ከኤልያስ
የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅሌት የክፍለ ዘመኑን ሪከርድ ሰብሯል!
“ስህተት የፈፀምነው ስለሰራን እኮ ነው” (አንድ እየሰሩ ሺውን መናድ?)
የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወዳዳሪ የሌለው ቅሌት በመፈፀም የዓመቱን ሳይሆን የክፍለ ዘመኑን ሪከርድ መስበሩን በሳምንቱ መግቢያ ላይ አብስሮናል!! (Scandal of the Century ይሏል ይሄ ነው!) እኔና እንደኔ ያሉ አንዳንድ ገራገሮች ነገርዬውን በቅሌት ብቻ ብናልፈውም ጥቂት የማይባሉ ደመ - መራራ የአገሬ ልጆች ግን የፌዴሬሽኑን እሳት አደጋ የማይመልሰው ከባድ አገራዊ ጥፋት “ከአገር ክህደት ለይተን አናየውም” የሚል መግለጫ እንዳወጡበት ሰምቻለሁ (ደማቸው ፈልቶ እኮ ነው!) ደግነቱ ግን መግለጫው አደባባይ አልወጣም፡፡ በየልባቸው ውስጥ ቀርቷል ተብሏል፡፡ ባለፈው እሁድ የብሄራዊ ቡድናችንን ድል ተከትሎ የተፈጠረውን ደስታ ሽፋን አድርገው፣ የሰው ንብረት ሲሰባብሩ ነበር የተባሉ አንዳንድ ጋጠወጦች ደግሞ ምን አሉ መሰላችሁ? “የፌዴሬሽኑ አመራር የፈፀመው ስህተት ከአሸባሪነት አይተናነስም!” ብለው ቁጭ አሉ፡፡
ለእነዚህ እንኳ ጆሮም ልንሰጣቸው አይገባም ባይ ነኝ። መቼ ራሳቸው ደግና ክፉውን ለዩና ነው ፍርድ የሚሰጡት፡፡ በአገር የደስታ ቀን ደስታ የሚያጠፉ ዋልጌዎች እኮ ናቸው! እነዚህንስ ለቃቅሞ ማረምያ ቤት መወርወር ነበር - ከጋጠወጥነታቸው ታርመው እንዲወጡ፡፡ ወደ ፌዴሬሽኑ ጉዳይ ስንመለስ--- እኔን ምን እንዳስገረመኝ ታውቃላችሁ? የፌዴሬሽኑ አመራሮች በእነሱ ብሶ በእኛ ላይ መነጫነጫቸው! ቆይ ግን ---አገርን ያህል ነገር ንደው፣ በስንት መከራ የተገነባውን አፍርሰው “ተሳስተናል” ስላሉ ብቻ በሰላም ወደየቤታችሁ ግቡ እንዲባሉ ፈልገው ነበር እንዴ ? ( “ደፍረውናል” ያለው ማን ነበር!) እናላችሁ-----አመራሮቹ መግለጫ የሰጡ እለት ከጋዜጠኞች ያልተጠበቁ ጥያቄዎች ሲወረወርባቸው የሚናገሩት ሁሉ ጠፍቷቸው ሲዘባርቁ ነበር አሉ፡፡ መዘባረቁን ያመጣው ምን መሰላችሁ --- “አመራሩ ሃላፊነቱን ይለቃል ወይ?” የሚለው የጋዜጠኞች ዱብእዳ ጥያቄ ነው፡፡ በቃ--- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን መልስ እኮ ነው የሰጡት፡፡ (እግር ኳስ ፖለቲካ ነው የሚባለው ለካ እውነት ነው!) በተለይ የፌዴሬሽኑ ዋናው ፕሬዚዳንት እኮ በትርፍ ሰዓታቸው በፓርቲ መሪነት የሚሰሩ ነው የመሰሉት። (ንግግራቸው ቁጭ እኮ ነው!) የለም ተሳስተሃል ከተባልኩ ደግሞ የፓርቲ መሪዎች የሚሰጡትን ዓይነት መልስ ሸምድደው እንደመጡ በእርግጠኝነት እገምታለሁ፡፡
