Saturday, June 1, 2013

ኑሮዬን ለማሻሻል ወደ ጉምሩክ...


ጊዜው በጃንሆይ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ አንድ ሰውዬ ነበረ፡፡ ፈጥኖ ደራሽ (ፖሊስ?) ነው፡፡ ፈጥኖ ደራሽ ማለት ያው ጦር ሠራዊት ማለት ነው፡፡ ግንኙነታቸው ከጀርመን ጋር ስለሆነ ጠመንጃቸው ማስ MASS ነው፡፡ የጦሩ ግን የአሜሪካ ኤም ዋን M-1- ነው ይባላል፡፡ በተረፈ ባብዛኛው ነገራቸው ፈጥኖ ደራሾች ልክ እንደጦር ሠራዊት ናቸው፡፡ ወጥቶ አደር በጠረፍ አካባቢ መዘዋወርና ወንበዴና ወመኔን መመንጠር ከፊናንስ ፖሊሶች ጋር በመተባበር ኮንትሮባንዲስቶችን ማሳደድና ህገ-ወጥ ንብረቶች መውረስ የአገሪቱን የንግድ አመራር ሥርዓት የማስያዝና የየበረሃውን ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ ነው፡፡ ዛሬም በረሃ፣ ነገም በረሃ ሁሌም በረሃ ነው፡፡ ቤተሰቡ አዲስ አበባ ነው፡፡ ደመወዙን በሙሉ ለቤተሰቡ ተቆራጭ ያደርግና ይሄዳል፡፡ እሱ የሚኖረው በበረሃ ቀለቡና ለሥጋ ተብላ በወር የምትሰጠው ሦስት ብር ብቻ ነው፡፡ ለወር የሥጋ መሸመቻ ሦስት ብር መንግሥት ይሰጠዋል፡፡ የዛሬን አያድርገውና ይበቃ ነበር፡፡ አሳምሮ፡፡ ዛሬ ሌላው ቀርቶ የኛ ሰፈር እንኳ ባቅሙ አንድ ኪሎ ሥጋ 140 ብር ይሸጣል፡፡ እና ፈጥኖ እረፍት የለውም፡፡ ደንቡ የአመት ፈቃድ ያገኛል ቢልም እሱ ግን በተግባር የሚያገኘው ፈቃድ በሁለትና በሦስት ዓመት አንዴ አሥር ቀን ለማትሞላ ጊዜ ያህል ነው፡፡ እሷኑ ከሚስቱ ተቀራርቦ ዘር ይተውና ይሄዳል፡ ልጁ ሲወለድ ክርስትና ሲነሳ፣ ሲገረዝ... ምናምን ሲል አባትየው የመገኘት እድል የለውም፡፡ ፎቶግራፍ ትልክለታለች በቃ ይሄው ነው፡፡ በመጣ ጊዜ ሁሉ ወሬው የበረሃ ብቻ ነው፡፡ አንዴ መጣና ለሚስቱ ስለበረሃ ኑሮው ያወራላታል፡ ምን ሆነ መሰለሽ ይላታል፡፡ ለግዳጅ ስዘዋወር ኢሚ፣ ኢልካሬ፣ ፊቅ፣ ጭናክስን፣ ቶጐጫሌ፣ ፌርፌር፣ ዶሎ... ወዘተ እያለ የበረሃውን ነጥብ ጣቢያ እየጠቃቀሰ ያወራላታል፡ በጥሞና አዳምጣው አውርቶ ሲጨርስ ሚስት ቀጠለች ባለቤቴ ሆይ አለችው፡፡
ይህ የምታወራልኝ ነገር ሁሉ ዋጋ የለውም፡፡ ከአንተ ጋር የተቀጠሩትና ትራፊክነት የተመደቡት ፖሊሶች ቦታ ተመርተው፣ ሰፈር መስርተው ቤት ሠርተው እቁብ ጠጥተው ቡችላ የሚያካክል ወርቅ ጣታቸው ላይ ሰክተው ሚስቶቻቸው በፈትል ቀሚስ በአንገት ሃብልና በጆሮ ጌጥ ተውበው ሁልጊዜ ሥጋ በልተው የራሳቸውን እድር መስርተው እንደልባቸው ተንደላቅቀው እየኖሩ ነው፡ በኪራይ ቤት የምንኖረው አንተና እኔ ብቻ ነን፤ እንኳንስ ፈትል ልለብስ ሳላይሽ ጨርቅ ያረረብኝ እኔ ብቻ ነኝ፡፡ አንድ ትራፊክ ማታ ሲመጣ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ጆንያ ከሰል ሳያሸክም አይመጣም፡፡ በሳምንት አንድ ጠቦትም አያጣም፡፡ አንተ ግን በሁለት አመትህ ስትመጣ ይዘህልኝ የምትመጣው አንዲት ብልቃጥ የፌርፌር ሽቶና ውቃቢ አለብኝ ያልኩህ ይመስል ያቺን ትንሿን አቡ ቢንቲ የምትባል የሱዳን ሽቶ ነው፡፡ ምንም ዋጋ የሌለው ነገር ነው እኛስ ሰው የምንሆነው መቼ ነው? ከጠፍር አልጋ ተላቅቀን አረግራጊ የሽቦ አልጋ ላይ የምንተኛው መቼ ነው? ፈትል ጥበብ የምለብስው መቼ ነው? አንተስ ከበረሃ መንከራተት የምትላቀቀው መቼ ነው? ... ትለዋለች፡፡ ታዲያ ምን ላድርግ? ይላታል፡፡ በረሃ የተፈጠረው ላንተ ብቻ ነው እንዴ? ቀይሩኝ በልና ማመልከቻ አስገባ አለችው፡፡ ተስማማ! ፃፈና አዘጋጀ፡፡
