላይዋን እውነትነት ቢኖራትም ለምናልመው ስርአት መሳካት ከአጉል ጠላት ጋር እንዳንዋዋል ግራ ቀኙን ብናይ የተሻለ ነው።
ጠላት ይሁን ወዳጅ
እንግዲህ ብርሃኑ ነጋ ያጥፋም ያልማም ዛሬ አንድ ህይወቱን ለአመነበት አላማ በመስጠቱ ብቻ ጠላት ይሁን ወዳጅ ሊያከብረው ይገባል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ገና አንዳርጋቸው ኤርትራ ከሄደ ጀምሮ የምናሳውን ተቃውሞ እርሱ ኤርትራ ስለገባ ብቻ የምንተውበት በቂ ምክንያት የለም። ተቃውማችን ደግሞ ደጋግሞ የተነገረና አርበኞች ግንቦት ይሁን ሻእቢያ ወያኔ የሚያውቁት ነው።
በአጭሩ የኤርትራ ነጻነት ወደ ባርነት ነው የተቀየረው። ምንም አይነት የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴ የለም። ገና ከጅምሩ የባህረ ነጋሽ ኢኮኖሚ ከተቀረው ኢትዮጵያ ጋር ሊነጠል እንደማይችል እየታወቀ…በስሜትና በጥላቻ ኤርትራ ከኢትዮጵያ በመገንጠሉዋ ‘በነጻነት’ ማግስት ቃል የተገባውና የተዘፈነለት ልማት እውን ሊሆን አልቻለም። የፕሮፓጋንዳ ልማት የተለወጠው ወደ ዝርፊያና ቅጥረኝነት ተግባር ነው። ኤርትራ በኢታሊያ ስር ሆና እንዳገር የቆየቺው ኢኮኖሚዋ በኢታሊያ እየተደጎመ ነበር። እውነተኛ የኢኮኖሚ እድገትዋ የታየው ከኢትዮጵያ ጋር በፊዴሬሺን መተዳደር ከጀመረች በሁዋላ ነው። የሻእቢያ ኤርትራ እስካሁን እንዳገር የቆየቺውም በጦር ሃይል ብቻ ነው። የጦር ሃይሉዋ ቢዳከም ትፈርሳለች። ወደፊት ኤርትራ እንደ አገር መቆየት የምትችለው ከኢትዮጵያ ጋር ስትቀላቀል ብቻ ነው። ከጉራ ውጭ ራሱዋን ችላ መቆም አትችልም ። እነዚህን ሃቆች ግን ሻእቢያ እያወቀ አይቀበልም። ሀቅ በጠብመንጃ የሚደመስስ ይመስለዋል። ለምን? ከተከዜ በስተደቡቡ ያለውን ሃብትና ገበያ ካልተቆጣጠርኩ ሞቼ እገኛለሁ ባይ ነውና። ሻእቢያ አስተሳሰቡ እንደ 19ኛው ክፍለ ዘመን ኮሎኒያሊሶች ቆሞ የቀረ ነው። ችኮ ነው። ሌሎች በአገራቸውና በቤታቸው መብት እንዳላቸው አይገነዘብም።
ይኽም ሆኖ ሻእቢያ ኢትዮጵያውያን አገር ወዳዶች ለምሳሌ እንደ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ የኤርትራ አየር ሃይል ያሰለጠኑ ባለውለታዎቹ… ከኤርትራ ተደራጅተው ወያኔን ለመፋለም እንዳኮበኮቡ ሲገነዘብና የኢትዮጵያን ህዝብም የዴሞክራሲያዊ ጥማት በቅንጅት 1997 ሲያጤን… ይኽቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም ብሎ ወዲያ ቆርጥሞአቸዋል። ይኽ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየን ሻእቢያ ጠንካራ ኢትዮጵያ መቃብሬን መቆፈሪያ ናት ብሎ የሚያምን መሆኑን ነው።
ከዚያም የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርን በመሃይሙና በጋብቻ በተሳሰረው መአዛው ጌጡ እንዲመራ አድርጎ በፈጠራ የወታደራዊ ኮሚኒኬ ሲያደነቁረን ነበር። መሃይሙ መአዛው ጌጡ ምክትል…. ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነገ ዋና የሆኑበት አርበኞች ግንቦት-7 ሻእቢያ ለምን ፈጠረ? መአዛውና ብርሃኑ ነጋስ በዚህ በተወሳሰበ የአገር ጉዳይ ላይ ምን መክረው ሊግባቡ ይችላሉ?
