Saturday, July 27, 2013

ሃይማኖት እና ብሄር ካለፈው እና ከአሁኑ ታሪካችን ተምረን ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እንታገል

by Ephrem Shaul
የዚህ ጹሁፍ አላማ ከታሪክ ስህተቶቻችን ተምረን ወደፊት የማይደገምበትን እውነተኛ ዲሞክራሲ ለሁላችን መፍጠር ላይ ትንሽ ሀሳቤን ለማካፈል ነው። የኢትዮጲያ ህዝብ ታሪክ ጥሩም መጥፎም ታሪክ እንደማንኛውም ሀገር አለን። አኩሪ ታሪክ ያመሰገብን እንደመሆናችን ሁሉ ክፉ የታሪክ አሻራም አለን። ዜጎች በነጻነት ለመኖር ያልታደልንበት አሳዛኝ እና አስከፊ ግዚያቶች በታሪካችን ጎልተው ይታያል። አሁንም በአስከፊ ሁኔታ በወያኔ ኢሃዴግ ተጠናክሮ አፈናው ቀጥላል። በዚህ እውነት ውስጥ የሚነሳው የኦሮሞ ህዝብ መበደል፣ አስከፊ እንዲሁም አሳዛኝ ሰቆቃ ነው። ይህ አስከፊ እንዲሁም አሳዛኝ ሰቆቃ መከሰቱ እጅግ አሳዛኝ ነው። መከሰቱን መካድ መፍትሄ አይደለም። የተፈጠረውን ግፍና ችግር በአግባቡ ተረድተን ስናበቃ ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣውን መንገድ መምረጥ ብልህነትና የዚህ ትውልድ የታሪክ ሃላፊነት ነው። የሰውነትና የዜግነት ግዴታም ነው። በተመሳሳይ የምናነሳው የኢትዮጲያ ሙስሊሞችን አሳዛኝ በደል ነው። አስልምና በአርብ ሀገራት ከፍተኛ ችግር በገጠመው የታርክ ዘመን ኢትዮጲያ ተቀብላ ያቆየችበት ታሪክ እንደመኖሩ ሁሉ አሳዛኝ ችግሮችም አሉ። ይህን በደል ተረድቶ ለሁሉም ዜጋ የምትሆን ኢትዮጲያን መፍጠር ግዴታችን ነው።
ይህ የታሪክ ክፉ ኣሻራ በኦሮሞ ክርስቲያኖችም ላይም ተፈጽማል። የሁሉም ብሄር ተወላጅ በሆኑ ፕሮተስታንት ተከታዮች ላይ ተፈፅማል። ኣርቶዶክስ ኢትዮጲያዊያን ላይ አሁን ያለው ስርአት ጣልቃ ገብቶ መቆጣጠሩ የታወቀ ነው። በሃገራችን ታሪክ ኦሮሞ፣ ሶማሌው አፋሩ ጋንቤላው አማራው ትግሬው ውላይታው ጉራጌው ሲዳማው ከንባታው ሱሪው ኮንሶ ኮሬ አደሬዉ ቤንሻንጉሉ ወዘተ ተበድላል። ሁላችን በታሪካችን ውስጥ ብሶት አለን። ይህን እውነት (fact) በአግባብ መረዳትና ማስረዳት ወሳኝ የአክቲቪስትና የፖለቲከኛ ስራ ነው። በአንጻሩ ደግሞ እምነትን መስበክ በሰላማዊ ትምህርት ማስፋፋት የሃይማኖት አባቶች (ቄስ ሽክ ፓስተር ወዘተ) ስራ ነው።
ፓለቲከኞች የራሳቸውን እምነት ለራሳቸው ይዘው ለሁሉም ዜጋ የሚሆን (ለሁልም ብሄር እና እምነት) በነጻነት እና በክብር የምንኖርበትን ሀገር እውን ለማድረግ መረባረብ አለባቸው።  ግዜን እውቀትን ገንዘብን አቅምን ማዋል ያለብን እዚ ላይ ነው። የሚባክን ግዜ የለንም የዜሮ ድምር ፓለታካም አያስፈልገንም። የእምነት ትንታንኔ ስራና አስተምህሮት የሃይማኖት አባቶች ስራ ነው። የፖለትቲከኛ ስራ ጨርሶ አይደለም። ይህን ብሄር ያንን እምነት የበላይነት ለማምጣት መሞከር ኢፍትሃዊና ኢዲሞክሪያሲያው ነው። የታሪክን ችግር መድገም ነው። የዲሞክራሲ ትግሉን አላማ መሳትና ግዜውን ማርዘም ነው። የራስን በደል ብቻ መመልከት ሌላውን አይመለከተኝም ማለት የታሪክን በደል እንደመካድ ይህም