(በፍሬው አበበ)
የራዲዮፋና ኤፍኤም (98.1) የብሮድካስት ባለስልጣን በሰራው የዳሰሳ ጥናት በተደማጭነት የአንደኝነት ደረጃን ተጎናጽፌአለሁ በሚል ሰሞኑን በተደጋጋሚ የሚያስተጋባውን “ጉሮ ወሸባዬ” ስሰማ ግር መሰኘቴ አልቀረም። ግር የተሰኘሁበት ዋና ምክንያት፤ ጣቢያው ከሌሎች ተወዳዳሪዎቹ የላቀ ማዕረግን እንዴትና በምን መለኪያ ሊጎናጽፍ ቻለ የሚለውን ጥያቄ ግልጽ በሆነ መንገድ ባለመመለሱ ነው።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሠረት የዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻልና ዕድገት በሚመለከት ጥናት አካሂጃለሁ ማለቱ አይከፋም። ይህም ሆኖ ጥናቱ ወቅታዊና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል የሚያንጸባርቅ እንዲሆን ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባ ነበር፤ አልሆነም እንጂ። በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ፕሮፌሽናል ጥናቶች በገለልተኛ አካል ቢካሄዱ ከተአማኒነት አንጻር ትልቅ ዋጋ ሊኖረው እንደሚችል እዚህ ላይ ማስታወሱ አግባብነት ይኖረዋል።
ባለስልጣኑ ከሚያዚያ እስከ ግንቦት 2004 ዓ.ም አካሂጄዋለሁ ያለውና ከአንድ ዓመት ቆይታ በኃላ በሐምሌ ወር 2005 ዓ.ም ይፋ ያደረገውን የዳሰሳ ጥናትን ለማጥራት ተጨማሪ ጥናትን የሚጠይቅ ነው። በዚህ ጹሑፍ የዚህ ጥናት አካሄድና ውጤቱ ላይ ያስተዋልናቸውን ችግሮች በተመለከተ መጠነኛ ዳሰሳ እናደርጋለን።
የዳሰሳ ጥናቱ በቂ ዝግጅት የተደረገበት አለመምሰሉ፣
የኤሌክትሮኒክስና የሕትመት ሚዲያዎችን በዳሰሰው በዚሁ ጥናት በአዲስአበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ 2ሺ 600 ያህል ተጠያቂዎች መሳተፋቸውን ያሳያል። ይህ የናሙና አመራረጥ ስብጥርንም በተመለከተ ሲያሰፍር ከፌዴራል መ/ቤቶች፣ ከአዲስ አበባ መ/ቤቶች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከቤተመጻህፍቶች፣ ከመዝናኛ ሥፍራዎች… መሆኑን ያትታል። እነዚህ ተቋማት (ሥፍራዎች) በምን መመዘኛ ሊመረጡ ቻሉ፣ ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዓለምአቀፍ ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች ወይንም ተዋንያንና የመሳሰሉት ሊካተቱ ያልቻሉበት ምክንያቱ ምንድነው የሚለውን ጥናቱ በትክክል ምላሽ አይሰጥም። በተጨማሪም ከመላሾቹ መካከል 50 በመቶ ወይም ግማሽ ያህሉ የትምህርት ደረጃቸው ዲግሪና ከዚያ በላይ እንዲሆኑ የተደረገበት ምክንያትስ ገጠመኝ ነው ወይስ ሆን ተብሎ የተደረገ ለሚለውም እንዲሁ ምላሽ የለውም። ይህን ያነሳሁበት ዋንኛ ምክንያት የትኛውም መገናኛ ብዙሃን በተለይም የፕሬስ ውጤቶች የራሳቸው አንባቢያን (ኦዲየንስ ታርጌት) ያላቸው በመሆኑ ነው። አንዳንድ መጽሔቶችና