Sunday, June 16, 2013

ግብፅ የሰጠችንን የቤት ሥራ ለምን አንሰራም?

ከማስተዋል
ከሳምንት በፊት የግብፅ ባለስልጣናት እና ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ ላይ ሲያሴሩ የሚያሳይ ቪዲዮ እንደወጣ መቸም ብዙወቻችን አይተናል ወይም ሰምተናል:: ቪድዮዉን ሲያይ አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ደሙ እንደፈላ በፌስ ቡክ እና በሌሎች መንገዶች ከሚሰጡ አስተያየቶች ለመታዘብ ችያለሁ፤ እኔም እራሴ በጣም ነው የተናደድኩት:: ነገር ግን አብዛኛወቻችን በጉዳዩ ላይ ስሜታዊ ሁነንእስኪ ትምጣ እና እናሳያታለንአልን እንጅ ግብፅ ብትመጣ የኛ ጠንካራ ጎን የቱ ላይ ነው? ደካማ ጎናችንስ? ጠንካራ ጎናችን እንዴት እንጠቀምበት ? ደካማ ጎናችንስ እንዴት እናሻሽለው የሚል ዉይይት እስካሁን አላያአሁም፤ እንዲሁ ስሜታዊ ሽለላ አሰማን እንጅ:: 

ግብፆች ሀገራችን ለማዳከም እና በዓባይ ላይ ምንም ሥራ እንዳንሰራ በዋናነት ያስቀመጧቸው ስልቶች የመጀመሪያው ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ የውስጥ ተቃዋሚወችን መርዳት ሲሆን ይህ ካልተሳካ ደግሞ ደግሞ ወታደራዊ ኃይል መጠቀም ነው:: ነገር ግን የአብዛኛዉን ሰው አስተያየት ስመለከት በግብፅ ኃይል እጠቀማለሁ ዛቻ መናደድ እንጅ ግብፆች ቁጥር አንድ ስልታችን ብለው ላስቀመጡት ኢትዮጵያዉያንን እርስ በእርስ ማዋጋት ምንም ትኩረት አልሰጡትም እንዲያዉም ይባስ ብሎ በካይሮ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች ያደረጉትን ሰልፍ ተከትሎ ሰልፈኞቹን ከመሳደብ በዘለለ ጉዳዩን ጠለቅ ብሎ የሚዳስስ አስተያየት እና ፅሁፍ አላስተዋልኩም ይህን ጉዳይ ሳስተዉል የግብፆች ወጥመድ ዉስጥ ሰተት ብለን እየገባን እንደሆነ ይሰማኛል:: ኦሮሞ ወንድሞቻችን ለምን ኢትዮጵያዊነታቸውን በአደባባይ ካዱ ? እነዚህን ኦሮሞ ወንድሞቻችን መሳደብ እና ማንቁአሸሽ ነው ወይስ ቀርቦ መማማር ኢትዮጵያዊነታቸዉን ከልባቸው እንዲቀበሉ የሚያደርጋቸው? 


በመጀመሪያ ደረጃ በካይሮ የሚገኙ ኦሮሞወች ያደረጉትን ሰልፍ ሲያይ የደነገጠ ካለ የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት ማወቁን እጠራጠራለሁ:: እኔ በበኩሌ ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸው ኦሮሞወች ጋር ባንድ ጣሪያ ስር የኖርኩበት ወቅት ስላለ የካይሮው ሰልፍ አላስደነገጠኝም :: ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ያጋጠመኝን ላካፍላችሁ:: ወቅቱ የፈረንጆች አዲስ ዓመት 2006 መግብያ ጃኗሪ አንድ ነው የተወሰኑ የኦሮሞ ባህል ልብስ የለበሱ የኦሮሞ ተማሪ ተሰባሰቡ እና ርችት እየተኮሱ በጭፈራ የፈረንጆችን አዲስ ዓመት 2006 ማክበር ጀመሩ፤ የፈረንጆችን አዲስ ዓመት አይደለም የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት ዩንቨርስቲዉ ዉስጥ በዚህ መልኩ ማክበር የተለመደ አይደለም :: ዝግጅታቸዉን ካጠናቀቁ በዝግጅቱ ተካፋይ ከነበሩ አንድ ኦሮሞ የዶርሜ ልጅ ጋር ስለሁኔታዉ ተጨዋወትን ለምን እንደዛ እንዳደረጉ ጠየቅኩት እሱም መለሰልኝእኛ ኦሮሞ እንጅ ኢትዮጵያዉያን አይደለንምስለዚህ መቁጠር የምንፈልገው በኢትዮጵያ ዘመን መቁጠሪያ ሳይሆን በአዉሮፕዉያን ዘመን መቁጠሪያ መሆኑን ለማሳየት ነው አለኝ:: ልብ በሉ ከዚህ ላይ ሁሉም ኦሮሞወች እንደዚህ ያስባሉ እያልኩ አይደለም፣ አብዛኛወቹ ኦሮሞወችም በዛ ዝግጅት ላይ አልተሳተፉም ነገር ግን እንደዚህ የሚያስቡ ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል ኦሮሞ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንዳሉ መካድ ግን እዉነታን ለመጋፈጥ መፍራት ነው :: 

