ነቢዩ ሲራክ (የማለዳ ወግ. . . )
የሳውዲ ንጉሳውያን ቤተሰብ አባል የሆኑት የ42 አመት እመቤት በምድረ አሜሪካ በቤት ሰራተኛቸው መብት ገፈፋ ተከሰው ለፍርድ ቀርበዋል። ልዕልቷ ኬንያዊዋን የቤት ሰራተኛቸውን በአነስተኛ ክፍያ ከ16 ላላነሱ ሰአታት በመክፈል እና የኬንያዊቷን ሰራተኛ ፖስፖርት ለባለቤቷ ባለመስጠታቸው ተከሰው በምድረ አሜሪካ ለወህኒ ከተዳረጉበት በ5 ሚሊዮን ዶላር ዋስ ቢፈቱም ዛሬም ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ሰምተናን። ይህንን ዜና ሳነብ ያን ሰሞን ” ጋዜጠኛ ነህ አሉ እርዳኝ? ” ብላ ከወደ ደማም በተንቀሳቃሽ ስልኬ እየደወለች የምታነባዋ ኢትዮጵያዊት እህት ፍዳ አስታወስኩ !
ዛሬ ረፋዱ ላይ ያነጋገርኳት ይህች እህት የሚደርስባት ግፍ ሳያንስ የተሰደደች የምትገፋበትን የወር ደመወዟን ላለፉት በርካታ ወራት እንዳልተሰጣት ገልጻልኛለች ። ዛሬ በጣሙን ከፍቷት እያለቀሰች ከገባችበት ስቃይ እታደጋት ዘንድ ተማጽናኛለች! አቅሙ ኖሮኝ ምንም ልረዳት ባልችልም አበሳዋን ግን እነግራችኋለሁ! ይህች ግፉዕ ደራሽ ያጣችው እህት በኮንትራት ከኢትዮጽያ ከመጣች አመት የደፈነችው በያዝነው ወር መሆኑን ገልጻልኛለች።
ከመጣች ቀን አንስቶ ለ16 ላላነሱ ሰአታት እንድትሰራ ስትገደድ ግልምጫ እርግጫና ስድቡን ችላ እንዳሳለፈች እያሳልፈችው ቢሆንም የማትቋቋመው ፈተና ገጥሟታል! የጋብቻ ቃል ኪዳን አስራ ሰርታ ራሷን ለመለወጥ የመጣችው እህት በአሰሪዎቿ ቤተሰቦች ጥቃት ተማራለች! ሚስት በቅናት ተነሳስታ ቁም ስቅሏን የምታሳያት ሳይበቃ የአሰሪዎቿ ሁለት ጎረምሳ ልጆች በየተራ ” እንድፈርሽ !” ብለው የሚያደርሱባትን ትንኮሳ መቋቋም አለመቻሏን እንባ እያዘራች ምርር ብላ እያለቀሰች አጫውታኛለች !
ይህች እህት ወደ ፍትህ አካል የሚያቀርባት ፣ ከገባችበት የመከራ ህይዎት የሚገላግላት የመብት አስከባሪ አካላት አጥታለች ። ኤጀንሲዋን አነጋግራ ” በርረሽ ወጥተሽ እጅሺን ለፖሊስ ስጭ!” ከማለት ያለፈ መፍትሔ አልሰጧትም። አጣብቂኝ የገባችው እህት መፍትሔ ታገኝ ዘንድ የሪያድ ኢንባሲ ሃላፊዎችን ተንቀሳቃሽ ስልክ ሳይቀር ሰጥች ለማረጋጋት የሞከርኩት ቢሳካም ወደ ሃላፊዎች ስልክ ደውላ ከችግሯ ይታደጓት ዘንድ ብትማጸናቸውም ተስፋ ከመስጠት አልፈው የሰሩት ስራ አለመኖሩን እንባ እያዘራች ስታጫውተኝ አሁን አሁን የኢንባሲው ሃላፊዎች ስልክ ስትደውል እንኳ ሊመልሱላት እንዳልቻሉ አጫውታኛለች ። እኔ እስከ ዛሬ ረፋዱ ድረስ ሃላፊዎችን ደውየ ለማነጋገር ያደረግኩት ሙከራ ስልካቸውን ስለማያነሱ ጥረቴ አልተሳካም !
ይህን ግፍ የሳውዲ ህግና መንግስትም አይደግፈውም! ይህ መሰሉን ግፍ በሰራተኛ ላይ መፈጸም ከባድ ቀጣት ቢኖረውም ህግ ፊት የሚያቀርባት ቀርቶ ከገባችበት መቀመቅ የሚያወጣት የሃገሯ ተወካዮችን አጥታ ኑሮን በመከራ እየገፋች መሆኑን ባደረግነው ውይይት ተረድቻለሁ! የሚያሳዝነው ይህች እህት ከዚህ ሁሉ ጭንቀት በኋላ ምን ልትሆን እንደምትችል አላውቅም! ግፉ ከቀጠለ በሚፈጠር ግጭት ምን ሊፈጠርባት እንደሚችል መገመት ይከብዳል! ጎረምሶቹ በጉልበት እንድረፈርሽ ሲሏትም ሆን ሚስት በቅናት ተነሳስታ በምታደርገው የመልስ ጥቃት እንድትጠነቀቅ አበክሬ ከመምከር ባለፈ ምንም ማለት አልቻልኩም! የሳውዲዋ ንግስት ፈጸመችው በተባለው እኛ የአረብ ሃገር ነዋሪዎች መብት ረገጣውን ለምደነው “እዚህ ግባ የማይባል !” የምንለው ጥፋት በነጻዋ አሜሪካ መድር መብት ነክተዋልና ቁም ስቅላቸውን እያዩ ነው ፣ የእኛዋ እህት ደግሞ የግፍ ግፍ እየተፈጠረባት የሃገሯ መንግስ ተወካዮች እንኳ ድረሱልኝ ተብለው ተጠርተው ሊደርሱላት ባለመቻላቸው በሳውዲ ምድር አበሳዋን እያየች ትገኛለች ! የነገን ግን እንጃ. . .
ለሁሉም እኔ ያየሁ የሰማሁትን ተናግሬያለሁ ! ጀሮ ያለው ይስማ . . .!
ቸር ያሰማን !
No comments:
Post a Comment