Saturday, June 8, 2013

ድንቁርና የሚድንም የማይድንም ሕመም ሊሆን ይችላል



ከጥቂት ቀናት በፊት አንዳንድ ሰዎች በዓባይ ጉዳይ ቀረርቶና ሽለላ ማሰማት ሲጀምሩ ከባድ የሆነ የመረጃ እጥረት መኖሩን ስለተገነዘብሁ ስለግብጽ የኃይል ሚዛን ደረቅ መረጃ የጦርነትን መጥፎ መልክ ከሚገልጽ አስተያየት ጋር አቀረብሁ፤ የወያኔ ሎሌዎች ወዲያው በእኔ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ከፈቱ፤  ድንቁርናው ከዚህ ይጀምራል፤ ማሪዮ ፊልሞና ብሩኖ ‹‹በአፍራሽ አስተሳሰባቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ዛሬም የግብጽን ጦር ገና ከሩቁ እንድንገብርለት ጉትጎታ ይዘዋል፡፡›› በማለት ውርጅብኙን ይጀምራል፤ አንድም ቦታ እኔ ያቀረብሁትን መረጃም ሆነ አስተያየት አንሥቶ ጉድለትን አላሳየም፤ ዓላማው መረጃው ወይም አስተያየቱ አይደለም፤ ለረጅም ጽሑፉ ዓላማው እኔ ነኝ፤ የአሉላ ሰሎሞን ጆቫኒ የግጥም ዓይነት መልክ ከመያዙ በቀር ያው ነው፡፡
ለእነዚህ ሰዎች መልስ የሚያስፈልጋቸው በእኔ ላይ የሰነዘሩትን ለማረም አይደለም፤ አንዳንድ ሰዎች መልስ አይገባቸውም ይሉኛል፤ እውነት ነው፤ እኔ በሥራዬ እቆማለሁ፤ ወይም በሥራዬ እወድቃለሁ፤ ነገር ግን ንጹሐን ወጣቶችን አዋቂዎች መስለው እንዳይበክሉ መከላከል ግዴታ ነው ብዬ አምናለሁ፤ ድንቁርና እንደተላላፊ በሽታ ነው፤ ይጋባል፡፡
ድንቁርና መጥፎነቱና አደገኛነቱ ከኋላውም ሆነ ከፊቱ የሚያይበት ዘዴ አለመኖሩ ነው፤ ለዛሬ፣ ለሆድ ብቻ መኖርን ዕለታዊ ዓላማው የሚያደርግ ነው፤ አንጎሉ በድንቁርና የተሞላ ለምንም ሌላ ነገር ቦታ የለውም፤ ይህ ድፍን ወይም ፍጹም ድንቁርና ነው፤ ተስፋ-ቢስ ነው፤ አንጎሉ ውስጥ ድንቁርና ያልደረሰበት ትንሽ ቦታም ቢሆን ከአለ የእውቀትን ዘር ለመዝራትና ብርሃን ለመፈንጠቅ ዕድል ይኖራል፤ አለዚያ ድቅድቅ ጨለማ ነው፡፡

ፊልሞን በሚል ስም ራሱን የሚጠራው ከሽፍንፍን መውጣት ያልቻለው ፈሪ ፊደልን ብቻ የተማረ መሀይም ነው፤ ይህንን አንብበህ መልስ ስጥበት ብሎ ያዘዘው ሰው የእኔን ጽሑፍ ካልሰጠው በቀር የእኔ ስም ባለበት ሰሌዳ ደርሶ ከሆነ ሰውዬው የማየት ችግርም አለበት ማለት ነው፤ በሰሌዳው  መጀመሪያ ገጽ ላይ የእኔ መጽሐፎች ሽፋኖች ይታያሉ የሎሌነቱን ተግባር ለመፈጸም የቀባጠረውን በዝምታ ማለፍ እሱን ራሱንም ሆነ በተለይም የአነበቡትን ሰዎች መጉዳት ሰለመሰለኝ ከእውነቱ ጋር እንዲጋፈጥ ማስገደድ ይገባኛል፤ ባንዳውን ምሁር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስን ማወቁን ሳደንቅለት ኃይለ ሥላሴ ጉግሳንና ጭፍሮቹን እንዳልረሳቸው ተስፋ አለኝ፡፡

 እኔ እስከማውቀው ድረስ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከእርሳቸው በበለጠ የጦርነትን ምንነት ጠንቅቆ የሚረዳ እና የጦርነትን አስከፊነት እንደክቡርነታቸው በቴሌቪዥን ሳይሆን በተግባር የሚረዳ ይመስለኛል:: እናም የሃገራችን ጥቅም ለማስከበር በሚደረገው ሰላማዊ እና ፍትሃዊ ስራ ከጎን ከመቆም ይልቅ በተንኮላቸው የማይወዱትን አካል ጠልፎ ለመጣል እስከጠቀመ ድረስ የሃገርን ጥቅም ለመሸጥ ጉጉነታቸውን አይቸበታለሁ፡፡

ይህንን ለመጻፍ የሚያስችል ድንቁርና ፍጹም ነው፤ ይህንን ፍጹምነት ሲያጠናክረው፤ –

ሰውየው እኮ ሃገራችን በደም አንባ ስትታጠብ በርሃብ አለንጋ ስትገረፍና ህዝቦቿ በአለም አደባባይ ስንዋረድ የኬንያዊውን የመሃመድ አሚንን ያክል ለሃገራችን ያላበረከቱ ግለሰብ ናቸው:: ዜጎች ያለፍርድ ሲረሸኑ ሲዋረዱ ሃገራችን የጨለማ ዘመን አገዛዘን እያማከሩ ሲሰሩ የነበሩ ሰው ስለሃገር ክብርና ስለሃገር እድገት ብዙም ይገዳችዋል ብሎ መጠበቅ ከሰማይ ደመናን እንደመዝገን ይሆናል::ተማሪወቻቸው እና ከሳቸው በእጅጉ በትምህርት እና በእድሜ የሚያንሱ ወጣቶች ለሃገራቸው እና ለህዝባቸው ነጻነት ሲዋደቁ ክቡርነታቸው ግን ለንደን እና ዋሽንግተን እየተንሸራሸሩ በነበረበት ወቅት በርሃብ እና በጦርነት እየነደደ ስለነበረው ህዝባቸው አንዲትም ቃል እንደተነፈሱ ታሪክ የላቸውም ::

