Tuesday, August 25, 2015

አሸባሪነት ሲሉ – ያኔ እሰከ ዛሬ (ታሪኩ አባዳማ)

ታሪኩ አባዳማ ነሐሴ 2007
ላለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት በላይ በወያኔ አገዛዝ ስር የጭካኔ በትር ሰለባ የሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ቁጥር በቀላሉ የሚሰላ ባይሆንም እንበለ-ሕግ ሰብአዊ መብት ማዋረዱ መርገጡ ግን እነሆ እስከ ዛሬ አላባራም። በአዲስ አበባ የሚፈፀመውን ግፍ እና በደል ሳይውል ሳያድር በትኩሱ ለማወቅ ዕድል ቢኖርም በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች በምስጢር እስር ቤቶች እየታጎሩ ፣ በየጉድባዎች እየተረሸኑ የሚገኙ ሰለማዊ ዜጎች እሪታቸው የገደል ማሚቶ መሆኑ ቀጥሏል። ዛሬም እሪሪሪሪ ተገፋሁ… የሚለው ኢትዮጵያዊ ድምፅ ከመቸውም ግዜ የበለጠ ጎልቶ እያስተጋባ ነው። ወያኔ ሆነ ብሎ በሚቀሰቅሰው የሀይማኖት እና የጎሳ አምባጓሮ ውድ ህይወታቸውን ያጡ ፣ ቤት ንብረታቸው የወደመ ፣ የተፈናቀሉ ምስኪን ዜጎች ቁጥር እያሻቀበ ነው።
አሸብር ዜናዊ አስታቅፎን በሄደው ‘የሽብር ህግ’ መሰረት ፍፁም ሰላማዊ የሆኑ የእስልምና ሀይማኖት መሪዎች እስከ ሀያ ሁለት ዓመት በሚደርስ እስራት ፍርደኛ ተብለው የወህኒ ኑሯቸው መራዘሙ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። ባለ ‘ራዕዩ መሪ’ ለገሰ ዜናዊ ያወረሰን የተወልን ሌገሲ።

ትናንት ሆነ ዛሬ ትልቁ ወንጀል ‘ነፍጠኛ ፣ ትምክህተኛ ፣ ጠባብ ፣ አክራሪ’ ቢሆንም – እነ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ስማቸው ግን ጎልቶ ከማይታወቅ በሺህዎች ሚቆጠሩ ተከታዮቻቸው ጋር ውድ ዋጋ ከፍለውበት ሳያበቃ ዛሬም በየጉድባው አማሮች ፣ ኦሮሞዎች ፣ የጋምቤላ ክልል ዜጎች…ወዘተ እየታደኑ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ‘ህገ መንግስቱን በሀይል ለመናድ’ የተነሱ ተብለው የታሰሩ ፣ የተደበደቡ ፣ የተገደሉ እና ቤት ንብረታቸው የወደመ ዜጎች ቁጥር አሁንም በአሀዝ የሚገለፅ አይደለም።
‘ፀረ-አሸባሪነት’ እንደ ‘ነፍጠኛ’ነት ሁሉ ለወያኔ ጎጣዊ እና ኢ-ሰብአዊ አገዛዝ አልመችም ያሉ ሰላማዊ ዜጎች የሚታደኑበት እና የሚመቱበት ከህጎች ሁሉ የበላይ ‘ህግ’ ሆኗል። ኢትዮጵያ የምትተዳደረው ደግሞ ህወሐት ራሱ ህግ በሆነባት አገር በመሆኑ ድርጅቱ አሸባሪ ወይንም ‘ነጭ ለባሽ’… ያለው ዜጋ ለምን እና እንዴት ተብሎ እንኳ ሳይጠየቅ በታማኝ ካድሬዎች ይመታል።
በአገሪቱ ያለው አንድ ህግ ነው – እሱም መለስ ዜናዊ ፅፎት የሄደው የህወሐት ፕሮግራም ነው። ህግ ተብሎ የታወጀ ማናቸውም ደንብ ከህወሐት ፈቃድ እና ፍላጎት ውጭ ከሆነ ተፈፃሚ አይሆንም። የህወሐት ፕሮግራም ህግ በሆነበት ሌላ ህግ የለም። የይስሙላው ሰነድ እንደ ህገ መንግሰት ለህወሐት ፕሮግራም እና አላማ ጭንብል ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም።
ለምሳሌ ይፋ በተፃፈው ህግ መሠረት “አንድ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ መሆኑ በህጋዊ ፍርድ ቤት እስካልተረጋገጠ ድረስ ነፃ ነው” ቢልም ቅሉ በዚህ ስርዓት ህወሐቶች የጠረጠሩት ሁሉ ነፃ መሆኑ እስካልተረጋገጠ ደረስ ወንጀለኛ ነው። ህወሀት የጠረጠረውን ‘ነፃ’ ነህ ብሎ የሚያሰናብት ፍርድ ቤት ይኖራል ብሎ መጠበቅ ደግሞ ህወሐትን ጠንቅቆ ካለመገንዘብ የሚመነጭ የዋህ ግምት ከመሆን አይዘልም። ፍረድ ቤት ይፈታ ሲል ህወሐት በበኩሉ አልፈታም ማለት እንደሚችል ደጋግሞ አሳይቶናል። ከፍርድ ቤት ደጃፍ ዳግም እያዳፉ ይወስዱሀል።
አንቀፅ 39 በግልፅ እንደሚደግገው ‘ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት እስከ መገንጠል’ ይችላሉ ይላል። በዚህ አንቀፅ መሰረት የመገንጠል ጥያቄ ማንሳት በጣም ህጋዊ ነው። ይሁንና በተገንጣይነት የሚከሰሰው ኦነግ ዛሬ ‘አሸባሪ’ ተብሎ አባላቱ እና የተጠረጠሩ ኦሮሞዎች በሙሉ እየተጋዙ ፣ እተገደሉ ነው – ምክንያቱም የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው የህወሐት ፖሊሲ ኦነግ ‘አሸባሪ’ ነው ብሎ ስለፈረጀ
ወያኔ አሸባሪዎች ብሎ ሲነሳ አንድ የሚገርመኝን ነገር ልጥቀስና ወደ ተነሳሁበት ልመልሳችሁ – በወያኔ መገናኛ አውታሮች ተደጋግሞ እንደሰማነው ሻ’ኣቢያ/ኤርትራ በኢትዮጵያ ውስጥ የማያቋርጥ ሁከት ለመቀስቀስ የአሸባሪነት ተግባር ይፈፅማል እየተባለ ነው። ይሁንና የወያኔ ፓርላማ አልቃይዳን እና አልሽባብን ጨምሮ ኦነግ ፣ ግንቦት 7 እና ኦብነግን ‘አሸባሪ’ ብሎ ‘ሲፈርጃቸው’ ሻ’ኣቢያን ግን ከቶ ስሙ በዚህ ዝርዝር ተራ እንዲጠቀስ አልፈለገም። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለመገንዘብ ካስፈለገ ህጉ ማለትም ህወሐት (እነ ስብሀት ነጋ) ስለ ሻአቢያ/ኤርትራ የሚሉትን መስማት ጠቃሚ ነው። ይህ ሀቅ ከፍ ሲል የተጠቀሰውን ህወሀት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ የሚጫወተውን የፈላጭ ቆራጭነት ሚና በጉልህ የሚያመለክት ነው ብዬ አምናለሁ።
በወያኔ ዘንድ ‘አሸባሪ’ የሚለውን መስፈርት ለማሟላት እንደ ሻ’ኣቢያ በግልፅ የጠላትነት ተግባር መፈፀም ብቻ በቂ አይደለም – ይልቁንም በአገሪቱ ውስጥ የህግ በላይነት ለዘለቄታው መስፈን ይገበዋል የሚሉ ሀይሎች ሁሉ ቀንደኛ አሸባሪ ናቸው። ምክንያቱም አካሄዳቸው በቀጥታ የወያኔን ተፈጥሮ የሚፃረር ነውና!!
