Tuesday, July 30, 2013

መቀሌ እየተንቀሳቀስች ነው ወጣቱ ዘረኝነት፣ መከፋፈል፣ የመብት ረገጣ በቃኝ እያለ ነዉ።

የሰላማዊ ሰልፍ «የአሸባሪዎች ተላላኪ ናችሁ። የመቀሌ ህዝብ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴ አይፈልግም» በማለት አንድነት ፓርቲን የሚመለከት በራሪ ወረቀት የመበተንም ሆነ የቅስቀሳ ስራ የሚያከናውን ሰው ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስዱ እየዛቱ ነዉ። ሆኖም በመቀሌ የሚገኙት የአንድነት አመራሮች ለሰላማዊ ሰልፉ ቅስቀሳ ለመጀመር ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ለአከባቢው ባለስልጣናት አሳውቀዋል፡፡
ባለስልጣናቱ ግን እንደተለመደው ሕገ መንግስቱን ማስከበር ሲገባቸው የዜጎች መብት ለማፈን እየሰሩ ናቸው። አቶ ጌታቸው ገ/ስላሴ የከንቲባ ጽ/ቤት ሀላፊ ፣አቶ ወልዳይ የተባሉና የመቀሌ ዞን የፀጥታ ኃላፊ፣ እንዲሁም «ከመቀሌ ወጣቶች ማህበር ተወከልኩ» ያሉ ግለሰብ፣ የአንድነት አመራሮቸን በመጥራት «መንግስት አጠቃላይ ግምገማ ላይ ስለሆነ የፀጥታ ኃይል እጥረት አለብን» በማለት «ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አትችሉም» ብለዋቸዋል፡፡ የአንድነት አመራሮችም «መልሳቸሁ ህግ የተከተለ አይደለም፤ እኛ ህገመንግስታዊ መብታችንን ጠይቀናል። በቂ መክንያት በመስጠትና አማራጭ ቀናት በማስቀመጥ በጽሁፍ ምላሽ ካልተሰጠን በቀር በምንም ሁኔታ ሰልፉን አናራዝምም» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

እንደሚታወቀው የደርግ ወታደራዊ አምባገነን ስርዓት እንዲገረሰስ የትግራይ ሕዝብ ትልቅ ሚና የተጫወተና እጅግ በጣም ትልቅ ዋጋ የከፈለ ነዉ። ነገር ግን ከመቼም ጊዜ በላይ፣ «የሕዝብ ብሶት የወለደን ነን። ለመብትህ ነዉ የምንታገለው» በሚሉ ነገር ግን በተግባር ከደርግ ባልተሻሉ ጥቂቶች እየደረሰበት ያለዉን ከፍተኛ ቀንበር እየከበደው ነዉ። ጥቂቶች ሃብታም ሲሆኑ፣ አባዛኛዉ የትግራይ ሕዝብ፣ እንደተቀረዉ ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ኑሮን ማሸነፍ አቅቶት እያቃሰተ ነዉ።

በባድመ ጦርነት ወቅት ከኤርትራ ተፈናቅለው በመቀሌ የሰፈሩ፣ በዚያ የቀበሌ ባለስልጣናት እያወቁ ቤቶች ሰርተዉ ሲኖሩ የነበሩና በአቶ አባይ ወልዱ ፣ የሕወሃት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ትእዛዝ ቤታቸው እንዲፈርስ የተደረጉ በሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን ማስታወሱ ይበቃል። ከአራት ሺሆች በላይ የሚሆኑ ቤቶች፣ የፍርድ ቤት ማዘዣ ሳይኖር፣ ነዋሪዎቹ ጉዳያቸውን አቤት የሚሉበትና የሚያስረዱበት እድል ሳይሰጥቸው፣ በጭካኔ እንዲፈርስ ተደርጓል።

ሕወሃት፣ የትግራይን ሕዝብ ከሌላዉ ሕዝብ፣ በዘር በመለየት፣ ከሕወሃት ዉጭ ሌላ አማራጮች እንዳያገኝ እየሰራ ነዉ። ከሕወሃት ዉጭ ያሉ ድርጅቶችን «ጠላት፣ አሸባሪ» የሚሉ ስያሜዎችን እየሰጠ ፣ ሕዝቡን ለማስፈራራት ቢሞክርም፣ የአንድነት ፓርቲ ግን ፣ እንዲሁም አረናዎች፣ እየታሰሩ፣ ወከባና እንግልት እየደረሰባቸው ለሕዝቡ አማራጭ እየሰጡት ነዉ። በአጼ ዮሐንስና በራስ አሉላ አባ ነጋ መንፈስ ሕዝቡን በኢትዮጵያዊነት ሥር እያሰባሰቡት ነዉ።
መቀሌ እንደ ጎንደርና ደሴም፣ ሐምሌ 28 ቀን ከባህር ዳር፣ ጂማና አርባ ምንጭ ጋር የሰላም የዲሞክራሲና የመብት ጥያቄን ለማንሳት እየተዘጋጀች ነዉ። በተለይም ወጣቱ ዘረኝነት፣ መከፋፈል፣ የመብት ረገጣ በቃኝ እያለ ነዉ።

No comments:

Post a Comment