Thursday, July 25, 2013

እንደዚህም ሆኖ ነበር

ሊ/ኤክማን ምስክር ተገኘ
የቀድሞው አየር ሃይል አባል
2013 የበጋ ወቅት ዋሽንግተንና አካባቢዋን በእጅጉ አድምቋት ሰንብቷል ። በየአመቱ የጁላይ ወር የመጀመሪያው ሳምንት እድለኛ በሆነችው በአንዷ የዩናይትድ ስቴትስ ከተማ በአበሻ ዘር ሞቅ ደመቅ ብላ መክረሟ የተለመደ ሆኖ ለ30 ድፍን ዓመታት ዘልቋል ።ዘንድሮ እድለኛዋ ግዛት የዋሽንግተን ዲሲ አጎራባች የሆኑት ሜሪላንድ ሲልቨር ስፕሪንግ፤ ኰሌጅ ፓርክ ነበሩ ።
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያችን ባንዲራ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አካል ላይ አሸብርቆ ሲታይ እንኳን ለራስ በእርቀት ለሚያየውም እንደ ክሪስማስ (እንደ ገና በዓል) አሸብርቆና ደምቆ መታየቱ እጅግ ማራኪ ትዕይንት ሲሆን በዚሁ ዓይነት አብሮ 30 ዓመታትን አስቆጥሯል።እሰየው የሚያስብል ነው።
ምክንያቱ የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያኖች የእግር ኳስ ዓመታዊ ውድድር ይሁን እንጂ በዋናነት ግን በዓለም ዙሪያ የተበተነ የአበሻ ዘር ኢትዮጵያዊ ሁሉ የበጋውን የዕረፍት ጊዜ ከወገኑ ጋር የሚያሳልፍበት ጥሩ አጋጣሚ እንዲሆን በሁሉም ልብ እሺታን ያገኘ ይመስላል ።እንዳለመታደል ሆኖ ግንቦት 91 ላይ በእኩይነት የተወለደው ኢትዮጵያዊነትን የማዳከም ሴራ በጭንጋፍነት መክኖ በምትኩ አንድ ህዝብነት ሲያብብ በእጅጉ የተስተዋለበት ህብረት ነበር ።
አምና ዳላስ ላይ ለሁለት እንዲከፈል የተደገሰለትን አድማ በትኖ በነይ እርግብ አሞራ የድል ዜማ ወጣቱ ኢትዮጵያዊነትን ሲታደግ ተስተውሏል ። ሳምንቱም በመላው የኢትዮጵያውያኖች የተለያዩ ቋንቋዎች ዜማ ደስታና ዳንኪራው ሲቀልጥ የአንድነታችን ምልክት ሰንደቅ አላማችንም በከፍተኛ ማማ ላይ ተውለብልባ ፤ በአንፃሩ ደግሞ የከፋፋዮች መንደር በሃዘን ተመትቶ ጭር ብሎ እንደዋለ የዓይን ምስክሮች ሆንን አልፏል ።
ዘንድሮ ሜሪላንድ ግዛት ስንደርስ ገና ከጅምሩ የኢትዮጵያውያን ቆነጃጅት በሰንደቅ አላማችን ልዩ ቀለማት አጊጠው ለተመለከታቸው ፤ የህዝቡን ብዛትና የአንድነት እልክን ለተመለከተ እውነትም ኢትዮጵያ አምላክ አላት የሚለውን ብሂል ለአፍታ አይጠራጠርም ። ዲታዎች እጅግ አማላይ የሆነ ዘግጅትና ድግስ ደግሰው የኢትዮጵያዊነትን ቅስም ሊሰብሩ ደፋ ቀና ቢሉም ሰፊውን ስታዲዮማቸውን በዚያ በጠራራ ፀሃይና የበጋ ሙቀት ታቅፈውት ከመዋል ያለፈ ያንን መንፈሰ ጠንካራ ህዝብ ከቶም ስሜቱን ሊያደፈርሱት አልቻሉም ።
ለትዝብት ከቃኘናቸው በርካታ ክንውኖች ውስጥ ሁሉም ህብረትና ወንድማማችነትን የሚያጠናክሩ ሲሆኑ በይበልጥ በኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) እና በቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ማህበር የተዘጋጁት ዝግጅቶች እጅግ የተሳኩና በጠንካራ ኢትዮጵያዊ ፍቅርና መንፈስ ላይ የተካሄዱ ነበሩ ።
የኢሳት 3ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ሲያከብር በሲልቨር ስፕሪንግ ደብል ትሪ ሆቴል ውስጥ ተሰብስቦ የነበረውን የኢትዮጵያዊ ህዝብ ብዛት ላስተዋለና የኢሳትን የሚድያ አገልግሎት በገንዘብ ለመደገፍ የሚደረገውን ትንቅንቅና እልህ ለተመለከተ አገር ቤት ላለው ገዢ ፓርቲ ነፍስ ይማር ከማለት ውጪ ሌላ ማለት አይቻልም ።
ሌላኛውና ትልቁ ዝግጅት የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ማህበር የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት ያከበረበት የጁላይ 4 ምሽት ነበር ። ይህ በዋሽንግተን ዲሲ በሰፊው አዳራሽ ውስጥ በልዩ አኳኋንና አቀራረብ በዓሉን ማክበር የጀመረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ማህበር ፍፁም ኢትዮጵያዊነትና ጠንካራ ህብረት የተስተዋለበት ነበር ።
ግንቦት 91 የመንግስት ለውጥን ተከትሎ በብቀላ እንዲፈርስ ዕጣ ክፍሉ የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በታሪኩ ለአፍታም የኢትዮጵያን የአየር ክልል በጠላት ያላስደፈረና በሙያ ብቃቱም ሆነ በጀግንነቱ ዓለም የመሰከረለት እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ።ዛሬ ያ ሰራዊት በግፍ ከአገር ተገፍትሮ እንዲባረርና በዓለም ዙሪያ
ተበትኖ እንዲሰደድ ሆኗል ። የኢትዮጵያን አንድነትና የህዝባችንን ክብር በመስዋዕትነቱ ያስከበረ ፤ ንፁህ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት የነበረው ባለሙያ የኢትዮጵያ ሰራዊት አካል ከሞተላት ምድር በጭካኔ ተባረረ ፤ ቤተሰቡ ፈረሰ ፤ ኑሮው ወደ ውርደት አዘቅት እንዲያሽቆለቁል ፤ በሃሰትም እንዲወነጀል ሆነ ። በደሙና በአጥንቱ የህዝቡን ነፃነት የታደገ ሰራዊት ሰላማዊ ህዝብ እንደጨፈጨፈ ተደርጐ ኢትዮጵያውያን ባልሆኑ የዘመኑ ከሃዲያን ተወነጀለ ፤ ዕጣ ፋንታው በባዕድ ሃገር በረሃ ላይ መሰደድ ሆነ ።
ብዙሃን ዛሬም ድረስ በውርደትና በመሸማቀቅ አገር ውስጥ እየኖሩ ቢሆንም የተሳካላቸውና እግዚአብሄር የረዳቸው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የሰው ልጆች መብት ወደ ሚከበርበት አገር ደርሰዋል ። እንግዲህ እነዚህ አባላት ናቸው ዛሬም ድረስ በህብረትና በመደጋገፍ ኢትዮጵያዊ ሃገራዊ ቁምነገሮችን እየተገበሩ ለ20 ዓመታት በፅናት የዘለቁት ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ጉልህ ታሪኩ ህብረት ነው ፤ መደጋገፍና ተቀራርቦ በፍቅር መኖር ነው ፤ ህዝብ ተበድያለሁና ለውጥ እፈልጋለሁ ሲልም የዚህ ትግልና ህዝብ አካል መሆን ነው ። ዘመኑን ሙሉ በህዝብ አጋርነቱ ፀንቶ ኖርዋል ፤ አለቆቹን ለህዝብና ለአገር ልዕልና ገብሯል ። ዛሬም ከሶስቱ ቀለማት ፤አረንጓዴ ፤ ቢጫ ፤ ቀይ ባንዲራ በስተቀር ሌላ ሰንደቅ ዓላማ ከኢትዮጵያ በስተቀር ሌላ አገርም የለውም ።
