Monday, July 29, 2013

አክራሪውና ሽብርተኛው ማን ነው?

ሰሞኑን ከሸህ ኑር ይማም ሞት ጋር በተያያዞ በርካታ ነገሮችን እየሰማን እንገኛለን፡፡ በመጀመሪያም ማንኛውም አካል ይህን ድርጊት የፈፀመ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ መሰረት መጠየቅና መቀጣት የለበትም የሚል የለም፡፡ የምንቃወመው ይህንን ድርጊት ለፕሮፓጋንዳ መጠቀሙ ላይ ነው፡፡ ‹‹የሸሁ ሞት ድራማ ነው ›› ያሉትን ይዘው አምባገነኖቹ ፕሮፓጋንዳቸውን እየነፉ ይገኛሉ፡፡ እኔ እንደገባኝ ‹‹የሸሁ ሞት ድራማ ነው ›› ያሉት ወኖች በሸሁ ሞት ሳያዝኑ ቀርተው አይመስለኝም፡፡ ሊሉ የፈለጉት ከአንባገነኖቹ በኩል የተሰራ ሴራ አለ ለማለት ፈለገው ይመስለኛል፡፡ ኢቲቪ ግን ይህን ሰዎቹ ያሉትን ጠምዝዞ ለፕሮፓጋንዳ ተጠቀመበት፡፡ ይህ በኢቲቪ በኩል የተለመደ ፍረጃ ነው፡፡ ስርዐቱ የሙስሊሙን የሃይማኖት ጥያቄ ላለመመለስ እየሄደበት ያለው መንገድ አሁን በሰላማዊ ሰልፉ ታጅቦ ህዝቡ እንዲያወግዛቸው ቢያስደርግም ዘለቄታዊ መፈትሄው የሚሆነው ጥያቄያቸውን መመለሱ ላይ ነው፡፡
በተለያዩ ከተሞች ይህንን ድርጊት እንዲያወግዙ የታዘዙት ሰልፈኞች የተለያየ ነገር ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይህም አንድነት ፓርቲ በደሴ ያካሄደውን ተቃውሞ ሰልፍ እንዲሁም ወደፊት ለሚያካሂዳቸው ሰላማዊ ትግሎች ላይ ጥላሸት ለመቀባት ታስቦ ነው ይህ የሚካሄደው፡፡ ከአንድ አመት በላይ ድምፃችን ይሰማ እያሉ ፍፁም ሰላማዊ የሆነ የሃይማኖት ጥያቄ እያቀረቡ የሚገኙትን የሙስሊም ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ፕሮፓጋንዳ ነዝቶ ከህዝብ ለመለየት እና ሰላማዊ ጥያቄቸውን ለማክሸፍ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሁሉ በጄ ተብሎ እንዲህ መሆን አያዋጣም የጭንቅ ቀን መምጣቱ አይቀርም፡፡ ያኔ ግን ከህዝብ የተጣላ መግቢያው የት እንደሆነ ይጠፋዋል፡፡ ፓርላማውን 99.6% የተቆጣጠረው አምባገነኑ ስርዐት ሚዲያውንም እንደዛው ስለተቆጣጠረ ፕሮፓጋንዳ ለመንዛት ተመችቶታል፡፡ ይህ ግን እስከ መቼ ያዘልካል? አይታወቅም፡፡

አቤ ቶኪቻው በፋክት መፅሄት ላይ ‹‹ ሀገራችን ኢህአዴግ አክራሪነት እንደሚያሰጋት ተሰጋ›› የምትል ፅሁፍ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ እናም ይበልጥ ለአክራሪነትና ለሽብርተኝነት ቅርብ የሆነው አምባገነኑ ስርአት እንጂ ሌላው ዜጋ አይደለም፡፡ እኔ የምለውን እሺ ብሎ የማይቀበል፣ እኔ አድርግ ያልኩትን ሳይቅማማ የማይፈፅም የሚል አምባገነን ፓርቲ እንዴት ሌላውን አክራሪ? ሽብርተኛ? ማለት ይችላል? በምንስ ሞራል? 

እውነት እውነት ናት፡፡ ዋጋዋም ከፍ ያለ ነው፡፡ ስለሆነም ሽብርተኞች የተባሉ ነገር ግን በተግባር ሽብርተኛ ያልሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ታስረው የግፍን ፅዋ እየተጎነጩ ይገኛሉ፡፡ ዛሬ ላይ ሆድ አደር የሆኑ ጋዜጠኞች እና ግለሰቦች በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ የምንሸወድ ያለን አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን በተለይ የኢቲቪ ቋሚ ተመልካቾች በእንዲህ አይነት ፕሮፓጋንዳ ግራ መጋባታቸው አይቀርም፡፡ ይህንን ክፍተት በተቻለ መጠን ለመድፈን መሞከር የነፃ ሚዲያዎችና የነፃ የዜጎች ድርሻ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment