Tuesday, July 30, 2013

የቁልቢ ገብርኤል ንግስና የመንግሰት አቅጣጫ (መልካም አስተዳደር ሙስና እና ሰድት)

በግርማ ሠይፉ ማሩ
የዛሬ ዓመት በቁልቢ በዓል ሲባርኩን የነበሩት የቀድሞ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ በአፀደ ስጋ ተለይተውን በሌሉበት አዲሱ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በተገኙበት የቁልቢን ባዕልን አክብረናል፡፡ በቁልቢ ገብርኤል ቅፅር ጊቢ ከአውደ ምዕረቱ ጀርባ ባለው መግቢያ ተሰቅለው ከነበሩት የቀድሞው ፓትርያርክ ምስሎች አንደኛው በፍፁም ደብዝዞ ሌላኛው በመስታውት ተሸፍኖም ቢሆን ግርማ ሞገስ ርቆት ቢታይም በሌላ በኩል ደግሞ በረጅም ተፅፎ የነበረውን የማዕረግ ስም ለመሸፈን በረጅሙ የኢትዮጵያ ባንዲራ በአገልግሎት ላይ ውሎዋል፡፡ ወጉ እንዳይቀር ከጎኑ በተቀጣጠለ ወረቀት የአዲሱን ፓትርያርክ ሰምና ሹመት ለመፃፍ የተደረገው ሙከራ አዲሱ ፓትርያርክ እንደቀድሞ ፓትርያርክ ደፋ ቀና የሚሉና እንደዚህ ዓይነት ቅንጡ ነገሮችን ለእጅ መንሻ ማቅረብ የጀመሩ አድርባዮችን ገና አላስጠጉም ማለት ይቻላል፡፡ እባኮዎትን እንዳያስጠጓቸው፡፡ ይህ ነገር ካስተማሩን ትምህርትም ጋር አይሄድም፡፡ እንደውም ወደ ቤቶዎ (ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን) ለመደበኛ አገልግሎት (በተለይ እንደዚህ ባለ በንግስ ወቅት) ሲመጡ እንደተለየ ነገር የሚያወሩትን ባይሰሟቸው ደግ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በእኔ እምነት የሆነ እክል ገጥሞዎት ከቀሩ ዜና ይሆናልና ለምዕመኑ ይቅርታ ተብሎ ሊነገረው ይገባል፡፡ በጤና ምክንያት ስለ አልተመቸኝ ወይም ለምዕመኑ እና ለቤተክርስቲያናችን የሚሆን ብርቱ ጉዳይ ገጥሞኝ ብንባል ነው ልክ የሚሆነው፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ቁልቢ ገብርኤል ለማንገስ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቢመጡ ነው ዜና የሚሆነው ብዬ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ምክር ቤት ፓትርያርክ ደግሞ በቤተክርስቲያን ንግስ ቦታ መገኘት ሊያስገርመን አይገባም፡፡ ምስጋናም አያሰጥም፡፡
በዚህ አጋጣሚ አንድ እውነት መናገር ይኖርብኛል፡፡ የቀድሞ ፓትርያርክ ቅዳሴ ሲቀድሱ እና ትምህርት ሲሰጡ እጅግ መሳጭ እንደነበር መካድ አይቻለም፡፡ ነብሳቸውን ይማርና በመጨረሻ ላይ ከሚያስገቡት ቀረርቶ መሳይ ማስፈራሪያና የካድሬ ከሚመስሉ መልዕክቶች በስተቀር፡፡ ለዛሬ ማስፈር የፈለኩት ግን መንግሰት በቤተ ክርስቲያናችን አንድ አቅጣጫ ያስቀመጠ ይመስላል፡፡ ይህውም አዲሱ ፓትርያርክ ትኩረት ሰጥተው ትምህርት የሰጡባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነርሱም መልካም አስተዳደር፣ ሙስና እና ስደት ናቸው፡፡ በእውነቱ መልዕክቶቹ ለክርስትያኖች ጠቃሚ ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁሉቱ የተነሱበት አቅጣጫ በራሱ አበረታች ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን መልካም አስተዳደርን