ለክቡር የኢት ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የፖሊስ ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ... እኔ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አባል አንበሴ ሞኙ አገሬን በውትድርና ለማገልገል በነበረኝ ፍቅር ላለፉት 10 ዓመታት በየበረሃው ስንከራተት መኖሬን ክቡርነትዎ ከግል ማህደሬ ይገነዘበዋል፡፡ ሠራሁ ሠራሁ ምንም ጠብ ያለልኝ ነገር የለም፡፡ ከሠፈራችን የመጨረሻው ደሀ የምባለው እኔ ነኝ፡፡ ይኼው እስከዛሬ የምተኛው ጠፍር አልጋ ላይ ነው፡፡ ... ከእኔ ኋላ ተቀጥረው ትራፊክነት የገቡ ጐረቤቶቼ ባለመሬትና ባለቤት ሆነዋል፡፡ ፋሚሊ አልጋ ላይ ተኝተዋል፡፡ ፊሊፕስ ራዲዮንም ገዝተዋል፡፡ ... ወዘተ ሆነዋል ይሄ ሁሉ ሲሆን የድህነት ሰለባ እኔ ብቻ መሆኔ ምን በበደልኩ ነው? why always me! ስለዚህ ክቡር ጌታዬ እኔም እንደሌሎቹ ኑሮዬን አሻሽዬ እኖር ዘንድ ወደ ትራፊክ ፖሊስ እንድዛወር ከጫማዎ ሰር ወድቄ እለምንዎታለሁ... አመልካች አንበሴ ሞኙ፣ የማይነበብ ፊርማ አለው፡ አማካሪዎቹ ተው ብለውት ነበር፡፡ እንዲህ አይባልም እንዲህ ተብሎ አይፃፍም ምቀኝነት ያስመስልብሃል፣ ጥርስ ያስነክስብሃል ተው ይቅርብህ ብለውት ነበር፡፡ አንበሴ ሞኙ ግን አመረረ የመጣው ይምጣ እንጂ ከሰው አንሼ አልኖርም ሃሳቤንም አልቀይርም ማመልከቻዬንም አላሻሽልም አለና በአቋሙ ፀንቶ ማመልከቻውን ይዞ ለክቡር አዛዥ አቀረበ፡ ጠቅላይ አዛዡ አነበቡት፣ ልባቸው ተነካ፤ ማመልከቻው ግርጌ ላይ ውሳኔያቸውን አስቀመጡ፡፡ የአመልካቹ ጥያቄ እውነት በመሆኑ አምኛለሁ፡፡ ታሪኩ ሁሉ ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ ከእዚህ ሁሉ ሰው እሱ ብቻ በድህነት የሚማቅቅበት ምክንያት የለም፡፡ የድርሻውን ማግኘት ይገባዋል፡፡ በመሆኑም በጠየቀው መሠረት ወደ ትራፊክ ተዛውሮ ኑሮውን ያሻሽል›› ብለው ወሰኑለት፤ ተቀየረ. ኑሮውን ቀየረ ብለዋል አሉ ይባላል፡፡
ድሮ እንደዚህ ነበር፡፡ ኑሮን ለማሻሻል የተሻለው የስራ መስክ ትራፊክነት ነበር፡፡ ዘንድሮስ? ኑሮን ለማሻሻል የተሻለ መንገድ እንደምንም ብሎ ገቢዎችና ጉምሩክ መስራት ወይም እዚያው አካባቢ ማንዣበብ ነው፡፡ በተለይ በኦዲተርነት ሙያ ያሉ ሰዎች ይፈለጋሉ፡፡ ስማቸው በጥሩም በመጥፎም እየተነሳ ያሉ ቡድኖች አሉ፡፡ ጉምሩክ ለመግባት የታደለ ሰው እንደምንም ናዝሬት ቅርንጫፍ ወይም ቦሌ ፍተሻ ከተመደበ የድርሻውን ቦጭቆ ለመሄድ ስድስት ወር አይፈጅበትም (የትኩረትና የቁጥጥር ነጥቦችን እያሳየን ነው) አቃቂና ሞጆ ደረቅ ወደብ ምቀኛ ይበዛበታል፡፡ እንደ አይጥና ድመት የተፋጠጡበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ለመጠባበቅ አይደለም ለመነጣጠቅ! በተለይ በክፍለ ከተማ ደረጃ ያሉ የግብር መሰብሰቢያ የተወሰኑ መስሪያ ቤቶችማ ህዝቡ ግብር ከፋይ ሳይሆን ገባር የሆነባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ የፈለጉትን ያህል እየገመቱ ግብር ከፋዩን እያስጨነቀና እያጨናነቀ ለማስከፈል ይደራደራሉ፡፡ 3 ሚሊዮን ብር ግብር መጥቶ ብሃል ይሉታል፡፡ 200,000 ብር ነው ግብሬ ይላሉ፡፡ ግማሹን ክፈልና ተደራደር ይሉታል፡፡ ግማሹን ለማስያዝ አቅም የለውም ያለው እድል አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ከክፍለ ከተማ አንዳንድ የግብር ሹመኛ ጋር መደራደርና አጉርሶ መለያየት፡፡ ባይሆን የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ሹመኞች ይሻላል፡፡ ኃላፊዎቹን ማግኘት ይቻላል፡፡ ቢሮአቸው ክፍት ነው፡፡ እነዚያኞቹ ግን ባላባት ቢባሉ ያንሳቸዋል፡፡ አይን ያስፈልጋቸዋል፡፡

ግርማ ለማ

No comments:

Post a Comment