Wednesday, June 12, 2013

የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማስቆም ግብፅ አሉ የሚባሉ አማራጮችን ሁሉ እንደምትጠቀም ገለፀች “የህዳሴ ግድብ ለሰከንድም ቢሆን አይቋረጥም” ኢትዮጵያ



በፀጋው መላኩ

የግብፅ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ሙርሲ የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ አስመልክቶ የሀገሪቱ እስላማዊ ፓርቲዎች በጠሩት ብሔራዊ ኮንፍረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እየገነባች ያለውን የህዳሴ ግድብ በናይል ውሃ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እንዳያሳድር ለመከላከል ግብፅ አሉ የተባሉ አማራጮችን እንደምትጠቀም ገለፁ።
ንግግራቸው የሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ በሆነው ናይል ቲቪ በቀጥታ የተላለፈ ሲሆን በዚሁ ንግግራቸው “እኛ ጦርነት አንፈልግም። ነገር ግን የውሃ ህልውናችን አደጋ ላይ እንዲወድቅ ግን አንፈልግም” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ “ግብፅ የጦርነት ፍላጎት የላትም” ካሉ በኋላ ይሁንና በአባይ ውሃ የሚፈጠረውን ማንኛውንም ስጋት ለመጋፈጥ ሀገሪቱ ዝግጁ መሆኗን ገልፀዋል። “አንድ ጠብታ የአባይ ውሃ ከሚቀንስ ደማችን አማራጭ ቢሆን ይሻላል” ያሉት ሙርሲ፤ በእለቱ በርካታ የንግግሩን ታዳሚዎች አስጨብጭበዋል። በርካቶችም ከመቀመጫቸው በመነሳት በጩኸት ድጋፋቸውን ሲሰጡ በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭቱ ታይተዋል። ንግግራቸው በድጋፍ ጩኸት የታጀበው ፕሬዝዳንት ሙርሲ በመሀል የሚያቋርጣቸውን የድጋፍ ጩኸት ጋብ እስኪል እየጠበቁ ረዘም ያለ ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ የንግግራቸውን ሰፊ ጊዜ የወሰደው የግብፅ ህዝብ ከአባይ ጋር ያለውን ታሪካዊ ቁርኝት በመተንተን ነበር። የግብጽን ህዝብ ጀግንነት በተለይም በአረብ አብዮት ወቅት ያሳየውን ወኔና ቁርጠኝነት ያደነቁት ፕሬዝዳንት ሙርሲ፤ በዚሁ ንግግራቸው ኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገር ብትሆንም ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው ውጥረት ግብፅ ማንኛውንም ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን የምትጠቀም መሆናቸውን አመልክተዋል። ግብፅ በናይል ላይ ልማቶች እንዳይካሄዱ የማትቃወም መሆኗን ቢገልጹም ይሁንና ይህ የሚሆነው የሚሰሩት ፕሮጀክቶች ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ህጋዊና ታሪካዊ መብቶች (legal and historical rights) እስካልነካ ድረስ ነው ብለዋል።
የህዳሴው ግድብ ግንባታ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ማለትም በግብፅና በሱዳን ላይ ሊያመጣ የሚችለው አሉታዊ ተፅእኖ የሚመረምር የኤክስፐርቶች ቡድን ተቋቁሞ የራሱን ገለልተኛ ጥናት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በቅርቡም የለቀቀው ሪፖርት የግድቡ ግንባታ በሁለቱም የተፋሰስ ሀገራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የማያደርስ መሆኑን ገልጿል።
የኤክስፐርቶቹ ቡድን ከሱዳን ከግብፅና ከኢትዮጵያ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች የተውጣጣ ሲሆን ግብፅ በግድቡ ዙሪያ ከሰሞኑ ጠንከር ያለ አቋም መያዝ የጀመረችው ሁለት አበይት ክንውኖችን ተከትሎ ነው። የመጀመሪያው የገለልተኛ ኤክስፐርቶች አጥኚ ቡድኑ የደረሰበትን ውጤት መልቀቁን ተከትሎ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ የአባይን ተፈጥሯዊ ፍሰት ማስቀየሷን ከመግለጿ ጋር በተያያዘ ነው።
ዤኑዋ ሰሞኑን ባሰራጨው ዘገባ የኤክስፐርቶቹ ቡድን ሪፖቱን ለሶስቱም ሀገራት ማስረከቡን ተከትሎ ከሙርሲ ፅህፈት ቤት የወጣው መግለጫ ሁሉም የሀገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት ሪፖርቱን በዝርዝር ለማጥናት የሚያስችል ብሔራዊ ውይይት (National dialogue) እንዲያካሂዱ ጥሪ አቅርበዋል። እንደ ዥንዋ ዘገባ ሙርሲ ወደዚህ ድምዳሜ የደረሱት ግብፅን ወክለው በቴክኒካል ኮሚቴው ላይ ከተሳተፉት ግብፃውያን ኤክስፐርቶች ጋር የተናጠል ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው።
በመጨረሻ ዘግየት ብለው የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ የግብፅ ባለሥልጣናት የግድቡ ግንባታ ሊያመጣ በሚችለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አሉታዊ ተፅዕኖ ላይ የኤክስፐርቶቹ ቡድን የጥናት ውጤት ተጨማሪ ጥናት እንዲካሄድ ፍላጎት ያላቸው መሆኑ ታውቋል። ግብፅ በአሁኑ ሰዓት 55 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ የአባይ ውሃን እየተጠቀመች ሲሆን በ2050 የህዝቧ ቁጥር ወደ 150 ሚሊዮን ስለሚደርስ ከአባይ ተጨማሪ 21 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የምትፈልግ መሆኗን የሀገሪቱ ብሔራዊ ፕላኒግ ኢንስቲትዩት ሰሞኑን በለቀቀው መረጃ ገልጿል።
አንዳንዶች ሙርሲ በአንድ ዓመት የፕሬዝዳንትነት ቆይታቸው ውጤታማ ስላልሆኑ አባይን የህዝቡን የውስጥ ጥያቄ እንደማስቀየሻ እየተጠቀሙበት መሆኑን ይገልፃሉ። ሙርሲ በሰኞ እለት ምሽት ንግግራቸው ሁሉም ግብፃውያን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በማለት በናይል ጉዳይ ላይ በአንድ ላይ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። “ግብፅ የአባይ ስጦታ ናት” የሚለውን የቆየ አባባል የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ሙርሲ በሰኞ ምሽት ንግግራቸው፤ “ግብፅ የአባይ ስጦታ ከሆነች አባይም የግብፅ ስጦታ ነው” ብለዋል። ፕሬዝዳንት ሙርሲ ንግግራቸውን እንዳጠናቀቁ ታዳሚው ከመቀመጫው ተነስቶ ያጨበጨበላቸው ሲሆን ከአዳራሹ ሲወጡም በሺ የሚቆጠሩ ግብፃውያን መኪናቸውን በሩጫ በመከተል ድጋፋቸውን ሲቸሯቸው የናይል ቴሌቭዥን የቀጥታ ስርጭት አሳይቷል።
የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት ባወጣው መግለጫ በግብፅም ሆነ በማንኛውም ወገን የሚቀርብ የግድቡን ግንባታ የማዘግየት ወይም ከነአካቴው የማቋረጥ ነገር ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም።
ግብፅ በህዳሴው ግድብ ሽፋን የውስጥ ችግሯን ለማቃለል የምታደርገው ጥረት የግብፅን ዘላቂ ጥቅም የሚያስከብር አይደለም ያለው ይኸው መግለጫ ጦርነትንና ሌሎች አፍራሽ ስልቶችን ስለመጠቀም የሚቀርቡት ሀሳቦችን ያረጁና ያፈጁ፣ የ21ኛውን ክ/ዘመን አስተሳሰብ የማይሸከሙ፣ ጤናማ ያልሆኑ አስተሳሰቦች እንደሆኑና ኢትዮጵያ በዚህ ቀረርቶ ተደናግጣ ግንባታውን ለሰከንድም ቢሆን እንደማታቆም አረጋግጧል።n

No comments:

Post a Comment