ስለሆነም ወያኔ አሸባሪ ብሎ ዛሬ እንደ አውሬ የሚያሳድዳቸው ንፁሀን ዜጎች አብላጫውን ለሰብአዊ መብት መረጋገጥ በፅናት የቆሙ ጀግኖች ናቸው የምንለውም ለዚህ ነው።
የወያኔ ካድሬ በ’ተጠረነፈው’ ፓርላማ ፊት ወይንም መገናኛ ብዙሀን ዘንድ ቀርቦ የተነፈሰው የጥላቻ ወገዛ ሁሉ እንደ ሕግ አንቀፅ ያገለግላል – በዚህም የተነሳ የወያኔ ’ፀረ-ሽብር’ ሰነድ ትርጉሙ እና አፈፃፀሙ አንዳች ወጥነት የሌለው – ይልቁንም የወያኔ ሹሞች በእጀ መናኛ ያሻቸውን የሚመትሩበት ፣ ባሻቸው ጊዜ የሚመዙት የበቀል በትር ነው።
ጋዜጠኛ ውብሸት አሸባሪ ነው ፤ መምህር በቀለ ገርባ አሸባሪ ነበር ፤ አርቲስት ደበበ እሸቱም አሸባሪ ነበር ፤ ርዕዮት አለሙ ፣ እስክንድር ነጋም አሸባሪ ናቸው… በቃ። ‘ፀረ-አሸባሪ’ ህግ በመደንገጉ ብቻ የመብት ጥያቄ አንግቦ በፅናት መቆም በወያኔ አይን ከአሸባሪነት ተነጥሎ የሚታይበት ነገር የለም – መብት ረጋጩን ወያኔ እምቢ ለመብቴ ብሎ መሟገት አሸባሪነት ነው። የወያኔን ህግ አልባ የስልጣን ዘመን ለማሳጠር የሚደረግ ማናቸውም እርምጃ ‘አሸባሪነት’ ነው።
ከፍ ሲል እንዳመለከትኩት ተቃዋሚ ፓርቲ በሙሉ በፀረ-አሸባሪ መነፅር እይታ radar ውስጥ ነው – ማለትም ተጠርጣሪ ነው… ስለዚህ ወንጀለኛ ነው። ነፃ ፕሬስ አሸባሪ ነው ፣ በነፃ መደራጀት አሸባሪነት ነው፣ ቦንድ አለመግዛት አሸባሪነት ነው ፣ ግንቦት ሰባት አሸባሪ ነው ፣ ኦነግ አሸባሪ ነው – እነኝህን ድርጅቶች የሚመለከት ዜና መዘገብ አሸባሪነት ነው ፣ የድርጅቶቹንም ሆነ የመሪዎቹን ስም ተሳስቶ እንኳ መጥራት አሸባሪነት ነው… በወያኔ ራዳር እይታ ይሄ ሁሉ ተጠርጣሪ በፍርድ ቤት ‘ነፃ’ መሆኑ እስኪረጋገጥ ወንጀለኛ ነው።
ነፃ ምርጫ ‘ሽብር’ ስለሚያስከትል ‘በጥርነፋ’ ቁጥጥር ስር ብቻ ይደረጋል – እናም 100% ድል አድርጎ ‘ከአሸባሪዎች’ የፀዳ ፣ ከተጠርጣሪ (ማለትም ወንጀለኛ) ‘የጠራ’ ፓርላማ ተመስርቷል።
ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ የመብት እና ነፃነት ጥያቄ ለማፈን ያዋጣኛል ብሎ የቀየሰው ስልት ‘በፀረ-አሸባሪ’ አዋጅ እንዲታጀብ የተደረገው ግን አለምክንያት እንዳልሆነ ብዙዎች ይረዳሉ ብዬ ገምታለሁ። በዲሞክረሲ ካባ ተከናንቦ ለመታየት የዞትር ምኞቱ በመሆኑ ‘ሽርክ’ ካደረገችው አሜሪካ ጋር ለመመሳሰል ብዙ ይመኛል። የአሜሪካ መንግስት ወያኔን ‘ሽርክ’ ያደረገው ለአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ብሎ ሳይሆን ወያኔ ዲሞክራሲያዊ ስለሆነ እንዲመስል ለማመልከት ይታክታል – እንደ አሜሪካ ሁሉ ‘ፀረ-አሸባሪ’ ህግ በማውጣት ፣ አሸባሪዎችን በማሳደድ ፣ በማሰር ተባባሪ እና ዘላቂ ወዳጅ መሆኑን ለማስመስከር ይታክታል… ።
