Monday, June 17, 2013

የግብፅ ነገር “አንተ አብራ፤ እኔ ልብላ!” ሆነ እኮ! (ከባልሽ ባሌ ይበልጣል!)

ከኤልያስ
የዛሬውን ፖለቲካዊ ወግ የምጀምረው ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ በወጣ አንድ አሳዛኝ ዜና ነው፡፡ እውነቱን ልንገራችሁ አይደል----እንደው ዝም ብለን እንፍጨረጨራለን እንጂ ገና ብዙ እኮ ነው የሚቀረን፡፡ (በሁሉም ነገር!) ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ሆና እንዴት የቆሻሻ ክምር ትሆናለች እያልን ዘራፍ እንል አልነበር? (ጉራ ብቻ ሆንን እኮ!) ባይገርማችሁ --- አሁን ነገርዬው ከዚያም ብሷል፡፡ እስቲ አስቡት--- በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 22 ሰዎች ተቆፍረው በግዴለሽነት በተተዉ ጉድጓድ ውስጥ ገብተው ህይወታቸው አልፏል ይላል - አሳዛኙ ዜና፡፡
ማነው ለእዚህ ተጠያቂው ካላችሁ ደግሞ ---“ጀብደኞቹ” እነመብራት ሃይል፣ እነቴሌኮም፣ እነውሃና ፍሳሽ፣ እነመንገድ ትራንስፖርት እና እነ አካባቢ ጥበቃ መ/ቤቶች ናቸው ይላል - ዜናው፡፡ ቆይ ግን--- እቺ ከተማ ባለቤት የላትም እንዴ ? (የሚያስብላት አባት ወይም እናት ማለቴ እኮ ነው!) እሺ-- ወላጆቿ እንደሞቱባት ይታወቃል (አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱን ማለቴ ነው!) ግን እንጀራ እናት እንኳን የላትም እንዴ? አያት ቅድመአያትስ? በቃ--- ምንም ዘመድ የላትም ማለት ነው፡፡ (ባይኖራትማ! ነው) --- ሁሉም እየተነሳ እኮ ደህናውን መንገድ ቆፋፍሮ እብስ ነው የሚለው! ዘመድ ቢኖራትማ… 22 ነዋሪዎቿ የመንግስት መ/ቤቶች በቆፈሩት ቆፍረው በተውት ጉድጓድ ውስጥ እየገቡ ሲሞቱ የሚቆረቆርላቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው የህይወት ካሳ እንዲከፈል ጥብቅና የሚቆም አይጠፋም ነበር፡፡
የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፣ ለደረሰው የህይወት ህልፈት ተጠያቂዎቹ ከላይ የተጠቀሱት የመንግስት ተቋማት ናቸው፡፡ እሳቸው “ተጠያቂ” ይበሏቸው እንጂ እስከዛሬ ግን የጠየቃቸው የለም፡፡ (“ሚስትህ ወለደች ወይ?” ቢሉት “ማንን ወንድ ብላ” አለ አሉ!) እውነቱን ለመናገር---ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው አውራው ፓርቲያችን ኢህአዴግ ነው፡፡ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ብቻ ሳይሆን በከረመባቸው 22 ዓመታት እቺን “ተጠያቂነት” የምትል ቃል ከዲስኩር ማሳመርያነት ባሻገር መሬት ላይ አውርዶ “ሊጠቀምባት” ወይም “ሊጠቅምባት” አልደፈረም፡፡
እንኳንስ እኛ ህዝቦቹ ይቅርና ራሳቸውም ተጠያቂዎቹ እኮ “ተጠያቂነት”ን በቅጡ አያውቁትም፡፡ (ተጠይቀው አያውቁማ!) በሌላ አነጋገር “ተጠያቂነት” የወረቀት ላይ “ነብር” ነው ማለት እንችላለን - እንደ አብዛኞቹ የጦቢያችን ህጐች! እናም መዲናችን ተጠያቂም ጠያቂም አጥታ ከምትባጅ ለምን መላ አንዘይድም፡፡ እንዴት ያለ አትሉኝም --- ለዚህች ባለቤት ላጣች ምስኪኗ መዲናችን “ሞግዚት” ብናፈልግላትስ? (ያውም የፈረንጅ ሞግዚት ነዋ!) ገንዘባችንን ይጭነቀው እንጂ ሞግዚት እኮ ሞልቷል - ከአውሮፓ አሊያም ከእስያ ማስመጣት እንችላለን፡፡ አያችሁ … ከተማ በማስተዳደር ጥሩ ልምድ ያለው የማኔጅመንት ተቋም (ዘመናዊ ሞግዚት ማለት እኮ ነው!) አስመጥተን መዲናዋን ይመራልናል (አገር በቀሎቹ አልሆንላችሁ ሲለንስ!) አይዟችሁ … የቅኝ ግዛት ነገር እንደሆነ አያሰጋንም፡፡ (በ21ኛው ክ/ዘመን ላይ እኮ ነን!) ደሞ ይሄ ሙያዊ እንጂ የኢህአዴግ ዓይነቱ የፖለቲካ ሹመት እኮ አይደለም! በዚያ ላይ የውጭውን ማኔጅመንት የምንፈልገው ለጥቂት ጊዜ ነው፡፡ ጥርስ ማውጣት ጀምሯል የተባለው ፓርላማችን፤ መንጋጋ እስኪያወጣ ብቻ! አያችሁ --- ፓርላማው መንጋጋ ያወጣ ዕለት “ተጠያቂነትም” የወረቀት ላይ ነብር መሆኑ ያከትምና የዱር ነብር ይሆናል!! ያኔ አዲስ አበባችንን ራሳችን ልናስተዳድር እንችላለን፡፡

(የተጠያቂነት ነብር አለና!) እኔ የምላችሁ … በቅርቡ በሰማያዊ ፓርቲ የተካሄደውን አወዛጋቢ የተቃውሞ ሰልፍ በተመለከተ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፤ “የኢህአዴግ ድራማ ነው!” ያሉት ነገር ገብቷችኋል እንዴ? ድራማው ምን እንደሆነ ስላልገባኝ እኮ ነው፡፡ የድራማ ነገር ከተነሳስ የሰሞኑ የኢህአዴግ ድራማ በጣም ተመችቶኛል --- አንዳንዴ ኢህአዴግ እያበዛው ነው እንጂ ፖለቲካ ሲባል እኮ ድራማ ነው፡፡ የእኛ አገር ብቻ ሳይሆን የዓለም ፖለቲካም ጭምር ድራማ ነው- የቀለጠ ትያትር! በነገራችሁ ላይ ባለፈው ማክሰኞ ማታ ከቤንሻንጉል ተፈናቅለው የነበሩ “የአማራ ተወላጆች” (አንዳንዶች “የኢህአዴግ ተወላጆች” ይሏቸዋል! ያደረጉትን የተቃውሞ ሰልፍ አያችሁልኝ … በአካል ሳይሆን በኢቴቪ! ከሰልፈኞቹ አንዷ ስለ ሰማያዊ ፓርቲ ምን ነበር ያለችው? “እነሱ ህገመንግስቱን ለማፍረስ የተነሱ ናቸው … ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ሊያራምዱ ፈልገው እንጂ ለእኛ አስበው አይደለም…” ወዘተ … ስትል የሰማኋት መሰለኝ (ኢተዓማኒ ድማራ ይሏችኋል ይሄ ነው!) አሁን እቺ ተፈናቃይ ሰልፈኛ ነች ወይስ ካድሬ? እንዴ … የሰልፉ ዕለት ማታ በኢቴቪ መግለጫ የሰጡት ሚኒስትር ዲኤታውም እንኳ እንደሷ አልተናገሩም እኮ! ይኸውላችሁ … አንዳንዴ ኢህአዴግ የድራማ ተዋናይ አመራረጥ ላይ ቀሽም ነው - “ካስቲንግ” አይችልበትም፡፡ አያችሁ … ተዋናይዋ እንደ ተፈናቀለ የአማራ ክልል ተወላጅ ሳይሆን ቅልጥ ያለች የኢህአዴግ ፖለቲከኛ ሆና ነው የተወነችው፡፡
