Wednesday, July 31, 2013

ኢራፓ በየሶስት ወሩ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ ገለፀ

በመስከረም አያሌው

ከጳጉሜ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በየሶስት ወሩ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ገለፀ።
ባለፈው ሐሙስ “ያለ ብሔራዊ መግባባት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትም ሆነ አስተማማኝ እድገት ሊመጣ አይችልም” በሚል መሪ ቃል በዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው ፓርቲው በመጪው ጳጉሜ 3 ቀን 2005 ዓ.ም የመጀመሪያውን ሰላማዊ ሰልፍ በብሔራዊ መግባባት ላይ የሚያካሂድ ሲሆን በ2006 ዓ.ም ደግሞ በየሶስት ወሩ ተከታታይ እና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ሰላማዊ ሰልፎችን ለመጥራት አስቧል።
“ሰላማዊ ሰልፍ የምናካሂደው መንግስት የሰልፍ መብትን ሰለሰጠ ለመሽቀዳደም” አይደለም” ያሉት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ፣ ይልቁንም ፕሮግራማቸው ከሁለት ዓመት በላይ የታሰበበት እድሜ ጠገብ አጀንዳ እንደሆነ ገልጸዋል። የሚካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች መንግስት የህዝቡን ጥያቄ አድምጦ እንዲመልስ እና ችግሮቹን እንዲፈታ ቅን እና ገንቢ በሆነ መንገድ ለማስጠንቀቅ መሆኑን የገለፁት አቶ ተሻለ፤ በሁለተኛነትም ሰልፉ ህዝቡ ችግር ከመድረሱ በፊት እንዲጠነቀቅ የማንቂያ ደወል ነው ብለዋል። ሰላማዊ ሰልፉም ሆነ ሌሎች ስብሰባዎችን የሚያደርጉት ህገ መንግስቱን በጠበቀ መልኩ እንደሆነ የገለፁት አቶ ተሻለ፤ መንግስትን ጨምሮ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰልፉ ላይ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። በጳጉሜው ሰላማዊ ሰልፍ ላይም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።
በብሔራዊ መግባባት ላይ ጳጉሜ ላይ የሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ዋና ዓላማው ኢትዮጵያውያንን ወደ ተስማማ አንድነት ማምጣት መሆኑን የገለፁት የፓርቲው የማስታወቂያ እና ህዝብ ግንኙነት ባለሞያው አቶ ጌታቸው አበበ በበኩላቸው፤ ከባንዲራችን ጀምሮ ባለው ጥልቅ ልዩነት ምክንያት የሌሎች ሀገራት ዜጎች በቀላሉ የሚያገኟቸውን መብቶች እኛ ግን እንድናጣ እያደረገን ነው ብለዋል። በተለይ ብሔራዊ መግባባቱ ከመንግስት (ገዢው ፓርቲ) ጋር ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋርም ጭምር እንደሚሆን ገልጸዋል።
የፓርቲው ም/ፕሬዝዳንት እና የህግና ፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊው አቶ ተሾመ ወልደ ሀዋሪያት በበኩላቸው እድገትም ሆነ የኑሮ መሻሻሉ ሁለንተናዊ መግባባትን ያነገበ፣ ህዝቡን በእኩልነት ያካተተ መሆን እንዳለበት ገልጸው፤ ከመጪው 2007 ዓ.ም ምርጫም በፊትም እነዚህን ነገሮች መስመር ለማስያዝ ማቀዳቸውን ገልጸዋል። ፓርቲው የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ የሀገሪቱን ህግና ደንብ ተከትለው የሚከናወኑ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ተሾመ፤ ፓርቲው በቀጣዩ ዓመት ሊሰራቸው ከያዛቸው እቅዶች መካከል በየ3 ወሩ ሰላማዊ ሰልፍ እና የቤት ውስጥ ስብሰባዎች መካሄድ ዋናው መሆኑን ገልጸዋል። ሰላማዊ ሰልፉም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክፍለ ሀገርም ለማካሄድ መታቀዱን ጨምረው ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment