Friday, June 21, 2013

***መሆን የምንፈልገው VS መሆን የምንችለው***

ባለፉት ብዙ ዓመታት መሆን የምፈልገውን ለመሆን ብዙ ስጥር፤ብዙም ስደክም ኖሪያለሁ፡፡ ዓላማዬን ለማሳካት ለዓመታት ያደረግሁት ጥረት የቱንም ያህል የበዛ የነበረ ቢሆንም ስኬታማ ለመሆን ግን አልታደልሁም፡፡ 
የዓመታት ጥረቴ እና ልፋቴ ያለምንም ውጤት መና መቅረቱን ስገነዘብ ቆም ብዬ ማሰብ እንዳለብኝ አመንሁ፡፡ እናም ቆም ብዬ ማሰብ ጀመርሁ፡፡ ያለፈው ዘመን የሕይወት ፍልስፍዬንም በጥሞና አጤንሁት
የሕይወት ፍልስፍናዬን በጥሞና መመርመሬ እንዲህ ወደሚል ድምዳሜ አደረሰኝ፡፡ ‹‹የሰው ልጅ በሕይወት ዘመኑ ስኬታማ ለመሆን ከፈለገ መሆን የሚፈልገውን ሳይሆን መሆን የሚችለውን ብቻ ለመሆን መጣር አለበት፡፡›› መሆን የምንችለውን ለመሆን ጥረት ከመጀመራችን በፊት ግን መሆን የምንችለውን ለይተን ማወቅ ግድ ይለናል፡፡ አዎ፡፡ መሆን የምንችለውን በሚገባ ለይተን ካላወቅን መሆን የምንፈልገውን ለመሆን ስለጣርን ብቻ ስኬታማ መሆን አይቻለንም፡፡
ከላይ የጠቀስሁትን አባባል የበለጠ ግልጽ ለማድረግ በምሳሌ ላስረዳ፡፡ ስነ-ፀሐይ የተዋጣላት ሙዚቀኛ መሆን የረጅም ጊዜ ህልሟ ነው፡፡ እናም ይህንን ህልሟን ዕውን ለማድረግ ጥረቷን ያጧጧፈችው ገና ከልጅነት ዕድሜዋ ጀምሮ ነበር፡፡ ስነ-ፀሐይ ግን እንደተመኘችው የተዋጣላት ሙዚቀኛ መሆን አልቻለችም፡፡
መቸም ስነ-ፀሐይ የረጅም ጊዜ ህልሟን ዕውን ማድረግ ያልቻለችው በቂ ጥረት ስላላደረገች አንዳልሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ከስነ-ፀሐይ ጋር የሚያያዝ አንድ እውነታ አለ፡፡ ይኸውም ስነ መሆን የምትችለውን ሳይሆን መሆን የምትፈልገውን ነበር ለመሆን ስትጥርና ስትደክም የኖረችው፡፡ ስኬታማ መሆን ያልቻለችበት ምክንያትም ይህ ነው፡፡
ስለዚህ ሁላችንም በቅድሚያ መሆን የምንፈልገው ነገር መሆን የምንችለው መሆኑን ማረጋገጥ ይገባናል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ጥረት ማድረግ መጀመር ያለብን፡፡ ያለበለዚያ ግን ልፋታችን ሁሉ መና ይቀርብናል፡፡

ከሰብኣዊ

No comments:

Post a Comment