(የአካባቢው ካድሬዎች ሂሳቸውን መዋጥ አለባቸው!) ምናልባት እኮ እሷ የተወነችው ህልሟን ሊሆን ይችላል። ኢህአዴግ ደግሞ የሷ ፖለቲከኛ የመሆን ህልም አይደለም ጉዳዩ -የሰማያዊ ፓርቲ አጀንዳ እንጂ። ለነገሩ … ህዝብን ሆኖ መተወን እኮ ከባድ ነው! (ህዝብን ይሆኑታል እንጂ አይመስሉትም!) የኢህአዴግ ካድሬዎች ግን ይሄን “ረቂቅ ጥበብ” የተረዱት አልመሰለኝም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በኢህአዴግ እርምጃ ተደስቻለሁ! (እሾህን በእሾህ የሚሉት ዓይነት እኮ ነው!) የሰማያዊ ፓርቲን ሰልፍ በኢህአዴግ ሰልፍ ነው የመከተው! (ያልተመጣጠነ እርምጃ ነው የወሰድኩት ብሎ ከመፀፀት ተርፏል!) አንዳንደ የታክሲ ረዳቶች (ወያላዎች) አንድን ሰው እንዲሳፈርላቸው ተለማምጠውት እምቢ ሲላቸው ምን እንደሚሉት ታውቃላችሁ? (ለነገሩ እናንተም ደርሶባችሁ ሊሆን ይችላል!) “ባቡሩ ሲመጣ ይወስድሃል” ይሉና ይፈተለካሉ (ከአፀፋ ምላሽ ሽሽት እኮ ነው!) ባቡሩ ምን እንደሆነ ገብታችኋል አይደል? መንገዱን ሁሉ እስርስር ያደረገብን የባቡር ሃዲድ ግንባታ ሲጠናቀቅ የሚመጣውን የከተማ ባቡር ማለታቸው እኮ ነው፡፡ እናንተ … የአራት ኪሎው ፓርላማ እኮ ፈፅሞ አልተቻለም፡፡ ከቀን ወደቀን ጡንቻ እያወጣ ነው።
የምክር ቤቱ አባላት “ጥርስ አውጥታችኋል” ሲባሉ “አናምንም፤ ድሮም ጥርስ ነበረን” አሉ እንጂ ትልቅ አብዮት እኮ ነው ያስነሱት! (ቀላል ቀወጡት!) እናላችሁ … ባለፈው ረቡዕ ማታ በኢቴቪ የቱሪዝምና ባህል ሚ/ርን ሲያፋጥጡ ደርሼ ምን ብሰማ ጥሩ ነው? የሉሲ የአሜሪካ ቆይታ በግልፅ ተብራርቶ ይነገረን ብለው ማፋጠጥ ያዙላችሁ! (ትርፍና ኪሳራዋን ማለታቸው መሰለኝ!) ሚኒስትሩም ሲመልሱ፤ ሁሉንም ገምግመን ስናጠናቅቅ ጥንካሬውንም ሆነ ከድክመታችን የተማርነውን ይሄ ነው ብለን እናቀርባለን” (ቃል በቃል ሳይሆን በደምሳሳው!) ምን ገረመኝ መሰላችሁ --- ፓርላማው ጡንቻ ማውጣት ከጀመረ አንስቶ “ከስህተታችን ተምረናል…”፣ “የአቅም ማነስ እንዳለብን ግንዛቤ ወስደናል”፣ “የአፈፃፀም ችግር እንዳለ ተማምነናል” ወዘተ … የሚሉ የመንግስት ሹመኞች በሽ በሽ ሆነዋል፡፡ እዚህች ጋ ግን አንድ ሃሳብ አለኝ … እኛን እየመሩ ከስህተታቸው ከሚማሩ ለምን ስልጣናቸውን አስረክበው ወደ ት/ቤት አይገቡም? ከምሬ እኮ ነው … እኛ ላይ ስህተት እየሰሩ መማርማ ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚለይ አይደለም፡፡
