Wednesday, July 31, 2013

መድረክ ሕዝባዊ ስብሰባ እንዲያካሂድ አዲሱ ከንቲባ ፈቀዱ

በዘሪሁን ሙሉጌታ

በቅርቡ ከአቶ ኩማ ደመቅሳ ላይ የአዲስ አበባ ከንቲባነትን የተረከቡት ከንቲባ ድሪባ ኩማ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ሐምሌ 28 ቀን 2005 ዓ.ም በመብራት ኃይል የሚያካሂደውን ሕዝባዊ ስብሰባ ፈቀዱ።
የአራት ፓርቲዎች ግንባር የሆነው መድረክ በማኒፌስቶውና በሌሎች የሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ በተደጋጋሚ ጊዜአት ጥያቄ ቀርቦ ውድቅ ሲደረግ መቆየቱን የተናገሩት የመድረክ ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንደሻው ናቸው። እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ መድረክ ሐምሌ 7 ቀን 2005 ዓ.ም መነሻውን 6 ኪሎ ያደረገ፣ መድረሻውን ደግሞ ድላችን ሐውልት ያደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የእውቅና ጥያቄ ቢቀርብም በከተማዋ በርካታ የኮንስትራክሽን ስራዎች እየተካሄዱ በመሆኑ ሰልፍ ማካሄድ አትችሉም የሚል ሐምሌ 1 ቀን 2005 ዓ.ም ከከንቲባው ጽ/ቤት በተፃፈ ደብዳቤ መከልከሉን አስታውሰዋል።
ሆኖም መድረክ በድጋሚ ደብዳቤ በመፃፍና በአካል በመጠየቅ ጭምር ለጊዜው በመብራት ኃይል የሚካሄደው ሕዝባዊ ስብሰባ እንዲካሄድ በአዲሱ ከንቲባ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።
መድረክ በአዳማ ከተማ ሐምሌ 7 ቀን 2005 ዓ.ም ማኒፌስቶውን ማስተዋወቁን፣ በተመሳሳይ በመቀሌም ሐምሌ 14 ቀን በማኒፌስቶውና ተያያዥ የሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች መወያየቱ እንዲሁም በአዲስ አበባም ከሁሉም ከተሞች ቀደም ብሎ የተያዘ ፕሮግራም ቢሆንም በአስተዳደሩ ተፅዕኖ ሳቢያ መዘግየቱን አቶ ጥላሁን ተናግረዋል። በቀጣይ በባህርዳርና በሐዋሳ ማኒፌስቶውን የማስተዋወቅና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሕዝብ ጋር መወያየቱን በስፋት እንደሚቀጥል ሊቀመንበሩ ጨምረው ገልፀዋል።
በመጪው እሁድ ከ7 ሰዓት ጀምሮ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የመብራት ኃይል አዳራሽ አራቱም ፓርቲዎች ያስተባበሩት ሕዝባዊ ስብሰባ ይካሄዳል። የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበርና ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ ንግግር ከሚያደርጉ የፓርቲው አመራሮች አንዱ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

No comments:

Post a Comment