Wednesday, July 31, 2013

የነጻነት ዋጋ ስንት ነው መጽሐፍ

ክፍል አንድ
የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ


ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል ሰውንም የሚያረክሰው ነው
ማቲዎሰ 1519
ምስጋናና አድናቆት፣
· ለመጪው ትውልድ ትምህርት የሚሰጥ፣ በታሪክም ሊዘከር የሚችል ብዙ ነገር እንደያዙ ወደ መቃብር የሚሄዱ አሉና አቶ ግርማ ሰው ሊያወቀው ይገባል ያሉትን ምንም ይሁን ምን ጽፈው በማቅረባቸው ላመሰግናቸው እወዳለሁ። እኔስ ይህችን አስተያየት እንድጽፍ ምክንያት ሆኖኝ የለ።

· አንድነትና መድረክ ውሃና ዘይት ሆነው በቀረቡበት ምርጫ አቶ ግርማ እጩ ሆነው ለማሸነፍ ያደረጉት ጥረት አድናቆት የሚቸረው ነውና እነሆ አድናቆቴ ይድረስዎ ብያለሁ። የምርጫ ዘመቻ ኃላፊ ሆና የሰራችው እህታቸውም ተግባር ለእህቶቻችን ምሳሌ የሚሆን ነውና የአድናቆቴ ተካፋይ ነች።የሴቶች ችግር ድፍሮ አለመግባት እንጂ ከገቡ ውጤታማ የፖለቲካ ስራ እንደሚሰሩ የጥሩ ዘር የምርጫ ዘመቻ ኃላፊነት አፈጻጸም በቂ ማሳያ ነው። 

