Saturday, July 27, 2013

ለሰነበተ የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ጥያቄ መልስ

በክፍሉ ሁሴን  
አፍቃሪ ወያኔ የፌስቡክ ወዳጄ “ሰላማዊት ስዮም”በጣለችልኝ የፍልሚያ ሸማ መሰረት ምላሹን ልሰጥ ለዛሬ ቃል ገብቼ ነበር።ሰላማዊት “እስቲ ስለዘንድሮ ፓይለቶች (ወያኔ የአየር ሃይል ፓይለት ይሁኑልኝ ብሎ በትዕዛዝ ወይም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አግባብ “ፓይለት” የሆኑትን ማለቷ ነው) አውቃለሁ የምትለውን ያህል ስለድሮዎቹ በሐውዜንና በመሳሰሉ ቦታዎች በገበያ ላይ ቦምብ እየጣሉ ሰላማዊ ሕዝብ ስለፈጁት ፓይለቶች ደም ከውሃ ይወፍራል በሚለው አይነት ሳትደብቅ ንገረን፤ለልጆችህም ንገራቸው (አባቴ የኢትዮጲያ ንጉሰ ነገሥት መንግስት አየር ሃይል ቆፍጣና መኮንንና ፓይለት የነበረ መሆኑን ዘወትር በኩራት የማነሳውን ተሸማቅቆ ሁለተኛ አያነሳውም በሚል የተወረወረ ወያኔያዊ አሽሙር መሆኑ ነው) ስትል “ተፈታተነችኝ።” ለእሷም ሆነ የታሪክን ሚዛን ለመጠበቅ ሲባል ምላሹን ለዛሬ ይዤ ለመቅረብ ቃል ስገባ እስከዚያው የዶ/ር ፈቃደ አዘዘን “ዲሞክራት ፓይለቶች”የሚለውን ግጥሙን ‘አያ ጎሽሜ’በሚል ርዕስ ካሰተመው መድብሉ እያነበባችሁ ጠብቁኝ ማለትን ዘነጋሁ።ግድየለም ይህ ምላሽ ካልተንዛዛ እዚሁ ላነሳው እሞክራለሁ።አሁን ወደ ጭብጡ።

የአንድ ደቂቃ አርምሞ (A minute of silence) ለኢትዮጲያውያን የጦርነት ሰለባዎች
ስለሐውዜን እልቂት ነገሩ በዝርዝር ሳይገባኝ መጀመሪያ የሰማሁት በ1982 ዓ.ም ግንቦት ወር መጨረሻ አካባቢ ነው።በዚያን ጊዜ ኢትዮ-ሊቢያ የጋራ የማዕድን ኩባንያ የሚባል መ/ቤት እሰራ ነበር።አብረውኝ ከሚሰሩ ሁለት የኩባንያው ፀሃፊዎች ጋር ከምሳ በኋላ ቡና ጠጥተን እየዘቀጠ በመሄድ ላይ ያለውንና ከሃያ ሶስት አመት በኋላም ምንም መሻሻል ያልታየበትን የአገራችንን ፖለቲካ በሹክሹክታ እንደተለመደው አንስተን መውቀጥ ጀመርን።ከእነዚሁ ከትግሪኛ ተናጋሪ (አንዷ ራሷን ከአድዋ አንዷ ራሷን ከኤርትራ የሚያጣቅሱ ነበሩ) ወገን ከሆኑ ጓደኞቼ ከአድዋ የሆነችውና በእድሜም ላቅ ያለችው በድንገት ወደኔ አተኩራ “እናንተ ጄኔራሎች ሲሞቱ ብቻ ነው የደርግ ክፋት የሚታያችሁ የትግራይ ሕዝብ በአውሮፕላን ሲጨፈጨፍ ግን ደንታ አይሰጣችሁም።”ጭውውታችንን በምናደርግበት ጊዜ በግንቦት ስምንት 1981 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ሳቢያ የኢትዮጲያን ጦር ሃይል  ከአረመኔነትና ከፈርጣጭነት ጋር ስሙ ዘላለም በክፉ እንዲነሳ ያደረገው ፈርጣጩ “ቆራጡ የአብዮታዊ ጦር ጠቅላይ አዛዥ”በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ቀሪዎቹ ከፍተኛ መኮንኖቹ ውስጥ ከአንድ ዓመት በኋላ በዚያው በገፊነት በሚታወቀው ግንቦት ወር አስራ ሁለቱን የፈጀበት ጊዜ ነበር።