አሜሪካ ከአሸባሪዎች ሴራ ለመከላከል ስትል ሶስት ሺህ ዜጎቿን ከቀጠፈው የሴፕተምበር 11 አሸባሪዎች ጥቃት ማግስት ‘ፀረ-አሸባሪ’ ህግ አውጃለች። የህጉ አቢይ አላማ የመላውን ዓለም አገር ዜጎች ወይም ዕምነት ተከታዮች በማስጠጋት የምትታወቀው አሜሪካ በዚህ አጋጣሚ ሰርገው ሊያጠቋት የሚሹ ድርጅቶችን ሆነ ግለሰቦችን ለመከታተል የሚያግዝ ህጋዊ መሣሪያ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው። ህጉ የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ሲባል በልዩ ሁኔታ እና የወንጀል ድርጊት ላይ ተፈፃሚ ከመሆን በስተቀር የአገሪቱን ህጎች ተክቶ የሚሰራ አይደለም። ያም ሆኖ አሻሚ ነው በሚል ብዙ ትችት የቀረበበት ሰነድ በመሆኑ አፈፃፀሙ እጅግ ብርቱ ጥንቃቄ ይደረግበታል -።
በዚህ መካከል የምዕራቡ ዓለም በተለይም ደግሞ አሜሪካ ለፀጥታ አስጊ ናቸው ብላ የመዘገበቻቸውን አክራሪ እስላሞች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ተባባሪ ትሻለች – ወያኔ ይህን የምዕራባውያን ስጋት ተንተርሶ የቅርብ ተባባሪ ሆኖ ቀርቧል። ተባባሪነቱን አንተርሶ ያወጣው ‘ፀረ-አሸባሪ’ ህግ ግን ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ አይነት መሆኑን ድፍን አለም ያውቀዋል።
እሩቅ ሳንሄድ አልቃይዳ አሜሪካ ላይ ጥቃት ማድረግ ሲጅምር ቦምብ ያፈነዳው ኬንያ እና ታንዛኒያ ርዕሰ ከተሞች ላይ በ1998 ኦገስት ነበር። ያ አሸባሪ ጥቃት በተፈፀመበት ቀን የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ናይሮቢ ነበርኩ። ሰሞኑን ደግሞ አንድ የወያኔ ተላላኪ እንደ ትኩስ ዜና ያንን ከአስራ ሰባት ዓመታት በፊት የደረሰ ጥቃት ሲዘግብ አስተውዬ ገረሞኛል። የፈራረሰ ግንብ እና በፊንጂ የቆሳሰሉ ሰዎችን በማሳየት ዜጎችን ለማስፈራራት የሚደረግ የሙያ ብቃት የነጠፈበት ሙከራ ነው።
በመሰረቱ ኬኔያ እና ታንዛኒያ ላይ የተፈፀመው አሸባሪ ጥቃት የሚሰጠን ትምህርት አለ ከተባለ አንድ ነገር ብቻ ነው። እሱም ቢን ላደን ናይሮቢ ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ኬንያ በውስጥ የፖለቲካ ውጥረት ስትታመስ መሆኑ። ተቀዋሚዎች ገዢውን ካኑ ፓርቲ ከስልጣን ለማውረድ ጠንካራ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ወቅት ነበር። ይሁንና ገዢው ፓርቲ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ተቃዋሚን ለማዳከም ሲል ‘ፀረ-አሸባሪ’ ቅብጥርሴ የሚባል ህግ አላወጣም። አሸባሪዎች በአገር ጥቅም ላይ የሚነሱ እንደመሆናቸው ሁሉም ዜጋ አገሩን ለመከላከል እኩል ሀላፊነት እንዳለበት በማመልከት ጉዳዩ በጥንቃቄ እንዲያዝ ተደረገ።
በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበሩት ዳንኤል አራፕ ሞይ ተቀናቃኞቻቸውን ፀጥ ለማሰኘት መልካም አጋጠሚ ነው ብለው አዋጅ ለማውጣት አልተጣደፉም። ይህ ከቶ ሊሆን ያልቻለበት አቢይ ምክንያት ደግሞ አገሪቱ በማይናቅ ደረጃ የህግ የበላይነት ያለበት በመሆኑ ነው። ጦር ሀይሉ እና የፍትህ ስርዓቱ ከፖለቲካ ፓርቲ ታማኝነት የላቀ ነፃና ብሔራዊ ቅርፅ የያዘ በመሆኑ ነው። የቢን ላደን አሸባሪ ቀጥተኛ ጥቃት ሰለባ የሆኑት ኬንያ እና ታንዛንያ ብዙ ዜጎቻቸው በጠራራ ፀሀይ ሲያልቁ እንኳ ነባር ህጋቸውን መሰረት ያደረገ ይፋዊ ክትትል እና እርምጃ ከመውሰድ በስተቀር ‘ፀረ-አሸባሪ’ የሚል አዋጅ በማርቀቅ ድብቅ እና በቀል የተላበሰ እንቅስቃሴ ለማድረግ አልዳዳቸውም – ለዜጎች ደህንነት በፅናት መቆም ይሏል ያ ነው።
አርብ ኤፕሪል 10 2015 Mwaura Samora የተባለ ታዋቂ ኬንያዊ ጋዜጠኛ. Kenya can’t, won’t be Ethiopia በሚል ርዕስ ፅፎ እንዳነበብነው “አልሽባብ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቃት ማድረስ ያልፈለገው አገሪቱ ከላይ እስከታች ባንድ የፖለቲካ ድርጅት ስር በስለላ ሰንሰለት ተቆልፋ መፈናፈኛ ስላጣች ነው” ብሏል። በተዘዋዋሪ ማውራ የሚለው – ኢትዮጵያውያን ቀድሞውኑ በአሸባሪ መንግስት መዳፍ እና ቁጥጥር ስር ስለሚገኙ ሌላ ተቀናቃኝ አሸባሪ አያነጣጥርባቸውም ነው። ዝርዝሩን ለማየት www.standardmedia.co.ke/article/…/kenya-can-t-won-t-be-ethiopia እዚህ ይጫኑ። ብዙ ወያኔዎችን ያንጫጫ ዘገባ ነበር። በነገራችሁ ላይ ማውራ በናይሮቢ ዩንቨርሲቲ ድህረ-ምረቃ ህንጻ ጎረቤቴ ሆኖ ለሁለት ዓመታት ያህል በቅርብ የማውቀው ጠንካራ ሰው ነው። ማውራ ሙያህን በሀላፊነት ስለምትወጣ thank you, I have a T-shirt that says this. As a journalist, I know it is true
አሜሪካ አሸባሪ ብላ የምትከታተላቸው ግለሰቦች የሚኖሩት አንድም በቶራቦራ ተራራ አለበለዚያም በየመን ብሎም በፓኪስታንና ሶማሊያ አሸምቀው ወይንም በተለያዩ አገሮች ስማቸውን ቀይረው ፣ የውሸት ፓስፖርት ይዘው በስጋት እና በጥንቃቄ ነው። አክራሪዋች የሚከተሉት ፀረ-አሜሪካ ጥላቻ አለም አቀፋዊ ባህሪ ቅርፅ እንዲይዝ እና ምዕራባውያን ዲሞክራሲያዊ አገሮች ሁሉ የጥላቻው እና የጥቃት ኢላማ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ። የነኝህ አገሮች ቡችሎች ናቸው የሚሏቸውን ድሀ አገሮችም ከማጥቃት እንደማይመለሱ አሳይተዋል።
ቢንላደን ፓኪስታን ተሸሽጎ ይኖርበት ከነበረው የተንጣለለ ቪላ ድረስ በማሳደድ እንዲወገድ መደረጉን እናውቃለን። የሚኖርበትን ስፍራ ለማወቅ ዘጠኝ ዓመታት የፈጀ ጥብቅ ክትትል ተደርጓል። ይሁንና ቢንላደን እንደ ጠላት ጦር መሪነቱ አገዳደሉ ፍትሀዊ ነበር ወይ ብለው የሚጠይቁ እና የሚሟገቱ የህግ ባለሙያዎች አሜሪካ ውስጥ አሉ። የህግ የበላይነት አለመጣሱን እየመረመሩ ነው።