እነዚህ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ለምን የዚህ አይነት አቁአም እንደያዙ ስትጠይአቸው የሚሰጧችሁ መልስ ባጭሩ ኢትዮ ዉስጥ በእኩልነት እና በፍትህ መኖር ስላልቻልን ብለው ይመልሱላችሁአል:: ታዲያ እንደዚህ ሲሉን ብንሰድባቸው ችግሩ ይፈታል ወይ ? በእኔ አመለካከት ስድብ ችግሩን አይፈታዉም የተሻለ የሚሆነው እርስ በእርስ በሰለጠነ መልኩ መማማር ነዉ:: ኢትዮጵያ ዉስጥ የብሔር ጭቆና የሚደርስበት ኦሮሞ ብቻ አለመሆኑን መተማመን ትልቅ ሀገር ከትንሽ ሀገር የተሻለ ያለዉን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሌሎች ጠቀሜታችን ማሳየት ሃገርን ወደ መገነጣጠል ቢሄድ ሊከተል የሚችለዉን ጦርነት እና ጥፋት መወያየት፣ መገንጠል በራሱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ዋስትና አለመሆኑን ከተሞክሮ ርትራን ሁኔታ ማሳየት፣ ሀገር እና ሃገርን የሚመራዉ ቡድን የተለያዩ መሆናቸዉን መረዳዳት እና ሌሎች የትልቅ ሀገር ጠቀሜታችን ማስገንዘቡ የተሻለ ይሆናል:: በተጨማሪም ኦሮሞ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሚያነሱትን ሃሳብ በሰለጠነ መንገድ በቅንነት በመረዳት የተሻለች ኢትዮጵያን እንዴት እንገንባ በሚለው ላይ መወያየቱ ጠቀሜታዉ ከፍተኛ እንደሆነ ይታየኛል:: 

በሌላ በኩል ህወሓት/ ኢህአዴግ ስልጣኑን ለማራዘም የሚጠቀምበት አንድ ስልት አለው ይኽዉም በሀገር አንድነት በሚያምኑት እና መገንጠል በሚፈልጉት ኢትዮጵያዉያን መካከል የኃይል ሚዛን እንዲኖር ማድረግ እና ሁልጊዜም ቅራኔ እንዲኖር ሌት ተቅን ተግቶ መስራት:: በሀገር አንድነት የሚያምኑት ጠንከር ብለው ለስልጣኑ አስጊ ሲሆኑ መገንጠል የሚፈልጉትን ለቀቅ በማድረግ እንዲጠናከሩ ይፈቅዳል (ለምሳሌ ከምርጫ 97 ማግስት ኢህአዴግ የወሰዳቸዉን እርምጃወች ልብ ይሏል) መገንጠል የሚፈልገው ሲጠናከር እና ለህወሓት/ ኢህአዴግ ስልጣን አደጋ ሲጋርጥ በአንድነት የሚያምኑትን ጠንከር እንዲሉና ሚዛኑን እንዲጠብቁ በማድረግ ለራሱ ፖለቲካዊ ትርፍ ይጠቀምባቸዋል :: ስለዚህ የህወሓት እድሜን ከሚወስኑት ወሳኝ ነገሮች አንዱ እና ዋነኛዉ የነዚህ ሁለት ኃይሎች የመተባበር እና የመተማመን ሁኔታ ነው:: ነገር ግን በአሁኑ ስዓት ይህን የሀገራችን የፖለቲካ ደካማ ጎን የምታዉቀው ግብፅ ለራሷ ጥቅም ልትጠቀምበት እንደሆነ በአደባባይ ነግራናለች፤ እኛ ከግብፅ ቀድመን የቤት ሥራችን ካልሰራን እና ችግራችን ካልፈታን ትናንት ርትራን በማስገንጠል ሀገራችን ላይ እንዳደረሰችዉ ከባድ ኪሳራ ይህኛዉም ዉጥኗ ሊሳካላት ይችላል::