መነሻ
አቶ ግርማ ቀጥተኛ ተሳታፊ ባልሆኑበትና በሰሙት ወይንም ሁለተኛ ደረጃ መረጃ ባገኙት ጉዳይ ሳይቀር በጣም እርግጠኛ ሆነው ድምዳሜ እየሰጡ ነው የጻፉት። ለምሳሌ አቶ ግርማ የቅንጅት ምክር ቤት አባል አልነበሩምና ስለ ውሳኔዎቹ የሚያውቁት በስሚ ነው። ነገር ግን በቦታው እንደነበሩና አብረው እንደወሰኑ ሆነው ጽፈዋል። / ኃይሉ ሻውል፣ / አለማየሁ አረዳን ኢህአዴግ ነው ብለው ይጠረጥሩታል ብለው ርግጠኛ ሆነው የጻፋትም ለድፍረታቸው ሌላው ተጠቃሽ ነው። በቃለ ምልልስ የሚናገሩዋቸውም ሆነ በአንዳንድ የህትመት ውጤቶች ላይ የሚጽፏቸው ለራስ የተለየ ግምት ከመስጠት የሚመነጩ አገላለጾች በመጽሀፉም ውስጥ መታየታቸው ለሶስት ዓመታት ብቸኛው ተቀዋሚ የፓርላማ አባል እየተባሉ መጠራታቸው የፈጠረው ስሜት ይሆን ብዬ ሰጋሁ።ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላልማቲዎሰ 2312
ጥቂቶች ከበው ፈርምልን ስላሉዋቸው፣ ጥቂቶች በአዳራሽ ንግግራቸው ስላጨበጨቡላቸው፣ ጥቂቶች በየመንገዱና መጠጥ ቤቱ አድናቂህ ነን ስላሉዋቸው ወዘተ 90 ሚሊዮን ሕዝብ ያመናቸው የተከተላቸውና የወደዳቸው አድርገው በማሰብ የምንናገረውን ሁሉ እውነት፣ የምንሰራውን ሁሉ ትክክል ነው ብሎ ይቀበለናል በማለት ራሳቸውን ያልሆኑት ብቻ አይደለም፤ ሊሆኑም የማይችሉበት ቦታ በማስቀመጥ ብዙዎች አይወድቁ አወዳደቅ ሲወድቁ አይቻለሁና አቶ ግርማም እዚህ መስመር ውስጥ እየገቡ መሆኑ ስለተሰማኝ ነው መስጋቴ። በዚህ ሁኔታ የት ይደርሳሉ ያልናቸውንና ብዙ ተስፋ የጣልንባቸውን ሰዎች አጥተናል። አቶ ግርማም ገና እድገታቸውን ሳይጨርሱ የውድቀቱን መንገድ የጀመሩት ይመስላል። ፖለቲካም እንደ ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ሆኗል።
አቶ ግርማ ስለ ቅንጅትና አንድነት የሂደቱ ዋና ተዋናይ የነበሩ በሚመስል መልክ ነካክተዋል። ማን ያርዳ የቀበረ ማን ይናገር የነበረ እንዲሉ የሁለቱም ሂደት ተካፋይ ነበርኩና የማውቀውን ልጻፍ ብዬ ሳስብ አንድ ጥያቄ ከህሊናዬ ድቅን አለብኝ። ህብረተሰቡ በሁለቱም ፓርቲዎች የተፈጠረውን አሳዛኝ ነገር ከልቡ ፍቆና ከትውስታ ማህደሩ አጥፍቶም ባይሆን ለመርሳት ሞክሮ የፖለቲካ ተሳትፎው እያንሰራራ ባለበት በዚህ ወቅት (ምርጫ 2007 ዋዜማ) ቁስሉን ነካክቼ መጥፎ ትውስታውን ቀስቅሼ እየጎዳው ይሆን ብዬ አሰብሁ። ሰዎች እውነትን እያዛቡ እንደ ስሜትና ፍላጎታቸው የሚናገሩትና የሚጽፉት ውሸት ወደ ታች ስር የሚሰደውና ወደ ላይም አብቦ የሚያፈራው ዝም ሲባልና እውነት ረጋግጣ እንድታደርቀው ማድረግ ሳይቻል ሲቀር ነው። እናም የአቶ ግርማን መጽሐፍ አንብቤ በዝምታ ማለፉ ተገቢ መስሎ አላገኘሁትም። ስለሆነም ቅንጅትና አንድነትን በተመለከተ አቶ ግርማ ባነሱት ጉዳይ ላይ አስተያየት የምሰጠው በዚህ መንፈስ በተቻለ መጠን ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ ይሆናል።
ከዛ በፊት ግን አንዳንድ ጉዳዮችን እንቃኝ። መጽሐፉ ወደ ማተሚያ ቤት ከመግባቱ በፊት አንድ ሁለት ወዳጆች ለጠቅላላ አስተያየት፣ እንዲሁም ለሥነ ጽሁፋዊ ይዘቱ ባለሙያ ቢያየው መልካም ነበር። ይህ አለመሆኑን ገና መግቢያውን ሳይጨርሱ ማወቅ ይቻላል። በመሆኑም ተገቢነት የሌላቸው ቃላት ፣እርስ በርስ የሚጣረሱ ገለጻዎች፣ መረጃ የማይቀርብባቸው የድፍረት ድምዳሜዎች ወዘተ በብዛት አሉበት። ሀራምባና ቆቦ ስለሚረግጥም የታሪኩ ፍሰት ተዛብቷል። ከቡና ላይ ወሬ ሊዘሉ የማይችሉ ነገሮችም ተካተውበታል፤ በተለይ ጸሐፊው የተከበሩ የፓርላማ አባል ከመሆናቸው አንጻር የሚናገሩትም ሆነ የሚጽፉት ይህን ደረጃቸውን የጠበቀ (ብዙ ቦታ ስለ ፕሮቶኮል ይገልጻሉና) በአጠቃላይ አድማጭ አንባቢውን፣ በተለየ ደግሞ የመረጣቸውንና የወከሉት የህብረተሰብ ክፍልን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን የተገባ ነው። አጠቃላይ ግምገማውን ለባለሙያ ልተወውና ከተነሳሁበት ጉዳይ አንጻር ብቻ ጥቂት ማሳያዎችን ላቅርብ።
3 - ተገቢነት የሌላቸው ቃላት፣

