Wednesday, July 31, 2013

ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞችና ኢትዮጵያዊ ክርስቲያኖች ግንኙነት ላይ ሊሰራ የታሰበው ሴራ ከየት የመጣ ነው?

ኢንጂነር ረዲ ዘለቀ


ዛሬ ስለአጋሮ ጮጬና ሊሙ ሻይ ትንሽ ልበላችሁ። ሊሙሻይ ማለት የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ የተማረበት ቦታ ስትሆን ይህ ጸሐፊ ተወልዶ ካደገበት ጋሌ ቡሳሴ 34 ኪሜ ያህል ትርቃለች። ጋሌ ተወልደው ያደጉ ልጆች ሁሉ ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ሌላ ቦታ መማር ካልፈለጉ በስተቀር የሚማሩት ሊሙ ሻይ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ /ርት ቤት ነው። ሊሙ ሻይ በመንግስት ቡና ተክል የጎማ አንድ የሚባለው ቦታ የሚገኝባት ሲሆን በተጨማሪ ከጥርኝ ዝባድ የሚያመርቱ ሰዎች ያሉባት ቦታ ነች። አሁን አሁን የጥርኝን ኢንቨስትመንት በርካታ ኢንቨስተሮች ላናውቀው እንችላለን። ይህንን ለማንሳትና ሊሙሻይንና የተወለድኩበትን አካባቢ እንድጎበኝ ያደረገኝ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ሙስሊምንና ክርስቲያንን የሚለያይ አንዳንድ አባባሎች ከሰማሁ በሁዋላ ነው። በነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል የሀይማኖትም ይሁን የዘር ልዩነት የለም። በእርግጥ አንዳንድ የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ጅማን የተለየ ችግር ያለባት ቦታ እንድትሆን ለማድረግ ሞክረዋል። ሆኖም የጅማ ህዝብ ፍቅር ነው። በልዩነት አያምንም። ይህንን ወደ ሁዋላ እመጣበታለሁ።በሊሙ ቡና ተክል የጎማ አንድ እርሻ ጣቢያ ቡና ለአካባቢው ህብረተስብ ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል። መቼም በርካታ የሀገራችን ከትሞች የሚያድጉት በከንቲቦች በኩል ስለሆነ የእነርሱ እድገት አይታየንም። ግልጽ ለማድረግ በተለያየ ቦታ የሚቀመጡ እና የተሾሙ ከንቲቦች ለራሳቸው እንጂ የተሾሙበትን ከተማ አያሳድጉም። የተሾሙበት ከተማ ማደጉን ለማወቅ ከተፈለገ የተሾመውን ከንቲባ የሰራውን የግል ቤት መቁጠር ይበቃል። ሊሙ ሻይ ከዛሬ ሀያ ሰባትና ሃያ ስድስት ዓመት በፊት እንደነበረች ነች ያለችው። አንድ ስንዝር ከፍ አላለችም። በቁመትም ይሁን በውፍረት የጨመረችው ነገር የለም። ይህ ጸሐፊ በሊሙ ሻይ በሚማርበት ጊዜ የነበሩት ነጫጭ ቆርቆሮዎች ግን ከሊሙ ሻይ አፈር ጋር ተመሳስለዋል። የውስጥ ለውስጥ መንገዱና የቆርቆሮዎቹ ቀለም የሚለዩት ቀና ብሎ ወደ ሰማይ በማየትና ቁልቁል ዝቅ ብሎ ወደ መሬት በማየት ብቻ ነው። በተረፈ በቀለም ሁለቱም አንድ አይነት አፈር ናቸው።

ከሊሙ ሻይ ሰደቻ፣ ጤሶ፣ ቂልጡ ወልቃ፣ በታች በቀኝ ከሔዱ ጮጬ በላይ በግራ ከሄዱ ሲምቢሮ፣ጌምቤ፣ ቡልቡሎ ብለው አሮጌዋ ከተማ አጋሮ ይገባሉ። ጌራና ሰንጠማ ወደዚያ አሉ። ለም አካባቢዎች ናቸው። በአንድ ወቅት ሰንጠማ አንድ ጉባኤ ነበር። በአጋጣሚ እኔም በዚህ አካባቢ ያለውን የሙስሊምና የክርስቲያን የፍቅር ግንኙነት ለማየት ሄጄ ነበር። ይገርማል በወቅቱ ጉባኤዉን ያዘጋጁት ኦርቶዶክሶች ነበሩ። እኔ በወቅቱ ያየሁትን ነው የምመሰክረው የነበረውን ጉባኤ ተቀምጦ በመማር ጭምር ያደመቁት ሙስሊሞች ነበሩ። በተለይ ከየ አካባቢው የመጡትን እንግዶች በመመገቡ ረገድ ሀላፊነት ተሸክመው የነበሩት ሙስሊሞች ስለነበሩ እኔ አንድ ሙስሊም ቤት ገብቼ እርጎ ጠጥቻለሁ። የጅማ አካባቢ ሙስሊምና ክርስቲያን ፍቅር ይህን ይመስላል። በሙስሊሞች በዓል ክርስቲያኖች ስላደረጉት ከጉዳዩ ጋር አያይዤ አቀርባለሁ። እንደነገርኩዋችሁ ለሽቶ መስሪያ የሚያገለግለው የጥርኝ ዝባድ የሚመረትባትና የሀገራችን የኢኮኖሚ ዋልታ የሆነው ቡና አብዛኛው ምርት የሚገኝባት ሊሙ ሻይ የመጀመሪያው ቡና ተገኝቶባታል የምትባለውና እንዲሁም በአሁኑ ስዓት የጂን ባንክ የሚገኝባት ጮጬን አቁዋርጦ የሚሄደው መንገድ እንኩዋን በክረምት በበጋም አስችጋሪ ነው። በእርግጥ መንገድን በተመለከተ በበርካታ ቦታዎች ላይ የዘነበ ቢሆንም ለነዚህ ከተሞች አለማካፋቱ ያሳዝናል። 