ይሄውላችሁ … ወደ ት/ቤት መመለስ እኮ ሞት አይደለም - ይቻላል! ካላመናችሁኝ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩትን እነ አቶ ልደቱና አቶ ስዬ፤ እንዲሁም ወ/ት ብርቱካንን ጠይቋቸው። ከስልጣን ወርደው አይደለም እንዴ በአሜሪካና በእንግሊዝ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርት የጀመሩት። ይሄን ያደረጉት እኮ ለጉራ ወይም ለቅንጦት አይደለም፡፡ ህዝብ ላይ ስህተት እየሰሩ መማር ተገቢ አለመሆኑን ስለተረዱ ይመስለኛል። መንግስትም ቢሆን እኮ አባላቱ የከፋ ወንጀል እስኪሰሩ ጠብቆ ወህኒ ከመወርወር ይልቅ ገና ምልክቱ ሲታይባቸው ወደውጭ አገር ልኮ ቢያስተምራቸው ተመራጭ ነው - ጥቂት አባላቱንም ከነአካቴው ከመጥፋት ያተርፍ ነበር፡፡ (ከሰማኝ አይደል?) እኔ የምላችሁ ግን … ግብፆች ሳንወድ በግድ ድምፁን አጥፍቶ የተቀመጠውን አገራዊ ወኔያችንን ቀሰቀሱት አይደል? (ሳይቸግር ጤፍ ብድር አለ አበሻ!) እንግዲህ ከየመረጃ ምንጮቹ እንደሰማነው፤ የግብፅ መንግስትና ፖለቲከኞች የተስማሙት “ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ እንድታቆም ማናቸውንም አማራጮች እንጠቀማለን” በሚል ነው፡፡
እኛ ጀግኖቹ የጦቢያ ልጆችስ? “ግድቡን ከመገንባት የሚያስቆመን የለም!” ( (ፈጣሪ የሰጠን ፀጋ እኮ ነው!) ለእስከዛሬውም ዓይን ዓይኑን ስናየው በመክረማችን በሰማይ ቤት ከመጠየቅ የምንድን አይመስለኝም! (አባይ እየተገማሸረ እኮ ነው ፆም ያደርነው!) ቆይ ቆይ … ግብፅ ምንድነው አለች የተባለው?” “የአባይ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ባለቤት እኔ ነኝ!” ምናምን ብላለች አይደል? ለካስ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን ይማረውና) በዚያ ግብፃዊ ጋዜጠኛ ኢንተርቪው ሲደረግላቸው “በ21ኛው ክ/ዘመን እንዲህ ያለ አስተሳሰብ---” ያሉት ወደው አይደለም - ብሽቅ አድርጓቸው ነው! እስቲ አስቡት---አባይ ከአገራችን ጉያ እየሸለለና እያፏጨ ሲወጣ እያየነው---ጫፉን መንካት አትችሉም ስንባል! (የልጅ ጨዋታ አደረጉት እኮ!) እኔ ግን ያልገባኝ ምን መሰላችሁ---- ግብፅ ግድቡን እንዳንገነባ የፈለገችው ውሃው ይቀንስብኛል ብላ ሰግታ ነው ወይስ በደረቅ ምቀኝነትና ንቀት ተገፋፍታ ምክንያቷ የትኛውም ቢሆን ግን “አንተ አብራ፤ እኔ ልብላ!” እንደማለት ነው፡፡ ወይም “ከባልሽ ባሌ ይበልጣል” እንዳለችው ራስ ወዳድ ሚስት መሆኗ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ አያዋጣም - (ኧረ ስንዝር አያስኬድም!) እኛ ግን “ጦርነት የታከተን ህዝቦች ስለሆነን ምርጫችን አናደርገውም” (ካልተገደድን በቀር!)

No comments:

Post a Comment