የጁላይ 4 የአየር ኃይሎች ምሽት በግርማ ሞገሱ ወደር አይገኝለትም ። ትልቁ ፤ ትንሹ ፤ ሲንየር ፤ ጁኒየር … አየር ኃይሎች በአየር ኃይልነታቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው አንድ መሆናቸውን ያሳዩበት ምሽት ነበር ። ከሊቅ እስከ ደቂቅ በአንዲት መስመር የኢሜል ትዕዛዝ መሰረት ዩኒፎርማቸውን አሟልተው በሰዓታቸው በቦታው ተገኝተዋል ። መንፈስ በሚፈነቅል አኳኋን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርገው እያውለበለቡ ኢትዮጵያ ሃገሬ “ ን አዚመዋል ።እርግጥ ውብ ደማቅ መልክት ነበር ያስተላለፉት።
ከቁጥራቸው ብዛትና የሙያ ስብጥር አንፃር በእርግጥም አየር ኃይሉ ደብረ ዘይት ሳይሆን በባዕዳን አገር ተበትኖ እንዳለ መረዳት አያዳግትም ። የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት ገደል ገብቷል አገር ያለ አጥርና መዝጊያ ወለል ብላ ተከፍታ ቀርታለች ነፍስ ይማር ህውሃት !
ዘንድሮ ዲሲ ላይ አንጋፋ በራሪዎች ፤ ዛሬም ድረስ ሮጠው ያልጠገቡና ክንዳቸው ያልዛለ ጎልማሳ ተዋጊ በራሪዎች፤ ኢህአደግን ወግድ ያሉ ትኩስ ወጣት በራሪዎች ፤ አንቱ የተባሉ የቴክኒክ ባለሙያተኞች ፤ ያስተዳደርና የፅህፈት ክፍል ሰራተኞች ፤ የሲቪል የአገልግሎት ፤ ስፖርተኞች ፤ የአየር ኃይሉ አባላት ቤተሰቦችና የአየር ኃይሉ ወዳጆች ከያሉበት ነቅለው በመምጣት በበዓሉ ላይ ታድመዋል ።
በዚህ ማህበር ቤተሰቡ የፈረሰበት ቤተሰቡን መልሶ ሰብስቧል ፤ አዲስ ቤተሰብ መስራቹን በሃይሎጋ ሽቦ ድል አድርጐ ደግሶ ድሯል ፤ ሲወልድም በእንኳን ደስ ያልህ የደስታ ተካፋይ ሆኗል ፤ ክርስትናና ሌላም ዝግጅት ላይ ታድሟል ፤ እንደገና መልሶ ድሯል ፤ አካል ሲዝልና አልጋ ላይ የዋለን አፅናናቷል ፤ ወደማይቀረው የሚሰናበተውንም በከፍተኛ ሃዘን አጅቧል ።
በተጨማሪም አገር ቤትም ሆነ በተለያዩ የዓለም ክፍል ያሉ የአየር ኃይሉም አባላት ዕርዳታ የሚሹትን በዕርዳታው ታድጓል ። የደከሙትን አፅናንቷል ። አገራዊ ጉዳዮች ውስጥም ያገባኛል ብሏል ።ይህ ማህበር ወደፊት ጠንክሮ ይቀጥላል ። ሰፊ ራዕይ አለው ። አገርና ህዝብን በሚጠቅሙ ልማት ላይ አስተዋፅዖ ያደርጋል ። ለማንኛውም የአገር ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ ይሰጣል ።
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ !

No comments:

Post a Comment