ከጅማ አጋሮ የሚሄደውን አስፓልት ተብየ መንገድ በጮጬ በኩል ቡልቡሎ በላይኛው በኩል ጌምቤ ላይ ቢያገኙትም ያው ጭቃና አቡዋራ ስለሌለው ነው እንጂ ከፒስታ አይሻልም። አጋሮ ይህ ጸሐፊ ተማሪ በነበረበት ጊዜ ግሩም የነበረች ከተማ ነበረች። ጅፍምቤ በሚባለው መናፈሻ ውስጥ የፈረንጅ አይጥ የሚባሉ ከድመት ዝቅ የሚሉ ከፍልፈል ከፍ የሚሉ በመናፈሻው ውስጥ ይረቡ የነበረ ሲሆን ያን ጊዜ በርካታ ሰዎች በመናፈሻው ውስጥ ያሉትን ትላልቅ አይጦች በማየት ይዝናና ነበር። በዚያን ጊዜ የመዝናኛ ከተማ የነበረችው አጋሮ ዛሬ ላይ በጣም ታሳዝናለች። የአሮጌ ከተማ ምሳሌ የመሆን ዕድልም የላት ቆርቆሮዎቹ አርጅተው አፈር ይመስላሉ። በርካታ ቤቶች ፈራርሰው ከተማዋን ፍርስራሽ ከተማ ሊያደርጉዋት አንድ ሀሙስ ነው የቀራቸው። የነዚህ አካባቢ ወጣት ነቃ ያለ ነበር። በዚያን ግዜ የነበረው የኩዋስ ፍቅር አሁን ላይ ቢኖርም ከዚያ አካባቢ ያሉ ተጫዋቾችን የመምረጡና የማሳደጉ ሂደት ስላልነበረ በርካቶች ባሉበት ቀርተዋል። ትዝ ይለኛል ሊሙሻይ ከጌንቤ፣አጋሮ ከጮጬ፣ ጌምቤ ከቡልቡሎ ሲጫወቱ የአጋሮ ልጆች የእግር ኩዋስ ጫወታ በእውነቱ ከሆነ ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጫወታ ጋር ይመሳሰል ነበር።

ከተሞች ከከተሞች ሲጫወቱ ገንዝብ ያለው በጭነት መኪና ገንዘብ የሌለውና የወዛደር ልጅ የነበረው በእርሻ ልማቱ ትራክተር ሁለቱም የሌለን እኛ የባላገር ልጆች ደግሞ በእግራችን በሩጫ የሶስት ሰዓት መንገድ ከትራክተር ጋር እየተሽቀዳደምን ሄደን ቡድናችንን እንደግፍ ነበር። በወቅቱ የማራዶና አይነት አቁዋም የነበረውና አጨዋውቱ ግሩም የነበረው አንበሱ ቶላ ዛሬ ትልቅ ሰውና የልጆች አባት ሆኖአል። ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ስለፔሌ የቴስታ ቁርጥ አመታት ሲናገሩ ልጅ ሆኜ እሰማ ነበር ያን ጊዜ የተመቻቸ ሁኔታ በነበረ ኖሮ እኔም ስለ አጋሮ ጌንቤ ጮጨና የሊሙሻይ ልጆች የቴስታ ቁርጥ መቻል በተናገርኩና ደስ ባለኝ ነበር። ነገር ግን ገበያና ድሀ ሳይገናኝ ሞተ እንደተባለው ሆነ እንጂ። ያው አውሬው ሲግኝ ድንጋዩ አይገኝ ነውና፤

ከላይ የጠቀስኩዋቸው ቦታዎች የነበሩ ወጣት የእግር ኩዋስ ተጫዋቾች ምንም ያህል ጎበዝ ቢሆኑም ያሉበት ቦታ ከአዲስ አበባ ርቀቱና ያን ጊዜ መራጮችም ተመራጮችም ከአዲስ አበባ ስለነበሩ ችሎታቸውን ለአካባቢው ሰዎች ከማሳየትና ሌሎችን አድናቂ ከመሆን አልዘለሉም። በእርግጥ አሁንም ቢሆን ምርጫው በችሎታ ብቻ ነው በሚለው ላይ ጥያቄ እንደሚኖር እሙን ነው። የዚህ አካባቢ ሰዎች ትዕግስተኞች እንግዳ ተቀባዮች ሲሆኑ ወጣቶቹ መልከ መልካምና ቆንጆዎች ናቸው። የኦሮሞን የዋህነት ለማየት ወደነዚህ አካባቢ መሄድ በቂ ነው። ማንኛውንም መንገደኛ አሳርፎ ቡና አጠጥቶ መሸኘት የተለመደ ነው። በገጠር አካባቢ የሚያዩዋቸው ሰዎች አርንጉዋዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ወይም ቡራቡሬ ቀሚስ ለብሰው ደማቅ ቀለም ያለው ጀንጥላቸውን ይዘው ሲሄዱ ወደ ሁዋላ ከሚያስሩት ባለቀልም ሻሽ ጋር የሚሰጣቸው ውበት እንዴት እንደሚያምር በወረቀት መግለጽ አይቻልም። ስዕል ችሎታ በነበረኝ ኖሮ የጅማ ልጆችን ቁንጅና ሩህሩህ ፊት በስዕል ባስቀመጥኩዋቸው ኖሮ እንዴት ደስ ባለኝነበር። 