በማስፈን እና ሙስናን ከቤቷ ጠራርጋ በማስወጣት ምሳሌ መሆን ይኖርባታል የሚል ነው፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ፈራ ተባ እያሉ በቤተ ክርስቲያን በየደረጃው የተንስራፈውን የመልካም አስተዳደርና ሙስና ለመጥቀስ የሞከሩ ቢሆንም ደፍረው ግን ዘመቻው ተጀምሮዋል ምዕመኑ ያግዝ የሚል ጥሪ ማስተላለፍ አልቻሉም፡፡ ይልቁኑም ይህ ጉዳይ በምዕመኑ የዕለት ተዕለት ተግባር እንዲገለፅ ብቻ የፈለጉ ይመስላሉ፡፡ በሁለቱም መንገድ ግን ዘመቻው መቀጠል እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ አንዱ ቤተ ክርስቲያናችን እንደተባለውም ለመልካም አስተዳደር መስፈን እና ሙስናን በመፀየፍ ምሳሌ መሆን የሚጠበቅባት ሲሆን እኛ ምዕመኖችም ይህንን በዕለት ከዕለት ኑሮዋችን የምናስመሰክረው የእይወታችን መንገድ መሆን አለበት፡፡ ይህ ከቤተክርስቲያን የሚጠበቅ አስተምሮ ሲሆን ከክርስቲያን ደግሞ የሚጠበቅ መደበኛ የህይወት ክፍል ነው፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ ያነሱት ሌላ ነጥብ ስለ ስደት ነው፡፡ ዳገት ላይ ሰው ጠፋ እየተባልን እኛም እያየን ባለንበት ሁኔታ ቅዱስነታቸው በሀገራችን የስደት ምንጭ ምን እንደሆነ ሳያስረዱን መንግሰትም ያስቀመጠውን አቅጣጫ መቀበላቸውን ሳይነግሩን እንዲሁ ሾላ በድፍኑ ወላጅች ልጆችን ምከሩ ሃምሳ እና ስልሳ ከዚያም በላይ እየከፈሉ ከመሰደድ በአገር መስራት ይሻላል የሚል ምክር አስተላልፈዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ እውነት እንነጋገር ከተባለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአገልግሎት የተላኩ የዓይማኖት አገልጋዮች ጳጳሳትን ጨምሮ ወደ ሀገራቸው የማይመለሱት በህገ ወጥ ደላላ ምክንያት ነው ልንባል አንችልም፡፡ የዓይማኖት አገልጋዮች አብዮታዊ ዲሞክራሲ አማሯቸው የአንድነት ፓርቲ ሊብራል አስተሳሰብ ናፍቋቸው ነው አገር ጥለው የሚጠፉት የሚል ጭፍን ፖለቲካ ዕይታ የለኝም፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተንሰራፈው ዘረኝነትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት መሆኑ ግን አንድም መጠራጠር አልችለም፡፡ የወላጆች ምክር ለዚህ ችገር በዚህ መንገድ መፍትሔ ያመጣል የሚል ዕምነትም የለኝም፡፡ መፍትሔው ቅድስት ቤተክርስቲያንን እንዲመሩ ሃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ዛሬ ነገ ሳይሉ ይህንን የዘረኝነትና የመልካም አስተዳደር ችገር መቅረፍ ይኖርባቸዋል፡፡ 
ሌሎች የሀገራችን ወጣቶች ሀገራቸውን ጥለው ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከመኖር በባሕርም በየብስም ያለውን አደጋ ሁሉ ችለን እንሄዳለን የሚሉበት ምክንያት ከላይ ለዓይማኖት አገልጋዮች ከምለው የሚለየው እነዚህ ወጣቶች አብዮታዊ ዲሞክራሲ አማሯቸው የአንድነት ፓርቲ ሊብራል አስተሳሰብ ፍቅር አስይዟቸው አይደለም፡፡ የእነርሱ ችግር በአገራቸው ተዘዋውረው ለመስራት የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ የሌለ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የሆነ ደግሞ እነርሱ ባይሉትም እኛ የምናውቀው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት ይህንን ሊያሳካ ስለአልቻለ ነው፡፡ መፍትሄውም ታዲያ ዜጎች በሀገራቸው የስራ ዕድል ሊፈጥርላቸው የሚችል ርዕዮትና አስተሳሰብ ያለው መንግሰት መመስረት እንዲችሉ ማድረግ ሲችሉ ነው፡፡ የወላጆች ምክር ግን መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ ሃምሳና ስልሳ ከዚያም በላይ ወጭ አድርጎ ወደ ሞት ሀገር መሄድ ተገቢ አይደለም እዚሁ ሀገራችን ውስጥ መስራት ይሻላል ብለዋል፡፡ ይህንን ቃል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሣለኝም በፓርላማ ለኢትዮጵያ ህዝብ በይፋ ብለውታል፡፡ እባካችሁ እናንት ከፍተኛ የመንግስትና የሃይማኖት አባቶች በዚህን ያህል ገንዘብ ስደትን የሚያስንቅ ስራ በሀገራችን አለ ካላችሁ በድዕረ ገፅ ላይ ይፋ አድርጉትና ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲመክሩ ከነመፍትሔው ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ነገር ማለት ግን አይቻለም ወጣቶች ከስደት ቀርታችሁ ይህን ማድረግ የምትችሉት በጥቃቅን ተደራጅታችሁ ነፃነታችሁን ለኢህአዴግ ከገበራችሁ ነው ይህ የሚሆነው የሚል ቅድመ ሁኔታ ወጣቱ አይቀበልም፡፡ ነፃነትን የማይቀማ ፕሮፖዛል የግድ ይላል፡፡
ይህን በሀገር ውስጥ መስራት ይቻላል የሚባለውን የስራ ዓይነት ዝርዝር እና ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎች በኢቲቪ እና ሬዲዮ ማቅረብ አይቻላም፡፡ ምክንያቱም በእነርሱ ዕይታ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ሀገረ ገነት ነች፡፡ ዜጎችም ወደ ስደት የሚሄዱት በሀገር ውስጥ የተፈጠረን መልካም ዕድል ችላ በማለት እና በህገወጥ ደላሎች አሳሳችነት ነው፡፡ ይህን የሚዘግቡት ጋዜጠኞች ዕድል አግኝተው ውጭ ሀገር ከሄዱ ከማይመለሱት ውስጥ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ጋዜጠኞችን መጥራት ይቻላል፡፡
ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ የመንግሰት አቅጣጫ ብዬ የጠረጠርኩት ነገር በእርግጥ ቤተ ክርስቲያናችን አጀንዳ ማድረግ የሚገባት ጉዳይ እንደሆነ ጥርጥር የለኝም፡፡ ምሳሌም ሆና ልትመራው ይገባል፡፡ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ ሙስና ለዓይማኖት አባቶችና ለቤተክርስቲያን አገልጋዮች አይደለም ለምዕመንም ፀያፍ መሆኑን ማስተማር ተገቢ ነው፡፡ ሀገር ለቆ ለመሰደድ ሰዕለት እየገቡ ምዕመኑንም እልል በሉ ማለት መቆም ያለበት ይመስለኛል፡፡ ልጄን ስለቷን ሰምቷት ወደ ሀረብ ሀገር ስለሄደች መቶ ዶላር ልካለች፣ ሴቶች በእልልታ ወንዶች በጭብጨባ እግዘሐብኤርን አመስግኑ መባል መቆም ይኖርበታል፡፡ ሙስሊም ወንድሞቼ በረሞዳን ሰሞን ይህ አቅጣጫ እናንተ ሰፈር የለም እንዴ እስኪ ጀባ በሉን፡፡ መልካም የረሞዳን ፆም ይሁንላችሁ እላለሁ በዚሁ አጋጣሚ በድጋሚ፡፡

No comments:

Post a Comment