june 16, 2013
የሕወሐት አባልና የአገር ውስጥ ደህንነት ዋና ሃላፊ አቶ ወልደስላሴ ከስልጣናቸው እንዲነሱ መደረጉን የቅርብ ምንጮች አስታወቁ። ወ/ስላሴ ከስልጣን እንዲነሱ ያደረጉት የደህንነት ዋና ሹም አቶ ጌታቸው አሰፋ መሆናቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል። የሁለቱ ሹማምንት ፀብ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ ቆይቶ መጨረሻ መፈንዳቱ ታውቋል። በመቀሌ በተካሄደው የፓርቲው ጉባኤ አቶ ጌታቸው የፓርቲው ማ/ኮሚቴ አባል ሆነው እንዳይመረጡ ሰፊ ቅስቀሳ ሲካሂድ የቆየው ወ/ስላሴ በመጨረሻም የአባላት ምርጫ ሲካሄድ ባቀረበው ተቃውሞ ላይ «..ጌታቸው የተሰጠውን የፓርቲና መንግስታዊ ሃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ አይደለም፤ የአልሙዲ ተላላኪና አሽከር ሆኗል… የአላሙዲ አገልጋይ ሆኖዋል… ስለዚህም በማ/ኮሚቴ አባልነት መካተት የለበትም..» ሲል መናገሩን ያወሱት ምንጮቹ፣ የወ/ስላሴ ተቃውሞ ተቀባይነት ባለማግኘቱ አቶ ጌታቸው በማ/ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ መደረጉን አያይዘው ገልፀዋል።…
አቶ ጌታቸው በቅርቡ በወሰዱት የአፀፋ እርምጃ ወ/ስላሴ ከአገር ውስጥ ደህንነት ሃላፊነታቸው እንዲነሱ በማድረግ እንደተበቀሏቸው ማወቅ ተችሏል። በጎንደር ተወልደው ያደጉትና በሰባዎቹ መጀመሪያ አመታት ሕወሐትን የተቀላቀሉት አቶ ጌታቸው በአብዛኛው አመራር « ጥሩ ሰው ነው፣ ላመነበት ነገር ወደኋላ የማያፈገፍግ..» ተብሎ እንደሚነገርላቸው ምንጮቹ ጠቁመዋል። በሟቹ የደህንነት ሹም ክንፈ ገ/መድህን ተተክተው በ1994ዓ.ም ወደስልጣን የመጡት ጌታቸው በተጨባጭ ሙስና ፈፅመዋል የሚል መረጃ እንደሌለ ያመለከቱት ምንጮቹ ነገር ግን በአብዛኛው ባለስልጣናት የሚፈፀመው መጠነ ሰፊ ዘረፋና ሙስና በተመለከተ በርካታ መረጃና ማስረጃ በጌታቸው እጅ እንደሚገኝ አያይዘው ገለፀዋል። በሌላም በኩል በ1994ዓ.ም በደህንነት ቢሮ የበታች ሹማምንት ሆነው በአቶ መለስ ከተመደቡት መካከል ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስና ወ/ስላሴ እንደሚገኙበት ያስታወሱት ምንጮቹ፣ አክለውም ሁለቱ የሕወሐት አባላት ከስር ሆነው ፈላጭ ቆራጭ አመራር ይሰጡ እንደነበረና በዚህ ተግባራቸው ከጌታቸው ጋር የከረረ ውዝግብ ውስጥ ገብተው መቆየታቸውን አስታውቀዋል። ኢሳያስ ከአቶ መለስና ስብሃት ጋር ስጋ ዝምድና እንዳለው ማወቅ ተችሏል። በተለይም በዚህ ጣልቃ ገብ አሰራር ተማረው የቆዩት አቶ ጌታቸው ከቅርብ አመት ወዲህ ከአቶ መለስ ጋር ጭምር አለመግባባት ፈጥረው እንደነበረ ሲታወቅ፣ አቶ መለስ የጤና ችግር ተፈጥሮቦቻው እንጂ በዛው ወቅት ከስልጣን ሊያነሷቸው ከወሰኑት ባለስልጣናት አንዱ ጌታቸው እንደነበሩና ከመለስ ህልፈት በኋላ የደህንነቱ ሹም የታቀደባቸውን እንደደረሱበት ምንጮቹ አስታውቀዋል። የጠ/ሚ/ሩን ህልፈት ተከትሎም አቶ ጌታቸው ስልጣናቸውን በማደላደል ጎልተው መውጣቸውንና በወ/ስላሴ ላይ የወሰዱት እርምጃ ማስረጃ እንደሆነ አያይዘው ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ የአቶ ጌታቸው ወንድም ዳንኤል አሰፋ የሕወሐት ማ/ኮሚቴ አባል ተደርጎ ባለፈው ጉባኤ መመረጡ ሲታወቅ፣ የዳንኤል ባለቤት የስብሃት ነጋ ዘመድ እንደሆነች ተጠቁሞዋል።
ከስልጣን የተነሳው ወ/ስላሌ ከበረሃ ጀምሮ በርካታ የድርጅቱን ታጋዮች በመረሸን እንደሚታወቅ ያስታወሱት የቅርብ ምንጮቹ « ፆታዊ ግንኙነት ስታደርጉ ተገኝታችኋል…» በሚሉና ሌሎች ተልካሻ ምክንያቶች እንዲረሸኑ በበላይ አመራር ውሳኔ የተላለፈባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የፓርቲው አባላት (ታጋዮች) ለመግደል ይጣደፉ ከነበሩት መካከል ኢሳያስና ወ/ስላሴ ዋናዎቹ ነበሩ ሲሉ ያስረዳሉ። አቶ መለስ ሁለቱን አባላት ወሳኝ በሆነው የደህንነት ቢሮ ቁልፍ ስልጣን የሰጧቸው « አድርጉ » የተባሉትን ያለማመንታት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው ብለዋል። ወ/ስላሴ ስልጣን በጨበጠ ማግስት በአንድ ቀን አርባ የቢሮው አባላትን ( መኮንኖች ተብለው ነው የሚጠሩት) እንዳባረረ የገለፁት ምንጮቹ፣ በየጊዜው በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላትን « ተሃድሶውን አልተቀበላችሁም፣ የቅንጅት ደጋፊዎች ናችሁ..» በሚሉና ሌሎች ምክንያቶች ከማባረር – እስር ቤት እስከመወርወር የደረሰ እርምጃ ሲወስድ መቆየቱን አስታውሰዋል። ከመለስ ጋር በሃሳብ ያለተስማሙ ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናትን በገዛ መኖሪያ ቤታቸው በገመድ በማነቅና በስለት በማረድ የጭካኔ ተግባር ያስፈፀሙት ወ/ስላሴና ኢሳያስ መሆናቸውን ምንጮቹ አጋልጠዋል። በግፍ የተገደሉት የመገናኛ ሚ/ሩ አቶ አየነውና የቤተመንግስት የደህንነት ሹም አቶ ዘርኡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አዜብ መስፍን በቅርቡ ቨርጂኒያ መጥተው እንደነበረ ምንጮች ገለፁ። ድምፃቸውን አጥፍተው የመጡት አዜብ በተጠቀሰው ከተማ እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ የገዙት መኖሪያ ቪላ ውስጥ ለጥቂት ቀናት እንደቆዩና ወደአገር ቤት እንደተመለሱ ምንጮቹ አስታውቀዋል። ከቪላው ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃዎች እየተጠናከሩ እንደሆነ ማወቅ ተችሏል።
No comments:
Post a Comment