በእርግጥ አንድ አስገራሚ ነገር ገጥሞኛል አብረን ተምረን በአንድ ወቅት ወደ መምህርነት የሥራ መስክ ገብተን የነበረ ጉዋደኛየን አግኝቸው ልጆች በመውለዱ ተደስቼ ልጆቹን ተዋወቅሁ። ልጆቹ ከእኔ ጋር እንጂ ከልጆቼ ጋር መግባባት አይችሉም። የሚችሉት ቋነቋ ኦሮምኛ ብቻ ነው። አባታቸው የኔ ጉዋደኛ ደግሞ ያለ አማርኛ አይችልም። ይገርማል መጪው የሀገራችን ችግር ቀጣዩ ትውልድ በቋነቋ መግባባት አለመቻል ነው።በተጨማሪ መጪውን ትውልድ የሚያግባባ ቋነቋ እየጠፋ መሔድ ነው። ይህንን ችግር በትግራይ፣ በአብዛኛው ኦሮሚያ፣ በአፋር፣ በሶማሊያና በደቡብ ክልል አይቼዋለሁ። ቀጣዩ የሀግራችን ችግር እንደ ባቢሎናውያን የቋነቋ መደበላለቅ ይሆናል። በትግራይም ይሁን በኦሮሚያ፣ በሱማሌም ይሁን በተለያዩ አካባቢዎች 10 ክፍል ተማሪዎች በአንድ ቋነቋ መግባባት እንደሚያስቸግራቸው ተገንዝቤያለሁ። ወደፊት የምንፈጥራት ኢትዮጵያ የመግባቢያ ቋነቋ ችግር ይገጥማታል የሚል ስጋት አለኝ። ሊታሰብበት ግን ይገባል። ሁሉም ብሔር ቋንቋውን ማሳደጉ እንዳለ ሆኖ ሁሉምን ሊያግባባ የሚችል ሁለትም ይሁን ሶስት ብሔራዊ ቋነቋ ግን ያስፈልገናል።

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞችም ይሁኑ ፖለቲከኞች ሊያሸንፉ ስለሚችሉበት ስልት እንጂ ካሸነፉ በኋላ ስለሚምጣው ችግር ደንታ ሳይሰጡት ቆይተው የፈለጉትን ስልጣን በዚያም በዚህም ብለው ይቀበላሉ። ነገር ግን ከስልጣን በኋላ ሊመጣ የሚችለውን አስችጋሪ ሁኔታ አይገነዝቡትም። ባለፈው ሳምንት ስለልማታዊ መንገስት በጻፍኩት ጽሁፍ ኢህአዴግ መጀመሪያ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር በወቅቱ የነበረው የሀገሪቱ የማስተዳደር ዕድልና የፖለቲካ ትርፍ ሊያስገኝለት የሚችለው የብሔር ፖለቲካ ስለነበር ይህንኑ አጀንዳ በመያዝ ሀገሪቱን በብሔር ከፋፍሎ ለበርካታ ዓመታት ሊገዛ ችሎአል። ሆኖም የያዘው ዓላማ ብዙም ርቀት እንደማያስኬደው የተረዳው ገዢው ፓርቲ በቀጥታ ወደልማታዊ መንግሥትነት ራሱን የለወጠ ሲሆን አሁን እያደረገ ያለውን ሥራ ሊሰራ ሞክሮአል። ሆኖም በእርጥብነቱ ያልታረቀ እንጨት ከደረቀ በሁዋላ ለማስተካከል መሞከር ውጤቱ መለመጥ ሳይሆን መሰበር ነው። የዚህ የልማታዊ መንግስት ጉዞ ጸሐፊና ከሊፋ አሁን በህይወት ያለመኖር ጉዞውን ከባድና ውስብስብ ያደርገዋል የሚል ግምት አለኝ።

ኢህአዴግ ልክ እንደማንኛውም የአፍሪካ መሪዎች ሁሉ የተከተለው የብሔር ፖለቲካ በኋላ በሀገሪቱ ላይ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ያለመረዳት ችግር ነበረበት። በእርግጥ በወቅቱ ገዥው ፓርቲ አካሄዱ በሀገሪቱ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር ያለመረዳት አይደለም። ሀገሪቱን ለመምራት ካለው ፍላጎትና የማስተዳደር ጉጉት ሲሆን እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚለው ብሂልም ጭምር ነው። ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ ዛሬ ኢህአዴግ በቀደደው የከፋፍለህ ግዛ ስልት በርካቶች እኛን ለመበታተን ሊጠቅሙበት እየሞከሩ ነው። በእርግጥ ማንም ባለው ነጻ አመለከከት የፈለገውን ሀሳብ ማንሸራሸር መብቱ ነው። ህዝብን የሚከፋፍልና የወንድማማችነትን ፍቅር የሚሸረሽር ሀገርን በቅኝ ገዥዎች ፈቃድ የሚበታትን ግን ሊሆን አይገባም።

የሌላ ሀገር ፖለቲከኞች በሀገራችን ያለውን የብሔርና የሀይማኖት ሁኔታ ለመተንተን ሲሞክሩ እኛ አንድ ጎኑን ብቻ ስናይ እነርሱ ግን ለሚሰጡዋት እያንዳንዱዋ ትችት የራሳቸው ምክንያት ይኖራቸዋል። ለበርካታ የዓለም ህዝብ ትልቁ ጥያቄ የሀገራችን የኢትዮጵያ ህዝብ በሀይማኖት፣ በቋንቋ ተለየይቶ የህዝቡ ተፋቅሮ መኖር በራሱ ትልቅ እንቆቅልሽ ነው። ቅኝ ገዥዎች አንድን ሀገር ቅኝ ሲገዙ የመጀመሪየ ሥራቸው ህዝቡ በብሔር የተከፋፈለ ከሆነ አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር ላይ በደል እንዲያደርስ መገፋፋት አንዱ ዘዴ ሲሆን ሌላው በማይመለከታቸው ነገር አንዱ አንዱን እንደበደለ ማድረግና አንዱ እንደተበደይ ራሱን እንዲቆጥር ማድረግ ናቸው፡፡ ተብድለሃል ያሉትን በዳዩን እንዲበቀል ሰላም እንዳይሰጠው በማድረግ ሀገሪቱ ሰላም እንድታጣ ማድረግ አንዱ ተግባራቸው ነው። ለምሳሌ በሰሜን ያሉ ሁለት ወንድማማች ትግሬዎችን ሲለያዩ ሀማሴን ትግሬ ከሌላው ትግሬ የተለየና የበለጣችሁ ናቸው እያሉ ይነግሩአችው ስለነበረ ከትግራይ ወንድሞቻቸው እንደሚበልጡ እንዲያስቡ አደረጉዋቸው፡፡ በአብዛኛው አንድ ቋንቋና በአብዛኛው አንድ ሀይማኖት ያላቸውን ህዝብ ለያዩት ይህ አንዱ ስልታቸው ነው። እነዚህ ቅኝ ገዥዎች በተለይ አፍሪካን በብሔርም ደረጃም ቢሆን እርሱ ከአንተ በታች ስለሆነ አንተ የበለይ ነህ የበላይነትህን አስጠብቅ በማለት ይሰብካሉ።