እኔን ካላመናችሁኝ ደግሞ ራሳቸው ፕሬዚዳንቱ ከተናገሩት ልጥቀስላችሁ ---- “መጀመርያ ይሄን ነገር እንደሰማሁ ሥልጣኑን እለቃለሁ ነበር ያልኩት” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣በኋላ ግን ሃሳባቸውን እንደቀየሩ ገልፀዋል (ሰይጣን አሳስቷቸው ይሆን?) የፌዴሬሽኑ ሃላፊ ከሥራ የመልቀቅ ሃሳባቸውን የቀየሩበትን ምክንያት ስትሰሙ ነው እኔ ካልኩት ሃሳብ ጋር (የፖለቲካ መሪነት ከምትለዋ ማለቴ ነው) በደንብ የምትስማሙት። ምን አሉ መሰላችሁ --- “ለማን ጥለን እንሄዳለን? ---የሚቀጥል ይኖራል የማይቀጥልም --- ክለቦች ከፈለጉን፣ ጉባኤው ከፈለገን ---መንግስት ከፈለገን -- የምንቀጥልም የማንቀጥልም እንኖራለን --- የናንተ ጭንቀት አይደለም --- ጉባኤው ይወስነዋል” የሚል ምላሽ ሰጡ - ለተሰበሰቡት የስፖርት ጋዜጠኞች። እውነቴን እኮ ነው የምላችሁ ---- አምባገነን የሥልጣን ጥመኞች ከሥልጣን የመልቀቅ ጉዳይ ድንገት ሲነሳባቸው የሚሰጡትን መልስ እኮ ነው ቃል በቃል ቁጭ ያደረጉት (እኔማ “አወይ መመሳሰል” አልኩኝ!) ሁሉንም አመራሮች ምን ያመሳስላቸዋል ያላችሁኝ እንደሆነ --- የራሳቸውን ጥፋት ወደማይናገረውና የማይጋገረው ግኡዙ ፌዴሬሽን ለማስተላለፍ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አለመኖሩ ነው እላችኋለሁ፡፡
እዚያው መግለጫ በሰጡበት መድረክ ያጉተመተሙት ነገር ቃል በቃል ባይሆን እንኳን በደምሳሳው - “ እርግማን እንጂ ምስጋና የሌለበት ፌዴሬሽን---ይብላኝ ለሚተካው እንጂ እኛማ በቅቶናል-- ዝርክርክ ፌዴሬሽን ነው” ወዘተ---በማለት ከመቅፅበት ባይተዋርና ባዳ አድርገውታል - የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን (ዋት ኤ ፒቲ! አለ ፈረንጅ) በነገራችሁ ላይ የጥፋቱ አንዱ ተጠያቂ ሆነው የቀረቡት የፌዴሬሽኑ አመራር ያቀረቡት ሰበብ ጭንቅላት አሲዞ “ወይ እቺ አገር!” የሚያስብል ነው፡፡ ምን ቢሉ ጥሩ ነው --- ሌላ የግል ሥራ እንዳለባቸውና በቂ ጊዜ እንደሌላቸው በግልፅ ተናግረዋል (አድናቂያቸው ነኝ !) እኔ የምለው ግን --- በቂ ጊዜ ያለው ሰው ለፌዴሬሽኑ ጠፍቶ ነው ወይስ ሥራው በበጎ ፈቃደኝነት ነው የሚሰራው? (ያለገንዘብ ማለቴ ነው!) የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በይቅርታ ብቻ እንታለፋለን ብለው ያሰቡት በአንድ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም ብዬ አስባለሁ።