· አሮጌ ውሻን ማስተማር ከባድ ነው ካልተባለ በስተቀር (ገጽ 7)

· በሀገራችን ፖለቲካ ዋንኛ ፈትፋች ስለሆንኩ ነው። (ገጽ 11/12)

· የየእለቱን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በስልክ በግንባር እየተገናኘን አመነዠክን። (ገጽ 22)

· ይህን እድፍ ሊያጸዳ የሚችል የማስተርስ ፕሮግራም በዓለም ላይ ያለ አይመስለኝም፡ (ገጽ 36)

· እኒህ የተማሩ ተብዬ ሲቪል ሰራተኞች ነጻ አውጪ እየጠበቁ ያሉ የመንግሥት ሎሌዎች ናቸው፡ (ገጽ 71) (በምርጫ 2002 ፓርላማ የመግባት ህልማቸውን ለማሳካት ለእውነትና ለህሊናቸው ሳይሆን ለአንድነት አመራር አጎብድደው ፓርቲውን የጎዱ ሰዎችን ዝም አንልሞች ሎሌ ማለታቸውን አቶ ግርማ ኮንነዋል (ገጽ 58 ርሳቸው ሲሉት ግን ቅዱስ ነው)

· 1997 ምርጫ አንጎቨር ባለቀቀው ስሜት ሀሳባቸውን አካፈሉኝ፡ (ገጽ 74)

· ሽማግሌ ተብዬዎች (ገጽ 91)

እነዚህ የተሰመረባቸውና ሌሎች በመጽሐፉ ውስጥ ያሉ ተመሳሳይ ቃላት ተኪ ቃል ሊገኝላቸው እየተቻለ አይደለም ባይገኝላቸው እንኳን እንዲያስተላልፉ ከተፈለገው መልእክት ይልቅ ጸሐፊውን ማስገመታቸው ሚዛን ይደፋል።

እርስ በርስ የሚጣረሱ ገለጻዎች፡
· ገና በመግቢያው ገጽ 9 ላይፍርሀት ሸብቦ ይዞን ነጻነታችንን ለድርድር እያቀረብን…” በማለት ጀምሮ ብዙ ቦታ ሕብረተሰቡን ፈሪ የሚለው የአቶ ግርማ መጽሐፍ ገጽ 75 ላይ ደግሞነገር ግን ሕብረተሰቡን በተወሰነ ደረጃ በዕቅድ እየተመራን ተጠናክረን ከደገፍነው በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታም ቢሆን ለአማራጭ ኃይል ደምጽ ሊሰጠን ዝግጁ መሆኑን የሚያሳይ ነውበማለት ደፋር ያደርገዋል። የአቶ ግርማ የጠራ እምነት የቱ ነው። ሕዝቡ የሚያምነው አማራጭ፣ ለድል ያበቃኛል የሚለው ፓርቲ፣ ቃሉን ጠብቆ የሚገኝ መሪ አጥቶ አንገቱን ደፍቶ መቀመጡ ፈሪ ያሰኘዋል?አቶ ግርማ ቢያንስ 1997 ምርጫን የሕዝብ እንቅስቃሴ ማስታወስ እንደምን ቸገራቸው? ውጤት የማን ነበር?

· “በአንድ ቀን 2000 የዕጩ ፖስተርና 500 የብርቱካን ሚደቅሳ ምስል ያለበትብርቱካን ትፈታየሚል መልእክት ያለበት ፖስተር በአራት ቡድን ተከፋፍለን አጠናቀቅን” (ገጽ 80) አቶ ግርማ ይህን ፈጽሞ ይረሱትና ገጽ 139 ላይብርቱካን በእስር እያለች በምርጫ ቁሳቁሶች ሁሉ የብርቱካን ምስል መኖር አለበት ከሚሉት ጋር አልስማማም ነበር። ለዚህም ነው በእኔ የምርጫ ዘመቻ ወቅት በቅስቀሳ ቁሳቁሶች ላይ የብርቱካን ምስል የሌለውይሉናል፤ የትኛውን እንመን። አንዲህ አይነቱ ነገር አጠቃላይ የመጽሐፉን ተአማኒነት ይጎዳዋል። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ በዚሁ እግረ መንገድ አንድ ጥያቄ ላንሳ።የብርቱካንን ጉዳይ ርሱትና ምርጫው ላይ አተኩሩልንበማለት ዲፕሎማቶችን ይማጸኑ ከነበሩት ሰዎች ጋርስ አይስማሙም ነበር?

