Tuesday, July 30, 2013

በርግጥ ወያኔ ራሱን ለማጥፉት ወኔ አለውን?

የሰውልጅ ሁሉ በጋራ የሚያልፍበት ሂደት አለ፦ ይወለዳል ፣ያድጋል፣ይሞታል። ወደዚህ አለም በመወለድ ይመጣል በመሞት ከዚህ አለም ይወገዳል።
የሰውልጅ ከዚህ አለም የሚወገድበት መንገድ ግን ይለያያል በበሽታ፣በአደጋ ፣በጦርነት ወዘተ።
ብዙ ጊዜ አይደለም እንጅ የሰውልጅ የራሱን ህይወት በራሱ የሚያጠፉበት ወይም የሚያስወግድበት መንገድ ይኖራል። የራሱን ህይወት በራስ ማጥፋት ከባድና ትልቅ ዉሳኔ ይጠይቃል ምክንያቱም ህይወት ለሰው ልጅ የከበረ ዋጋ ያለው እና ዳግመኛ የማይገኝ ስለሆነ ነው።
አንዳንዶች በምድር ላይ ያለውን ውጣ ውረድ መቋቋም አቅቷቸው ራሳቸውን ያጠፋሉ፤በየአረብ አገራቱ በየጊዜው የምንሰማው የሴት እህቶቻችን ሞት የዚህ ውጤት ነው አንዳንዶች በሌሎች ላይ የፈፀሙትን በደል ህሊናቸው መሸከም አቅቶት ከመኖር መሞት ይሻላል ብለው ራሳቸውን ያጠፋሉ፣ሰሞኑን በአሜሪካን አገር ሶስት ወጣቶችን አግቶ ብዙ ሰቆቃ ሲያደርስባቸው ቆይቶ ሴቶቹ ነፃ ሲወጡ እርሱ ግን ራሱን አጥፍቷል።
ሌሎች ግን የራሳቸውን ህይወት ለሌሎች የነፃነት ማግኘት ዋጋ አድርገው ይሰጣሉ፣እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁናቴ ራሳቸውን አቃጥለው ከዚህ አለም ያስወገዱት የቱኒዚያዊው መሃመድ ቦአዚዚ እና ኢትዮጵያዊው የኔሰው ገብሬ ተጠቃሽ ናቸው።ዛሬ እነዚህ ጀግኖች በህይወት ባይኖሩም ታሪካቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ በክብር ይዘከራል።

እነዚህ ጨለማውን ለማብራት ራሱን አቅልጦ እንደሚያልፈው ሻማ ናቸው። ልክ እንደ ሰው ልጅ መንግስታትም ድርጅቶችም ይፈጠራሉ፣ይኖራሉ፣ጊዜያቸውን ጨርሰውም ያልፋሉ ወይም ይወገዳሉ። ወያኔም የዛሬ 40 ዓመት ግድም በደደቢት ተወልዶ ላለፉት 21 ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ተጣብቆ እጅግ የሚዘገንኑ በደሎችን እየፈፀመ እስከዛሬ ቆይቷል። አሁን ግን ወደማይቀረው ሞት በፍጥነት እየገሰገሰ ይገኛል።
በእርግጥ ወያኔ በማይድንባቸው ብዙ በሽታወች ተይዞአልና ይሞታል። ከበሽታወቹ ዋናወቹ ደግሞ ካልገደሉ የማይምሩት ዘረኝነትና ሙሰኝነት ናቸው፣እንደእኔ እምነት በወያኔ ስርዐት ውስጥ  ዘረኝነትና ሙሰኝነት በስፋት አለ ማለት ብቻ ሳይሆን ዘረኝነትና ሙሰኝነት የስርዐቱ ህይወት ናቸው፤ ዘረኝነትና ሙሰኝነት ከወያኔ ስርዐት ተወገዱ ማለት ስርዐቱ ሞተ ማለት ነው።
ታድያ ሰሞኑን የወያኔ መንግስት ጥቂት በሙስና የተጨማለቁ ባለስልጣትን አስሮ ሙስናን ከስርዐቱ ለማስወገድ የህዝቡን እርዳታ ሲጠይቅ እራሱን በራሱ ለማጥፋት እርዳታ እየጠየቀ መሆኑን አላወቀውም ወይስ  እራሱን አጥፍቶ ታሪክ መስራት አምሮታል?
ይህ ቢሆንማ መልካም ነበር እኛም በረዳነው ነበር።ነገር እኔ ጥያቄ አለኝ፦በርግጥ ወያኔ ራሱን ለማጥፉት ወኔ አለውን? እኔ አይመስለኝም።ታዲያ ምን እናድርግ? ወያኔ ወደማይቀረው ሞት በፍጥነት እየገሰገሰ ነውና እያንዳንዳችን ሞቱን የበለጠ ለማፋጠን በቻልነው አቅም ሁሉ እንግፋው።
ቸር እንሰንብት
እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ዳንኤል ከኖርዌይ


No comments:

Post a Comment