ስህተት ነው። የሁሉንም በደል ተረድተን በጋራ መስራት አርቆ አሳቢነትና አስተዋይነት ነው። ለሁላችንም ነጻነትና ፍትህ የምትሆን አገርን መገንባት ትክክለኛ ራዕይ: ድፍረት: ቆራጥነት ይጠይቃል። የአመራር ችሎታ ግድ ይላል። ይህ ወያኔ ኢሃዴግ እንደሚለው በወሬ ሳይሆን ተግባራዊ ቁርጠኛነት ይጠይቃል። ይህ የትላንት እና የዛሬ በደሎችን እንዳይደገም ዋስትና ይሰጣል ዘላቂ መፍትሄውም ይህ ብቻ ነው። ቅንነትን ሁላችን ከያዝን ከባድ አይደለም። የአመራር ችሎታ ማለት (leadership quality) ህዝብን ፍትሃዊ በሆነ ስርአት የዜጎችን ነጻነት አክብሮ እና አስከብሮ መምራት ማለት ነው። ግጭት አምጪ ሀሳብችን ወይም ድርጊት ማስፋፋት ለማንም አይጠቅምም የአመራር ችሎታም ጨርሶ ኣይደለም። አሳዛኝ የታሪክ ስህተቶችን ተረድተን ካለፈው ስህተት መማር ወሳኝ ነው። ነገር ግን የተፈጠሩ ስህተቶችን ተከትለን ሌላ ኢፍትሃዊ ስርአት ለማምጣት ማስብ የለብንም በጣም አደገኛ ስህተት ነው። ከችግሩ ሳንወጣ እዛው እንድንዳክር ከማድረጉም በላይ እንደ እስተሳስብም የተሳሳተ አካሃድ ነው።
በኢትዮጲያ ውስጥ ለኢትዮጲያ አንድነትና ነጻነት የታገሉ የታሪክ ደማቅ አሻራ የጻፉ የተለያየ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጲያዊያን (ሙስሊምና ክርስትያን) በገዛ ሀገራችን በታሪክ ተበድለን መቆየታችን አሳዛኝ ነው። ያልተበደለ ህዝብ የለም በዳዪ ደግሞ አንድ ቡሄር አይደለም። በአንድ ብሄር ስም ስልጣን ላይ የወጡ ገዥ መደቦች ናቸው (የተለያዮ አምባገነን ስርአቶች ናቸው) በስልጣልን ላይ ያለው የወያኔ ሰርአት ከትግራይ ህዝብ ተለይቶ መታየት አለበት። ስርአትንና ብሄርን ለይቶ ማየት ለአክትቪስት ወይም ፖለቲከኛ ሀሁ/ABCD ነው። አሁን ስልጣን ላይ ያለው ሰርአት በኦሮሞ ላይ የሚያደርሰውን በደል የሚያስፈፅምለት ኦህዴድ ተብሎ የተደራጀው የኦሮሞ ተወለጅ ናቸው። በተመሳሳይ በአዴን በአማራው ላይ፣ ህውሃት በትግራይ ህዝብ ላይ ደህዴን በደቡብ ፤ አጋር የሚላቸው ድርጅቶች በሶማሌው፣ በጋምቤላው በአፋሩ በቤንሻንጉሉ ላይ ተጋግዘው ነው ህዝቡን ስቃይ የሚያበሉት። ይህ እውነታው ነው፤ ይህንንም መቀበል የተሳሳተ መስመር ከመከትል ያድናል መፍትሄውም የአሁኑን የአንባገነንነት ስርአት የመጨረሻ አድርጎ ዲሞክራሲ ለሁሉም ለማስፈን መታገል ነው። ከታሪክ በአግባብ ተምረን ስናበቃ ስህተቱን አውግዘን መልካሙን ደግም ለማበልጸግ መስራት አለብን። ከታሪክ መማር እንጂ የታራክ እስረኛ መሆን የለብንም። ራእይ ያለው ትውልድ መሆን ያስፈልጋል። ራዕያችን ደግሞ ዲሞክራሲያዊና ሁሉን ያሳተፈ መሆን አለበት (inclusive democracy)። ውድድር የበዛበት አለም ውስጥ ነው የምንኖረው። ችግራችንን ለዘለቄታው በአፋጣኝ ፈተን አስከፊ ስርአትን ለውጠን በአዲስ መንፈስ በፍትህና ዲሞክራሲ መመራት አለብን። ከታሪክ መማር ወሳኝ የመሆኑን ያህል ፤ የታሪክ እስሪኛ መሆን ለግለሰብም፣ ለቤተሰብም፣ ለብሄርም፣ ለእምነትም፣ ለሃገርም ሆነ ለአለምም አይጠቅምም።  