ለአድዋዋ መልሴ በመፈንቅለ መንግስቱ ያለቁት ጄኔራሎች አብዛኞቹ በመንግስቱ ኃ/ማሪያም ደደብ አመራር እየተንዛዛ የሄደውንና አላስፈላጊ ከፍተኛ እልቂትና የንብረት ወድመት ያደረሰውን የርስ በርስ ጦርነት ለመግታት እንጂ በግልማ ከሰው የተለየ ችግር እንደሌለባቸው እንዲያውም የተንደላቀቀ ኑሮ ሊገፉ ይችሉ እንደነበር ላመላክታት ሞከርኩ።ይህ አይነቱ ሚዛናዊ ክርክር ያኔም ብዙ ዋጋ እንደሌለው ዛሬም ብዙ ዋጋ የለውም።ያም ሆኖ እንደወያኔ፣ሻዕቢያና ደርግ የመሳሰሉ እኩይ ድርጅቶች በጫሯቸውና ሆነው ብለው እሳቱን ለረጅም ጊዜ እንዲቀጣጠል በማድረግ ላለቁት ሲቪሎችም ሆነ የኢትዮጲያ ጦር መለዮ ለባሾችና የተገንጣይ አስገንጣይ ቡድን ጀሌዎች የአንድ ደቂቃ የአርምሞ ጊዜ ባለሁበት ወስጄያለሁ።
መንግስቱ ፈረጠጠ፤መለስ ነገሰ፤የሐውዜን ድራማ በቴሌቪዥን ቀረበ
አሰቃቂው ድራማ በቴሌቪዥን በቀረበ ማግስት ከአድዋ የሆነችው ባልደረባዬ ሰላምታ ሳታቀርብልኝ በፊት ይህ ነው ሊሉት በማይችሉት ከፍተኛ ስሜት ተውጣ እየተፍነከነከች “ትናንት ማታ አየህ የሐውዜንን ጭፍጨፋ?”ስትል ጠየቀችኝ።”ህፃናትን ሳይቀር  በጀሌነት አሰልፎ ሆነ ብሎ ሲቪሉ ስር ተጠልሎ የሚዋጋ አጋሚዶ እንዲህ ያለ እልቂት ያስከትላል።”ነበር መልሴ።ለነገሩ ፊልሙን ከሁለት ደቂቃ በላይ አላየሁትም፤ምን ሊያደርግልኝ ከፊልሙ አቀራረፅ ተልዕኮው ግልፅ ሆኖ ሳለ!ተልዕኮውን ገብረመድህን አርአያ ኋላ ላይ ግልፅ እንዳደረገልን ሁሌም ስንጠረጥር እንደነበረው የወያኔ የለየለት የመሰሪነት ውጤት ነው።ገብረመድህን አርአያ ቀድሞ የወያኔ አባል የነበረና ወያኔ በረሃብተኞች ስም የመጣውን እርዳታ ቸብችቦ ከጦር መሳሪያ ግዢ በተጨማሪ እንዴት አመራሩ እንደደለበበት በሰጠው የማያወላዳ መረጃ መሰረት የቢቢሲው ማርቲን ፕሎት አንድ ሰሞን አለምን ያነጋገረና ቦብ ጊልዶፍ የሚባለውን “በጎ አድራጊ”የፈረንጅ አቀንቃኝ ጭምር ያበሳጨ ፕሮግራም እንዲሰራበት ያደረገ ውስጥ አዋቂ ነው።ገብረመድህን ስለሐውዜኑ እልቂት የሚከተለውንም ይለናል።
“ወያኔ ኤርትራን ለማስገንጠል ከሻዕቢያ ጋር በምታደርገው መሞዳሞድና በሌሎችም ምክንያቶች በትግራይ ሕዝብ የተጠላችበት ጊዜ ስለነበር ሰው አጣች፤የሚመለመል ጠፋ።ስለዚህ ተንኮል አሰቡ።በለገሰ አስፋው የትግራይ አስተዳዳሪነት ጊዜ አንድ ክፍለ ጦር ሐውዜን ገባ ወጣ እንዲል አደረጉ፤ወያኔ ትልቅ ስብሰባ ሐውዜን ላይ ሊያደርግ ነው የሚል የውሸት መረጃ ለለገሰ አስፋው እንዲደርሰው አደረጉ።በዚያን ጊዜ ይህን ያቀነባበረው ሃይሉ ሳንቲም የሚባል የወያኔ የወታደራዊ ደህንነት ነው።ቀደም ብለው ባሰቡበት መሰረትም ፊልም ቀረጻ እንዲሰለጥኑ ተክለወይን አስፍሃ፣ሱራፌል ምህረተአብ፣ኢያሱ በረሄ ወዘተ ሱዳን ተላኩ።ደርግ መረጃው እውነት እንዲመስለውም የተወሰኑ ታጋዮች በሐውዜን ገበያ ቦታ ውር ውር እንዲሉ ተደረገ።ደርግም ተጨማሪ ማጣራት ሳያደርግ ስድስት ሚጎች ልኮ አስደበደበ።ያ ሁሉ ድብደባ ሲደረግ እነኢያሱ በሰለጠኑት መሰረት ተራራ ላይ ቆመው ከሁሉም አቅጣጫ እያንዳንዱን ሚግ ቪዲዮ ይቀርጹ ነበር።”
