Wednesday, June 19, 2013

አንድነት ፓርቲ በፀረ -ሽብር ሕጉ ላይ ሕዝባዊ ንቅናቄ ሊጀምር ነው

በዘሪሁን ሙሉጌታ

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ከአራት ዓመት በፊት የፀደቀውን የፀረ-ሽብር ሕጉን ለማሰረዝና ይሄንኑ ሕግ ተላልፈዋል ተብለው በእስር ላይ የሚገኙ የፓርቲውን አመራሮችንና ጋዜጠኞችን ለማስፈታት በአይነቱና በይዘቱ ለየት ያለ ሕዝባዊ ንቅናቄ እንደሚጀምር አስታወቀ።
የፓርቲው የስራ አስፈፃሚ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዳንኤል ተፈራ በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት የአንድነት ፓርቲ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ሰለባ ከሆኑ ፓርቲዎች አንዱና ግንባር ቀደሙ መሆኑን በመጥቀስ አዋጁን ለማሰረዝ በሚሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ አዋጁ ሕገ-መንግስቱን በግልፅ የሚጥስ መሆኑን ማስረጃ በማቅረብ ጭምር ክስ ለመመስረት መታቀዱን ተናግረዋል።
የህዝባዊ ንቅናቄ አተገባበሩን በተመለከተም በነገው ዕለት በፓርቲው ጽ/ቤት የፖለቲካ እስረኞች ቤተሰቦች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ወኪሎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ጋዜጠኞች በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ንቅናቄው መጀመሩ በይፋ እንደሚበሰር አመልክተዋል።
ሕዝባዊ ንቅናቄው “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል መሪ ቃል የሚጀመር ሲሆን ለቀጣዮች ሶስት ወራትም በተከታታይነት እንደሚቀጥል ከአቶ ዳንኤል ገለፃ መረዳት ተችሏል።
ፓርቲው ባስቀመጠው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ መሰረት በአዲስ አበባና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች መዋቅሮቹን ሲያደራጅ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ዳንኤል ሕዝባዊ ንቅናቄውን ትርጉም ባለው ደረጃ ማንቀሳቀስ የሚያስችል በአዲስ አበባ በ23ቱም ወረዳዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጪ በዋና ዋና ከተሞች መዋቅር መመስረቱንም አረጋግጠዋል። የሕዝባዊ ንቅናቄውን ዓላማ ከዳር ሊያደርስ የሚችል ግብረኃይል መደራጀቱን አያይዘው አመልክተዋል።
ሕዝባዊ ንቅናቄው የሚካሄደው የድጋፍ ፊርማ በማዘጋጀት፣ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍና የአደባባይ ላይ ሕዝባዊ ስብሰባዎች በማካሄድ እንደሆነም አቶ ዳንኤል ገልፀዋል።

No comments:

Post a Comment