አንድ የጠላት ጦር መሪ እጁ ላይ የጦር መሳሪያ ሳይኖር እና በወገን ላይ ተኩሶ አደጋ ለማድረስ ማነጣጠሩ ሳይረጋገጥ እንዲገደል ማድረግ በአሜሪካ ሆነ በአለም አቀፍ ህግ ያስጠይቃል በሚል የቢንላደንን አገዳደል የሚያጣይቁ ብዙ ናቸው። ከዚህ በመነሳት ለመሆኑ ቢንላደን ላይ ለመተኮስ የሚያበቃ በቂ አስገዳጅ ሁኔታ ነበር ወይ – ማርኮ ወይንም በቁጥጥር ስር አውሎ ለፍርድ ማቅረብ ለምን አልተሞከረም ይላሉ። እንግዲህ አስቡት ቢንላደን ለምን በህጋዊ ፍርድ ቤት ቀርቦ ይፋ በተጠራ ችሎት ጉዳዩ አልታየም ብለው የሚንገበገቡ ለህግ የበላይነት ያለማወላወል የተሰለፉ አሉ… አሜሪካ ለዚህ አይነቱ አቋም መኖር ዋስትና የሚሰጥ ህግ ያለበት አገር ነው። ታዲያ ሰሞኑን ብርሀኑ ነጋ አሜሪካ ተመልሶ እንዳይገባ ለማስወሰን ውጪ ጉዳይ ቢሮ ደጅ የሚጠኑ ታጋዮች መኖራቸውን ስሰማ በሳቅ ፈንድቼ ነበር።
በዳበረው የምዕራብ ዲሞክራሲ ዜጎች ካለ አንዳች ስጋት በነፃ ሀሳባቸውን የሚገልፁበት ፣ የሚፅፉበት ፣ የሚደራጁበት ፣ የፖለቲካ ዕምነታቸውን አለ አንዳች መሸማቀቅ የሚያራምዱበት ነው። በአጭሩ ሰብአዊ ክብር በህግ የበላይነት በማያሻማ መንገድ የተረጋገጠበት ሥርዓት ነው። ሀይማኖት ፣ ዘር ፣ የቆዳ ቀለም ፣ ፆታ ወይንም ፆታዊ ዝንባሌ ሌላውን የማግለያ መሣሪያ የማይደረግበት ህግ አለ። ህግ ሲጣስ ይፋዊ ተጠያቂነት አለ። ስለሆነም አሜሪካ እና ምዕራባውያን ላይ ያነጣጠረው አሸባሪነት በዲሞክረሲ እና በነፃ አኗኗር ላይ የታወጀ የሀይማኖት አክራሪዎች ጥቃት ነው የሚባለው ለዚሁ ይመስለኛል።
ለአሜሪካ መንግስት አሸባሪ ማለት የአሜሪካንን ህልውና ፣ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት እና አኗኗር ለማደፍረስ በሰላማዊ ህዝብ ኢላማ ላይ ጥቃት ለመፈፀም የተሰለፈ ሀይል ነው። አሜሪካንን ለመምሰል የሚንደፋደፈው ወያኔ አሸባሪ ብሎ የሚያሳድዳቸው ዜጎች… እነ ብርሀኑ ነጋ የሚያነሱት መሰረታዊ ጥያቄ የአሜሪካ መንግስትና የመንግስታቱ ድርጅት የቆሙለትን የሰብአዊ መብት ድንጋጌ የሚያንፀባርቅ ነው።
አሜሪካ እና ወያኔ በፀረ ሽብር አቋም ተባባሪ ናቸው ይባል እንጂ ስለ አሸባሪ እና ሽብር እንዲሁም ሽብረተኞች ያላቸው ትርጉም የሰማይ እና ምድር ያህል ልዩነት አለው። በመሠረቱ ትብብሩ አሜሪካ ስጋት አለ ብላ በምትገምተው የሶማልያ እና መካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ቅርብ ክትትል ለማድረግ እንድትችል ነዳጅ እና ስንቅ ማከማቻ ለመሻት እንጂ ለዋሽንግተን ከዚያ የዘለለ ትርጉም የለውም – ትብብሩ በተመሳሳይ አመለካከት እና አቻ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ ቢሆን ኖሮ ወያኔ አሸባሪ ያለውን አሜሪካ አክብሮ ማስተናገድ ባልቻለ ነበር። ወያኔ ይህን ትብብር በአገር ውስጥ የሚነሱ ፍትሀዊ እና ሰብአዊ መብት ጥያቄዎች ለመጨፍለቅ ሲል የሚጠቀምበት መሆኑ ለአሜሪካ ሚስጥር አይደለም።
ግልፅነት እና ተጠያቂነት የማዕዘን ድንጋይ በሆነባት አሜሪካ የፖለቲካ መስመሬን አልተቀበለም ተብሎ በአሸባሪነት የሚፈረጅ ድርጅት ወይም ዜጋ የለም – ‘ቲ ፓርቲ’ የተሰኘው አክራሪ የሪፐብሊካን አንጃ የኦባማን አስተዳደር ጥላሸት በመቀባት እና ዘረኛ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። ህገ መንግስታዊ መብታቸው ነው ተብሎ በፈለጉት ቦታ ስብሰባ ጠርተው ያሻቸውን ቅስቀሳ ያደርጋሉ። በድርጅትነት አልተመዘገቡም ፣ አሸባሪ ናቸው ብሎ የጠየቃቸው የለም – ይሄ ነው ሰፊው ልዩነት።