ጥፋታችንን በአደባባይ ካመንን ህዝቡን አስደምመነው ሁሉም ነገር “ቢዝነስ አስ ዩዥዋል!” ይሆናል በሚል ሳይሆን እንደማይቀር በግምት ላይ የተመሰረተ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ እንዴት መሰላችሁ ---- ስህተትን ማመን ለእኛ ብርቃችን መስሏቸው እኮ ነው! ይሄ ሁሉ የመጣው ደግሞ ለመረጃ ዋጋ ስለማይሰጡ በተፈጠረ የመረጃ ክፍተት ይመስለኛል! ለመረጃ ዋጋ ቢሰጡማ--- ድልን ወደ ሽንፈት ሊለውጥ አቅም ያለው የብጫ ካርድ መረጃ የት እንደገባ አናውቅም በማለት፣ ስንገነባ የከረምነውን የኳስ ውጤት አይንዱብንም ነበር፡፡ እናም በዚህ አጋጣሚ “ስህተት ሰርተናል” ብሎ በአደባባይ ማመን ብርቃችን እንዳልሆነ የሚመለከተው ወገን ሁሉ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን፡፡ እድሜ ለኢህአዴግ! ላለፉት 22 ዓመታት እኮ ይሄንኑ ነው ያስተማረን - ሁሌም መሳሳት! ሁሌም ስህተትን ማመን! (ሂስን መዋጥ ይሉታል በፓርቲው ቋንቋ!) ለነገሩ ስህተትን በማመንና አጥፍተናል ብሎ በይፋ በመናገር አውራው ፓርቲያችን ፈርቀዳጅ ባይሆን ኖሮ፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽናችን በአንድ ጊዜ ሁለት ሪከርዶችን ይሰብር ነበር - አንደኛው የክፍለዘመኑ ቅሌት በሚለው ዘርፍ ሲሆን ሌላው ተሳስተናል በሚለው ዘርፍ ይሆን ነበር፡፡ ችግሩ ግን ተቀደመ፡፡
እኔ ግን የፌዴሬሽኑን አመራሮች በተመለከተ አሁንም ድረስ ያልተዋጠልኝ ነገር ምን መሰላችሁ? እግር ኳስ ተጫውታችሁ ዋንጫ አምጡ ያላቸው እኮ የለም! ምነው ታዲያ አንድ ተጫዋች ያየውንና በፊፋ የተላከውን ብጫ ካርድን የተመለከተ መረጃ ለሚመለከተው ወገን ማቀበል እንዲህ አቀበት ሆነባቸው? ሌላው የገረመኝ ጥፋትን ከማመን ጎን ለጎን የተደረደሩት ሰበቦች ናቸው - “በሌሎች ጉዳዮች ተወጥረን ነበር”፣ “የተጫዋቾችን ቪዛ ለማስመታት ስንሯሯጥ ነበር” ወዘተ--- ፋይዳቸው ፈፅሞ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ እንዴ --- ዋና ስራቸው ምን ሆነና? ለምሳሌ--- አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የምርጫ እለት እጩዎች አልመለመልኩም ቢል የሚሰማው ያገኛል እንዴ? (እንስራዋን ጥላ ወንዝ ወረደች አሉ!) አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ሹክ ያለኝ ነገር ደግሞ ትንሽ አስደንግጦኛል፡፡ በአመራሮቹ መካከል መኮራረፍ… አለመከባበር… የቀናነት ጉድለት…በአጠቃላይ ኮሚዩኒኬሽን የሚባል ነገር ጨርሶ እንደሌለ ነግሮኝ የባሰ ተስፋ አስቆርጦኛል። ነገርየው ለጊዜው ያስደንግጠኝ እንጂ ረጋ ብዬ ሳስበው እንደ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሃሳቤን ቀይሬአለሁ፣ ለካስ --- የኩርፊያ ነገር የጦቢያችን ልዩ ምልክት ነው፡፡
