Tuesday, August 11, 2015

ብቃት የተላበሰ አመራር የለንም ሲሉ አቶ አለምነው መኮንን ተናገሩ

Alemnew Mekonenየብአዴን የጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን ብአዴን የየተመሠረተበትን 35ዓመት ህዳር 11 ቀን 2008 ዓ.ምለማክበር በማሰብ፣ ከሚዲያ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ብአዴን የህዝቡን ፍላጎት የሚያሟላ ብቃት የተላበሰ አመራር የለውም ብለዋል።
በግዮን ሆቴል ብአዴን በጠራው የሚዲያና ኮምኒኬሽን ባለሙያዎች የተሳተፉበት ስብሰባ ላይ ማብራሪያ የሰጡት አቶ አለምነው መኮንን፤ ብአዴን ያለበትን ተግዳሮቶች በዘረዘሩበት መግለጫቸው፣ ባለፉት 24 ዓመታት የህዝቡን ፍላጎት የሚያረካ የተሟላ የአመራር ብቃት አለመታየቱን አምነዋል፡፡ “ሕዝቡ በመቶ ኪሎሜትር እየሄደ፣ አመራሩ በ80 ቢሄድ የ20 ኪሎሜትር ክፍተት አለ» በሚል በምሳሌ ያስረዱት አቶ አለምነው፣ በአመራር ብቃት በኩል ሕዝቡ የሚፈልገውን እርካታ ለማምጣት አልቻልንም ብለዋል።


በክልሉ ፍትሐዊ አስተዳደርና ሕዝብ በየደረጃው የሚጠቀምበት አሰራር እንዲሁም ወጣቶችን በልማት ለማሳተፍና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የተሰራው ስራ አመርቂ አለመሆኑን ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
ልማትን በተመለከተም በክልሉ ከአካባቢ አካባቢ ልዩነቶች አሉ ያሉት አቶ አለምነው፣ እንደየአካባቢው ባህርይ ልዩነት ማጋጠሙ የሚጠበቅ ቢሆንም የአካባቢዎችን ዕድገት ለማመጣጠን መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ብአዴን የዛሬ 35 ዓመት በ38 ታጋዮች የጫካ ትግል መጀመሩን ያብራሩት አቶ አለምነው፣ ንቅናቄው ከ1973 አስከ 1983 በትጥቅ ትግል አምስት ክፍለጦሮችን ይዞ መቆየቱን፣ በአሁኑ ወቅት የንቅናቄው አባላት ቁጥር 1 ነጥብ 6 ሚሊየን መድረሱን በመግለጽ ንቅናቄው ከፍተኛ ስኬት አስመዝግቦአል ሲሉ በኩራት መንፈስ ተናግረዋል፡፡
የብአዴን ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑበት የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮምቴ ከአምስት ዓመት በፊት ያስቀመጠውን የአመራር መተካካት ወደጎን በመተው በዕድሜ መግፋትና በጤና ችግሮች ውስጥ ያሉ ነባር የድርጅቱ አመራሮች አሁንም በስልጣን ላይ ናቸው።
በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ድርቅ በተነሳበት በዚህ ወቅት፣ ድርጅቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት ልደቴን አከብራለሁ ማለቱ በስፋት እያነጋገረ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ከአስር ሸህ በላይ የሚበልጡ የሂሳብ መዝገቦች ምርመራ ባለመደረጉ በንግድ ስራ የተሰማሩ ነጋዴዎች በስራችን ላይ ጫና እየተፈጠረብን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የነጋዴዎቹ አቤቱታ ብአዴን ሰሞኑን ባደረገው ጉባኤ ላይ ቀርቧል።
የክልሉ ገቢዎች ባለሰሰልጣን የታክስ ኦዲት ና የህግ ማስከበር ዋና ስራ ሂደት ዳይሬክተር አቶ ጠብቀው ወርቁ የክልሉ መንግስት ባዘጋጀው የምከክር መድረክ ላይ ” የነጋዴዎች ቅሬታ ትክለለኛ እና ፍርሃት ፈጣሪ ነው ” በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ከፊደራል መንግስት ወደ ክልል መንግስታቶች በድጉማ መልክ የሚፈሰውን ገንዘብ በክልሎች በገቢ አቅም ለመተካት የሚሰራው ስራ ላፉት 25 ዓመታት አለመሳካቱ ተገልጿል። የፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር እንዳለው ክልሎች በተሰጣቸው ኮታ ልክ ገንዘብ ሰብስበው ራሳቸውን ባለመቻላቸው፣ መንግስትን በከፍተኛ እዳ ውስጥ ጥለውታል ብለዋል።
በዚሁ ስብሰባ ላይ የሀገሪቱን ብድር ቀጣዩ ሶስት ትውልድ ከፍሎ አይጨርስውም ሲል የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ሚንስትር ተወካይ ገልጸዋል። ኢህአዴግ ካለፉት መንግስታት አራት እጥፍ የሚልቅ ገንዘብ ከውጭ መንግስታት እና እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ቢበደርም የአገሪቱ እዳ የመክፈል አቅም አነስተኛ በመሆኑ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገልጿል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment