Wednesday, June 19, 2013

የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ስህተት መስራቱን አምኖ ሕዝቡን ይቅርታ ጠየቀ

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቦትስዋና አቻው ጋር ሰኔ 1 ቀን 2005 .ም ባደረገው ጨዋታ ሁለት ቢጫ ካርድ አይቶ የነበረው ምንያህል ተሾመ መሰለፉ ስህተት እንደነበረ የኢትዮጽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በማመን ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ ጠየቀ።
የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮምቴ አባላት ትላንት በግዮን ሆቴል በሠጡት መግለጫ ብሄራዊ ቡድኑ ከደቡብ አፍሪካ  አቻው ጋርከመጫወቱ በፊት ችግር ስለመፈጠሩ ከፊፋ ደብዳቤ ደርሶት እንደነበርም አምኗል።
 ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ ናቸው ከተባሉት መካከል  የብሄራዊ ቡድኑ ቡድን መሪ አቶ ብርሀኑ ከበደ፣ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ረዳት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፣ የቡድኑ ተጨዋች ምንያህል ተሾመ እና የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ኃላፊዎች ይገኙበታል።
ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በጥፋተኞቹ ላይ በቅርቡ ተገቢውን ቅጣት በመውሰድ  ውሳኔውን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ጨምሮአስታውቋል።
የቡድኑ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በተፈጠረው ስህተት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀው፤ ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ለሚካሄደውጨዋታ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አሰልጣኙ አያይዘውም በጨዋታውም አሸንፈን ወደ አለም ዋንጫ እንደምንሳተፍ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።
በፊፋ ህግ መሰረት ሁለት ቢጫ ካርድ ያየ ተጨዋች ተከታዩን አንድ ጨዋታ የሚቀጣ ሲሆን ይህን ተጨዋች ሳይቀጣ ማሰለፍበጨዋታው የተገኘውን ነጥብ እና ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣትም ያስከትላል።

No comments:

Post a Comment