ይህ ሊታመን የማይችል ነው የሚል ወያኔ ከሚነግድበት የሐውዜን ድብደባና በዚያን ጊዜ ከነበረው የፊልም ቀረጻ ቴክኖሎጂ ተነስቶ ወያኔ ደርግ ድብደባ እንደሚያደርግ አስቀድሞ መረጃ ካልደረሰው በቀር እንደዚያ ተንፈላሶ ገፅ በገፅ (footage by footage ) ሊቀርፅ እንደማይችል፤ይልቁንም ሕዝቡን ከአካባቢው እንዲወጣ ማስታወቂያ ከማስነገር ፈንታ ገብረመድህን እንዳለው ሕዝቡን በማስፈጀት ኢሰብዓዊ በሆነ ፕሮፖጋንዳ መዋጮና ምልምል መሰብሰብ ዋነኛ ግቡ እንደነበር ሲረዳ ለሐውዜን እልቂት ዋነኛው ተጠያቂ ወያኔ መሆኑን ይገነዘባል።ይህም ብቻ አይደለም።ገብረመድህን ሌላም ጉድ ይነግረናል።ለወያኔ ፀረ ኢትዮጲያ አላማ ተባባሪ አልሆን ያሉ በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ከበሬታ ያላቸውን ሰዎችም ከጉልበት በስተቀር ዘዴ ላልፈጠረበት ደርግ የወያኔ አባል እንደሆኑ አስመስሎ ማህተሙን አሳርፎና በረቀቀ መረጃ እንደተገኘ አድርጎ ባሰረገለት መሰረት ትላልቅ ሰዎች እንዲገደሉና በዚህም የትግራይ ሕዝብ ተበሳጭቶ የወያኔ ተባባሪ እንዲሆን አድርጓል።ቀይ ሽብርን በመፍራት ወደወያኔ የተቀላቀሉ የአስራ ሁለት የአስራ ሶስት አመት ሕጻናትንም በኋላ ላይ የበረሃ ሕይወትን መቋቋም ሲያቅታቸውና ወላጆቻቸውን ናፍቀው ፈቃድ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ፈቃዱን የሚሰጥ መስሎ “ወደትውልድ ቀዬያችሁ መሄድ የምትፈልጉ እጃችሁን አውጡ ብሎ አመራሩ ካታለላቸው” በኋላ እንሄዳለን ብለው ራሳቸውን ያጋለጡ ልጅ እግር ታጋዮች እየተለቀሙ ተረሽነዋል።ገብረመድህን “አረመኔው ወያኔ”እነዚህን በጥይት ደብድቦ የገደላቸውን ሕጻናት “ናብ እነይ”(ወደ እናቴ) በሚል ቅጽል ስም እየጠራ እንደሚያላግጥባቸውም ይናገራል።እጅ በሰጡና በተማረኩ የኢትዮጲያ ወታደሮች ላይም ወያኔ የፈጸመውንም ፍጅት በስፋት ገብረመድህን አውስቷል።ዝርዝሩን ከአንጀቱ ለሚፈልግ ብዙ ሳይደክም ያገኘዋል።አሁን ወደሐውዜን ፍጅት እና ወታደር ከአለቃው የሚሰጠውን ትዕዛዝ ያላንዳች ጥያቄ መፈጸም ስላለበት ጉዳይ እንመለስ።
አላግባብ የተከሰሱና የተፈረደባቸው ኢትዮጲውያን ፓይለቶች ብቻ ስለመሆናቸው
ባንድ አጋጣሚ የተዋወኩት የቀድሞ የባህር ሃይል መኮንን የነበረና ወያኔ ሲገባ እንደማንኛውም የኢትዮጲያ የጦር ሃይል ባልደረባ ተይዞ ወያኔ “ተሐድሶ”በሚለው እስር የተንገላታ እንዳጫወተኝ ወያኔ ጦሩን በወያኔያዊ መሰሪነቱ እየከፋፈለና እርስ በርሱ እንዲወነጃጀልና እንዲሁም ለአገሩ በመዋጋቱ ወንጀል እንደሰራ ሊያሳምነው ሲሞክር አንዳንድ ቆራጦች “አዎ ወንጀል ሰርተናል!ወንጀላችን መሸነፋችን ነው!ለናንተም መሳሪያችንን አውርደን እጅ መስጠታችን ነው!ብለው ከመሸም በኋላም ቢሆን እንደተጋፈጡት አጫውቶኛል።እውነት ነው።