ጋዜጦች አንባቢያቸው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ሊሆን ይችላል። የሌሎቹ ምሁራን ወይም ሴቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ዋናው ነገር የመገናኛ ብዙሃኑ አንባቢ፣ አድማጭና ተመልካች በዕድሜ፣ በጾታ፣ በትምህርት ደረጃ… ሊለያይ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች የበዛ የመሆኑ ጉዳይ ነው። በዚህም ምክንያት የኦዲየንስ ሪሰርች (የአንባቢያንና ተመልካቾች ጥናት) ለማካሄድ ገና ሲታሰብ እነዚህን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ ካላስገባ ውጤቱ የተወሰኑ ወገኖችን ብቻ የሚጠቅምና ሚዛናዊነት የጎደለው ሊሆን እንደሚችል ይታወቃል።
የሚያስገርመው፤ የሕትመት ኢንዱስትሪውን በተመለከተ ከመላሾቹ መካከል አዘውትረው ጋዜጣና መጽሔቶችን እንደሚያነቡ የተናገሩት 28 በመቶዎቹ ሲሆኑ 54 በመቶ ያህሉ ግን አልፎ አልፎ እንደሚያነቡ በጥናቱ ሰፍሯል። በተጨማሪም መላሾቹ መረጃ የሚያገኙበትን ሁኔታ ተጠይቀው አብዛኛዎቹ ማለትም 35 በመቶ ገደማ ከአዟሪዎች ላይ በሳንቲም ተከራይተው የሚያነቡ መሆናቸውን መልሰዋል። ቀጣይነት ያለው የንባብ ባህል ያላዳበሩ መላሾችን በጥናት ውስጥ አብዝቶ የማካተቱ ፋይዳ ምን ውጤት ሊያመጣ ይችላል የሚለው በቅጡ የታሰበበት አይመስልም። ወይንም መላሾች በቅጡ መልስ ሊሰጡበት በማይችሉበት ወይም በማያውቁት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ የመደረጋቸው አግባብነት ጥያቄ ያስነሳል። ከመላሾቹ አጠቃላይ መረጃ ተነስተን አብዛኛዎቹ አልፎ አልፎ ብቻ የሚያነቡ (54 በመቶ ናቸው) ናሙናዎችን መነሻ አድርጎ የተካሄደ ጥናትስ ተቀባይነቱ፣ ተአማኒነቱ አሁንም ጥያቄን ማጫሩ የሚቀር አይሆንም።
ወቅታዊነትን ያልጠበቀ መሆኑ፣
የትኛውም ጥናት የሚሰራው በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለይቶ ለማረም፣ መልካም ጎኖችን ለማጎልበት እንደሆነ ይታመናል። በዚህ ምክንያት ይህ ጥናት ከተካሄደ ከአንድ ዓመት በኋላ መለቀቁ በዚህ ወቅት ያለውን ተጨባጭ የሚዲያ ከባቢ ለማሳየት አቅም የሚያንሰው አድርጎታል። ይህም ብቻ ሳይሆን ውጤቱም ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣረስ ሆኗል።
ለዚህ ትንሹ ማሳያ ይህ ጥናት ይፋ በተደረገበት በዚህ ወቅት በጥናቱ የላቀ ውጤት ካገኙት ፕሬሶች መካከል እንደፍትህ፣ ፍኖተ ነጻነት፣ ነጋድራስ፣ መሰናዘሪያ፣ (ጊዜውን ጠብቆ እየወጣ አይደለም) እና የመሳሰሉ የሕትመት ውጤቶች በተለያዩ ምክንያቶች ከገበያ ከወጡ የመቆየታቸው ጉዳይ ነው። ምንም እንኳን ጥናቱ በተሰራበት ወቅት እነዚህ ፕሬሶች በሕትመት ላይ ነበሩ የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ ቢችልም በአሁኑ ወቅት ሕትመት ላይ የሌሉትን እንዳሉ በማስመሰል የጥናት