· “አንድነትን የመሰረቱት የቅንጅት አመራር አባላትሌላ የግል አጀንዳ ያልነበራቸው ይልቁንም በሙሉ ልብ የዚህች ሀገር ፖለቲካ በትብብር መያዝ ይኖርበታል ብለው ያመኑ የነበሩ ናቸውብለው ገጽ 53 ላይ በልበ ሙሉነት አስነብበውን ብዙም ሳንሄድ ገጽ 57 ላይለእኔ ብዙም ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ የሚመሰረተውን ፓርቲ ለመምራት የሥልጣን ሽኩቻ እንደነበረ በግልጽና በሹክሹክታ ይሰማ ነበርይሉናል። ሰዎቹ ምንም የግል አጀንዳ ያልነበራቸው ከሆኑ የሥልጣን ሽኩቻው ድንገት በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የተፈጠረ ነው እንበል? እንዴት ሆኖ። የሥልጣን ሽኩቻ እንደነበረ ከሰሙስ ሌላ የግል አጀንዳ ያልነበራቸው የሚል ምስክርነት ለመስጠት እንደምን ደፈሩ። መጽሐፉ ማስተዋል የጎደለው የሌሎች ሰዎች እርዳታም ያልጎበኘው መሆኑ ነው ለዚህ አይነት ጉልህ ስህተት ያበቃው።

እውነት ሳይሆን ድፍረት፣
· “ልደቱም ከዶ/ አለማየሁ ጋር ከተስማማ ቅንጅት ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ ለመሆን የሚከለክለው እንደሌለ አምኗል” (ገጽ 31) አቶ ግርማ ከልደቱ ተገናኘተው ራሱ ነግሮአቸው ካልሆነ በስተቀር አምኗል የሚለው ማስረጃ ሊቀርብበት አይችልም። ሁለቱ ደግሞ እዚህ ደረጃ የደረሰ መቀራረብ ያላቸው አይመስለኝም። ማስረጃ የማይቀርብበት ነገር ደግሞ አሉባልታ ይሆናል።

· “/ አለማየሁን መኢአዶች እንደማይመርጡት ይታወቃል፣ ምክንያቱም / ኃይሉ ሻውል በግልጽ በርሱ የፖለቲካ አቋም እምነት የላቸውም፣ እንደውም ኢህአዴግ ነው ብለው ነው የሚጠረጥሩት” (ገጽ 32) አቶ ግርማ የቅንጅት ምክር ቤትም ሆነ የሥራ አስጻሚ አባል አልነበሩም። ከኢ/ ኃይሉም ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው አልገለጹም፣ ታዲያ ምን ሰምተው ምን አይተው ነው፡ይታወቃል፣ እምነት የላቸውም የሚጠረጥሩትየሚሉትን ርግጠኛነትን የሚገልጹ ቃላትን ለመጠቀም የበቁት፤ ለእኔ ይህ ድፍረት ነው፤ ያውም ለራስ ያልተገባ ቦታ ከመስጠት መታበይ የሚመጣ ድፍረት።