ወያኔ አሸባሪ ብሎ የሚያስራቸው ወይም የሚያሳድዳቸው ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ለመኖር ወስነው ነገር ግን ሰብአዊ ክብራቸው በህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ብሎም በትግል የተሻለ የፖለቲካ አመራር እናመጣለን ብለው የቆሙ ናቸው። ወያኔ ‘አሸባሪ’ ብሎ የፈረጃቸው በውጭ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ደግሞ በምዕራብ አገሮች ይፋ በከፈቱት ፅ/ቤት እና አድራሻ መሆኑን እናውቃለን። እነ ብርሀኑ ነጋ አሜሪካ ውስጥ አንቱ ተብለው ክብር እና ሞገስ ያለው የጥበብ ሥራ መስክ ላይ ተሰማርተው ህጋዊ እና ይፋ የሆነ ህይወት ይኖራሉ። ብርሀኑ ነጋ አሜሪካ ብቻ ሳይሆን ወደ ፈለገው የዓለም ክፍል በፈለገ ግዜ በይፋ መንቀሳቀስ የሚችል ‘አሸባሪ’ በሚል ክስ ግን ወያኔ ሞት የፈረደበት ወይም የፈረጀው ኢትዮጵያዊ ነው። ብርሀኑ ነጋ – ቶራቦራ አልተደበቀም ወይም እንደ አሸባሪ ሸሽጉኝ ፣ መታወቂያዬን ደልዙ ሲል አልታየም።
እስቲ ገምቱት ወያኔ እና አሜሪካ በፀረ-ሽብር ሽርክና መስርተዋል። አሜሪካ አሸባሪ ያለችው ግለሰብ ወይንም ድርጅት በየትኛውም የአለም ክፍል ቢሸሸግ (ኢትዮጵያን ጨምሮ) መኖሩ ሲደረስበት ፈጣን እርምጃ ይወሰድበታል። ወያኔ አሸባሪ ያለው ግለሰብ/ቦች እና ድርጅት/ቶች ግን ዋና ፅህፈት ቤታቸው ሳይቀር በይፋ አሜሪካ እና በተለያዩ አውሮፓ አገሮች ነው። የድርጅቶቹ መሪዎች በአሜሪካ እና አውሮፓ በነፃ እና ህጋዊ በሆነ ሰነድ ይንቀሳቀሳሉ ፣ ሰርተው ማደር ብቻ ሳይሆን ለድርጅቶቻቸው ድጋፍ ለማሰባሰብ ቅስቀሳ ያካሂዳሉ ፣ ስብሰባ ይጠራሉ ፣ አላማቸውን በይፋ ያስተዋውቃሉ ፣ ድጋፍ ያሰባስባሉ። ወያኔ የሚያላግጥበትን ‘ህገ-መንግስት’ በሀይል መናድ አስፈላጊ መሆኑን ፣ ጭምብሉን ከስክሶ መጣል ተገቢ መሆኑን ጭምር በይፋ ያስተምራሉ – ፍትሀዊ ጥያቄ መሆኑንም ይሰብካሉ።
በዓለም ውስጥ ተፎካካሪ የፖለቲካ ሀይል አሸባሪ የሆነባት ብቸኛዋ አገር የወያኔይቱ ኢትዮጵያ ናት። ትናንት ሆነ ዛሬ የዜጎች ትልቁ ወንጀል በህግ የበላይነት ካልሆነ በግለሰቦች እና በቡድኖች ፈቃድ አንገዛም ማለታቸው ነው። የህግ በላይነት ደግሞ በፎቆች ርዝመት ፣ በባቡር መስመሮች ስርጭት ፣ በግድቦች ስፋት የሚለካ የሚተካም አይደለም። የህግ በላይነት እስኪረጋገጥ ፣ ህዝብ የፈቀደው የፖለቲካ ሀይል ስልጣን የሚይዝበት እና የሚወርድበት አግባብ እስኪሰፍን እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ለመታገል ቆርጠው ለተሰለፉ ክብር ይሁን።
As a journalist, I know it is true!!

No comments:

Post a Comment