Wednesday, July 31, 2013

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መዝገብ የሙያ ምስክሩ ቃል ተሰማ

“የፅሁፎቹ አንደምታ አመፅን የሚቀሰቅስ ሆኖ መቅረቡ
ከሕገ-መንግስቱ ጋር አያጣርሰውም?”
ዐቃቤ ሕግ
“ጋዜጠኛ ተመስገን ከሕገ-መንግስቱ ጋር የሚጣረሱ ኀሳቦችን አልፃፈም”
የሙያ ምስክሩ

በአሸናፊ ደምሴ

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የክስ መዝገብ ስር ሦስተኛ የመከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት የሙያ ምስክሩ ትናንት በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጡ። በዚህም መሠረት ህዝብን ለአመፅ የሚቀሰቅሱ ፅሁፎችን አትሞ አሰራጭቷል በሚል ክስ የተመሰረተበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከሕገ-መንግስቱ ጋር የሚጣረስ አንዳችም ፅሁፍ አላሰራጨም ሲሉ የሙያ ምስክሩ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነት የማስትሬት ዲግሪ ያላቸውና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት መምህርና በሚዲያ የማማከር ሙያ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት የሙያ ምስክሩ አቶ እንዳልካቸው ወ/ሚካኤል፤ በችሎቱ ተገኝተው ከጠበቆችና ከዐቃቤ ሕግ ለቀረበላቸውን ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል። በዚህም መሠረት ከፍትህ ጋዜጣ ባህሪ ከጋዜጠኝነት ሙያ አንፃር መተላለፍ ስለሚገባቸው ኀሳቦችና ገደብ ስለተጣለባቸው ሁኔታዎች ጭምር በመተንተን፤ የጋዜጠኛው አስተያየትን የመፃፍ መብት ተከትሎ ለሚከሰቱ ስህተቶች ስለሚደረጉ ማስተካከያዎች ጭምር ምላሽ ሰጥተዋል። ምስክርነታቸውንም ሲጀምሩ “ጋዜጠኝነት ከማንኛውም ወገን ተፅዕኖ ነፃ በመውጣት፣ የማኅበረሰቡን ችግር ያለወገንተኝነት ማሳየት ኃላፊነቱና ግዴታው መሆኑን” አስምረውበታል።
አንድ ጋዜጠኛ ዜና ሲፅፍ ክስተቱን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሊያቀርብ የሚገባው ሲሆን፤ አስተያየቱን ሲያሰፍር ግን በተፈጠረው ክስተት ላይ ያለውን አቋም ጭምር የሚያሳይበት ነው ብለዋል። አንድ ጋዜጠኛ ባቀረበው አስተያየት ላይ ሌላ ወገን ቅሬታ ቢኖረው በቀጣዩ ዕትሞች ሀሳቡን ማስተናገድ ተገቢ መሆኑን የጠቀሱት የሙያ ምስክሩ፤ ይህ ካልሆነ ግን ስህተት ይሆናል ብለዋል። አያይዘውም በወቅታዊና በሚመለከታቸው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የግል አስተያየቱን መፃፍ የጋዜጠኛ ሙያዊ ግዴታ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። 
በተለይም በ1ኛ ክስ ስር የተጠቀሱትን “ሞትን የማይፈሩ ወጣቶች” እና “የፈራ ይመለስ” በተሰኙት ርዕሶች ስር ጋዜጠኛው ያሰፈራቸው ኀሳቦች የወቅቱን የዓለምና የአካባቢያዊ አገሮች ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባና አመፅን የሚቀሰቅስ አይሆንም ወይ? በሚል ለቀረበው ጥያቄ ሲመልሱ፤ የሚዲያ ስራ ወቅትን የተከተለ ስለመሆኑ አስታውሰው፤ ጋዜጠኛውም በፅሁፎቹ የዓለምን ወቅታዊ ክስተት እንደ ምሳሌ ማሳየቱ ወጣቱን ለአመፅ ከመቀስቀስ ይልቅ መንግስትን ከሌሎች አገሮች እንዲማር በማሳሰቡ አደጋን የመቀነስ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ብለዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን በፅሁፎቹ ተደጋግሞ ወጣቱ ትውልድ ሕገ-መንግስቱንና ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ መብቱ ሲነካ መብቱን መጠየቅ መልመድና ኃላፊነትን የመሸከም አቅም ሊገነባ እንደሚገባ ጠቁሟል ብለዋል። ይህም በማንኛውም መልኩ ሕጋዊ መሆኑን አስረግጠዋል። 
“የሁለተኛ ዜግነት ኑሮ በኢትዮጵያ እስከመቼ?” በሚል ርዕስ ስር የሰፈረው የጋዜጠኛው ሀሳብም እውነታ ላይ ተመስርቶ የተፃፈ አስተያየት መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት የሙያ ምስክሩ፤ በፅሁፍም ውስጥ “መንግስት ዘረኛ ፖሊሲን ይከተላል” በሚል የሰፈረው ሀሳብ አስተያየት በመሆኑ ምንም ስህተት የለውም ሲሉ የጋዜጠኛውን ኀሳብ በነፃነት የመግለፅ መብት አስረድተዋል።
አስተያየት ሊሰጥበት የሚገባና የማይገባ ተብሎ የተቀመጠ ነገር የለም፤ ነገር ግን በሕገ-መንግስቱና በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ስር ገደብ የተጣለባቸውን ጉዳዮች የሚነኩ ፅሁፎች በጋዜጣው ሠፍረው አለማግኘታቸውንም በተጠየቁ ጊዜ መልሰዋል። በመሆኑም በጋዜጠኛው ተፅፈው በጋዜጣው የተነበቡ ፅሁፎች በሙሉ የጋዜጠኝነት መርሆዎችን ያልጣሱና አደጋን ለመቀነስ የተሰሩ ናቸው ብዬ አምናለሁ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በታተሙት ፅሁፎች ውስጥ አመፅን የመቀስቀስ አንደምታ ያላቸውና “ሆ ብለህ ተነስ!” የሚሉ ሀሳቦችን ከሰላማዊ ትግል ጋር በምን ማገናኘት ይቻላል? ዴሞክራሲያዊ አካሄድን የሚጣረስ አይደለም ወይ? ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሲሰጡ፣ “ጋዜጠኛው የግብፅን፣ የቱኒዚያን የሊቢያን አገራት ወጣቶችን ሚና በማጣቀስ የኛም አገር ወጣቶች ሕግና ስርዓትን በተከተለ መልኩ መብታቸውን ስለመጠየቅ ማሳሰቡ ትክክል እንደሆነ አስረድተዋል። ለጋዜጠኛው የክስ መንሰኤ የሆኑት ፅሁፎች መፍትሄ ጠቋሚዎች ናቸው ወይንስ የመጨረሻውን አማራጭ አመላካች በሚለው ጉዳይ ላይ ፅሁፎቹ ዝርዝር የመፍትሄ ሀሳቦች አልተጠቆመበትም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠ ሲሆን፤ የሁለቱንም ወገኖች የፅሁፍና የሰነድ አስተያየት ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ለነሐሴ 28 ቀን 2005 ዓ.ም በመስጠት ተጠናቋል።

No comments:

Post a Comment