ወደ ሃላ እያዪ ወደ ፊት በትክክል መሄድ አይቻልም። አንድ ምሳሌ ልጨምር የመኪና ሹፌር በጎን መስታወቶቹ ወደሃላ አይቶ አደጋ እንዳይጥመው ይከላከላል ነገር ግን ወደፊት በአግባቡ ካላየ አደጋ የገጥመዋል፤ ወደፊትም መሄድ አይችልም። በዘላቂ በመፍሄ ላይ ያተኮረ አቅጣጫ ላይ ሙሉ አቅምን ማዋል አስፈላጊና ወሳኝ ነው። የምንታገለው ስርአት ሌት ተቀን ተግቶ ስልጣን ላይ ለመቆየት ይሰራል። ሲለው ይገላል ሲያሻው ያስራል የሃገሪቱን ሰልጣን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ በሙሉ ተቆጣጥራል። ይህ ስልጣን ሊያረጋግጥ ፈፅሞ አይችልም። ወሳኙ የህዝብ ድጋፍ ነው። ይህ ደግሞ አንባገነን ስርአቶች ጨርሶ የላቸውም የህዝብ ድጋፍ ኖራቸው አያውቅም ሊኖራቸውም አይችልም።
ዲሞክራሲ እና ነጻነትን ለማምጣት ነው ትግሉ። ከዚህ የወጡ እርስ በርስ የሚያጋጩ አስትያየት ሲስነዘር ወደ መፍሄ እንደማይወስድ በግልጽ መንገር የሁላችንም ግዴታ ነው። ወደ መፍሄው እንጂ ወደ ብጥብጥ የማይወስደውን መንገድ መምረጥ  ደግሞ በሳልነት ነው። ስህተትን ተቀብሎ ማረም ስህተቱን የሰራው ወይም ሊሰራ ያሰበ አካል ሃላፊነት ነው። ከወያኔ ስህተት ተቃዋሚ መማር አለበት። የወያኔን አድሎአዊና ከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲን ስንቃውም እኛ እንደማይደገም ማረጋገጥ መቻል አለብን። በታሪክ ጎልተው የሚታዩ አስከፊ በደሎች ኣሁን ባለንበት ዘመን በወያኔ ኢሃዴግ ተባብሶ ቀጥላል። ዜጎች በነጻነት እንዳያምኑ በእምነት ተቍማት ጣልቃ ገብነቱ ከፍታል። ዜጎች በነጻነት ሀሳባቸውን እንዳይገልፁና በነጻነት በሚመርጡት መሪዎች እንዳይተዳደሩ አፈናው ቀጥላል። ጋዘጠኞች፣ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች ኣባላትና ደጋፊዎች አሸባሪ ተብለው በሃሰት ተከሰው ታስረዋል። የሃይማኖት ነጻነት የጠየቁ ሙስሊም ኢትዮጲያዊያን አሸባሪ ተብለው በሃሰት ተከሰው የድራማ ፕሮፓጋንዳ በአደባባይ ተሰርቶባቸው በግፍ ታስረዋል። ሁሉ ብሄር በግፍ ተጨቁኖ ጥቂት የስርአቱ ደጋፊዎች ተንደላቀው የሚኖሩበት ሀገር ሆናለች ኢትዮጲያ። ይህ ፈጽሞ ፈትሃዊ አይደለም። መጻፍ እና ሀሳብን በነጻነት መግለጽ አሽባሪነት ተብሎ የሚያስፍርጅበት ክፉ ስርአት ተፈጥራል። ይህ ለማንም አይበጅም ለሀገር፣ ለህዝብ፣ ለራሱ ስልጣን ላይ ላለው አስከፊ ስርአት አደጋ ነው።
በተመሳሳይ ለሃይማኖት ነጻነት የሚደረግ ትግል የሌላውን እምነት ነጻነት ማክበር አለበት። እዚህ ላይ ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ የሁሉም እምነት አባቶች እና የእምነቶቹ ተከታዮች ሃላፊነትና ግዴታ ነው። የሃይማነት ነጻነት ትግል ወሳኝ ነው ነግር ግን አካራሪነትን ጨርሶ በየትኛውም እምነት ውስጥ ማስከተል የለበትም። ሀይማኖት የግል ሀገር የጋራ እንደሚባለው። ሀይማኖትና ፖለቲካ መደበላለቅ የለባቸውም። ሀይማኖት የግል ስብእናችን ነው። እያንዳንዳችን ፈጣሪያችንን የምናመልክበትን መርጠን የምንከተለው ነው። በኛና በፈጣሪያችን መሃል የምንከተለውን መንገድ የሚመራን ነው። ለሁሉም እምነት መከበር ደግሞ በጋራ ሁላችን መስራት አለብን። በተመሳሳይ የተሳሳተ አስተሳሰብንም በጋራ ሁላችን መቃወም አለብን። የጋራ በሆነችው አገራችን ደግሞ ለሁላችን በፍትህና በነጻነት እንድንኖር በጋራ የምንመራበት ሁሉን አሳታፊ ዲሞክሪያሲያዊ ስርአት መገንባት አለብን። ሀይማኖትና ፓለቲካ መደባለቅ የለበትም ፤ የእምነት ነጻነትንም ለሁሉም ለማምጣት አይችልም። ይህ እውነታን ለመገንዘብ ፖለቲካል ሳይንስ ማጥናት አያስፈልግም ፤ ስፔስ ሳይንስም አይደለም። ይህን ችግር ለዘለቄታው መፍታት የዚህ ትውልድ የታሪክ ሃላፊነትና ግዴታ ነው። ሀገር እንድታድግ የዜጎች ነጻነት መከበር አለበት ፤ ይህ ደግሞ ዜጎች ያላቸውን በጥረት ራስን የማሳደግና የማበልጸግ ራእይ ለማሳካት ወሳኝ ነው። የሃገርም እድገ መሰረት ነው። ለብሄራዊ ራዕይ እና መግባባት ወሳኝ ነው። ባለንበት ግሎባላይድ አለም ተፎካካሪና ውጤታማ ለመሆን ትክክለኛ ራዕይ እና ጠንክሮ መስራት ወሳኝ ነው ። ለዚህ ደግሞ ዜጎች የምንሰራበትን እደል ለመፈጠር የዜጎች ነጻነት ያለማወላወል መከበር አለበት።  የምንመኛት ኢትዮጲያ ለሁላችን ሀገር መሆን አለባት። ለኦሮሞው፣ ለአማራው፣ ለሶማሌው ለትግሬው ለአፋሩ ለጋምቤላው ለሃረሬው ለቤንሻንጉሉ ለሲዳማው ለጉራጌው ለወላይታው ለሃዲያው ለኮንሶው ለሱሪው ለኒያጋቶም … ወዘተ  እንዲሁም ለክርስትያኑ ለሙስሊሙ ለባህል እምነት ተከታዩ እምነት ለሌለው በአጠቃለይ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጲያን እውን ማድረግ ነው መፍትሄው።
አንድነታችን ሁሉንም ያከበረና ያቀፈ መሆን አለበት። የሁላችንም ኩራት የሆነች ኢትዮጲያን እውን ማድረግ አለበት። ለዚህ ደግሞ የውስጥ ችግሮቻችንን እውነትኛ ዲሞክራሲ ስርአት ላይ መስርተን በአፋጣኝ መፈታት አለብን። እውነተኛ ዲሞክራሲ ከገነባን አብዛኛውን ህዝብ ከሚውክለው ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ትግሬ ብሄሮች እስከ አነስተኛ ህዝብ ቁጥር ያላቸውን ቤንች፣ኮንሶ፣ አላባ፣ እና በጣም ጥቂት ህዝብ ቁጥር  ያላቸውን ኒያንጋቶም፣ ሙርሲ፣ ካሮ የሁሉም መብት ተከብሮ በሰላም በፍቅርና አንድነት የምንኖርባት ኢትዮጲያን እውን ማድረግ ነው ያለብን። በዚህ አይነት መሰረት ላይ የቆመ አንድነት ተሰሚነት ያላት በአካብያዊ ፖለቲካም ሆነ በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የራስዋን አውንታዊ ሚና የምትጫወት ጠንካራ ኢትዮጲያን እውን ማድረግ ያስችላል።
እንደ አገር አንድ መሆን ይበጀናል አንድነታችን ደግሞ ሁሉያን ያቀፍ እና ያሳተፈ (inclusive) እንዲሆን ሁላችንም መስራት አለብን። አሁን ያለንበት የአለም እውነታ የሚያሳየን የአንድነትን ጥቅም ነው። ሀገራት ጥቅማቸውን ማስጠበቅ የሚችሉት በጠንካራ መሰረት ላይ የቆመ አንድነት ሲኖር ነው። አለም ላይ ያለው ተጨባጭ እውነታ የሚያሳየን ይህን ነው። በአለማችን ጠንካራ አቅም ያላት ሀገር ስንሆን ተሰሚነታችን ይጨምራል። ፈተናዎችን በተሻለ አቅም ማሸነፍ ያስችለናል። አውሮፓ(EU)፣ አፍሪካ (AU)፣ ደብቡ አሜሪካ (ECLAC) የአንድነትን ጥቅም አስልተው አንድነቱን አጠናክራል። በአንድ ድምጽ በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር አየሰሩ ነው።  