አሁን ለምሳሌ ከጥቂት አመታት በፊት እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለሁለት የተሰነጠቀው የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር አመራሮች እርስ በርሳቸው ይነጋገራሉ ብላችሁ ታስባላችሁ? (የሚያስታጥቃቸው አጥተው ነው እንጂ ከመጨራረስ ወደኋላ የሚሉ አይመስለኝም) ስንቶቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው ከኢዴፓ ጋር መልካም ግንኙነት ያላቸው? (ያልተኮራረፉት ማለቴ ነው!) ኢህአዴግና መድረክ አንነጋገርም ብለው ከተፈጠሙ ስንት ዘመናቸው ሆናቸው? ፖለቲከኞችስ እሺ---የሚፎካከሩበት ጉዳይ ራሱ እሳት ነው (የስልጣን የቤት ስሙ እኮ እሳት ነው!) ግን እሱም ቢሆን አደጋ አለው(ሥልጣን ያለስልጣኔ “hard” ነዋ!) ቆይ ቴሌና መብራት ሃይል---ውሃ ፍሳሽና መንገድ ትራንስፖርት መች በወጉ ይነጋገራሉ? ከቶውንስ መች ይናበባሉ? ቢነጋገሩ ኖሮማ---ከተማዋ በየተራ እየተቆፋፈረች ይሄን ሁሉ ምስቅልቅል አናይም ነበር (ማን ነበር ምስቅልቅሉ ቢኖርም የእድገት ምስቅልቅል ነው ያለው?) እናላችሁ… ነገርዬው አገራዊ ጉዳይ (ችግር) በመሆኑ አገራዊ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል እላለሁ።
በህግና በቁጥጥር ወይም በተጠያቂነት ምናምን ግን አይደለም (እንደማያዋጣ አይተነዋላ!) ይኸውላችሁ --- ይሄ ችግር የሚፈታው በሌላ ሳይሆን በአገር ሽማግሌ ብቻ ነው!! ቀልድ እንዳይመስላችሁ --- ነገርየው ትንሽ መረር፣ ትንሽ አረር ብሏል፡፡ እስቲ አስቡት----ግብፆች በአባይ ግድብ ጉዳይ ላይ ገዢው ፓርቲ ወይም ተቃዋሚ ሳይሉ በአንድ ሸንጎ ተሰይመው ሲያሴሩብን ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች “የአገር ጉዳይ ነው”ብለው ለአምስት ደቂቃ እንኳን መች አንድ ላይ ተቀመጡ (እርግማን አለብን ይሆን?) የሆኖ ሆኖ ግን ይሄ አገርን እስርስር ያደረገ የኩርፊያ ሰንሰለት የግድ መበጠስ አለበት ባይ ነኝ ! በነገራችሁ ላይ የሽማግሌዎች ቡድን የሚያስፈልገው የተቃዋሚ አመራሮች ወህኒ ቤት ሲገቡ ለማስፈታት ብቻ እኮ አይደለም፡፡ እንዲህ ራሳችንን በኩርፊያ ስናስርም ሽምግልና ያስፈልገናል - ከራሳችንም ከሌላውም ጋር የሚያስታርቀን፡፡ ያለበለዚያ እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ብዙ የቅሌት ሪከርዶችን ስንሰብር መክረማችን ነው፡፡ (መናናቅ ባመጣው ጦስ!) የፖለቲካ ወጌን ላጠናቅቅ ስል አንድ ሸጋ ወሬ ደረሰኝ (መረጃም ማስረጃም የሌለው) ምን መሰላችሁ---ከፌዴሬሽኑ አመራሮች መካከል ሁለቱ ሂሳቸውን የዋጡ አመራሮች የሥራ መልቀቂያ ጠየቁ የሚል ነው። አንጀቴ ቅቤ ጠጣ የሚያስብል ባይሆንም አበረታች እርምጃ መሆኑን ግን ማንም አይክደውም። አገር እየናዱ ይቅርታ ከመጠየቅ የሥራ መልቀቂያ መጠየቅ ይሻላል ባይ ነኝ (ተጠያቂነቱም ሳይቀር ነው ታዲያ!)
No comments:
Post a Comment