ብርሃኑ ነጋ በተንኮል ያንስ እንደሆን ነው እንጂ ከኢሳያሳም ሆነ ከመሃይሙ መአዛው ጋር የእውቀት እኩያ አይደለም። የጋለ የስልጣን ፍላጎት ፣ ችሎታና ትምህርት ያለው ሰው ነው። ከዚህም አልፎ ተርፎ በታሪካዊ ግንቦት 7-1997 ምርጫ የህዝብ ውክልና አግኝቶአል። ብርሃኑ ነጋ ስልጣን ቢይዝ አገር ለማስተዳደር ብቃት ካላቸው ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው። ታዲያ ለምን ሻእቢያ ከመሃይም መአዛው ጌጡ ጋር ያጣምደዋል? እርሱስ እንዴት ይኼን ይቀበላል? ለምን የብርሃኑ ነጋ ምክትል ተመጣጣኝ ትምህርት ያለው ሰው አይሆንም?
ብዙ ነገሮች ማንሳት ይቻላል። ከልምድ ግን ለሕዝብ የሚያስቡ ጥሩ ህልም ያላቸው ሰዎች በወያኔም በደርግም ሆነ ባሻእቢያ በተኩላዎች ተበልተው እንደቀሩ ነው የምናውቀው ። ግልጽ በሆነ አነጋገር ዛሬ ብዙ አገር ወዳጆች እንደሚመኙት የብርሃኑ ጦር እንጦጦ ሊደርስ ቢቃረብ እንኩዋን ነጻነት ያለው ድርጅት እስካልሆነ ድረስ ምንይልክ ቤተ መንግስት ቀድመው ዘው የሚሉት እነ መአዛ ጌጡ አይነቶች ናቸው። ለዚህ ነው ትግል ሲጀመር ውጤቱ እንዲያምር በራስ ሕዝብ ውስጥና በራስ ቁጥጥር ስር ማካሄድ አስፈላጊ የሚሆነው።
በሻእቢያ ከተያዘች ኤርትራ ጋር ተጣምዶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በጎ ለውጥ ሊመጣለት ይችላል ብሎ ቁዋሚ ጥቅም እንጂ ቁዋሚ ወዳጅ የለም እያለ ፊሺካ የሚነፋ ሰው.. ከእባብ እንቁላል እርግብ የሚጠብቅ ነው። የፖለቲካን ውስብስብነት ያልተረዳ ነው። የፖለቲካ ትግል ስልጣን ይዞ ሃብትን መቆጣጠር ነው ግቡ። ደግሞ ኢሳያስ ጅሉዬስ ኔሬሬ አይደለም። የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት የነበሩት ኔሬሬ ለኣፍሪካ ክብር ብለው የየጋንዳውን ኢዲአሚን ወታደራቸውን ልከው ከስልጣንአባረው ነበር። ኢስያስ ግን ደሴ ስህን ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን መጨረሱን ለመናገር እንኩዋን ያፍራል። ምን ያሳፍራል ይኼ? ለነገሩየ ሚያሳፍረውን ታሪኩንም ዛሬ እናውቃለን። የአንደኛ አመት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ በኢትዮጵያ ደህነት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ አንደራ ተልኮ የናቱን ጡት የነከሰ ባንዳ መሆኑን። የሚገርመው እንዲህ አካባቢንው እያተራመሰ ለምን እስካሁን በስልጣን ቆየ ነው። በኔ ግምት ኢትዮጵያን የማፍረሱ ሁነኛው መንገድ እርሱ የያዘው የቤት ስራ መሆኑን የሚያውቁ ጠላቶች ቆይ! ቆይ ! ቀኑ አልደረሰም እያሉ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ በፕሮፓጋንዳ አልፈረሰቺም። በጦር ሃይል ግን ልትፈርስ ትችላለች።