አውሮፓ የተለያዮ ሀገራትን አሰባስቦ ጠንካራ አቅም ገንብታል። እነዚህ ሀገራት በጣም አስከፊ የእርስ በርስ ግጭት አሳልፈዋል። ያሳለፉት ታሪክ እስረኛ ሳይሆኑ ከታሪክ ተምረው ጥቅማቸውን ለማስከበር በጋራ እየሰሩ ነው። እስያም በተመሳሳያ የራሳን ብዙ የትብብር መድርኮች ፈጥራለች (SASEC, ACD, APDC..)። አረብ አገራት የራሳቸውን የትብብር መድረክ ፈጥረዋል (Arab League, GCC )። አገራት የጋራ ጉዳያቸውን እየፈለጉ በጠንካራ ትብብር እየሰሩ ነው። ከዚህ ሪጅናል ትብብር (regional cooperation) በተጨማሪ በተለያየ አካባቢ እና በተለያየ አለም ክፍል የሚገኙ ሀገራት የተለያየ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ፣ ውታደራዊ እና የጽጥታ ትብብር መስርተው ይሰራሉ። ጥቅማቸውንም በጋራ ያስከብራሉ። አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ (EU-US) ትራንስ አትላንቲክ ኮኦፐሬሽን፣ ኢስት ኤዥያ ላቲን አሜሪካ ኮኦፐሬሽን፣ ቻይና አፊሪካ ፣ ሰሜን አሜሪካ አፍሪካ ወዘተ። በዚህ በትብብር አገራት ጥቅማቸውን በሚያሰጠብቁበት አለም ጠንካራ አንድነት ከሌለን ተወዳዳሪ መሆን ይቅርና ተሰሚነትም አይኖረንም። መበታተን የራሳችንንም ሰላም አያስገኝልንም። መበታተን ዲሞክራሲን ፈጽሞ ጋራንቲ አያደርግም።
ይህን አለማቀፋዊ ሁኔታ፣ ተፈላጊውን ከፍተኛ ደረጃ ጠንካራ ፉክክርና ትብብር ግምት ውስጥ ያላስገባ ጥላቻን የሚያባብስ እርስ በእርስ የሚያጋጭ አክራሪነትን የሚያበረታታ አስተያየት ሲሰጥ ከየትም ይምጣ ከየትም፡ ከማንም ይምጣ ከማንም ስህተት መሆኑን ሁላችን በጋራ አንድ ሆነን ልንናገር ያስፍልጋል። ከታሪክ ስህተት መማር እንጂ የታሪክን ስህተት ማስቀጠልም ሆነ በሌላ አካል መድገም የለብንም። የምንኖረው ግሎባላይድ በሆነ አለም ነው (globalized world). ሀገራችን በውስጥ ትክክለኛ ዲሞክራሲ ላይ ተመስርታ ስታበቃ፤ ከምስራቅ አፍሪካ፣ አፊሪካ እንዲሁም ከመላው አለም ጋር ጤናማ ግንኙነት መፍጠር አለብን። በጅብቲና በአካባቢው ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ገብተን የምንበጠብጥበት (intervening in other countries internal affairs) በፓለቲካም ይሁን በኢኮኖሚ ወይም ሀይማኖትን መሰረት አድርገን ማስብም ይሁን ማቀድ ጤናማ አስተሳሰብ አይደለም፤ መልካም የጉርብትና ትብብር እና ሰላም አይፍጥርም። ከአለም አቀፍ ህግጋትም ጋር ይጣረሳል ከፍተኛ ችግርም ያስከትላል (severely violets international laws and results serious and long term consequences on our country).
