Wednesday, August 26, 2015

ትኩረት ፍለጋ.... ለኔ፣ እኔ፣ የኔ

ትኩረት ፍለጋ Attention seeking በሽታ ነው።
ሆኖም ይህ ክፉ ባህሪ አደገኛ የአዕምሮ በሽታ መሆኑን ስለማናውቅ በደፈናው "ትኩረት ሽቶ/ሽታ ነው" እንላለን። ብዙ ጊዜ ሕፃናት ላይ የሚታየው ትኩረት ፍለጋ እድሜ ሲጨምር እየለቀቀ የሚመጣ ቢሆንም አንዳንድ ሰዎች ላይ ከበጎው ትኩረት መሻት መስመር ያልፍና የእኔነት ደዌ ይጣባል።
ባህሪው በአዋቂዎች ላይ ሲሆን የሕይወትን ዋጋ እስከመክፈል እንደሚያደርስ በሥነልቡና ዘርፍ የተሰማሩ የጤና ባለሞያዎች ይገልጻሉ። የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ ሲሉ የትኛውንም፣ ማንኛውንም ዋጋ ይከፍላሉ። ሊዋሹ ይችላሉ፣ ወይም ለትኩረት ሲሉ ብቻ ገንቢ የሆኑ ሥራዎችን በመስራት ለስኬታማነት ይደክማሉ።

የሕክምና ባለሞያዎች ሰዎች ትኩረት ለማግኘት፣ በሰው ለመታየት ሲሉ ያላቸውን አሉታዊ ጎን ሰውተው ለሚፈጽሙት ተግባር ብዙ ምክንያቶች ያስቀምጣሉ
1.ሕፃን ሆኖ በቤተሰቦቹ በቂ እንክብካቤና ትኩረት ያልተቸረው ሰው በሌሎች ያለመፈለግ ስሜት ውስጡ ሲያድር የእዩኝ-እዩኝ ባህሪዎች ይጠናወጡታል
2.ቅናት:- የሌላው መፈለግ እና መወደድ የሚያንጨረጭረው
3.የራስን ማንነት ዋጋ ማሳነስ:- ይሄን ጉድለት ለመሞላት ፣ ዋጋን ከፍ ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ትኩረት አደናው ይጧጧፋል።
4. ግብዝነት:- ከማንም የበላይ ነኝ፣ ስለዚህ ሁሉም ዐይኖች እኔን ማየት አለባቸው። ሁሉም ሰው ስለእኔ ማውራት አለበት ብሎ መናወዝ
5. ራስ ወዳድነት:- ከኔ ወዲያ ላሳር የሚለው ሰው በሌላው ቸል ከተባለ ያንን ግለሰብ ይጠላል
ባለሞያዎቹ ከነዚህ በተጨማሪ የሚዘረዝሯቸው የበሽታው መንስኤዎች ቢኖሩም እኔ ላብቃ።
ይህን ጉዳይ እንድመለከት ያስገደደኝ ባለው ፖለቲካ፣ ባለፈው ታሪክ፣ በትግል ስልቱ፣ በሙዚቃው፣ በሥነ ጥበቡ...በቀናነት እና በቅንነት የማይቀበሉትን "አልተቀበልነውም፣ በዚህ መልኩ ቢሞከር የተሻለ ነው" እያሉ የጎደለውን ከመሞላት ይልቅ እንቅልፋቸውን አጥተው የጎደለውን የሚያጎድሉ፣ በኔ ዛቢያ ያልተሽከረከረ ሁሉ ገደል ይግባ የሚሉ እና እንጦሮጦስ እንዲወርድ የሚተጉ በተቃዋሚው ጎራ ያሉ ሰዎች በመብዛታቸው ነው። የአካባቢ፣ የማህበረሰብና የባህልን ትስስር ያላገናዘበ የእኔነት ንዳድ ሕዝብን የሚያጨራርስ ቢሆን እንኳ ትኩረት ካገኙበት ደንታ የላቸውም። "ደንቆሮ ነው" ከሚሉት የተሻለ አስተሳሰብ ይዞ ለውጥን ለማምጣት ከመቀራረብ ይልቅ በመጥለፍ፣ በማዋረድ፣ በማሴር ላይ መጠመድ እና የራስን ሐዲድ መገንባት ሱሳቸው ነው። የሚዘሩት ምን እንደሚያፋራና ምን እንደሚያሳጭድ ለማሰብ አፍታ ጊዜ የላቸውም:: ጨለማ ብለው የሚፈርጁትን በብርሀን ሳይሆን በጨለማ ለማጣፋት እስከመሞከር ይገፋፋል።ዓለም ሁሉ በነርሱ ቦይ እንዲፈስ ይፈልጋሉ::
በፓርቲ ደረጃ :-
የበፊቶቹ እነርሱ ያላደርጉት ነገር በወቅቱ እንቅስቃሴ ውስጥ ከሌለ ሁሉ ረብ እንደሌለው ያስባሉ። የዛሬዎቹ እነርሱ ዛሬ ፓርቲ ካቋቋሙ የፓርቲ እና የትግል ስልት ሀሁ...ን ሊያስተምሩ ይዳዳቸዋል። "ከደሮው ምን በጎ ስልት ነበር፣ አሁኑስ ምን ጠንካራ ስልት አለ?" ብሎ የማመዛዘኛ ሰዐት የለም::
በጋዜጠኛ ደረጃ:-
ባለሚዛን ጋዜጠኛ፣ሟች እና ገዳይን እኩል ልመዝን ብሎ የሚመጻደቅ
በምሁር ደረጃ:-
ከወንበር ፈቅ የለም። ብቻ ሌሎች የሚሞክሩትን እየጠበቁ ማጣጣል። ጥቅስ እየጠቀሱ ትንታኔ እየሰጡ መራቀቅ። ከገዢው ሥርዓት ድርጎ ካገኘ ለገዳይ ርዕዮት ዓለም እየተነተነ የመግደልን ምክንያታዊነት እስከማስረዳት ያደርሳል
ሌላው:-
አንድነት ይሁን ኦፌኮ ፣ ሰማያዊ፣ አርበኞች... ሁሉም አይረቡም። "አማራጭ?" ሲባሉ መልስ የለም። በፓርቲው ውስጥ ያሉት ሰዎች ከዱላ ይልቅ ዱለት፣ ከውርደት ይልቅ ከብር ያገኙ ይመስል::
በአዋቂ ሰው መሽጎ ያደረው ይህ የጨቅላ አስተሳሰብ አደገኛ በመሆኑ "ንቆ ማለፍ" በሚል ቸልተኝነት ሊታለፍ እንደማይገባ የጤና ባለሞያዎች ያስጠነቅቃሉ:: ስለዚህ ከትኩረት ፍለጋቸው ጀርባ ሆኖ የሚነዳችው የበሽታው ምክንያት ተመርምሮ አፋጣኝ የአዕምሮ ሕክምና ያስፈልጋቸዋል:: ሁላችንም ሳናውቀው የዚህ በሽታ ተጠቂ ሆነን ሳናስተውል ስር ሊሰድ ስለሚችል ራሳችንን እንመርምር::
የራስ ፍቅር እና ትኩረት ፍለጋ ሌሎችን በጭፍን መጥላት፣መጽሐፍ ማቃጠል ብቻ ሳይሆን ራስንም እስከማቃጠል ያደርሳል::

No comments:

Post a Comment