Wednesday, July 24, 2013

የዓለም ባንክ ከፋይናንስ ድጋፉ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሊመረምር ነው

ዓለም ባንክ የብድር አሰጣጡን ከሰብአዊ መብት መከበር ጋር እንዲያያዝ ሂውማን ራይት ዎች ከፍተኛ ውትወታ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹን ጥያቄ በመቀበል የባንኩ የቦርድ አባላት በዚህ ወር መጨረሻ ላይ ስብሰባ የሚቀመጡ መሆኑ ታውቋል። የሂውማን ራይትስ ዎች አባላት ባንኩ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ መንግስታት ሰብአዊ መብትን በከፍተኛ ደረጃ ስለሚጥሱ የገንዘብ ድጋፉን ከሰብአዊ መብት መከበር ጋር አያይዞ እንዲለቅ ሲወተውቱ የነበረ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
የባንኩን ከፍተኛ አመራሮች በዚሁ ዙሪያ በማሳመኑ በኩል ከሰሞኑ በቀረቡት ሪፖርቶች ላይም ኢትዮጰያ አንዷ መሆኗ ታውቋል። የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቱ ከሰብአዊ መብት ጥሰት ነፃ የሆነ ልማት (Abuse-free development) በሚል ርዕስ ባለ 59 ገፅ ሪፖርት ማቅረቡ ታውቋል። ሪፖርቱ ካቀረባቸው የማሳመኛ ነጥቦች መካከል ከባንኩ የገንዘብ ድጋፍ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያና በባንግላዴሽ የደረሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚመለከተው የሚገኝበት መሆኑን ከዋሽንግተን ዲሲ የተለቀቀው የሂዩማን ራይትስ ዎች መረጃ ያመለክታል።

ዓለም ባንክ በፍፁም ድህነት ውስጥ ያሉ ሀገራትን ለማገዝ ፖሊሲ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም አንዳንድ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ግን የባንኩ እገዛ የሰብአዊ መብት ጥሰትን የሚያካሂዱ ሀገራትን ጭምር ያጠቃለለ ነው በማለት ወቀሳ ሲያካሂዱበት ቆይተዋል። በተለይ ሂውማን ራይትስ ዎች ባንኩ ለኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ ከማድረጉ በፊት የሰብአዊ መብት መከበርን እንደ ቅድመ ሁኔታ እንዲያስቀምጥ ረዘም ላሉ ዓመታት ሲወተውት ቆይቷል።
ባንኩ በዋነኝነት እየተተቸ ያለው በእሱ የፋይናንስ እገዛ በሚንቀሳቀሱ ፕሮጀክቶች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይካሄዳሉ የሚል ነው። የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይካሄድባቸዋል ከተባሉት መካከልም አንዱ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ነው። ባንኩ በቀጣዩ ጥቅምት ወር አጠቃላይ ስብሰባ የሚያደርግ ሲሆን፤ በተለይ ከባንኩ ፋይናንስ አቅርቦት ጋር በተያያዘ አሉ የሚባሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፈትሻል ተብሎ እንደሚጠበቅ የሂውማን ራይትስ ዎች መረጃ ጨምሮ ያመለክታል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥትን በተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ይፈፅማል በሚል መግለጫዎችን ሲያወጣ የቆየ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የድርጅቱን መግለጫዎች በሬ ወለደ ነው በማለት ሲያጣጥል መቆየቱ የሚታወቅ ነው።


No comments:

Post a Comment