ውጤት ይፋ ማድረግ ባለስልጣኑን በእጅጉ የሚያስገምት ቀሽም ስህተት ነው። በተለይ ፍትህና ፍኖተነጻነት ጋዜጦች ከሕትመት የወጡበት ምክንያት ጀርባ የባለስልጣኑ እጅ እንዳለበት በይፋ እየተናገሩ ባሉበት ሁኔታ ሕትመቶቹ በስራ ላይ እንዳሉ አስመስሎ የጥናት ውጤት በዚህ ወቅት ይፋ ማድረግ በስህተት ወይም በገጠመኝ የተከሰተ ነው ብሎ ማለፍ ያዳግታል። እንዲያውም አድራጎቱ ባለስልጣኑን የሚያስገምት ነው።
በጥናቱ የተካተቱ የተሳሳቱ መረጃዎች፣
መቼም አንድ አገር አቀፍ ጥናት ሲሰራ ለውጥ ያስገኛል ተብሎ ነውና መረጃዎቹ ተአማኒ እንዲሆኑ የማድረጉ አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም። በጥናቱ ይፋዊ ዶክመንት ላይ “ተዘውታሪ ጋዜጦችና መጽሔቶች” በሚል ርዕስ “አዲስ ጉዳይ መጽሔት”ን በተራ ቁጥር 5 ላይ ያስቀምጠዋል። ወረድ ብሎ ደግሞ በተራ ቁጥር 13 ላይ “ሮዝ መጽሔት” በሚል ደረጃ ይሰጣል። የሚገርመው ግን ጥናቱ በተሰራበት ወቅትም ቢሆን “ሮዝ” የሚባል መጽሔት አለመኖሩ ነው። ለምን ቢባል የቀድሞ ሮዝ መጽሔት፤ አዲስ ጉዳይ በሚል ስያሜ መለወጡን ከሁለት ዓመት በፊት ያጸደቀው ራሱ ባለሰልጣኑ ነበር። ባለስልጣኑ ግን በጥናቱ ውስጥ ሮዝ እና አዲስ ጉዳይ መጽሔትን የተለያዩ ሁለት መጽሔቶች በማድረግ፣ በገበያ ላይ ያልነበረ መጽሔትን እንደነበረ አድርጎ አጥንቻለሁ እያለን ነው። ሌላ ላክል፤ “ጽጌሬዳ” በመባል የሚታወቅ መጽሔት ከሕትመት የወጣው በ1997 ዓ.ም ገደማ ነበር። ይህ መጽሔት ከሕትመት ከወጣ ከሰባት ዓመት በኋላ በሚያዚያና ግንቦት ወር 2004 ዓ.ም ባለስልጣኑ ባካሄደው ጥናት ተነባቢ መጽሔት ሆኖ እንዳገኘው እያበሰረን መሆኑ አስቂኝ ነገር ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በሕትመት ላይ ያሉ እንደሰብሰሃራን ኢንፎርመር፣ ሊግ ስፖርት፣ ናሽናል ኮንስትራክሽን፣ ቱባ፣ ዘመን እና የመሳሰሉ ጋዜጦችና መጽሔቶችን በጥናቱ ሳያካትታቸው ቀርቷል። ይህ ግድፈት ባለስልጣኑ እከታተላቸዋለሁ የሚላቸውን የፕሬስ ውጤቶች በቅጡ እንኳን ለይቶ እንደማያውቃቸው በቂ ማሳያ ነው።
በዚሁ ጥናት ከገበያ ከወጣ አንድ ዓመት እየደፈነ ያለው ፍትህ ጋዜጣ በ4 ኛ ደረጃ ሲቀመጥ ነጋድራስ በ21 ደረጃ ተቀምጧል። ጥናቱ በተሰራበት ወቅት ጋዜጦቹ በሕትመት ላይ የነበሩ ከሆነም በዚህ ወቅት ጥናቱ ሲለቀቅ ከገበያ መውጣታቸው ታሳቢ ተደርጎ ተስተካክሎ በሕትመት ላይ ያሉትን ብቻ ሊያሳይ በሚችል መልክ መቅረብ ነበረበት። አለበለዚያም በግልጽ ጋዜጦቹ በዚህ ወቅት እየሠሩ አለመሆኑን (ሕትመታቸው መቋረጡን) በጥናቱ ውስጥ ማመልከት ይገባ ነበር። ለምን ቢባል በባለስልጣኑ ሴራ ከገበያ ወጥተናል የሚሉ ጋዜጦችን አሁንም እንዳሉ አስመስሎ በጥናት አካቶ ማቅረብ ራስን ከማታለል በላይ ዋጋ ያለው ነገር አይደለምና ነው። ይህ ዓይነቱ ትንሽ የሚመሰል ግን ግዙፍ ስህተት የጥናቱን ተአማኒነት በእጅጉ ጎድቶታል።
ባለስልጣኑ በሰኔ ወር 2005 ዓ.ም በስርጭት ላይ ይገኛሉ ብሎ ከዘረዘራቸው 25 መጽሔቶች መካከል በዚህ ጥናት የተካተቱት ዜና መጽሔት፣ ሮዳስ፣ ፋሽን፣ሃትሪክ ስፖርት፣ ታይም፣ ዘኢኮኖሚስት፣ ኒውስዊክ መጽሔቶች አልተካተቱም። ምናልባት ዘኢኮኖሚስት፣ ኒውስዊክ፣ ታይም የተባሉት የውጪ አገር መጽሔቶችን ለማለት ተፈልጎ ከሆነም ሌላው የጥናቱ አንድ መሠረታዊ ችግር ተደርጎ የሚታይ ነው። የቋንቋ፣ የዕድሜ፣ የተደራሽነት ፣የአቅም ሰፊ ልዩነት ያላቸውን የአገር ውስጥና የውጪ አገር ሕትመቶች በአንድነት ላይ ለመመዘን መሞከሩ በራሱ ችግር ያለው ሲሆን በዚህ የተሳሳተ መረጃም የአገር ውስጥ ጋዜጦችና መጽሔቶች ከውጪዎቹ ጋር ተወዳድረው የተሻለ ተነባቢ ሆነዋል የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስም ፌዝ ይሆናል።
በተጨማሪም የፖለቲካ ልሳናትን ከቢዝነስ ጋዜጦች ጋር ቀይጦ ማጥናቱ ራሱን የቻለ ትልቅ ስህተት ነው። ለምሳሌ በጥናት ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ የአንድነት ፓርቲ ልሳን የነበረው “ፍኖተ ነጻነት” ጋዜጣ፣ የኢህአዴግ ልሳናቱ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ”፣ “አዲስ ራዕይ”፣ “ወይን” የተባሉ የሕትመት ውጤቶችና እናገኛለን። ልሳናቱ በዓላማቸውም ሆነ በባህርያቸው እንዲሁም በአንባቢዎቻቸው ትኩረት ከቢዝነስ ጋዜጦች ይለያሉ። ልሳናቱን በአመዛኙ ያነቧቸዋል ተብሎ የሚገመቱት የየፓርቲዎቹ አባላቶችና ደጋፊዎቻቸው ናቸው። እንደቢዝነስ ጋዜጦች አንዱ ከሌላው ተወዳድረው የሚሸጡ አይደሉም፤ እንዲህ እንዲሸጡም ባህሪያቸው አይፈቅድላቸውም። ለአብነት ያህል አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ወይን፣ አዲስራዕይ የተባሉት የኢህአዴግ ልሳናት በኮፒና በስርጭት ብዛት ከተዘረዘሩት ሕትመቶች ጋር ሲነጻጸሩ ላቅ ያሉ መሆናቸው የሚካድ አይደለም። በጥናቱ ውጤት መሰረት ግን እነዚህ ከሰላሳና አርባ ሺ ኮፒዎች በላይ ስርጭት ያላቸው ልሳኖች ያውም አልፎ አልፎ በሚያነቡ ተጠያቂዎች ተነባቢ እንዳልሆኑ ተደርገው እንዲቀመጡ ሆኗል። ይህ የዳሰሳ ጥናት ሕትመቶችን በባህርያቸው ለይቶ ማየት አለመቻሉ ዘይትና ውሃን ለማደባለቅ የመሞከር ያህል ነው።
በመጨረሻም፤ ጥናቱ የቱንም ያህል ጉድፎች ቢኖሩበትም ባለስልጣኑ እንዲህ ዓይነት ጥናት በማካሄድ በኤሌክትሮኒክስም ሆነ በሕትመት ሚዲያዎች የሚታዩ ድክመቶችን ለማረም ያሳየው ተነሳሽነት የሚደነቅ ነው። ለቀጣይ በሚካሄዱ መሰል ጥናቶች ቢያንስ የዘርፉን ባለቤቶች (የዘርፉ ተዋንያንን) ከማግለል ይልቅ ለማሳተፍ በመሞከር፣ ሒደቱም ወቅታዊነቱን የጠበቀ በማድረግ፣ ተአማኒነት የተላበሰ የጥናት ውጤት ለማቅረብ ይተጋ ዘንድ ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።
(ምንጭ፡-ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 412 ረቡዕ ሐምሌ 24/2005)
No comments:
Post a Comment