ቅኝ ገዥዎች እንደሱማሌ ያሉ በቋንቋም በሀይማኖትም አንድ የሆነውን ህዝብ አንዱን ጎሳ ከአንዱ ጎሳ የበለጠ ነው፡፡ በማለት ሲለያዩ ቀሪዎቹን የሲጃራ ሱሰኛ በማድረግ ቅኝ የመግዛት ዓላማቸውን ሲያሳኩ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን በሱማልያ እስከሁን የሲጋራ ዋጋ ርካሽ ነው። በሮፓ አንድ ዘለላ ሲጋራ የማይገዛው ባሱማሊያ አንድ ዳርዘን ይገዛል፡፡ የዚህ በሱማሊያ የሲጋራ መርከስ ዓላማ ቅኝ ገዥዎች የሱማሌ ህዝብ ሲጋራን በርካሽ አግኝቶ በመጠቀም ከሱሰኝነት እንዳይወጡ ለማድረግ ነው። በሌላ በኩል አንዱን ጎሳ የሌላው ጎሳ የበላይ አድርገው የገነቡት ግንብ በሱማሌዎች ዘንድ ዘመን ሊሽረው አልቻለም። 

በዚህም አንዲት ታላቅ ሀገር የነበረች ሀገር በውስጥ ፖለቲካዋ ዳግም ማገገም እንዳትችል አድርገው ሲሰሩዋት ከጎረቤት ሀገር ጋር መልካም ግኑኝነት እንዳይኖራት ከኢትዮጵያ ከሁለት አምስተኛው ያህል ያላነሰውን መሬት የእነርሱ እንደሆነ በማስተማር ገነቡአቸው። ሱማሌዎችም ባላቸውና ለም በሆነው ሰፊ መሬት ተጠቅመው ሀገራቸውን ከማሳደግ ይልቅ ቅኝ ገዥዎች በነገሩዋቸው የተንኮል ትምህርት እንደ እውነት በመቁጠር የሚወለዱ ህጻናት ልጆቻቸውን በኢትዮጵያ በርካታ መሬት አላችሁ እያሉ አሳደጉዋቸው። ልጆቻቸውም በኢትዮጵያ ስላለ መሬታቸው እየነገሩ ስለሚያሳድጉአቸው ልጆቻቸው ባሉበት በሶማሊያ ያላቸውን መሬት ተጠቅመው ሀገራቸውን ከማሳደግ ይልቅ በኢትዮጵያ ስለሌላቸው መሬት በቅዠት ሲባክኑ ይስተዋላል። በዚህም ሱማሌያውያንን በውስጥ በጎሳ በውጭ ከጎረቤት ሀገር የማይሆን ተስፋ በመስጠት በታተኗት።

ቅኝ ገዥዎች በአፍሪካ ስላሉት ጎሳዎች፣ ብሔሮች፣ሀይማኖቶች ገዶአቸው የሚያደርጉት ነገር የለም።ነገር ግን አፍሪካ ለእነርሱ የመኖርና ያለምኖር የህልውና ጉዳይ ነች። ስለዚህ አፍሪካውያን ስለሀገራቸው ዕድገት ከመስራት ይልቅ እርስ በርስ እየተነታረኩ እየተላለቁ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ያደርጋሉ። እነርሱ ጸቡንና ጭቅጭቁን ቀስቅሰው መልሰው ሽማግሌ በመሆን መልሰው እርቁ ዘላለማዊ እንዳይሆን በገደብ ያደርጉታል። በዚህም ያስቀመጡትን ካርድ ሰዓት እየጠበቁ በመምዘዝ ያባሉአቸዋል። ትክክለኛ አፍሪካውያን አፍሪካ ብለው ከተነሱ በአንድም ወይም በሌላ ከምድረ ገጽ ያጠፉአቸዋል። እንደ ሳሞራ ማሽል ያሉ አፍሪካውያን ዛሬ የሉም። አፍሪካውን በአፍሪካ ረዘም ያለ ጊዜ ለመኖር ለዘብተኛ መሆን አለያም በሚሆነው ሁሉ ለቅኝ ገዥዎች ማደር ግድ እየሆነ መጥቶአል። በሀገራችን በብሔርና በእምነት ጉዳዮች ሲመጡ ነገሮችን በመጡበት መንገድ ከመሄድ ይልቅ አመጣጣቸውን ማየት ተገቢ ነው። ቅኝ ገዥዎች በአድዋ ድል ምክንያት ከአፍሪካ መውጣታቸውን የሚረሱ ጅሎች አይደሉም።

የአፍሪካ ሀገር መሪዎች ህዝባቸውን ሲመሩ ለህዝባቸው አይመቹም በእርግጥ ለምን ሁሉም የአፍሪካ መሪዎች ለሚያስተደድሩት ህዝብ ምቹ እንደማይሆን ፈጽሞ ግልጽ አይደለም። በእርግጥ የበርካቶች የእፍሪካ መሪዎች አማካሪዎች ምዕራብያውያን ናቸው። እነዚህ ምዕራባዊያን በሚገርም ሁኔታ የአፍሪካ ሀገራትን ተቃዋሚዎችን በአንድ በኩል ሲደግፉ በአንጻሩ ደግሞ መንግሥትንም ማማከራቸው በራሱ ለአፍሪካ ያላቸውን ትኩረት ያሳያል። ቅኝ ገዥዎች በነበሩባቸው የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ ይገነቡት የነበረው መንገድ ከማዕድን መቆፈሪያ ቦታ ማዕድኑን እስከ ወደብ ማጓጓዣ ሲሆን ለአፍሪካውያን ይሰጡ የነበሩት ትምህርት ደግሞ ቲዎሎጂ ነበር። ለዚህም ምሳሌ ታንዛኒያ ነጻ በወጠችበት ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ የቲዎሎጂ ማስትሬት የነበራቸው ምሁራን ሲኖሩ እንድ ኢንጂነር ግን አልነበራትም። 

ይህ የሚያሳየው ህዝቡን ለነጮች እንዲገዙ የሚያባብሉ ቀሳውስትን እንጂ ሀግሪቱን የሚያሳድጉ መሐንዲሶች እንዲኖሩ አለመፈለጋቸውን ያሳያል። በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ምክንያቶች በትግል መሪዎቻቸውን ያስወገዱ የአፍሪካ መሪዎች ከጥያቄዎቻቸው መልሶች በኋላ ሊረጋጉ አልቻሉም። እንደምሳሌ ሊቢያንና ግብጽን መመልከት ይቻላል። አፍሪካውያን በጎሳና በብሔር መጣላት መቼ አቁመው ከነዚህ ከተረግሙ የምዕራባውያን ይገላገሉ ይሆን ለሚለው ጥያቄ መልሱ በዚህ ጸሐፊ እይታ ትንሽ አስቸጋሪ ይመስላል። በየትኛውም የሂሳብ ስሌት ምዕራብያውያን የሀገራችን፣አማሮች፣ደቡቦች፣ትግሬዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ጉዳይ አሰስቦአቸው ይጨነቃሉ ማለት ዘበት ነው። በዓለማችን የዴሞክራሲ ሀገር ነች በምትባለው አሜሪከ በዓለማችን እጅግ አስቀቂው እስር ቤት ጉዋንታናሞ ይገኝባታል። ነገር ግን በሌሎች ሀገራት በተለይ በአፍሪካ ሀገራት ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ያስጨንቀኛል ስትል ደግሞ ይታያል።

አሁን በሀገራችን እየታየ ያለው ሁኔታ በእርግጥ አሳሳቢ ነው። በተለይ በዲያስፖራው አካበቢ ያለው የመቃወም ሁኔታ ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ያገናዘበ አይመስለኝም። በአንድ ወቅት በካናዳ ሀገር ከሚገኝ ፓል ቶክ አዘጋጆች ጋር የመወያየት ዕድሉን አግኝቼ ለመነጋገር ሞክሬ ነበር። በእርግጥ ቃለ ምልልስ የሀገሪቱን ሁኔታ ያላገናዘቡ ተቃዋሚዎች መኖራቸውን ያየሁበት ዕድል ነበር ማለት ይቻላል። በሁኔታው አንዳንድ ኢትዮጵያውያን በብሔር አመለካከት ጫፍና ጫፍ ላይ መቆማቸውን ለማየት ዕድል ሆኖኛል። በዚህ ወቅት ከኢንተርናሽናል ላይቭ ስቶክ የግሪን ሀውስ ግንባታ ጨረታ አሸንፌ በትግራይ ክልል በመቀሌና በአጽቢ ሥራ እንሰራ ስለነበረ የትግራይን ሁኔታ ጊዜ አግኝቼ ለማየት ሞክሬ ስለነበረ ጥሩ ግንዛቤ የጨበጥኩበት ወቅት ነበር። በወቅቱ እኔ በትግራይ ያየሁት ሁኔታ በርካታ ልጆች 10 ክፍል ዉጤት ስላልመጠላቸው በትግራይ በተለይ በመቀሌ ጎዳናዎች ብዙ ወጣቶች በየመንገዱ ቆመው ሥራ ሲፈልጉና ሲንከራተቱ ያይሁበት ወቅት ነበር። በዚህ ወቅት እኔ እንዳየሁት በትግራይ ክልል እንኳን 10 ክፍል ትምህርት ይቅርና ከዩኒቨርስቲም ወጥተው ሥራ ያላገኙ በርካታ ወጣቶች ነበሩ። እኔ በተደጋጋሚ ጎዴ ለተልያዬ ስራ ሄጄ ስለነበረ በሱማሊያ ክልል በጣም ቦርደርና በረሃ ቦታዎች በአስተማሪነት ተቀጥረው የሚሰሩ አብዛኛዎቹ እንደውም ሁሉም ማለት በሚቻልበት ሁኔታ በዚህ አካባቢ የትግራይ ልጆች በአስተማሪነት ተቀጥረው እንደሚሰሩ አውቅ ነበር። እውነቱን ለመናገር ከባህር ጠለል በላይ 270 ብቻ በሆነ በረሃ ሄዶ ለመቀጠር ትግሬ መሆናቸው ረድቷቸዋል ማለት አይቻልም። በዚህ ከፍተኛ ሙቀት ባለበት በረሃ ለመቀጠር ያስገደዳቸው በተወለዱበት ክልል ያለው የሥራ ማጣት ችግርነው። በዚያ አካባቢ ያሉ ወጣቶች በስራ ማጣት እየሆነ ያለውን ሁሉ ለመጻፍ አንዳንዱን የወጣቶቹን መልካም ፈቃድ መጠየቅ ያስፈልጋል። ምክንያቱም አንዳንድ ያይሁዋቸው ነገሮች ዘግናኝ በመሆናቸው።

