Wednesday, August 26, 2015

'አስተርጓሚ'

የትናንትናው የገንዘቤ ዲባባ ቃለ መጠይቅ ላይ የነበረው ጉደኛ 'አስተርጓሚ' ተብዬ ላይ ትዝብታችንን መግለፃችንን ተከትሎ፥ የተለያዩ ወዳጆች፣ በውስጥ መልእክትም በአደባባይም፥ “ቋንቋ አለመቻል ምንም ማለት አይደለም።” “የውጭ አገር ቋንቋ ባይችል አያስወቅስም።” እና መሰል የመከላከያ ነገሮችን ተናግረዋል።
እርግጥ ነው ቋንቋ አለመቻል ምንም ማለት አይደለም። እንኳን የውጭ ቋንቋ ይቅርና፣ የቤተሰቦቹን ቋንቋ ባይችልም ምንም ማለት አይደለም። ሲጀመር ቋንቋ ክህሎት እንጂ እውቀት አይደለምና ባይችሉ አያሳፍርም። መቻሉም ቢያስደንቅ እንጂ፥ የሚያስኮፍስ ነገር አይደለም። ሰው እንደዋለበትና እንደፈለገው ልክ የትኛውንም ቋንቋ ማወቅና በአግባቡ የመጠቀም ክህሎቱን ማሻሻል ይችላል።

ችግሩ ቋንቋውን ተጠቅሞ ስራ ልስራ ሲባል ነው። ስራው አስተርጓሚነት መሆኑ ደግሞ ነገሩን ይበልጥ አሳፋሪ ያደርገዋል። አስተርጓሚ ጠያቂውንና ተጠያቂውን እንዲያገናኝ የተሰየመ ድልድይ ነው እንጂ የራሱን ሀሳቦች እየሰነቀረ፣ እየተነተነና እንደፈለገው እየጠመዘዘ የሚኖር ማለት አይደለም። እንደዚያ ሲያደርግ ደግሞ ቋንቋው ላይ በቂ የሚባል ችሎታ ስለሌለው፣ ሰው ካልጠፋ በቀር የአስተርጓሚነት ስራውን መስራት እንደሌለበት የሚያሳይ ነገር ነው።
የራሱን ጥያቄ ጠይቆ፣ ራሱ ለመመለስና፣ የሚሰጠውን መልስ በፈለገው መልኩ ለማስተካከል፥ ለኤፍሬም ኢቲቪ የተሻለ ቦታ ይሆንለት ነበር። ደግሞም ይህ ችግር ድንገት የመጣ ሳይሆን፣ በመገንባት ሂደት ውስጥ እዚህ የደረሰ ለመሆኑ አንድ ማሳያ ነው።
በነገራችን ላይ፥ ትናንት የጠቀስነው "It was a very slow race...and then in the last two laps you took off; was that your plan?" የሚለው ጥያቄ ትርጉም ናሙና (sample) ነው እንጂ፥ ሙሉ ቃለ ምልልሱን በራሱ መንገድ ነው ሲያስተረጉም የነበረው። ከጋዜጠኛዋም ከገንዘቤም በኩል ጭራሽ ያልተጠቀሱ ነገሮችን ሳይቀር አካቷል።
ይልቅስ በዚህ ዓይነት የፈጠራ አስተርጓሚነቱ፥
“ሩጫሽ ለግድቡ ያለውን አስተዋፅኦ...”
“ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ላለችው እድገት...” ምናምን ብሎ አለመተርተሩ ገርሞኛል።
“መልካም አስተዳደርና ህዳሴ ያንቺን ውጤት በማሻሻል ረገድ...”
“you know, my country registered (ማስመዝገብ ለማለት። ሃሃሃ...) economic growth...”
LOL.
ለማንኛውም ጓዶቼ፥ ቋንቋ እንደማንኛውም ክህሎት (skill) ነውና፣ እሱን ተጠቅመው የማስተርጎም ስራ የሚሰሩ ሰዎች በሚሰሯቸው ስራዎች፥ “ምን ችግር አለው?” ተብሎ ሊስተባበል አይገባም።
ምን ችግር አለው ማለት ከጀመርን ግን...
1. ብዙ ጎበዝ ልጆች እድሉን ሳያገኙ ቀርተው ውድድሩን የሚያቋርጡ ሯጮች ቢወከሉ ምን ችግር አለው?
2. ስለሩጫ በደንብ የማያውቅ ሰው ቢያሰለጥን ምን ችግር አለው?
3. መኪና መንዳት በደንብ የማይችል፣ ወይም መንጃ ፍቃዱን በህገ ወጥ መንገድ ያገኘ ሰው መኪና ነድቶ ሰዎችን ቢፈጅ ምን ችግር አለው?
4. የሆስፒታል ፅዳት ሰራተኛ እንደ ነርስ በድፍረት መርፌ ቢወጋ, it is not a big deal.
ሌላም ሌላም ነገሮች ላይ ምን ችግር አለው ማለት እንቀጥላለን።

No comments:

Post a Comment