በሃገራችን የውስጥ ጉዳይ ለፍትህ መታገል ለነጻነት መታገል ይገባል ትክክልም ነው። ይገባልም። ይህ ትግል ለኦሮሞ ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆን ለኦሮሞ ክርስቲያኖች፤ ሙስሊምም ክርስቲያንም ለልሆኑ ኦሮሞዎች፤ ኦሮሞ ለልሆኑ ክርስያኖች፤ ኦሮሞ ላልሆኑ ሙስሊሞች በአጠቃላይ ለሁሉም ኢትዮጲያዊያን ነጻነትና ፍትህ መታገል የሰውነት፣ የኢትዮጲያዊነት የሞራል ግዴታ ነው። ለመብት ስንታገል የህዝቦችን አብሮ የመኖር አሴት (solidarity, coexistence, and multiculturalism, merits of unity) ፍቅር፣ መዋድድና መከባበር (love, tolerance, respect for diversity) ለግል ክብር፣ ተዋቂ ለመሆን፣ ለስልጣን ስንል ለመናድ መሞክር ማናችንም ጨርሶ ማድረግ የለብንም። እኛ ስናልፍ ሀገርና ህዝብ አያልፍምና።  ለኦሮሞ መብት መከበር ሁላችን መታገል አለብን። ለአማራውም፣ ለትግሬውም ለሱማሌው ለወላይታው  ወዘተ ፤ እንዲሁም ለሙስሊሙ ለክርስትያኑ ለማያምነው ወዘተ በአጠቃላይ ለሁላችን መብት ሁላችን በጋራ መስራት አለብን። ከአለንብት የበድል አዙሪት የምንወጣው ያኔ ብቻ ነው።
ያለፉ የታሪክ ስህተቶችን መካድም አይጠቅምም (denial of historical injustice) ። ችግሩን የፈጠሪው አንድ ብሄር ደግሞ አይደለም (blaming one ethnic group for historical injustice is unjust)። ጥቂት ገዥ መደቦች (few ruling group) ናቸው ። በተመሳሳይ በግል ጥቅምና ለተዋቂነት በሚደረግ ርጫ እንዲሁም በስሜት ላይ የተመሰረተ የጥላቻ ፖለቲካ (emotion driven politics) ፤ ግትርነትና (rigidity) አግላይ የፖለቲካ አቁአም (exclusionist  politics) ለማንም አይጠቅምም። የአጭር ግዜ ፓለቲካ (short termism) የጥላቻ ፖለቲካ (spreading of negative consciousness and hatred) ለማንም አይጠቅምም።
ለፍትሕና ለነጻነት መታገላችን ሰብአዊነትን እና ሁሉን ያሳተፈ መሆኑን ማረጋገጥ አለብን። ኢንፓውርመንት (empowerment) ማለት ህዝብ መብቱን እንዲጠይቅ ማሳወቅ እና ማስተባበር ማለት ነው። ፈትሃዊነትን ከልብ የተቀበለ ህዝብና ህዝብን በሃይማኖት ማበጣበጥን ያወገዘ መሆን አለበት። ጤናማ አክቲቪዝም (activism for democracy, freedom, sustainable & long term peace and justice) እና ኢንፓወርመንት (empowerment) ትርጉሙ ይህ ነው። ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እንታገል።
ይህን ጽሁፍ ወደ ኦሮመኛ እና ሌሎች የሃገራችን ቋንቋዎች በቀጥታ ለሚተርጉምልኝ ምስጋናዬ ወደር የለውም።  እንደ አስፈላጊነቱ የእንግሊዘኛ ትርጉሙን ከተጨማሪ ማብራሪያ ጋር አዘጋጅቼ ብቅ እላለሁ።
ከምስጋና እና ታላቅ አክሮት ጋር በዚህ ላብቃ።
ቤልጂየም (Belgium)
አስተያየቶን በሚከተለው ኢሜል ይላኩልኝ።   fiftoze@yahoo.co.uk

No comments:

Post a Comment