ሆኖም ከላይ እንደነገርኩዋችሁ ሚዲያ ፓል ቶክ ቀርቤ አንዳንድ ጥያቄዎችን እንደሚጠይቁኝ ተነጋግረን ለፓል ቶኩ እንደቀረብኩ ከተወሰኑ ጥያቄዎች በሁዋላ የተጠየቅሁት ጥያቄ አስገራሚ ነበር። የመጀመሪያያው ጥያቄ የህውሃት የበላይነት ነግሶአል ይላል። ይህ በወቅቱ የሚታወቅም ስለነበረ ችግር ያለው ጥያቄ ነው የሚል እምነት ስላልነበረኝ ተግባባን። ቀጠዩ ጥያቄ የህውሃት የበላይነት ስለነገሰ አማራውና ሌላው ህዝብ እየተጭቆነ ነው ይላል። አስረጂኝ ስላት ለምሳሌ ብላ ያነሳችው በትግራይ ትምህርቱ እስከ 12 ክፍል የሚሰጥ ሲሆን የሌላው ክልል ግን 10 ክፍል ላይ እንዲቆም መደረጉ እያበሳጫቸው እንደሆነ ገለጠችልኝ። እውነት ለመነጋገር ይህንን አይነት የተበላሸ ኢፎርሜሽን የሰጣት ኢትዮጵያጵያዊ ሊሆን እንዳማይችል ግንዘቤ የያዝኩ ይመስለኛል፡፡ በአብዛኛው አማራው እንደተበደለ ነግራኛለች። በሀገራችን ደግሞ በርካቶች የሚሉት አማራ ጨቋኝ እንደነበረ ነው። እኔ የተባለው ነገር ስህተት እንደሆነ በተለይ ህውሃት ለትግራይ ህዝብ ጠብ ያለ ሥራ እንዳልሰራ ለማስረዳት ሞክሬ በተለይ በመቀሌ ከሲሚንቶ ዋጋ ይልቅ ዉሃ እንደሚወደድ የማውቀውን ለመናገር ብሞክርም እኔ ያየሁትን ስነግራት ከማመን ይልቅ ለተናገርኩት እውነት ማስተባበያ ትሰጥ ነበር። እንግዲህ በኢትዮጵያ ሁሉም ጨቁዋኝ ሁሉም ተጭቁዋኝ ከሆነና አንዱ ባንዱላይ ጥርስ ከነከሰ ይህቺ ሀገር ምን ይሻላታል ለሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ለዚህ ጸሐፊ ፈተና ነው። ባሚቃጥላው ካሚዲያው ጋር የነበረንን ቆይታ በጥልቀት አቀረውባለሁ፡፡

በተለይ ዲያስፖራው ለሚቃወምባቸው ነገሮች ሁሉ አጣርቶ ቢሆን መልካም ነው። ገዥዎች በገዥነታቸው ለመቀጠል የህዝቡን አንድነት መለያየት ይፈልጉታል። እኛ ደግሞ በመለያየት ፈጥነን እናግዘቸዋለን። በዚህም የገዥዎችን ዕድሜ እናራዝማለን። ለራሱ የሚለያይ ደግሞ ጽንቶ መቆም አይችልም። እኛ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊ ወንድም እንጂ ጠላት የለንም። በተለይ ተተኪው ትውልድ ከዚህቀደም አባቶቻችን በጥላቻ የሄዱበት መንገድ ካለ ልንከተለው አይገበም። ፍቅር ሁሉን ያሸንፋል። በአሁኑ ሰዓት በሀይማኖትና በብሔር ለመከፋፈል እየተሄደ ያለው ነገር አስቸጋሪ ይመስላል። እኔ በማውቀውና በሀገራችን ባሉት ሁኔታዎች ሁሉ ህዝቡ ከመሪዎቹ የተሻለ አመለካከት አለው። በሀይማኖትም ይሁን በብሔር ሳይለያይ እንደነበረ ይታውቃል። ከላይ የጅማ ዞንን ሁኔታ ለመጥቀስ የሞከርኩት በአንድ ወቅት የአካባቢውን ሁኔታ ጥላሽት ለመቀባት በአንድ ወቅት ባጂማ የተፈጸመው በጥቂትና ከየትኛውም አካል ይሁን በቅጥረኝነት መንፈስ የፈጸሙተ ወነጃል እንጂ የጅማ ሙስሊም ወንድሙ እንኩዋን ሲሞት ሲታመም ማየትም ይሁን መስማት አይፈልግም። በጅማ በተለይ በገጠር አካባቢ መውሊድ ሲደረግ ክርስቲያኑ በሬ አዋጥቶ ይሰጣል። ሙስሊሙም መውሊድ ሲያወጣ ለክርስቲያኑ በሬ ያርዳል። ሁለቱም በሙስሊሙም ይሁን በክርስቲያኑ በዓል በደስታ ያሳልፋሉ። በጅማ ያለው ሁኔታ ይህንን ይመስላል።