ያ ሁኔታ በወቅቱ ብዙ ያላጤንኩትን ያንድ ባላገር አነጋገርንም አስታውሶኛል።”የወታደር ቁምነገረኛ ባመቱ ድሃ ነው።”ብሄራዊ እርቅ፤ኢትዮጲያዊነት ወዘተ ለማይገባው ወያኔና ሻዕቢያ ጦሩ መሳሪያውን አውርዶ እጁን ሰጠ፤በዚህም መታሰር፣ መጋዝ ብቻ ሳይሆን በጦር ሜዳ ውሎ ወያኔንና ሻዕቢያን ለረጅም ጊዜ እንዳላርበደበደ ከኢትዮጲያ ባህልና ልማድ ውጪ በበቀል ውርደትን እንዲሸከም ተደረገ። ሲመሩት የነበረው ጦር በከሃዲ የእረኛ ጦር እንዳይሆን ሆኖ መዘረሩ ያበሳጫቸው በወታደራዊ ብቃታቸውና አመራራቸው የሚታወቁት ሜጄር ጄኔራል ግዛው በላይነህ ከጡረታቸው ላይ ሆነው “ጦሩ መባረር ሲያንሰው ነው”ብለው በቁጭት ለጦቢያ መፅሄት ጻፉ።በዚያ ፅሁፋቸውም አቻቻው ጄኔራል ነጋ ተገኝ ተቃውመዋቸው ምልልስ እንዳደረጉ አስታውሳለሁ።ሁለቱም ትክክል የሆኑበትን ነጥብ በወቅቱ አንስተዋል።እዚህ ለማሳየት የተፈለገው በርስ በርሱ ጦርነት ለደረሰው እልቂት ሐውዜንንም ጨምሮ ተጠያቂዎቹ የሻዕቢያ፣የወያኔና የደርግ ከፍተኛ አመራር ናቸው።The Ethiopian Air Force is the air arm of the Ethiopian National Defense Forces
ባጭሩ ለማስቀመጥ እስካሁን ባለኝ መረጃ በጦር ወንጀለኝነት ተከሶ የተፈረደበት የተዋጊ አውሮፕላን ወይም የአየር ሃይል ፓይለት ሄርማን ጎሪንግ የተባለ የናዚ ጊዜ የአየር ሃይል አዛዥ ነው።እሱም የተከሰሰውና የተፈረደበት በጦርነቱ ጊዜ ይመራው ለነበረው የጀርመን አየር ሃይል በሰጠው ትዕዛዝ ሳይሆን ይበልጡን በናዚ አባልነቱ ባሳየው የይሁዲዎች ፍጅት ነው።ከዚህ ውጭ በቅርቡ አንድ የአርጀንቲና የቀድሞ የባህር ሃይል ፓይለት (ከመርከብ የሚነሱ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን የሚያበር) አርጀንቲና በአምባገነን ወታደራዊ አገዛዝ በነበረች ጊዜ በእስር ላይ የሚገኙ ሲቪል ተቃዋሚዎችን በባህር ሃይሉ ከሚገኝ መደብ እያወጡ አይናቸውን እየሸፈኑ በአውሮፕላን ከጫኑ በኋላ ከሰማይ ወደባህር እየወረወሩ በመግደል የብዙ ጊዜ የበረራ ድርጊት ላይ ተሳትፏል ተብሎ አገር ቀይሮ ይሰራበት ከነበረው የሆላንድ አየር መንገድ ድርጅት ተይዞ ለፍርድ መቅረቡን አስታውሳለሁ።በተቀር ከሽምቅ ውጊያ ወደለየለት የፊት ለፊት ጦርነት በተለወጠ ትዕይንት ውስጥ የቅርብ አለቃውን ትዕዛዝ በተዋረድ አክብሮ የተዋጋንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት የጦር ቀጠና ውስጥ የተሳተፈን እግረኛ ወታደር ሆነ የአየር ሃይል ፓይለት በጦር ወንጀለኝነት ከሶ የሚያንገላታ በቀለኛና አላጋጭ የቧልት ፍ/ቤት በወያኔ ቁጥጥር ስር ካለችው ኢትዮጲያ በስተቀር የትም የለም።