የተማሪ ቤት ግቢን የረገጠ ይህንን አይጽፍም፤ አንደአለቆቹ መሸጦ አስተማሪ ቤቱ ድረስ እየሄደ ፊደል ያስቆጠረው ሳይሆን አይቀርም፤ ፊደሉን ማወቁን እንደመጨረሻ ትምህርት ወስዶታል፤ በአንድ በኩል የሚያሳዝን ሰው ነው፤ በሌላ በኩል ግን ድፍረቱ ድንቁርናን የሚያበረታና ለጥቃት የሚዳርግ ነው፤ ለኮሎኔል መንግሥቱ ጂቡቲ ጦርነት ብትከፍት ኢትዮጵያ እንደማታሸንፍ ነግሬው ነበር፤ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የክምችት ክፍል ሄዶ በጓደኞቹ እርዳታ ትንሽ ቢቆፍር በደርግ ዘመን ‹‹ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ሆነዋል፤›› በማለት የተናገርሁትን ያገኘውና ዓይኑን ይከፍትለት ነበር፤ ምስክሮቹ ሁሉ በሕይወት ባሉበት ጊዜ እንዲህ ያለ ውንጀላ አያዋጣም፤ ወይም እኔን በባንዳነት ከራሱ ጋር ሊያዛምደኝ ፈልጎ ከሆነ ያማ መንገድ አያስሄድም፤ እግዚአብሔር ይመስገንና በዚህም በዚያም ከባንዳ ጋር ንክኪ የለኝም፡፡
እኔ ስለጦርነት የጻፍሁት ለሚያውቁና ማሰብ ለሚችሉ ሰዎች ነበር፤ የሚያውቁ ሰዎች የምላቸው የአሥራ ዘጠነኛውን የመጀመሪያ አጋማሽና የሃያ አንደኛውን ምዕተ-ዓመታት ሁኔታዎች ተገንዝቦ ማመዛዘን የሚችለውን፣ በአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ-ዓመት መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ በአድዋ ላይ የተቀዳጀችውን ድል በኩራት እያስታወሰ በሃያኛው ምዕተ-ዓመት ደግሞ በማይጨው ላይ በኢጣልያ ጦር የተሸነፈችበትን ውርደት የሚያውቅና የሚሰማው፣ በዚያው ላይ ኢጣልያ በአድዋ መሸነፍ የተማረች ስትሆን ኢትዮጵያ በአድዋ ድልም ሆነ በማይጨው መሸነፍ ሳትማር መቆየቷን የሚያውቅና የሚቆረቆር፣ ካላወቀም ለማወቅ የሚጓጓ ሰው ነው፤ ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ጦር ከወያኔ ጀሌ ጋር፣ ከሻቢያ ጀሌ ጋር፣ ከሶማልያ ጋር፣ በቅርቡም ከኤርትራ ጋር፣ በኋላም ከሶማልያ አክራሪዎች ጋር በተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ የሚያኮራ ነገር አልታየም፤ ይህንን ሁሉ እውነት አውቆና አመዛዝኖ ለማየት የማሰብ ችሎታን ይጠይቃል፤  ማሪዮ ፊልሞና ለዚህ አልታደለም፤ በቅዠት ዓለም ውስጥ ሆኖ ራሱን አሉላ የሚለው ብሩኖም እንዲሁ ያልታደለ ሎሌ ነው፤ ለሁለቱም ከጉራዕና ከጉንደት በኋላ ታሪክ የለም፤ እዚያ ላይ ቆሟል፤ የደበዘዙ ዓይኖችና የደነዘዙ አንጎሎች በአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ-ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የሆነውን ይዘው 2005ን ለመደልደል የሚፈልጉ እንደፊልሞንና እንደአሉላ ሶሎሞን ያሉ ምስኪኖች እንዳይታዘንላቸው ትዕቢታቸው አያስቀርብም፤ እንዳይተዋቸው መርዛቸው ብዙ ሰዎችን ሊጎዳ ይችላል፤ ያለው አማራጭ ድንቁርናቸውን ማጋለጥ ብቻ ነው፡፡
የታሪክ ዋናው ዓላማ ጥቅም ዓይኖችን በአለፈው ነገር ላይ ተክሎ ወደኋላ ለማየት ሳይሆን ከፊታችን የተደቀነውን የዛሬውን ችግር ለመወጣት ከአለፈው ስሕተት መማር ነው፤ አንድ ጥያቄ፡– የኢትዮጵያ ድንበር ከዓባይ ጀምሮ ወደሰሜን እየሰለለ የሄደው ለምንድን ነው? እነፊልሞንና እነአሉላ ሶሎሞን ይህንን የማስተዋል ብቃት የላቸውም፤ ቢያስተውሉትም ስለማያስቡ አያሳስባቸውም፤ ማሰብ ቢችሉ የሚደነፉበትንና ግጥም የሚጽፉበትን ወደእፍረት ይለውጥባቸው ነበር፤ በቅርቡም በባድመ ጦርነት ፉከራውና ሽለላው ወደእፍረት ሲለወጥ አይተናል፤ ድንቁርና የሚደነድነው እውነትን፣ ከእውነት ጋርም እውቀትን እያፈነ ነው፡፡
በ1864 ዓ.ም. አካባቢ በጦርና በጋሻ አሸንፈናል፤ ዛሬም በ2005 ዓ.ም. በዚያው ዘዴ እናሸንፋለን ማለት የድንቁርና ዘውድ ነው፤ እኛ እንዳልተለወጥን ሌሎችም አልተለወጡምና በ1988 ዓ.ም. በአድዋ ኢጣልያን ድባቅ መተናል፤ እያልን ስንፎክር በ1928 ተመልሶ ሲመጣ በማይጨው ድባቅ መታን፤ ያን ጊዜ የሆነውን ማን ነው ከታሪክ የተማረው? ዛሬ ኢጣልያ ቢመጣ ፊልሞንና አሉላ ከነጓደኞቻቸው መንገድ መሪዎች መሆናቸው እጅግም አያጠራጥርም፤ ምክንያቱም እኔ የግብጽን ኃይል ለማሳወቅ የፈለግሁት እንዳንዘናጋ ሲሆን የእነማሪ ፊልሞንና አሉላ ጆቫኒ ፍላጎት ደግሞ ለማዘናጋት መሆኑ ነው፤ ዋናው ጥያቄ ግን ለምን እንድንዘናጋ ይፈልጋሉ? የኢትዮጵያ መዘናጋትና ለአደጋ መጋለጥ ምን ይጠቅማቸዋል? የሚለው ነው፤ መልሱ ውስጥ አልገባም፤ ፡፡
ዘመኑ እውቀት የረከሰበት ነው፤ ዛሬ አንድ ሰው የፈለገውን እውቀት ለማግኘት ከስንፍናና ከእኩይ ትዕቢት በቀር የሚያግደው የለም፤ በድንቁርና ከመኩራራት ፈርጠም ብሎ በእውቀት መስተካከልና ለወደፊቱ ማሰብ ቀና ይሆናል፤ ድንቁርናን የሚድን ሕመም እናድርገው፡፡

No comments:

Post a Comment