ሆኖም አንድ የፖለቲካ ተንታኝ በአንድ ቦታ ላይ ስለ ሰላማዊ ትግል ለሙስሊሞች ባስተማሩበት ጊዜ እርሳቸው ባደጉበት ቦታ የክርስቲያን ሀይማኖት ተከታዮች ጥቂት እንደሆኑ እነርሱም ቢሆን አንገታቸውን ደፍተው የመሔድ ግዴታ እንዳለባቸው ባይሆን ግን ከፍተኛ ቅጣት እንደሚወሰድባቸው ሲያስተምሩ፤ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ አንገቱን ደፍቶ ለመሄድ እንደሚገደድ ይህ ባይሆን ግንአንገቱን በሜንጫ እንደሚባል በምሳሌ ሲያስተምሩ ነበር። በእርግጥ የቅኝ ገዥዎች መምጫ አይታወቅም። ሀገራችን ኢትዮጵያ ልታድግ ትችላለች የሚል ስጋት ሊኖርባቸው ይችል ይሆናል። በዚህም አንድ ድንጋይ ፈልገው በዚያ ድንጋይ እርስ በርሳችን አየተወራወርን የተወሰነ ዓመት ወደኋላ እንድንሄድላቸው ይፈልጋሉ። ከኢዲሞከራቱ ኢሀአዴግም ነጻ የምንወጣው በመለያየት አይደለም፡፡

ቅኝ ገዢዎች በተለያየ ሁኔታ ወደኋዋላ እንድንሄድ የሚፈልጉበት ዋናው ምክንያት አፍሪካ ራስዋን የምትችል ከሆነ የሪሶርስ ችግር ስለሚገጥማቸው እንዲሁም የፋብሪካ ውጤታቸውን የሚያራግፉበት ቦታም ጭምር ማግኘት እንደማይችሉ ስለሚያውቁ በተቻለ መጠን አፍሪካ ላይ ከፍተኛ ሥራ ይሰራሉ። በእርግጥ ይህንን እኔ ለኒያ የተከበሩ የፖለቲካ ተንታኝ ማስረዳት ለቀባሪ እንደማስረዳት ወይም ልጅ ለእናትዋ ምጥ እንደማስተማር ይቆጠራል። ሆኖም ግን አሁን እርሳቸው። የያዙት አቋም ቀባሪ አያደርጋቸውም። እርሳቸው ከኔ የተሻለ ስለ መብት ያውቃሉ። ማንም ሰው የፈለገውን አመለካከት የመያዝ መብት ደግሞ አለው። በዚህ መብቱም ተጠቅሞ የወደደውን የመደገፍ የጠላውን የመንቀፍና የመቃወም ማለት ነው። 

በዚህም ዴሞክራት የሚባለው ዓለም _ዴሞክራት ከሚባለው ዓለም የሚለየው የአስተሳሰብ ነጻነት ላይ ነው። ሰው ሰው በምሆኑ ብቻ የተሰጠው ሰብአዊ መብቶች አሉት ከነዚህ ውስጥ ደግሞ እንዱ የመኖር መብት ነው።እርሳቸው በያዙት አመለካከት ደግሞ የአንድን ሰው በህይወት የመኖር መብት የሚወሰነው የአካባቢው ሰዎች የሚከተሉትን ሀይማኖት መከተል አለመከተል ላይ ነው። ይህ አይነቱ አስተሳሰብ ደግሞ እንኩዋን እኔና ተናጋሪው ለራሳቸው ትክክልኛ አመለካከት ነው ብለው ያምናሉ የሚል እምነት የለኝም።

ሀገራችን ኢትዮጵያ እስልምናንም በዚህደረጃ ለማድረስ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለች ሀገር ስትሆን እስልምናና እና ክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች ተቻችለው በመኖርም ቢሆን በዓለም ምሳሌ ናቸው። በአንድ ውቅት ሙስሊም የሆነ መሪ ወይም ክርስቲያን የነበረ መሪ በሙስሊሙም ላይ ወይም በክርስቲያኑ ላይ ያደረሰው በደል ካል በወቅቱ የነበረውን ግለስብ እንጂ የኢትዮጵያን ሙስሊሞችም ይሁን ክርስቲያኖች አይወክልም። ልክ ዛሬ የአንዳንድ ሰዎችአመለካከት የኢትዮጵያን ሙስሊሞችም ይሁን ክርስቲያኖችንን እንደማይወክለው ማለት ነው። ኢትዮጵያ ሀገራችን በህዝቡዋ መካከል በሀይማኖት ልዩነት የለም። አንዱ የአንዱን ሀይማኖት አክብሮ በመኖር ብቻ ይታወቃሉ። የሙስሊሙን በዓል የሚያደምቀው ክርስቲያኑ ሲሆን የክርስቲያን ወንድሙን በዓልም ሙስሊሙ ያደምቅለታል። 

አንድ ግብጻዊ ዶክተር ረጂብ መሐመድ ጥናታዊ ጽሁፍ በአብደላ መሐመድ ተተርጉሞ በዶ/ ኪሮስ መኮንን የታተመውየዘይላን ሙስሊሞች ታሪክ መሰል የጻፉ ግለሰብ ጽሁፉ በእውነቱ ከሆነ ከደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ጋር ይመሳሰላል። ደራሲ ተስፋየ ገብረአብ የጉዞ ማስታውሻዎችንና አንዳንድ ጽሁፎችን በምጻፍ ይታወቃል።ተወልዶ ላላደገባት ኤርትራ ግን የተሻለ ፍቅር እንዳለው ግን ስረዎቹ ሁሉ ያሳብቁበታል። ቢሾፍቱን እንደሚወድ ሁልጊዜ ሲወተውት ይሰማል። ነገር ግን ተወልዶ ያላደገባትን ኤርትራ ሀግሩዋንም ይሁን ባለስልጣናቱን ሲተች አይሰማም። ለነገሩ የቡርቃ ዝምታ ዋና መልዕክትስ በኢትዮጵያ የማይጠፋ እሳት ለመለኮስ አልነበር?