ኢትዮጲያን በመዝረፍ ረገድ ስግግብነታቸው ወያኔንና ሻዕቢያን ባያጋጫቸው ኖሮ እንደግርማ ዋቅጅራ ባሉ ራሳቸውን የህግ ባለሙያ ብለው በሚጠሩ ቅጥረኞች አማካይነት ወያኔ ሊበቀል እስር ቤት አጉሯቸው የነበሩት የቀድሞ ቆፍጣና፣እውቅና በበረራ ሙያ የተካኑ የአየር ሃይል አብራሪዎች በሐውዜን ስም ለረጅም ጊዜ በእስር ላይ ቆይተው በቀል የተፈፀመባቸው እነኮሎኔል ብርሃነመስቀል ሃይሌ፣ኮሎኔል ግርማ አስፋው፣ሌተና ኮሎኔል ሰለሞን ከበደና ሻምበል ክፍሌ ውቤ ብቻ አይሆኑም ነበር።ሌላው ቀርቶ ወያኔ በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ከአየር ሃይል ተሰናብተው በሲቪል ፓይለትነት ኢትዮጲያ አየርመንገድ አገልግለው ወደጡረታ በመግባት ላይ የነበሩትን እነኮሎኔል ተካ መኮንንን፣ኮሎኔል ጥግነህ ሃብተጊዮርጊስን ጭምር ኤርትራን ደብድባችኋል ብሎ አስሯል። የ”ባድሜ ሉዓላዊነት” ፉክቻ አስፈታቸው።ከላይ እንደተመለከተው መንግስቱ ኃ/ማሪያም እስከዛሬ ድረስ ለጦሩ መሸነፍ የራሱን ደደብ የ”አብዮታዊ ጦር ጠቅላይ አዛዥነትና” ፈርጣጭነት እንደማይቀበል ሁሉ በመሰሪነት የሚያስከነዳው ሟቹ መለስ ዜናዊና በአምሳሉ የፈጠረው ወያኔም በሐውዜንና በመሳሰሉት ለደረሰው እልቂት የራሳቸውን ሃላፊነት ትተው ሌሎችን ይበቀላሉ።አጋጣሚ ሆኖ በሐውዜን ጉዳይ ለረጅም ጊዜ ተከሶ ለአገሩ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለው ኮሎኔል ብርሃነመስቀል ሃይሌ ከአባቴ ጋር አንድ ላይ ተፈሪ መኮንን የተማረ በፓይለት 11ኛ ኮርስም አንድ ቅጥር ከመሆናቸውም በላይ ከአየር ሃይል ተመርጠው ገና በመቋቋም ላይ የነበረውን የምድር ጦር አየር ክፍል (Army Aviation ) እንዲያደራጁ ተልከው ጎን ለጎን ለረጅም ጊዜ አብረው አገልግለዋል።አባቴ በሚያዝያ 1966 ዓ/ም አካባቢ የአገልግሎት ህይወትን ቶት በሲቪል ፓይለትነት ወደአየርመንገድ ሲዛወር በእነብርሃነመስቀል ላይ ከደረስባቸው እንግልት ሊተርፍ ችሏል።ለነገሩ ኮሎኔል ብርሃነመስቀልም ደርግ ከመወድቁ አንድ ሁለት አመት በፊት ከአየር ሃይል ለቆ አየርመንገድ መጀመሪያ በበረራ አስተማሪነት በኋላም ዳሽ 5 ወይም ባፋሎ (Buffalo) በሚባል ካናዳ ሰራሽ አውሮፕላን ላይ ሲያገለግል ከነበረበት ነው ወያኔ ወደኋላ ሄዶ ያሰረውና የተበቀለው።በሐውዜንና በመሳሰሉት ለደረሰው ጭፍጨፋ እንዲሁም የራሱን ወንጀል ለመሸፈን ከቅርብ አለቃቸው የተሰጣቸውን ጥብቅ ትዕዛዝ መከተል የነበረባቸውን ኢትዮጲያውን መኮንኖች በግፍ ላንገላታበትና ላሰቃየበት እንዲሁም ለፈጸመው የአገር ክህደት አንድ ቀን ወያኔን ለመፋረድ መረጃዎቻችንን እያጠራቀምን እንገኛለን።እዚህ ላይ የጠቀስኳቸው የአየር ሃይል መኮንኖች ሁሉ ስማቸው ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በዚያም ሆነ በዚህ ከዚህ ቀደም በአደባባይ ስለተጠቀሰ መረጃው ሙሉ እንዲሆን ፎቶግራፍም ጭምር አያይዤያለሁ።በመጨረሻም ለወዳጄ ሰላማዊት ስዩም የዶ/ር ፈቃደን “ዲሞክራት ፓይለቶች” የሚለውን ግጥም አለመጋበዝ “ወዳጅነታችንን”የሚያሻክረው ስለመስለኝ እነሆ ጀባ ብዬለሁ።
ዲሞክራት ፓይለቶች
ሲበርሩ–ምንድን ይጭናሉ?
ሲተኩሱ–ምን ይተኩሳሉ?
ሲጥሉ–ምን ያፈነዳሉ?
ካናት በሚያፈሱት ካናት በሚረጩት፤
ከአጤውና ከደርግ በምን ይለያሉ?
በፊት “ለእናት ሀገር”፤
“ለድንበር ነፃነት”ከተመሠረቱት
በይሁዳ አንበሳ መፈክር ካደጉት
ኋላም በደርግ ዓለም “በልዩ ሁኔታ በአዲስ ወኔ መንፈስ
ዳግም ከታነፁት”
“በሶሺያሊስት ምግባር፤ለሰው ልጅ ደህንነት ከተኮተኮቱት”
“ለዓለም ወዛደሮች፤ለምድር ጎስቆሎች”
“ለኢትዮፕ ሰፊ ሕዝቦች፤ቤዛ እንዲሆኑት”
“በእውቅ ተመልመለው፤በእውቅ ከተገነቡት”
“ከማይደፈሩት–ከማይገሰሱት”
“በዓለም ተደንቀው ባለም ከሚፈሩት”
ከአጤውና ከደርግ፤
“ጀግና አየር ኃይሎች”
“ቀይ-ብስል ፓይለቶች”
በምን ይለያሉ “ዲሞክራት ፓይለቶች”?
ቅንጨና ፍርፍሩን
የዶሮ ፍትፍቱን
ብሩንዶ ስጋውን
ጥብስና ክትፎውን
ደሃ የሚመኘውን
በልሙ የሚቆርጠውን
በኮዳ ውሃውን–ጠላውን ማርጠጁን
በቅርጫት ዳቦውን-ሸሚዝ-ኮትሱሬውን
የብርቱካንና የፓፓያ መዓት
ሊረጩ ነው ጧትጧት?
ከመና ፋብሪካ ሰማያ ሰማያት?
ፅጌረዳ አበባ እርግብ ይረጫሉ?
“አንቺ ሆዬ”ን እና “ትዝታ”ያዜማሉ?
ሕዋውን በ”ባቲ”በፍቅር ይሞላሉ?
ከአጤውና ከደርግ የአየር ላይ ሀይሎች
በምን ይለያሉ “ዲሞክራት ፓይለቶች”?
ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ሚያዝያ 01/1988 2:59 ማታ ላይ እንደገጠመው።ማለፊያ ጥያቄ ነው ዶ/ር ፈቃደ ያቀረበው።የአጤውና የደርግ ፓይለቶች ከ”ዲሞክራት”ፓይለቶች የሚለዩት ቢያንስ መሃል ከተማ ላይ አውሮፕላን ማብረር ሲያቅታቸው ገበያ ላይ ለቀው በጃንጥላ ለማምለጥ “ድፍረት” አልነበራቸውም።ማብረር ሳይችሉ ቦምብ ጭነው ለመሄድም የሚያስችል “ዲሞክራሲም”በአጤውና በደርግ ጊዜ ለነበሩት ፓይለቶችም አልነበረም።ልዩነቱ እሱ ነው።
Email: kiflukam@yahoo.com

No comments:

Post a Comment