· “የሚያሳዝነው ብርቱካንን ያሰራት ኢህአዴግ ሆኖ ሳለ እንዲሁም በአንድነት ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ የሥልጣን ተዋረድ እያለ እና ብርቱካን ስትታሰር ድርጅቱን ማን እንደሚመራ በግልጽ እየታወቀ በአንድነት ምርጫ ግዜ የተለያዩ ተፎካካሪዎችን በመደገፍ ግልጽ አቋም ይዘው የነበሩ ሰዎች በብርቱካን እስር የነዚህ ተፎካካሪዎች (በግልጽ / ግዛቸውና / ያዕቆብ በመጨረሻ / ያዕቆብ ከፓርቲ ሲለቅ ውንጀላው ቀርቶለት ከወንጃዮቹ ጋር አጋር ሆኗል ) እጅ አለበት የሚል የሴራ ጉንጎና የተጀመረው። (ገጽ 58) አንቀጹ ግልጽ የሚል ቃልን አራት ግዜ ከመደጋገሙ በስተቀር ራሱ ግልጽ አይደለም። ይህ ደግሞ በእውነት ሳይሆን በድፍረት ሲጻፍ የሚያጋጥም ችግር ነው። ብርቱካን በታሰረችበት ወቅት የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ አባል ነበርኩና አንደ አቶ ግርማ በድፍረት ሳይሆን በግዜ በቦታና በድርጊት በበቂ ማስረጃ መግለጽ እችላለሁ። ግን አሁን ምን ይጠቅማል። አቶ ግርማ የፓርላማ ቆይታቸውን ለሁለተኛ ዙር ለማራዘም አስበው የምርጫ ዘመቻ በግዜ መጀመራቸው ይሆን!!

ለማንኛውም ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ በአጭሩ
_ ብርቱካን በፖሊስ ስትጠራ አመራሩ ከጎኗ ሊቆም ሲገባ የራስሽ ጉዳይ ብሎአል። እንጂ ለእስራቷ እጁ አለበት አልተባለም። አቶ ግርማ ለዚህ አንድም ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም።

_ የኢ/ ግዛቸውን ተተኪ ሊቀመንበርነት ማንም አልተቃወመም። ጥያቄው የነበረው ተገቢ አመራር ስጥ ነው።

_ / ያዕቆብ ከሊቀመንበርነት ፉክክሩ የወጡት ጉባኤው ከመድረሱ አስቀድሞ በመሆኑ ለውድድር የቀረቡት / ግዛቸውና / ብርቱካን ናቸው። አቶ ግርማ ከፈለጉ ሁለቱ ያገኙትን ድምጽም ልነግራቸው እችላለሁ። ሙሉ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱንና የቆጠራ ውጤቱን የሚገልጸው ሰነድም በቢሮ ይገኛል የሰነድ አያያዛችሁ አያስተማምንም እንጂ።

_ ሴራ ያሉትንና ለማለትም ያበቃዎትን አንድ ሁለት ምሳሌና ማስረጃ ቢያቀርቡ ለውይይት ያመች ነበር። በወቅቱ የተባሉ የተደረጉት ሁሉ የፓርቲውን ሕገ ደንብ ተከትለው ነው። አንድነት መስመሩን እየሳተ ነውና ወደ መስመሩ ለመመለስ ይቻለን ዘንድ እንወያይ ማለት በምን መስፈርት በምንስ አረዳድ ነው ሴራ የሚሆነው? ከመድረክ ጋር የሚፈጠረው ግንኙነትሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ያፈታልእንዳይሆን ይመከርበት ይታሰብበት ማለት እንደምን ሴራ ይሰኛል? ለፓርቲው ፕሮግራም ተግባራዊነት እንትጋ፣ ለህገ ደንቡ እንገዛ፤ ካለው ተምረናል የምንለውን በተግባር እናሳይ ወዘተ ማለትን ምን አይነት ህሊና ነው ሴራ የሚለው? አቶ ግርማ አንድም የተጣሰ መርህ እስከዛሬ ሳይታየኝ አለሁ ብለዋልና ያንን ለማሳየት ስሞክር እነዚህንም ለማብራራት እሞክራለሁ። የሳምንት ሰው ይበለን።¾ 


(ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ 8 ዓመት ቁጥር 412 ሐምሌ 24/2005)በታምራት ታረቀኝ

No comments:

Post a Comment