የቡርቃ ዝምታ መጽሐፍ ምስጢር እኛው እርስ በራሳችን እንድንጫረስ የተጠነሰሰ ሴራ ነበር ማለት ይቻላል። ህዝቡ ኢትዮጵያዊ ሀገሪቱም ኢትዮጵያ ሆና ሊሳካ አልቻለም እንጂ፤ ይህንን ለማለት ያበቃኝ ግብጻዊው ዶክተር በመጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በኢትዮጵያ ክርስቲያኖች መበደላቸውን ያውሳሉ። ከእስገራሚ አስተያይታቸው ውስጥ አንዱ ህበሾች ከሌላ ሀይማኖት ጋርተስማምተውና ተቻችለው የመኖር ችግር አለባቸው ይላል። ይህ እንግዲህ መርዝን ለመርጨት ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የመነጨ አስተሳስብ እንጂ በህይማኖት ያለመቻቻል ችግር በግብጽ እንጂ በኢትይጵያ የለም።

አሁን ባለንበት የሀያኛው ክፍለ ዘመን በግብጽ ያሉ ክርስቲያኖች በሐይማኖት አመለካከታቸው ብቻ በዙሪያቸው ካሉ አክራሪ ሙስሊም ወንድሞቻቸው በርካታ ችግር እየደረሰባቸው ነው። ዶክተሩ በጽሁፋቸው ጥናት ማድረግ የፈለጉት ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉት ሙስሊሞች ችግር ነው። መጻፍ የፈለጉትም ቢሆን በዘይላ የነበሩት ሙስሊሞች ስቃይ ተረድተው አይደለም። እንዲሁም የራሳቸው እያረረባቸው የእኛን ማማሰል ፈልገውም አይደለም። ሁኔታው ታስቦበትበፖለቲካ ሂሳብቅመራ ተሰልቶ የተሰራ ነው።የግብፅ ምሁራን ኢትዮጵያን በመበታተን ግብጽ የተሻለች ሀግር እንድትሆን ይፈልጋሉ። ሆኖም ይህ አመለካከታቸው ለቅኝ ገዥዎች እንጂ ለአፍሪካውያን አይጠቅመንም። ለግብጽ ዕድገት የሚጠቅመው የኢትዮጵያ ማደግ ነው።

ኢትዮጵየዊ ያልሆነ ሰው ስላልሆነው ነገር አስተያየት መስጠት እንዴት ይችላል። በሀገራችን ያለው ችግር ከእኛ ወዲያ ማን ሊያውቀው ይችላል? የዶክተሩ ጥናታዊ ጽሁፍ ስለኢትዮጵያውያን አዋቂ ከኔ ወዲያ ላሳር የሚል ነው። በእርግጥ በሀገራችን አንዳንድቦታ የሙስሊሙ ቁጥር የሚበዛ ሲሆን አንዳንድ ቦታ ደግሞ የክርስቲያኑ ቁጥር ይበዛል። ሆኖም ከመከባበር በቀር በዚህ ቦታ የኔ ቁጥር በዝቶአልና አንገትህን ድፋ ያለበለዚያ አንገትህን ትቀነጠሰለህ የሚል ሰምተንም አይተንም አናውቅም። ወደፊትም ይህን አስተሳሰብ ወደፊትም አናየውም።

የፖለቲካ ተንታኙ ይህንን ከየት እንደተማሩት ባላውቅም ይህ ጸሐፊ ተወልዶ ባደገበት በጅማ ጋሌ ዱራሲ ቀበሌ ከህዝቡ ቁጥር 97% ሙስሊም ሲሆን ቀሪው 3% የማይበልጠው ክርስቲያን ግን መብቱ ተጠብቆለት ተፋቅሮና ተከባብሮ አብሮ ይኖራል።እኛ ልጆቻቸውም በህይማኖት እንደምንለያይ ትልቅ ሆነን በቅርብ ነው ያወቅነው። ምክንያቱም ጥምቀት ሲሆን የክርስቲያኑ ቁጥር አነስትኛ ስለነበረ ሙስሊሙ ሁሉ ወጥቶ ታቦቱን አጅቦ በዓሉን አድምቆ ያስገባል። በሙስሊሙም በኩል መውሊድ ሲሆን ክርስቲያኑ ተገኝቶ አብሮ ያከብራል። በመውሊዱም ቦታ ይሁን በጥምቀቱ ለክርስቲያኑና ለሙስሊሙ ይታረዳል። አንዱ በአንዱ በዓል ይደሰታል። በሌላው ዓለም የሌለው የምግብ ልዩነትም ቢሆን በሀገራችን ልክ እንደ ፖለቲካ ተንታኙያልተሻል አመለካከት ያለው ሰው ያመጣው ሊሆን ይችላል። የሚል ግምት አለኝ። በቅርቡ ለታሰሩት ሙስሊም መሪዎች አስፈቺና ጫና የሚፈጥር አካል ክርስቲያን ወጣቶች ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው። የዚህ መልካም ወንድማማችነት ሥራ አባል ለመሆን ይህ ጸሐፊ መልካም ፈቃድ አሳይቶአል።

በቅርቡ አምስት ወር ያልበለጠ ታሪክ እንደነገርኩዋችሁ እኔ ባደግሁበት በጅማ ዞን በጋሌ ዱራሲ የከረስቲያኑ ቁጥር አናሳ በመሆኑ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አርጅቶ ስለነበረ ቤተኬስቲያኑ እንዲታደስ ሀሳቡን ያቀረቡት ሙስሊሞች ሲሆኑ የቤተክርስቲያኑ አሰሪ ኮሚቴዎች ሙሲሊሞች ነበሩ። እኔ ክርስትና ለተነሳሁበት ቤተክርስቲያን ዕድሳት መዋጮ እንድከፍል የጠየቁኝም ሙስሊም ኮሚቴዎች ናቸው። ይህንን ማረጋገጥ ለሚፈልግ ሚዲያም ይሁን ግለሰብ ሙሉ መረጃ ለመስጠት ይህ ጸሐፊ ሙሉ ፈቃድ አለው ቸር ይግጠመን።

No comments:

Post a Comment