Tuesday, June 4, 2013

የግብጽ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ላይ ሲመክሩ የሚያሳይ ቪዲዮ የፋ ወጣ


1ግንቦት ፳፯ (ሀያ ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም


ኢሳት ዜና:-የግብጹ ፕሬዚዳንት ሙሀመድ ሙርሲ የተለያዩ  የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን በመሰብሰብ በመሰራት ላይ ባለው የአባይ ግድብ ዙሪያ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ወይይቱ ለተቃዋሚዎች ሳይነገር በቀጥታ በቴሌቪዥን እንዲተላለፍ በመደረጉ ተቃዋሚዎች ቅሬታቸውን ሲገልጹ የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ደግሞ ይቅርታ ጠይቋል።
አሶሽየትድ ፕሬስ እንደዘገበው በውይይቱ ላይ የተለያዩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች አስገራሚ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። ፕሬዚዳንት ሙርሲ በቅርቡ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የተቋቋመው የሶስትዮሽ የጥናት ቡድን ያወጣውን ሪፖርት መደምደሚያ ለፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ካቀረቡ በሁዋላ ፣ መሪዎቹ የፖለቲካ ልዩነታቸውን ትተው በአንድነት እንዲሰለፉ ጠይቀዋል።
ፖለቲከኞችም ውይይቱ በቀጥታ በቴሌቪዥን እንደሚቀረጽ ሳያውቁ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
አይማር ኑር የተባሉት የሊበራል ጋሀድ ፓርቲ መሪ ” ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የጦር ጄቶችን ገዝታለች የሚል ወሬ መንዛት” እንዲሁም ” ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የስለላ እና የወታደራዊ ቡድን በማዋቀር እና ወደ አዲስ አበባ በመላክ በውስጥ ፖለቲካቸው ውስጥ ጣልቃ መግባት” ያስፈልጋል የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል።
የእስላሚክ ኮንሰርቫቲቭ ኑር ፓርቲ መሪ የሆኑት ዩኒስ ማክዩን በበኩላቸው ” ግድቡ ለግብጽ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ፣ ካይሮ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች መደገፍ አለባት ብለዋል። ” ኢትዮጵያ የተዳከመች አገር ናት፣ ከተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መደራደሪያ እናደርገዋለን ያሉ ሲሆን፣ ይህ ሁሉ ካልተሳካ ግን የደህንነት ሰዎቻችንን በማሰማራት ግድቡን ማውደም አለብን” በማለት አክለዋል።

አይማን ሩር የተባሉት ፖሊቲከኛ ደግሞ ” ግብጽ በአይር ላይ ነዳጅ የሚቀዱ ተዋጊ ጀቶች እንደገዛች የሚያሳይ ወሬ በመንዛት የዲፕሎማሲ ድል ልታገኝ ትችላለች ” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
የግብጽ የመገናኛ ብዙሀን በቀጥታ የተላላፈው ስርጭት በእጅጉ አበሳጭቷቸዋል። አንዲት ጋዜጠኛ “በአባይ ጉዳይ ግልጽነት ይኑር ብለን ስንጠይቅ የአለም መሳቂያ እስክንሆን ድረስ ገመናችን ይውጣ ማለታችን አልነበረም” ብላለች።
የሙርሲ መንግስት የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ይቅርታ ጠይቀዋል። ውይይቱ በቀጥታ በቴሌቪዥን እንዲተላለፍ የተወሰነው በመጨረሻ ሰአት ላይ በመሆኑ ለተወያዮቹ አልነገርናቸውም ነበር ብለዋል።

No comments:

Post a Comment