በሌላ በኩልም ሻእቢያ ተሰፋዬ ገብረ አብን ቀጥሮ በተለይ አማራውንና ኦሮሞውን ለማለያይተት ቆርጦ መንሳቱን አይተናል። አዲስ አበባን የተቆጣጠሩትም የአኖሌ ሃውልት አቁመዋል.. ምንም እንኩዋን ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሳይቀሩ በታሪክ ተደረገ የሚባለው ተረት መሰረት የሌለው እንደሆነ ቢመሰክሩም። ፕሮፌሰር ሃይሌ ላሪቦ ጦርነቱ እንዴት እንደተካሄደ የሰጡትን ትንታኔ ማንም አቅም ኖሮት አልሻረውም።
እነ ብርሃኑ ነጋ ግራና ቀኙን አይተው መንገዳቸውን ቀጥለዋል። ያለሙት ህልማቸው እውን እንዲሆን ፈጠሪ ይርዳቸው። እኛ በእነርሱ መንገድ የማንስማማው ሰዎች ምን እናድርግ? ምንስ እያደረግን ነው? እነርሱን በመቃወም ብቻ አገራዊ ግዴታችንን መወጣት አንችልም። በመጀመሪያ ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ ማቆም አለብን። በስብአዊነትም ደረጃ ወገኖቻችን ተረድተው ይሁን ሳይረዱ በሻእቢያ ጥርስ ውስጥ መግባታቸው ብቻ ሊያሳስበን ይገባል። እዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ በከተተን ወያኔ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ማድረግ አለብን። ሞራላቸው ጠንክሮ እንዲቀጥል ብሄራዊ አጀንዳ ያነገቡትን የሰላማዊ ተቃዋሚ ሃይሎች ካለመታከት መደገፍ አለብን።
ጎጃሜ እንዳለው… “ጦር ይቅር! ጦር ይቅር! የለም ! የለም! ጦር አይቅር! ጦር አይቅር! የቀረ እንደሆን … ይላል ቅር… ቅር!” …. ነውና ነገሩ በመሃከል አገር ውስጥ የአርበኝነት ትግል ካስፈለገ የሚነሳበት ወቅት ሩቅ ላይሆን ይችላል።
ከአርበኞች ግንቦት-7 ለሕዝብ የሚለቀቀው መረጃ በተጨባጭ እንዲቀርብ መታገል አለብን። ለምሳሌ ብርሃኑ ነጋ እንደገባ ተደረገ የተባለው ውጊያና ወያኔም አመነ የተባለው ነገር አንዳንድ ጥሩ የወታደራዊ እውቀት ያላቸው ታዛቢዎች ተአማኒነቱን ከጦርነት ህግ አኩዋያ ውድቅ አድርገውታል። እንደነዚህ ተንታኞች ከሆነ በጦርነት ጊዜ መግደልና መሞት ብቻ ሳይሆን ያለው ምርኮኛም መኖር አለበት። የአርበኞች ግንቦት የወታደራዊ ኮሚኒኬ ግን መግደል ብቻ እንጂ ምርኮኛ አይነካካውም። በዚህም ምክንያት እንደ ጎሹ ወልዴ መድህን የፈጠራ ሊሆን ይችላል ብለው ያስጠነቅቃሉ።
እንደማጠቃለያ
ኢትዮጵያ ጥንታዊና የህዝቡዋ ትስ’ር በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ ወታደር ባይኖርም ህዝቡ አብሮ መኖር የሚችል መሆኑን ደርግ በፈረሰ ጊዜ በአይናችን አይተናል። ለዴሞክራሲ ስርአት መረጋገጥ ያለውን ጉጉትም ከፍተኛ ነው። ኤርትራ ግን ከሻእቢያ ወታደር ውጭ ፈራሽ ናት። የሻእቢያ መሪዎችም በኢትዮጵያ ላይ እንደ ኮሶ ተጣብተው መኖር ስለሚፈልጉ እነርሱ ተወግደው ለታሪክ ከበሬታ ያላቸው መሪዎች ካልመጡ የኢትዮጵያ አንድነት ጠላትነታቸው አይለወጥም። ምንም ለዴሞክራሲ የሚሆኑ እርሾዎች የሉም። ስለዚህ መጀመሪያ የትግላችን ኢላማ መሆን ያለበት ኢትዮጵያን ዴሞክራሲይዊ አገር ማድረግ ነው። ይኼ ነው የኢትዮጵያም ቁዋሚ ጥቅም። ይኽን ደግሞ ከሻእቢያ ጉያ ሆነን እናደርገዋለን ማለት እጅግ ከፍተኛ አደጋ አለው። ከመደነቁዋቆር ወደ ቄያቺን እንመለስ።

No comments:

Post a Comment