በነገራችን ላይ ሀገራችን ዉስጥ በመንግስት ላይ ቅራኔ ያለው ኦሮሞ ብቻ አይደለም ሌሎችም ብዙ ጥያቄ አሉ:: ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በመገንባት በእዉነተኛ ምርጫ በሕዝብ የተመረጠ መንግስት ስልጣን ላይ እንዲወጣ ከማድረግ አንስቶ የፕሬስ ነፃነትን ማክበር፣ የመንግስትን በሃይማኖት ጣልቃ መግባትን ማስቀረት፣ የብሔር ጭቆናን ማስወገድ እና እኩልነትን ማስፈን፣ ትክክለኛ ፌደራሊዝም እንዲተገበር ማድረግ አሸባሪ እና ሌላም ስም እየተሰጠ ግባብ የታሰሩትን መፍታት እና እርቅ እንዲኖር ማድረግ፣ ሙስናን መዋጋት እና ሌሎች ሀገሪቱ ዉስጥ ያሉትን ችግሮች መፍታት ካልተቻለ ከግብፅ ጋር ሳይሆን የምንዋጋዉ ግብፆች እንዳሴሩልን ልክ እንደከዚህ በፊቱ እርስ በእርስ እንዳይሆን እሰጋለሁ:: እነዚህ ችግሮች መፈታት ያለባቸው ግብፅ ትመጣለች ተብሎም ሳይሆን ለሀገራችን በዘለቄታዉ ከፍተኛ ችግር ስለሚፈጥር አሁንም እየጎዳን እንደሆነ ስናምን ነው::በእርግጥ እነዚህ ችግሮች ባንድ ሌሊት አይፈቱም ነገር ግን አሁን ባለዉ አኩአን ጉዞአችን ወደ ሁኗል ስለዚህ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ወደፊት መራመድ መጀመር ይኖርብናል:: 

ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ሳንፈታ የዓባይ ግድብን ተሳክቶልን ብንጨርስ እንኩአን እርስ በእርስ ስንዋጋ እንደተከዜ ድልድይ ላለመፍረሱ ዋስትና የለንም፤ የጋዳፊዋን ሊቢያን ታሪክ እንዳንደግመውም ስጋት አለኝ:: ጋዳፊ የምዕራብ ዜና ማሰራጫ እንደሚነግሩን ሙሉ በሙሉ መጥፎ ሰው አልነበረም፤ ስልጣን ላይ እንደወጣ ባብዛኛዉ በምዕራብ ሃገራት የነዳጅ ካምፓኒዎ እጅ የነበረዉን የሀገሪቱን ነዳጅ በመዉረስ ከነዳጁ የሚገኘዉን ገንዘብ ለሕዝቡ ትምህርት፣ ጤና፣ ምግብ እና እንዲሁም ለሌሎች ጥቅማጥቅም እንዲሆን ከማድረጉም በላይ በነፍስ ወከፍ ጥሬ ገንዘብ ለዜጎች ያድል ነበር:: ሀገሪቱንም በመሰረተ ልማት እና በሌሎች ዘርፍች በከፍተኛ ደረጃ ለመለወጥ በቅቶ ነበር፤ ነገር ግን ጋዳፊ ዘረኛ እና አምባ ገነን ነበር:: የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ተቁአማት በአብዛጋዉ ስርጥ የተባለ ቦታና ዙሪያ የሚኖሩ እሱ የሚወለድበትየቃዳድፋጎሳ አባላት ነበር የተቆጣጠሩት፤ በዚህም ምክንያት በቤንጋዚ እና ሌሎች አካባቢ የሚኖሩ ሌሎች ሊብያዉያን ከፍተኛ ቅሬታ ነበራቸው:: ምንም እንኩአን እነዚህ ሊብያዉያን የምዕራቡን ዓለም የሚወዱት ባይሆኑም ጋዳፊን ለመጣል ግን ጠላቶቻችን ከሚሏቸዉ ምዕራባዉያን ጋር ተባብረዋል በመሀልም አርባ ዓመት ሙሉ ጋዳፊ ሲገነባዉ እና ሲያስገነባዉ የነበረው ነገር ሁሉ ወድሟል:: እኛም ከዚህ መማር ይገባናል:: 

እኛ ከተግባባንና ከተባበርን "ድር ቢያብር አንበሳ ያስር" ነውና የማንመክተው ዉጫዊ ኃይል አይኖርም እርስ በእርስ መግባባት ካልቻልን ግን የሚያጠፋን ጠላታችን ሳይሆን የእርስ በእርስ ቅራኔአችን ይሆናል::

No comments:

Post a Comment